‹‹ፓርኩን በ2030 የአፍሪካ ዲጂታል ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ ነው›› አቶ ሄኖክ አህመድ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ

ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መበልፀግ የላቀ ድርሻ እንዳለው ይታመናል። ኢትዮጵያም በተለይም የምጣኔ ሀብቷን ለማሳደግና በዘርፉ ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር ያስችላት ዘንድ የተለያዩ የልማት ግቦችን አቅዳ ስተገብር ቆይታለች፡፡ ለዚህም ይረዳት ዘንድ በአፍሪካ ቀዳሚ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል ይሆናል ያለችውን በ2003 ዓ.ም በ200 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የኢይ.ሲ.ቲ ፓርክ ማቋቋሟ ይታወሳል። የቴክኖሎጂ ዘርፉን የማሳደግ ዓላማ ሰንቆና ለ300 ሺ ሰው የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሎ የተቋቋመው ይሄው ፓርክ በተለያዩ ሀገራዊና ውስጣዊ ችግሮች ምክንያት እንደታሰበው ውጤታማ ሳይሆን መቅረቱ ይነገራል፡፡

ይሁንና ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ግን መንግሥት እንደሀገር ካስቀመጣቸው ቁልፍ የልማት መርሀ ግብሮች መካከል የቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ አንዱ በማድረጉ በዘርፍ መነቃቃት እየታየ ነው፡፡ በተለይም ፓርኩ ራሱን ችሎ እንዲቋቋም በማድረግና በመስኩ ላይ ይነሱ የነበሩ የመሰረተ ልማትና መሰል ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣም በዚህና በቀጣይ የልማት ሥራዎች ዙሪያ ከፓርኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሄኖክ አህመድ ጋር ቆይታ አድርጓል እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ፓርኩ መጀመሪያ ሲመሠረት ከያዘው ዋነኛ ዓላማ እና ተልዕኮ አንፃር ውጤታማነቱ እንዴት ይለካል?

አቶ ሄኖክ፡– እንደሚታወቀው ፓርኩ የተጀመረው ከዛሬ 14 ዓመት በፊት በቀድሞ ኮሙዩኒኬሽን ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንደፕሮጀክት ተይዞ ነበር፡፡ በደንብ ቁጥር 177 በሚኒስትሮች ምክር ቤት በተቋቋመ ኮርፖሬሽን ስር ሆኖ የተመሰረተው ይህ ፓርክ በወቅቱ በጎሮ ቦሌ ለሚ አካባቢ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል ኢትዮ አይ.ሲ.ቲ ቪሌጅ በሚል የተቋቋመ ነው፡፡ ነገር ግን ደግሞ ኮርፖሬሽኑ የታሰበው አንድ ፓርክ ብቻ ሳይሆን በርካታ ፓርኮችን እያለማ ለማስተዳደር ተብሎ ነበር፡፡ ከዚያ አንፃር የመጀመሪያ የተባለው ይሄ ፓርክ ሲሆን፤ በወቅቱ የነበረው መሰረታዊ ሃሳብ አንደኛው በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ሥራ ጠባቂ ሳይሆን በአይ.ሲ.ቲ ዘርፍ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ለማበረታታትና ድጋፍ ለማድረግ የሚያስፈልጋቸውን እንደ ቢሮ፣ ኢንተርኔት፤ መብራትና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ሳይቆራረጡና በአስተማማኝና በተሟላ ሁኔታ በማቅረብ የራሳቸውን ድርጅት እንዲፈጥሩ ያመቻቻል የሚል ነው፡፡

ሁለተኛው የተነሳው በዚህ ዘርፍ ሥራ ለመፍጠር የሚያስችል የሰው ሀብት ለማፍራት ሲሆን፤ ራሱም ሥራ ይፈጥራል፤ የፈጠረው የሰው ኃይልም ከዚህ እየወጣ ለተለያዩ ድርጅቶች ተቀጥሮ እንዲሰራ ለማድረግ ትልቅ ህልም ሰንቆ ነበር፡፡ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብ ደግሞ ሶስተኛው ዓላማ ነበር፡፡ በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአይ.ሲ.ቲ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እውቀታቸውና መዋእለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ለማድረግ የተመቻቸ ሁኔታ ለመፍጠር ያለመ እንደነበር እሙን ነው፡፡

