በፈረጃ ዱካ!

ስለ ኢትዮጵያ ፊልም ሲነሳ ብዙዎች ያላቸው አመለካከት ትዝብት ውስጥ የሚወድቅ ነው፡፡ አንዳንዱማ የኢትዮጵያ ፊልም ጉዳይ ሲነሳ አውሊያው እንደተነሳበት ጠንቋይ ሊርገፈገፍ ሁሉ ይችላል፡፡ የባህር ማዶውን እንጂ የኢትዮጵያን ፊልም አለማየት እንደስልጣኔ የሚቆጥሩም በሽ ናቸው፡፡

ትልቁ ችግር በፊልሞቹ መንገሽገሻችን ሳይሆን እኔስ የበኩሌን ምን አደረግሁ? ብለን አለመጠየቃችን ነው፡፡ ትችት ያለ ነገር ቢሆንም ከራስ ሲጀምር መልካም ነው፡፡ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥተን ለትችት የሚያበቃ ሥራ አልሰራንም፡፡ አሜሪካውያን ለገናናው የፊልም ኢንዱስትሪያቸው ዛሬም ድረስ በኩራት የሚያወሩትን አንድ ነገር ሠርተዋል፡፡ በፊልሙ ጥበብ የበለጸጉ ሆነውም ሁሌም በምሳሌነት እናነሳቸዋለን፡፡ በእርግጥ አፍሪካውያንም እንደ ናይጄሪያ አይነቶቹን አንረሳም፡፡

ሆሊውደ የተመሰረተው በራሱ አቅም እንዳይመስላችሁ፣ በሕዝብ ገንዘብ ነው፡፡ ሆሊውድም የአንድ ትልቅ ባለሀብት ወይንም የራሱ ብቻ አይደለም። ሆሊውድ መላው አሜሪካውያን እንደ ዓይን ብሌናቸው የሚመለከቱት የራሳቸው ንብረት ነው፡፡

የአሜሪካ የፊልም ጥበበኞች ልክ እንደዛሬ እንደኛው የፊልም ኢንዱስትሪ ባለቤት ከመሆናቸው በፊት ፊልም የሚሠሩት ፕሮዲዩስ የሚያደርጋቸውን ባለሀብት እየፈለጉና እየተለማመጡ ነበር፡፡ ከዚያም ኋላ ባለገንዘቦቹ ባለቤት ናቸውና እንዳሻቸው ይዘውሯቸው ነበር፡፡ ስለፊልሙ ምንነት ያልገባቸውም ናቸውና ባለሙያዎቹን የሚያስጨንቁት ትርፍ እንዲያመጡላቸው ብቻ ነው፡፡

ሌላው ነገር ግድ አይሰጣቸውም፡፡ በዚህም ላይ ትርፉን ለራሳቸው ብቻ በማግበስበስ፤ ለፊልሙ የሚደክሙት አንድም ጠብ የሚል ርስት ለማግኘት አልቻሉም፡፡ በዚህ ሁሉ ምርር ስልችት ያላቸው የፊልሙ ጠቢባን ተሰባስበው ተማከሩ፤ አወጡ አወረዱ፡፡ ድንገት ግን አንዲት ሀሳብ ብልጭ አለችላቸው፡፡ ይህም የሕዝብ ፊልም መሥራት የሚል ነበር፡፡ እናም ሕዝባቸውን በማስተባበር ገንዘብ ሰበሰቡ፡፡ እንደቀድሞው ፕሮዲዩስ የሚያደርጋቸው አካል እግር ላይ መውደቁ ቀርቶ በሰበሰቡት ገንዘብ ፊልም ሠሩ፡፡

በአንድ አልቆሙም፤ ሁለት…ሦስት… እያለ ቀጠለ። በዚህም የቀድሞ ባለሀብቶችንና ፕሮዲዩሰሮችን ከጨዋታ ውጪ አደረጓቸው፡፡ ነገሩ እያማረበትና ተመልካችም የሚፈልገውን እያገኘ፤ ቁጥሩም እየጨመረ ሄደ፡፡ የገንዘብ አቅማቸውም ፈርጣማ ሆነና በአጭር ጊዜ ውስጥ የሆሊውድ የፊልም መንደርን አቋቋሙ፡፡ በመሳሪያና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እራሳቸውን በሚገባ በማጠናከር ከሀገራቸው አልፈው መላው ዓለምን ያጥለቀልቁት ጀመር፡፡