በዋናነት ደግሞ ለኢንዱስትሪው ብቁ የሆነ የሰው ኃይል የምንፈጥርበት ማዕከል ይሆናል ተብሎ እንደመታሰቡ፤ ይህንን ዓላማ ለማሳካት በወቅቱ ጥናት ተደርጎ ነበር፡፡ ጥናቱን ያሸነፉት ዊፕሮና ሲስኮ የተባሉ ዓለም አቀፍ የህንድ ድርጅቶች ናቸው፡፡ በወቅቱ እነዚህ ድርጅቶች የአዋጭነት ጥናት ሰርተዋል፤ በዚያ መሰረት እንቅስቃሴ ሲደረግ ነበር፡፡ በዚያ እንቅስቃሴም ጥረት ሲደረግ የነበረው የተወሰኑ ድርጅቶች ወደ አይ.ሲ.ቲ ፓርክ እንዲገቡ ነበር ፡፡ ይሁንና እንደተጠበቀው የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሊገቡ አልቻሉም፡፡

የኢትዮ- ቴሌኮም ዋና መስሪያ ቤትም እዚሁ ግቢ ውስጥ እንዲሆን እንቅስቃሴ ሲደረግ ነበር። ይሁንና በተለያዩ ምክንያቶች የሕንፃው ግንባታ ተቋርጦ ቆይቷል። እነዚህ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ባለበት ሁኔታ ለውጡ መጣና በመንግሥት ውሳኔ ኢንፍርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ኮርፖሬሽን ስር እንዲዞር ተደርጎ ለአምስት ዓመት ያህል በዚያ ሲተዳደር ቆየ፡፡ በዚህ ወቅት የገጠመው ችግር ኮርፖሬሽኑ የሚያስተዳድራቸው ፓርኮችና የአይ.ሲ.ቲ ፓርክ ባህሪ የሚለያይ በመሆኑ እነዚያ ፓርኮች ብዙዎቹ የቀላል ማምረቻ ኢንዱስትሪ ላይ የተሰማሩ በመሆናቸው እንደታሰበው ውጤታማ ሥራ መሥራት አልተቻለም፡፡ ደግሞ ኢንዱስትሪዎቹ ከፓርኩ በተለየ መልኩ በአብዛኛው የሚፈልጉት የጉልበት ሰራተኛ ሲሆን፤ በተጨማሪም የሚቀጥሩት በብዛት መካከለኛ የእውቀትና የልምድ ደረጃ ያላቸውን ነው፡፡ እንደአይ.ሲ.ቲ ያሉ ፓርኮች ግን ከፍተኛ የእውቀት ደረጃ የሚጠይቅ ቴክኖሎጂ ፓርክ በመሆኑ አብሮ ለማስተዳደርም ሆነ ለመምራት አዳጋች ነበር፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ፓርኩን ለየት የሚያደርገው የሥራ እድል መፍጠር ብቻ ሳይሆን ማፍሪያ ኢንኩቬሽን ጭምር ሆኖ የሚያገለግል መሆኑ ነው፡፡ አስቀድሜ እንዳልኩት ወጣቶች ሰልጥነው፤ ራሳቸውን አብቅተው፤ የየራሳቸውን ኩባንያ እየፈጠሩ የሚሄዱበት፤ ቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረግበት፤ ሰዎች የሚሰለጥኑበት፤ ኩባንያዎች አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ድጋፍ የሚደረግበት ማዕከል ነው፡፡ እንደሌሎቹ ፓርኮች ሼድ አናከራይም፤ ምርት የሚመረትበትም አይደለም፡፡ ስለዚህ ይሄ ችግር ስለተፈጠረ መንግሥት እንደገና ፓርኩ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ተጠሪነቱ ሆኖ ግን ደግሞ ራሱን ችሎ እንዲቋቋም ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ በቦርድ እንዲመራ ተደርጎ ነባሩን ተልዕኮ በመያዝ ከአዳዲስ አላማዎች ጋር ራሱን እያስተዳደረ ይገኛል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ፓርኩ በአዲስ መልክ ከተቋቋመ በኋላ ምን ምን ሥራዎችን አከናውኗል?

አቶ ሄኖክ፡– ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በአዲስ መልክ ለመደራጀት የሚያስችሉትን ስራዎች ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በዚህ ሂደት ፓርኩ ያጋጠመው የመሰረተ ልማት ችግር ነበር፡፡ እንደኢንተርኔት፣ መብራት፣ ውሃ፣ አካባቢው ደግሞ ከአዲስ አበባ ትንሽ ራቅ ስለሚል ትራንስፖርት፣ የምግብ አገልግሎት በአቅራቢያው ያለመኖር የመሳሰሉት ችግር ፈተና ሆነውበት ቆይተዋል። ስለዚህ ለሥራ ምቹ ያልሆኑ ብዙ ችግሮች ነበሩ፤ እነሱን ለማስተካከል ጥረት ሲደረግ ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም ወደ ፓርኩ ገብተው ከነበሩት 100 የሚደርሱ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት ጥለው ወጥተዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት የመሰረተ ልማት ችግሩን መቋቋም ባለመቻላቸው ነው፡፡

እንደሚታወሰው ከውጭ የመጣው የቴክኖ ሞባይል መገጣጠሚያ ኩባንያ ብቻ ነበር፡፡ በተለያየ ጊዜ የተለያየ ችግር አጋጥሞት ነበር፤ ወደ ሙሉ የማምረት አቅም እንዲመጣ ድጋፍ ስናደርግለት ቆይተናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ሌሎች ኩባንያዎችም ገብተዋል፡፡ ለምሳሌ በዳታ ሴንተርና ቢዝነስ ዘርፍ የገቡ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ዳታን እንደአገልግሎት ለማቅረብ የመጡ የውጭ ድርጅቶች አሉ፡፡ ለአብነት ብንጠቅስ ዊንጎ አፍሪካና- ራይክሲዮ የሚባል ነው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ለራሱም ለውጭም አገልግሎት የሚሰጠው ሳፋሪ ኮም ኢትዮጵያ ድርጅት ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ዳታ ሴንተሮች 50 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት የተደረገባቸው ናቸው። በዚህ ዘርፍ በመሰረተ ልማት ብቻ ይህንን ያህል ኢንቨስትመንት ከዚህ ቀደም አልተደረገም፡፡

ለእነዚህ ድርጅቶች የኃይል አቅርቦት ከአቅራቢያችን ካለ ቅርንጫፍ ጣቢያ 13 ሜጋ ዋት እንዲያገኝ፤ ወደፊት ደግሞ 200 ሜጋ ዋት የኢንተርኔት ኮኔክሽን እስከ 40 ጂቢ ድረስ አስገብተናል፡፡ ሌሎች አገልግሎት ለመስጠት የሚያስቸግሩ ሕንፃዎችን አስተካክለናል፡፡ እኛ ከመጣን ከ 30 በላይ የሚጠጉ ድርጅቶች በፓርኩ ኢንቨስት ለማድረግ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩት 25 ነበሩ፤ ቢሆንም ሁሉም ግን በሥራ ላይ አልነበሩም፡፡ የተወሰኑት ከፓርኩ ውጪ ቢሮዋቸውን አድርገው የሚሰሩ አሉ፤ ይሁንና እስካሁን ድረስ አድራሻቸውን ያላገኘናቸው አሉ። ቀሪዎቹ አድርሻቸው ይታወቃል፤ ‹‹የመሰረተ ልማት ችግር ስላለ ዘግተን ወጥተናል›› ያሉትን እንዲመለሱ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ የተወሰኑት ደግሞ ጀኔሬተርና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን አሟልተው ለመስራት ጥረት እያደረጉ ነበር፡፡

ሕንፃውን ለረጅም ዓመታት ተከራይተው የጠፉና መመለስ ያልቻሉትን ድርጅቶች ወደ ህግ እንልከዋለን። ምክንያቱም ሕንፃው የተሰጣቸው እንዲያለሙበት በመሆኑ ለመስራት ፍቃደኛ ካልሆኑ በኮሜቴ በያዙት ቦታ አስወጥተን ለሚያመርት ለሌላ ድርጅት እናከራየዋለን። በተጨማሪም መሬት ለ60 ዓመት በሊዝ ለማከራይት የተሰጠን፤ ከዚያ 60 ዓመት ውስጥ 16 ዓመቱ አልፏል። የሚቀረው 44 ዓመት ነው፤ በእነዚህ ዓመታት የሚጠበቀው ለአገልግሎት ሰብ-ሊዝ ሕንፃ ገንብተው እዚሁ አይ.ሲ.ቲ ባርክ ውስጥ እንዲሰሩ ነው፡፡