በአንድ ፊልም የተጀመረችው ትንሽ ሀሳብ ዛሬ የስኬት ጫፍ ላይ ደርሳለች፡፡ የፊልም ጥበብ በቁሙ ሳር የሚበቅለበት መቼ መሰላችሁ?፤ የንግድና የሸቀጥ የሆነ እለት ነው፡፡ የዚያኔ ጥያቄው ምን በምን መልኩ ሰርቼ የፊልሙን ኢንዱስትሪ ላሳድገው ሳይሆን ምኑን ከምኑ አድርጌ ኪሴን ልሙላው ይሆናል፡፡ ስለዚህ ዓላማውም ማስደሰት የሚፈልገውን አካል አስደስቶ የማይሞላውን ሆድና ኪስ መሙላት ነው፡፡ ፕሮዲዩስ የሚያደርጉ አካላት ስለ ፊልም ካልገባቸው ዘርፉ የንግድ ብቻ መሆኑ አይቀርም፡፡ ስለዚህም ዋናው ነገር `የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው` ነው፡፡

ባለሀብቶች ፕሮዲዩስ ማድረጋቸው ባልከፋ፤ ግን ደግሞ ሌላ ያስከተለው ጦስም አለ፡፡ የፊልም ኢንዱስትሪው እራሱን ችሎ እንዳይቆም አድርጎታል። እንዴት? ሲባል ከፊልሞቹ የሚገኘው ትርፍ በሙሉ ተጠራርጎ የሚገባው ወደ ኢንዱስትሪው ሳይሆን ወደ ባለሀብቶቹ ፕሮዲዩሰሮች ኪስ ነው፡፡ ተረቱም፤ `ላለው ይጨመርለታል` ነውና ከተዋንያን እስከ ትልልቅ ባለሙያዎች የሚያዋጣው የፊልሙ ኢንዱስትሪ የሚያገኘው የሻይ መጠጫ ነው፡፡

የሀገራችን የፈረጃ ፊልም ሀሳብ ታዲያ በሻይ መቃጠሉ በዚህ ይብቃና ሁላችንም ችለን እናስችል የሚል ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡ ጽንሰ ሀሳቡ ከላይ ካነሳነው ከሆሊውድ የፊልም ኢንዱስትሪ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ልክ እኛ ሀገር ውስጥ እንደምንመለከተው ሁሉ በኛ የፊልም ኢንዱስትሪ የነበሩ ችግሮች በሙሉ እነርሱም ዘንድ ነበሩ፡፡

በፖለቲካም ይሁን በኪነ ጥበብ ነጻነት ማለት ሕዝብ ነው፡፡ ከነበርንበት እቅፍ አምልጠን በሕዝብ እቅፍ ውስጥ ስንገባ የዛኔ ነው ነጻና የሕዝብ አገልጋይ የምንሆነው፡፡ ታዲያ የፊልሙን ኢንዱስትሪ ከነጋዴው አስጥለን እኛም የምንፈልገው አይነት ፊልም ማየት እንድንችል ነጻነት አያስፈልገውም?፡፡ በእርግጥ የፊልም አፍቃሪና ወዳጆች ብቻም ሳይሆኑ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለፊልሙ ይህ ነጻነት አያስፈልገውም የሚል እምነት አለው ተብሎ አይታሰብም፡፡

“ፈረጃ” በሕዝብ ሊሠራ የተዘጋጀ የሕዝብ ፊልም ነው፡፡ በዚህ ታላቅ ጽንሰ ሀሳብ ውስጥ፤ “ፈረጃ” ማን ነው? ማንስ እንበለው?፣ ፈረጃ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የበኩር ፊልሙ ነው፡፡ ምክንያቱም እስከዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ ሕዝብ በራሱ ገንዘብ የሠራው ፊልም ባለመኖሩና በፈረጃ ደግሞ በመጀመሩ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜም በፊልማችን ውስጥ የሚጠቀሰው የፕሮዲዩሰር ስም ከባለሀብቶችና ተቋማት ውጪ ሊሆን ነው፡፡

ከሦስት ዓምታት በፊት የዚህ ፊልም ሀሳብ ተወለደ። በማን? በትወና ብቃቱ ብዙኃኑን ሲያስደምም በቆየው በወጣቱ ተዋናይ ሔኖክ ወንድሙ ነው። ሔኖክ ይህን ለመሥራት እንዴትስ አሰበ? ከቀናቶች በፊት ፊልሙ የደረሰበትን ደረጃ ለሕዝብ ለማሳወቅ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ እንዲህ ሲል አብራርቷል፤ “እኔ አንድ ኢትዮጵያዊ ነኝ። ዛሬ እዚህ ጋር በክብር እንድቆም ያደረገኝ የኢትዮጵያ ፊልም ነው። ታዲያ እኔን ያስከበረኝ ፊልም፤ ዛሬ ላይ ሲበላሽ እንዴትስ ዝም ብዬ አያለሁ…ምን የመቀየር ምኞት ቢኖረኝ ለብቻዬ ልለውጠው የምችለው አልነበረም። እናም አሰብኩ። በተለያዩ ሀገራት ስዘዋወር የተመለከትኩትን ተሞክሮ ለሀገሬ ፊልምም ቢሆን ብዬም ተመኘሁ። እናም፤ የኢትዮጵያን ፊልም ሊለውጥ የሚችለው እራሱ ሕዝቡ እንደሆነ ተረዳሁ። እኔም ማድረግ የምችለው ይህን ነበር፤ ፊልሙን ለሕዝብ መስጠት። ከዚህ በመነሳትም ለማሳያ የሚሆን አንድ ነገር ማድረግ ነበረብኝ፤ ከልጅነቴ ጀምሮ የማውቀውን “ፈረጃ” የተሰኘ ግለሰብን ታሪክ፤ ለዚህ አጨሁት፡፡ እናም ይህን ታሪክ ወደ ፊልምነት በመቀየር ሁሉንም ነገር ማድረግ እንደምንችል ለማሳየት፤ ሀሳቤን ይዤ ወደ ሕዝቡ ዘንድ ሄድኩ፤ ሕዝቡም አላሳፈረኝም። እኔ “ፈረጃ” ስል ጀምሬዋለሁ፤ ነገ ላይ ደግሞ ይህን የተመለከተ ሌላውም ይቀጥላል”፡፡

ለኛ የፊልም ኢንዱስትሪ የሚያስፈልገው ይሄው ነው፡፡ ፊልማችን ተለውጦ ለማየት ሌላ ተአምር አያስፈልገንም፡፡ “አንድነት ኃይል ነው…ድር ቢያብር አንበሳ ያስር…ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ፤ ለሃምሳ ሰው ጌጡ…” እያልን ስንፎክርና ስንተርት የምንኖር እኛን ቀርቶ በሕዝብ ፊልም ሆሊውዶች እንኳን የደረሱበትን አይተናል፡፡

ፈረጃ ከየት ተነስቶ የት ደረሰ? የፊልሙ ግራና ቀኝ አዝማቾች ለዚህ ጥያቄ፤ ለሚጠብቃቸው ሕዝብ በመግለጫው አስረድተዋል፡፡ የፊልሙ ደራሲና አስተናባሪ ሔኖክ ወንድሙ፤ የሮዝ ፊልም ኢንተርቴመንት ባለቤት ግሩም ብርሀነ ጸሐይ እና የኢነርጂ ፊልም ፕሮዳክሽን ሥራ አስኪያጅ ዳንኤል ግርማ፤ በኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ የመጀመሪያውን ታሪክ ለመሥራት ጥምረት ፈጥረዋል። በጋራ ለመሥራት የመጀመሪያቸው አይደለም፤ ከዚህ ቀደም በፊልም ያቤጽ፣ ምናለሽ፣ ቁራኛው፣ ሀገር ስጪኝ እንዲሁም ከሙዚቃ ሥራዎች ደግሞ የቴዲ አፍሮን ማር እስከ ጧፍ ቪዲዮን ጨምሮ በበርካታ ሥራዎች ውስጥ ተቀናጅተው ሠርተዋል፡፡ አሁን ደግሞ ይሄው በ”ፈረጃ” ፊልም፤ እንችላለን ብለው ተነስተው ከሕዝብ አደራን ተቀብለዋል፡፡ ሕዝቡም ከኪሱ ገንዘብ አውጥቶ ሲሰጥ እነርሱን አምኖና የሀገሬን የፊልም ኢንዱስትሪ ይለውጣል በማለት ተስፋ ነው፡፡