አካባቢው ለኢንቨስተሮች ሳቢ እንዲሆንና በዋናነት ለሀገሪቱ ቴክኖሎጂ አቅም በሀገር በቀል ድርጅቶች ለመጠቀም እንዲያስችል የአቅም ግንባታ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ስለዚህ ፓርኩ በ2030 የአፍሪካ ዲጂታል ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው። በአሁኑ ወቅት እየተንቀሳቀሰ ያለው ይህንን ራዕይ ይዞ ነው ፡፡ ይህም ሲባል በ2030 ከውጭና ከሀገር ውስጥ ድርጅቶችና ከግለሰቦች የሥራ ፈጠራ ክህሎት ያላቸውን ወደ ፓርኩ ለማስገባት ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ምርቶቻውንና አገልግሎታቸውን ይዘው ወደገበያ እንዲወጡ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል፡፡ ዓላማችን የዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሆነው ከሀገር ውስጥ አልፈው ወደ ውጭ መላክ እንዲችሉና የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገቡ ለማድረግ ነው፡፡

በዋናነት ግን ቅድሚያ ትኩረት የሰጠነው አቅማችንን በማጎልበት የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ማርካት ለሚያስችል ሥራ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ወጣቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀምጠው በኢንተርኔት አማካኝነት ዓለም አቀፍ ሥራ የሚሰሩበት እድል በማመቻቸት አገልግሎትን ኤክስፖርት በማድረግ የውጭ ምንዛሬ ለማስገባት የሚያስችል ሥራ ለመስራት ዝግጅት አድርገናል፡፡ እዚህ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን ጋብዘን ወደ ፓርክ እያስገባን ነው፡፡ ትልቅ ትኩረት የሰጠነው ከውጭ ምንዛሬ ማስገባት አንፃር ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሎ የታሰበው ነው፡፡

ሁለተኛው በአይ ቲ ዘርፍ የማማከር አገልግሎት የሚሰጡ ኩባንያዎች አቅማቸውን የማሳደግ ሥራ ይሰራል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ በዘርፉ ለሚገኝ ማንኛውም እውቀት ለውጭ ድርጅቶች የምናወጣውን ወጪ ለመቀነስ የሀገር ውስጥ አቅምን ለማጎልበት ጥረት ይደረጋል፡፡ በዋናነትም ኢትዮጵያ ውስጥ በውጭ ኩባንያዎች በሚሰሩ ማንኛውም ፕሮጀክቶች አማካኝነት የእውቀት ሽግግር እንዲመጣ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው፡፡

የኤሌክትሮኒክስ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን ማልማት ደግሞ ሌላኛው የትኩረት መስካችን ነው። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ ከኤርፎን ጀምሮ የማኑፋክቸሪንግ ውጤቶች የምታስገባው ከውጭ ነው፡፡ ለእነዚህ ቁሳቁሶች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የምታውሉ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፤ ለሌላ ልማት መዋል የሚገባው ሀብት እየወጣ ይገኛል፡፡ ይህም ምጣኔ ሀብቷን በሚፈለገው ደረጃ እንዳታሳድግ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል። በመሆኑም ይህንን ከውጭ የሚገባው የአይሲቲና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን በተወሰነ ደረጃ ለማስቀረት የሚያስችል ሥራ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃርም ፓርኩ በረጅም ጊዜ እቅዱ ይፈፅሟል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ቀድሞ በነበረው የተቋሙ አደረጃጀት ኢትዮ- ቴሌኮም ፓርኩ ውስጥ እየገነባ የነበረውን የሕንፃ ግንባታ ያቋረጠበት አብይ ምክንያት ምን ነበር? በቀጣይስ ምን ታስቧል?

አቶ ሄኖክ፡- እንደተባለው ግንባታው በወቅቱ ባለመጠናቀቁ ወጪው ከእጥፍ በላይ ጨምሮ ተቋርጧል። ኮንትራቱ የተሰጠው ለውጭ ድርጅት በመሆኑ የዶላር ጥያቄ ነበረበት፡፡ በመሆኑም መረጃው ያለኝ ይህንን ወጪ መሸከም የሚያስችል በጀት ባለመኖሩ ግንባታውን ማቋረጥ ግድ ይላል። አሁን ግን ለመስራት ዝግጁ ነን ብለው ኮንትራት እየተፈራረምን ነው፡፡

በመሰረቱ ቀድሞም ቢሆን ከፓርኩ ጋር የሊዝ ኮንትራት አልተፈራረምንም ነበር፡፡ በመሆኑም የሊዝ ኮንትራቱን ለመፈረም የህግ ጉዳዮችን ጨርሰናል። እንግዲህ የሚጠበቀው ከዚህ በፊት የተሰጠው የቻይና ኮንስትራክሽን ኩባንያ ነበር፤ ኩባንያው ለመቀጠል በተደረገው ጥረት መሰረት ሕንፃው ይጠናቀቃል፤ ነገር ግን የታወቀው ከተያዘለት በጀት እጥፍ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑ ከዚህ የቻይና ድርጅት ጋር ድርድር እየተደረገ ነው፡፡ ይሄ ድርድር በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንዲገባ እኛም እየተከታተልን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ታዲያ ኢትዮ ቴሌኮም ግንባታውን አጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ ምን ምን ነገሮች ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል?

አቶ ሄኖክ፡– የአይ.ሲ.ቲ ኢንዱስትሪ አንዱ ምሰሶ ቴሌኮም ነው፡፡ በዋናነት ኢትዮ ቴልኮም ለአይ.ሲ.ቲ ኢንዱስትሪ የሚያደርገው ድጋፍ መካከል የአይ.ሲ.ቲ መሰረተ ልማት መዘርጋት ተጠቃሽ ነው፡፡ በመሆኑም የኢትዮ ቴሌኮም ወደ ፓርኩ መምጣት ተከትሎ ሌሎች ከእርሱ ጋር የሚሰሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎችም ወደ እዚህ ይሳባሉ ማለት ነው። ይህም የፓርኩን አቅም ከፍ ለማድረግ ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ወደ ፓርኩ ለመግባት ጥያቄ አቅርበው የገቡ አዳዲስ ድርጅቶች በምን በምን መስክ እየሠሩ ነው?

አቶ ሄኖክ፡– ወደ አይ.ሲ.ቲ ፓርክ ለመግባት ሶስት ዘርፎች ያሉ ሲሆን፤ ተጨማሪ አምስት የልማት የትኩረት አቅጣጫዎች አሉ፡፡ እነዚህ ዘርፎችም አስቀድሜ እንደገለፅኩት ቢዝነስ ፕሮሰስ አውትሶርሲንግ (ቢፒኦ)፤ አይ.ሲ.ቲ ሰርቪስ ፤ ኤሌክትሮኒክስ ዘርፎች ናቸው። ቢፒኦ ሲባል ሀገር ውስጥ ሆኖ የአይ.ሲ.ቲ አገልግሎት ለውጭ ሀገራት መሸጥ ማለት ነው፡፡ የአይ.ሲ.ቲ መሰረተ ልማት፤ ሶፍትዌር መሸጥ፤ ማማከርና የመሳሰሉት ሥራዎች የሚከናወንበት ነው፡፡ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችም የሚያመርቱም ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ አዳዲሶቹ ኩባንያዎች በእነዚህ ሶስት ዘርፎች ውስጥ መርጠው መሰማራት የሚችሉበት እድል አለ፡፡

ሌላው ድርጅቶቹ ለእነዚህ ሥራዎች አስቻይ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ሲባል በተጠቀሱት ዘርፎች ላይ የሚያቀርበው ዕቅድ (ፕሮፖዛል) በተለይ የሥራ እድል ከመፍጠር አንፃር ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ነው፡፡ በተጨማሪም ብቁ የሰው ኃይል በመፍጠር፤ ከውጭ የሚገባውን ከመተካት እና ወደ ውጭ በመላክ ረገድ፤ በቴክኖሎጂ ሽግግርና አጠቃላይ በኢኮኖሚው ላይ ያላቸው አስተዋፅኦ የሚያሳይ ሥራ ይዘው ከቀረቡ በፓርኩ ውስጥ ከሚገኙ ሕንፃዎች ወይም መሬት በሊዝ ተከራይተው መስራት ይችላሉ፡፡