እንዳደግንበት ባህላችን አደራን የተሸከመ እንቅልፍ የለውምና የፊልሙ አዘጋጆች፤ ፈረጃ በአሁኑ ሰዓት ሁሉን አጠናቆ ወደ ቀረጻ ለመግባት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ፊልሙን ለመሥራት የተመደበለት የገንዘብ መጠን 3.7 ሚሊዮን ብር ሲሆን፤ እስከዛሬ ድረስ በጎ ፈንድ ሚ፤ ከሕዝብ ለመሰብሰብ የተቻለው የገንዘብ መጠን 2.6 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ታዲያ ይህ ፊልሙን ያሠራል?፤ ለዚህ ጥያቄ መልስ የሰጠው ሔኖክ ወንድሙ እንዲህ ብሏል “የተሰበሰበው ብቻ ፊልሙን ያሰራል ወይ፤ አያሰራም፡፡ ግን ሕዝባችን ደግነቱን አሳይቶኛል፡፡ ያውም በዚህ የችግር ሰዓቱ ካለችው ላይ አንስቶ ሰጥቶናል፤ በእጅጉ ምስጋና ይገባዋል፡፡ ከአሁን ወዲያ፤ ሕዝቡን ለማስጨነቅ እኔ በግሌ አልፈልግም። ከራሳችን ኪስ አውጥተንም ቢሆን የቀረችዋን እንሞላታለን፡፡ የፊልሙ ቀርጻም በቅርቡ ይጀምራል”።

አዘጋጆቹ ይህንን ፊልም ከሕዝብ ተቀብሎ መልሶ ለሕዝብ መስጠት በሚል ዓላማ ተነስተዋል። ግን ታዲያ ሕዝቡ በምን መልኩና እንዴትስ ነው ሊሳተፍበት የሚችለው? ለሚለው ጥያቄ፤ እንቅስቃሴው “አምስት ብር ከፍሎ ፊልም መመልከት” የሚል ነው፡፡ ይህ ማለት ይመለከተኛል የሚል አንድ ሰው ለዚህ ፊልም የ5 ብር የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ድር ቢያብር.. ማለት እንግዲህ እዚህ ጋር ነው፡፡

ለፊልሙ ወጪ ያስፈልጋል የተባለው 3.7 ሚሊዮን ብር ነው፤ ይህን በሂሳባዊ ቀመር ብናሰላው፤ ከ90 ሚሊዮን በላይ ከሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል 7 መቶ አርባ ሺህ ሰው፤ እያንዳንዱ አምስት አምስት ብር ብቻ ቢያዋጣ ፊልሙን ሠሩት ማለት ነው፡፡ መላውን ሕዝብ ትተን፤ የፊልም አፍቃሪያንና ወዳጆችን ብቻ ብናስብ እንኳን በአንድ ጀንበር ሁለትና ሦስት ፊልሞችን ለመሥራት ይቻላል፡፡ እዚህ ጋርም “ድር ቢያብር፤ አንበሳ ያስር” ልንል እንችላለን፡፡ ታዲያ ይህንን አንበሳ ለማሰር የማይፈልግ ማን ነው?

ገንዘብ ከሕዝብ ተዋጣ፤ ፊልሙም ተሠራ፤ ቀጣይስ? ከፊልሙ የሚገኘው ገቢ ጉዳይ በማን ኪስ ይግባ? በማንም ኪስ አይገባም! የቄሳርን ለቄሳር…ስለዚህ፤ በረሀብ ጥም ለተጎሳቆለው የፊልም ኢንዱስትሪ ይውላል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ከፈረጃ ቀጥሎ የሚወለዱ ሌሎች ፊልሞች ይኖራሉ ማለት ነው፡፡ አዎን ይኖራሉ፤ በፈረጃ ብቻ እንደማይቆም አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡

በሆሊውድ የፊልም መንደር የጉዞ መነሻና ዛሬ የደረሰበትን ለተመለከተና በቅጡ ለተረዳ፤ እኛም በፈረጃ ፊልም ጅማሮ ላይ እያከልንበት ነገ ላይ ልክ እንዲሁ ለመሆን እንደሚችል አያጠራጥርም። ነገር ግን አንድ ፈረጃ ብቻውን ተውልዶ እሱም ሌላ ሳይወልድ ከመከነ ይሄኔ ጥበብም አልኖረች ፊልምም አልተሰራች፡፡