በዚህ ረገድ የሊዝ ዋጋ በጣም ከፍ ያለ በመሆኑ ማሻሻያ ሰርተን ወደ ቦርድ ልከናል፡፡ ማሻሻያው እስኪተገበር ድረስ በነበረው እየሰሩ፤ ፀድቆ ወደ ትግበራ ሲመጣ ደግሞ በተሻሻለው ተመን እንደሚሰሩ ውላቸው ላይ ተካቷል፡፡ በዚህ መሰረት አዳዲስ የገቡት ድርጅቶች በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ሥራ እንደሚጀምሩ ይጠበቃል፡፡ ከዚያ በኋላ ፓርኩ የተሰጣቸውን ተልዕኮ ያሳካሉ ተብሎ ይታመናል፡፡ በተለይ ከውጭ የሚገባውን ምርት በመተካት ሀገሪቱ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማዳንና አገልግሎትን በመሸጥ ለሀገር ጥቅም እንዲያስገቡ ይታሰባል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ፓርኩ ሲቋቋም በዋናነት ሶፍትዌር በመገንባት ረገድ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት ነበር፤ አሁን ላይ ያ ተስፋ ምን ላይ ደረሰ?

አቶ ሄኖክ፡- እንደተባለው ፓርኩ ከሚሰጣቸው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎቶች ውስጥ አንዱ ሶፍትዌር ልማት ነው፡፡ ስለዚህ በዋናነት ከውጭ የምናስገባውን ሶፍትዌር እዚሁ ማስቀረት ነው፡፡ በዚህ ረገድ የመጀመሪያና ዋነኛው ትኩረታችንም ሶፍትዌር ማልማት ነው፡፡ ምክንያቱም ደግሞ ሃርድ ዌር የምንለውና የአይ.ሲ.ቲ ግብዓትን ማምረት ላይ ብዙ የሚቀረን በመሆኑ ነው፡፡ ግን ደግሞ ከውጭ የሚገባውን በአምስት ዓመታት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ለመተካት አቅደናል፡፡ በሶፍትዌር ልማት ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ የምናሳካው በመሆኑ ትኩረት አድርገን እየሰራንበት ነው፡፡ አሁን ካሉት ድርጅቶች ውስጥ የተወሰኑት ወደዚህ ልማት ዘርፍ የገቡ ናቸው፡፡

ከዚህ ቀደም ገብተው ያለሙ አሉ፡፡ ለምሳሌ ከገባ አስር ዓመት የሆነው ድርጅት አለ፤ በእነዚህ ዓመታት ይሄ ድርጅት ሲሰራ የነበረው ሶፍትዌር ልማት ላይ ነው፡፡ ከሰራቸው ሥራዎች ውስጥ የመሬት ማኔጅመንት ላይ የካዳስተር ሥራ፤ ሴፊቲኔት፣ ጤና ላይ የክትትልና ቁጥጥር ሶፍትዌር የሰራው ይሄ ድርጅት ነው፡፡ በተጨማሪም 3ሚሊዮን የማይክሮ ፋይናንስ ተበዳሪዎችን ወደ ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ለማስገባት ፕሮጀክት አሸንፎ እየሰራ ነው፡፡ ስማቸው ጎልቶ አይውጣ እንጂ ሌሎችም አሉ፤ ከፊሎቹ ኔትወርክ ላይ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ የማማከር አገልግሎት የሚሰጡ አሉ፡፡

ያም ቢሆን ግን ፓርኩ ሲቋቋም ይዞት ከተነሳው ራዕይ አንፃር አሁን እየተሰራ ያለው በቂ የሚባል አይደለም። እንደሚታወሰው ደግሞ በአስር ዓመት ውስጥ 300 ሺ ሰው ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል። አሁን ላይ መፍጠር የተቻለው የሥራ እድል ሁለት ሺ እንኳን አይሞላም።

ስለዚህ ፓርኩ አንዱ አልተሳካለትም የምንለው የትኩረት ላአቅጣጫ ከሥራ እድል ፈጠራ አንፃር ነው። አሁን የመንግሥት ውሳኔ ከኢንዱስትሪያል ፓርክ ኮርፖሬሽን ራሱን ችሎ እንዲደራጅ የተፈለገበት ዋነኛ ዓላማ ዘርፉን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግና እንደታለመው ከፍተኛ የሥራ እድል ለመፍጠር ነው፡፡ በአሁኑ ያለውን ከ1ሺህ 200 የሥራ እድል በሶስት ዓመታት ውስጥ አስር ሺ ለማድረስ እንዲያገኙ አቅደን እየሰራን ነው፡፡ እንደተባለው በአስር ዓመት ውስጥ 300ሺውን ለማሳካት እንተጋለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- መንግሥት በ2025 ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመፍጠር እየሠራ ላለው ሥራ የፓርኩ ሚና ምንድን ነው?

አቶ ሄኖክ፡– አስቀድሜ የጠቀስኳቸው ሥራዎች በሙሉ የዲጂታል 2025 ስትራቴጂ ውጤቶች ናቸው። ስትራቴጂው አንዱ ያስቀመጠው ቢፒኦ ነው፤ በዚህም የሥራ እድል መፍጠር፤ አገልግሎትን ወደ ውጭ ልኮ የውጭ ምንዛሬ ማምጣት ነው፡፡ ሁለተኛው የሰው ኃይል ልማት ነው፡፡ ሁለተኛው በስትራቴጂው ጎልቶ የወጣው የሰው ኃይል ልማት ነው፤ የሰው ኃይሉን በስፋት ማሰልጠንና ወደ ሥራ ማስገባት ነው፡፡ ሶስተኛው ኢትዮጵያን በቴክኖሎጂ አቅም ማሳደግ ነው፡፡ አራተኛው አዳዲስ ሥራ ፈጣሪዎችን የተመቻቸ ሁኔታ በማምጣት ወደ ልማት እንዲገቡ ማድረግ ነው፡፡ ሌላኛው የቴክኖሎጂ ሽግግር ማምጣት ነው፡፡ እንደ አጠቃላይ ፖሊሲውን ለማስፈፀም የተቋቋመ ድርጅት እንደመሆኑ ኃላፊነቱ ትልቅ ነው ማለት እንችላለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- ፓርኩ ለሀገር የውጭ ምንዛሪን በማስገባት ረገድ ምን አይነት ሚና እየተጫወተ ነው?

አቶ ሄኖክ፡- አስቀድሜ እንደገለፅኩት አሁን ላይ ፓርኩ በአዲስ መልክ እየተደራጀ እንደመሆኑ በስፋት የሚጠቀስ ገቢ እያስገኘ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ለጊዜው ወደ ውጭ መላክ የምንችለው የሰው እውቀትን ብቻ ነው፤ ወጣቶች እዚህ ሆነው ሥራ እየሠሩ የውጭ ምንዛሪ ለሀገራቸው እንዲያስገቡ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረግን ነው፡፡ በመካከለኛ ጊዜ እቅዳችን ግን ሶፍት ዌር በስፋት በማልማት ሀገርን ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት አድርገን እየሠራን ነው፡፡ በረጅም ጊዜ ደግሞ ኤሌክትሮኒክስ አምርተን ከእኛ አልፈን የአፍሪካን ገበያ የመቆጣጠር ዓላማ አለን፡፡

ለዚህ ደግሞ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት የፈረመች በመሆኑ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል፡፡ ሆኖም ወደፊት የሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ምርት እዚህ ሀገር ገበያ ላይ እኩል የሚስተናገድበት ሁኔታ ስለሚፈጠር ከወዲሁ ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል። ደግሞም ኢትዮጵያ ካላት ሕዝብ ቁጥር አኳያ አብዛኞቹ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ገበያ ይፈልጉታል፡፡ ያኔ ተወዳዳሪ መሆን ካልቻልን ከባድ ይሆናል፡፡ እየሰራን ያለነው በሚቀጥለው አምስት ዓመት ውስጥ ይህንን አቅም መገንባት አለብን ብለን ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ኩባንያዎች አቅም እንዲፈጥሩ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- መንግሥት ከአምስቱ ምሰሶዎች አንዱ ቴክኖሎጂን አንዱ ማድረጉ ለዘርፍም ሆነ ለፓርኩ ሥራ ምን አስተዋፅኦ ይኖረዋል?