ታዲያ ፈረጃ ፊልም ይዞ የመጣው አዲስ ነገር ምንድነው? የመጀመሪያው ነገር የዚህ ፊልም ፕሮዲዩሰር ከዚህ ቀደም እንደምንሰማው እገሌ፤ እገሊት የሚባል ነገር የለውም፡፡ አንድና አንድ “የፊልም አድናቂና ወዳጆች” ናቸው። ነገሩ ሲፈታ ሕዝብ እንደማለት ነው። በመቀጠል ለዚህ ፊልም ወጪ የሚደረገው 3.7 ሚሊዮን ብር መሆኑ ነው፡፡ ሌላ ወሰን መስበሩ ነው። ይህ ለፊልም ጥራት ማረጋገጫ ባይሆንም ግን ሳይወድ በግዱ ልዩ ማድረጉ አይቀርም። ቀጥሎም በድምሩ የሚሳተፉ ተዋንያንን ቁጥር ስንሰማ ለታላቁ ሩጫ ይመስለን ይሆናል፤ ግን አይደለም። ለታላቁ ፊልም እንጂ፡፡ በትንሹ ከ4ሺህ ሰው በላይ ይሳተፍበታል።

የፊልሙ ዋና ገጸ ባህሪ አንደኛው የሕይወት ክፍል ነው። ቀጥሎም በፊልም ጥበብ ሙያ ለየት ብሎ ከመጣባቸው ነገሮች አንደኛው በቀረጻው፤ የምስልና ድምጽ ጥራቱን ፈርጣማ ለማድረግ የሚጠቀመው መሳሪያ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁና በአይነታቸው ለየት ያሉ መሆናቸው ነው።

በሌላ በኩል የተመራረጡ የባለሙያዎች ጥምረት ተፈጥሯል። ሌላውና ዋነኛው ነገር ኢንዱስትሪው ለመጀመሪያ ጊዜ ከየትኛውም አካል ጫና ነጻ በመሆን ለራሱ ገቢ ማስገባቱ ነው፡፡ ትልቁ ችግር የነበረው የባለሙያዎች፤ የላብ የወዝ ነገር መፍትሄ ያገኛል። በሠሩትና በለፉት መጠን የሚገባቸውን ያገኛሉ፡፡ ከሁሉም ላቅ ያለ ሌላም ትልቅ ጉዳይ አለ፤ ይሄውም የዘርፉና የሙያው ነገር ነው፡፡ እንዲህ ነጻ ካወጣነው፤ ባለሙያውን ይህን ሥራ! ይህን አትሥራ!፤ ያን ቁረጥ! ያን ፍለጥ! የሚል አይኖርም። ስለሆነም የፊልም ባለሙያዎቹ የሚጨናነቁት ትርፍ አግኝቶ ፕሮዲዩሰሩን ስለማስደሰትና ከዕዳ ነጻ ስለማውጣት አይደለም። ጭንቀታቸው ቆንጆ ፊልም ሠርቶ የሚሠሩለትን ሕዝብ ስለማስደሰት ነው፡፡

ሕዝቡም ማየት የሚፈልገውን ነገር ከማየቱም በላይ፤ የኢንዱስትሪው ገቢ መልሶ እራሱኑ የሚደጉም ይሆናል፡፡ በፈረጃ ፊልም የሚገኘው የዋናው ገጸ ባህሪን፤ አንደኛውን የሕይወት ክፍሉን ተከትሎ ከ4 ሺህ እስከ 5 ሺህ ድረስ ያሉ አጃቢ ተዋንያን ይሳተፉበታል፡፡ ይህ ቦታም ፊልም የመሥራት ፍላጎት ላለው ሁሉ ክፍት ስለመሆኑ አዘጋጆቹ ይናገራሉ፡፡

እንግዲህ፤ የሀገሬ ልጅ፤ አይሆንም አትበል፤ ይሆናል፡፡ ፊልም ለቅንጦት ነው አትበል፤ አይደለም። ሌላው ያድርገው አትበል፤ ይህች ሀገር ያላንተ ማንም የላትምና፡፡ አንድ ቀን አደርገዋለሁም አትበል፤ ዛሬም ያው አንድ ቀን ነውና፡፡ ይህን ስል ስለ ፈረጃ ፊልም ብቻም አይደለም፡፡ እነርሱ ጀምረውታል ሌሎች ለቀጣዩ ይዘጋጁ፡፡ ከአጋም ጋር ለተጣበቀ ቁልቋል ከዚህ የተሻለ ምንም መፍትሄ የለውም፡፡ በፈረጃ ዱካ ስንል፤ ዱካ አንድም ያስቀምጣል፤ አንድም ፈለግ ነውና ያስከትላል፡፡

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን የካቲት 14/2016

 

Recommended For You