አቶ ሄኖክ፡– የዘረዘርናቸውን የልማት መርሀ ግብሮች ለማሳካት የመንግሥት ትኩረት ወሳኝ ነው። አንድ ተቋም የሀገሪቱ ቴክኖሎጂ አቅም እንዲሆን ለማድረግ የመንግሥት ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ ደግሞም ሁለት መቶ ሄክታር መሬት አዲስ አበባ ውስጥ አጥሮ ማስቀመጥ ቀላል ነገር አይደለም። ከዚያ ይጀምርና ይህ ቦታ እንደ መብራት፣ ቴሌ ፣ ውሃ፣ መንገድና መሰል በመሰረተ ልማትና ለሥራው የሚያስፈልጉ ሕንፃዎችን እንዲሞላ የማድረጉ ኃላፊነት ነው፡፡ ስለዚህ የመንግሥት የተመረጠ የልማት መስክ ባይሆን ኖሮ ፓርኩ ራሱ እውን መሆን ባልቻለ ነበር፡፡

አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ሀገሪቱም ሆነ ሕዝቡ ከዚህ ተቋም ምን ይጠብቅ?

አቶ ሄኖክ፡– ፓርኩ አንዱ የገጠመው ነገር የመሬትም ሆነ የሕንፃ ሊዝ ዋጋ ውድ መሆን ነው፡፡ በተጠናው ጥናት መሰረት ለሀገር ውስጥ ቀርቶ ለውጭ ድርጅቶችም ጭምር ውድ ነው፡፡ በተለይ የማምረቻ ኢንዱስትሪን ለመሳብ የሚያስችል አይደለም፡፡ ለምሳሌ ቴክኖ ድርጅት እያመረተ ያለው ከጠቅላላ አቅሙ ከግማሽ በታች ነው። መሠረታዊ ችግሩ የዶላር እጥረት ነው፡፡ ሌላው ፓርኩ አጥር የሌለው በመሆኑ የደህንነት ጉዳይ ስጋት አለበት። ምክንያቱም የመሬት ወረራ ያጋጠመው በመሆኑ ነው። መንግሥት ከከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች የተሰጠንን ትኩረት ያህል ተቋሞችም ሆነ ኃላፊዎች ሙሉ ትኩረት ሰጥተውታል ብዬ አላምንም፡፡ በእርግጥ አንዳንዱ ትኩረት የማይሰጠው ከመረጃ እጥረት የተነሳ ነው፤ ሌላው ደግሞ ካለመናበብ የሚመነጭ ችግር ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን ይህ ፓርክ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን ጭምር የማያውቅም አለ፡፡ በመሆኑም እዚህ ፓርክ ውስጥ ያለው ሀገራዊ አቅም ሊታወቅና ለስራው ስኬት መደገፍ ይገባዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡

በዋናነት ፓርኩ በቀጣይ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን በመጠቀም የታለመለትን ግብ ለማሳካት መትጋት ይጠበቅበታል፡፡ ይህም ግቢውን ለሥራም ሆነ ለኢንቨስትመንት ሳቢና ምቹ ከማድረግ ይጀምራል። ፀጥታውን ማስጠበቅና ለኩባንያዎቹ የሚያስፈልገውን አገልግሎት መስጠት አለብን፡፡ ለምሳሌ ከከተማ ወጣ ያለ በመሆኑ የትራንስፖርት፣ የምግብ አገልግሎት መስጠት አንዱ ሥራ ነው፡፡ እነዚህን ሥራዎች ለማከናወን ከፍተኛ የፋይናንስ እጥረት አለብን፡፡ ኃላፊነቱን ስንረከብ የተነሳነው ከዜሮ ነው፤ ግን አሁን ላይ ኦፕሬሽናል የሆኑ ሥራዎችን እየሰራ ያለው ሙሉ ለሙሉ ራሱን ችሎ ነው፡፡ ግን ደግሞ ትልልቅና ሰፊ የሰው ኃይል የሚፈጥሩ ኩባንያዎችን የመፍጠር ራዕዩን ለማሳካት ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስ ድጋፍ ያስፈልገዋል፡፡ በዚህ ዘርፍ ሀገር የሚኮራበት የአይሲቲ ኩባንያ የመፍጠር ሂደቱ አሁንም ርብርብ ይሻል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ሄኖክ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን የካቲት 14/2016

Recommended For You