ይህቺ “ዳግም”የምትባል ቃል በአንድ ወቅት የወቅቱን የቃላት ገበያ ምንዛሪ ተቆጣጥራ እንደነበር ይታወሳል። በተለይ ወደ ትምህርት ሚኒስቴርና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (የግል) አካባቢ የዘወትር ፀሎት እስከ መሆን ደርሳ እንደነበር ሁላችንም፣ ለአቅመ ማወቅ የደረስን ሁሉ እናስታውሳለን።
በተለይም በዘጠናዎቹ መጨረሻና በሚሌኒየሙ መግቢያ አካባቢ የእንትና ኮሌጅ “ዳግም እውቅና አገኘ”፤ እንቶኔ ዩኒቨርሲቲ “የዳግም እውቅና ፍቃድ ተሰጠው”፤ “እንትና ሕንፃ ሦስተኛ ፎቅ ላይ ሦስት ክፍሎችን ተከራይቶ ‘እንትና ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት’ በሚል ስያሜ ተማሪዎችን ተቀብሎ ሲያስተምር የነበረው ተቋም ተነጥቆ የነበረው ፍቃዱ ተመልሶለት ዳግም እውቅናን በማግኘት ወደ ሥራ ገብቷል”(ይህ ባለ ሀበት “ልጆቹ ስፖርት የሚሰሩት የቱ ጋ ነው?”ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ፣ “እሱን እያሰብንብት ነው”ሲል የሰጠው መልስ እስከ ዛሬም ድረስ ብዙዎችን እንዳሳቀ ነው።)
መቼም የትምህርትን ነገር ትምህርት ያነሳዋልና ነው እንጂ ከላይ ያሉትን ወደ ማስታወስ ያዘገምነው የዛሬዋ “ዳግም”ከእነዛኛዎቹ “ዳግሞች”ጋር የምትገናኝ ሆና አይደለም። “ይገናኛሉ”ማለት ግድ ከሆነ እንኳን፣ በአንድ ወቅት ታግደው የነበሩ መሆናቸው ሲሆን፤ በማን?፣ ለምን?፣ እንዴት? ወዘተ በሚለው ይለያያሉና ግንኙነታቸው ከሴማንቲክስ የሚያልፍ አይሆንም።
ዳግም ወደ ተግባር ወደ ገባው፣ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል ከመሄዳችን በፊት ስለ ባህል ማዕከላት፤ ወይም የባህል ማዕከላትና የትምህርት ተቋማት ትስስር አንዳንድ ሃሳቦችን እናንሳ።
በግልፅ እንደሚታወቀው ሁለቱም ማኅበራዊ ጉዳዮች ናቸው። ሁለቱም የማንነት መገለጫዎች ሲሆኑ፤ ሁለቱም የእውቀት ምንጮች፣ ሁለቱም ማኅበራዊ ተሳትፎን ግድ የሚሉ ናቸው።
የባህል ማዕከላትና የትምህርት ተቋማት ተመጋጋቢዎች ሲሆኑ፤ ሁለቱም ተደጋጋፊዎች ናቸው። ሁለቱም ሀገር እንደ ሀገር እንዲቆምም ሆነ ሀገር እንደ ሀገር ሆኖ ወደ ፊት እንዲራመድ አስፈላጊዎች ሲሆኑ፤ ሁለቱም የአንድ ሀገር የወደ ፊት አዝማሚያ ጠቋሚዎች ናቸው። ባይሆኑ ኖሮ ባህላዊ እውቀት፤ ባህላዊ ትምህርት፤ ባህላዊ መድኃኒት፤ ባህላዊ እሴት (ቁሳዊም፣ መንፈሳዊም)፤ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ወዘተ ይሉ ጉዳዮች ባልኖሩም ነበር።
ባህል የማንነት መገለጫ ባይሆን ኖሮ እነ “ሄቦ”(በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከሚገኙ ማኅበረሰቦች አንዱ የየም ማኅበረሰብ ዘመን መለወጫን የሚቀበልበት፤ ግጭት የሚፈታበት፣ ሰላም የሚሰፍንበት፤ እንዲሁም በድብቅ የተሠሩ ወንጀሎች የሚጋለጡበት ሥርዓት) ባልነበሩም ነበር፤ ባህል፣ ሳይንስ ∙ ∙ ∙ አንድነት፣ ትስስር፣ ተደጋጋፊነት ወዘተ ባይኖራቸው ኖሮ እነ ዩኔስኮ (የመጀመሪያዋ አባልና፤ ከአፍሪካ ቅርሶችን በዩኔስኮ በማስመዝገብ ቀዳሚዋ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ 195 አባል ሀገራት ያሉት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት)ን የመሳሰሉ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ተቋማት ባልተፈጠሩም ነበር። ወደ ሀገራችን ስንመጣም ያውና ተመሳሳይ ነው።
ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በስሩ በሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል አማካኝነት ሰኔ 2010 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ”የባህል ማዕከላት ሚና ለኢትዮጵያዊነት ግንባታ” እና ”በኢትዮጵያዊነት ፊልሞች ውስጥ ኢትጵያዊነት አለን?” በሚል ርእስ ለሁለት ቀናት የቆየ ውይይት አካሂዶ ነበር። በውይይቱም በርካታ ጥናቶች የቀረቡ ሲሆን፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ታድመው ነበር።
ከጥናት አቅራቢዎቹ አንዱም ሠዓሊና ቀራፂ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን ሲሆኑ፣ “የባህል ማዕከላት የሰው ልጅ የፈጠራ ጥበባት መለማመጃ ቦታዎች በመሆናቸው፤ ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆኑ ማንኛውም ዜጋ ሊጠቀምባቸው መቻል አለበት። ይህም ተግባራዊ መሆን ሲጀምርና የባህል ማዕከሉ በመደበኛነት ሁሉንም ማገልገል ሲጀምር የሚጠበቀውን ማየት እንጀምራለን”በማለት ነበር የባህል ማዕከላትን አስፈላጊነት ያስረዱት።
በዚሁ መድረክ ለአንድ ሀገር ሕዝቦች የባህል እና የኪነ ጥበብ እድገት የባህል ማዕከላት ሚና ከፍተኛ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ሽመልስ “የአንድ ሀገር የባህል ማዕከል የሕዝቦቿ የባህላቸው ውጤት በመሆናቸው በተለይም እንደ እኛ ሀገር ብዝሃ ባህል ያለን ሕዝቦች ስንሆን የባህል ማዕከላት ሚና ላቅ ያለ ነው። በመሆኑም በዘርፉ የሚጠበቀውን ውጤት ለማስመዝገብ እንዲህ ያሉ ውይይቶችን ከባለድርሻ አካላት ጋር መወያየቱ ጠቃሚ ነው”በማለት መናገራቸው፤ የወቅቱ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ወይዘሮ ፎዚያ አሚን በበኩላቸው፤ “የሀገር ግንባታ በብዙ አስተሳሰቦች፣ እውቀቶችና ጥረቶች የሚመጣ ነው። በኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል አዘጋጅነት የሚደረገው ይህ ውይይት እንደ ፌዴራል ተቋም ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ጉዳዮች ለመሥራት የጀመርነው እንቅስቃሴ ማሳያ ነው”ማለታቸው በወቅቱ ሰፊ የመገናኛ ብዙኃንን ሽፋን ማግኘቱ ይታወሳል።
በመሆኑም፣ ባህልን፣ ትምህርትን፤ እንዲሁም፣ የባህል ማዕከላትን እና የትምህርት ተቋማትን ነጣጥሎ ማየት ከመክሰር ያለፈ ትርፍ የለውም ማለት ይሆናል።
ለመግቢያ ያህል ይህንን ካልን ወደ አአዩ ባህል ማዕከል እንመለስ። ማለትም:-
“በተማሪዎች ጥያቄ በኪነ ጥበብ አፍቃሪያን ውትወታና በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቀና ትብብር ባለፈው ኅዳር 13 ቀን 2016 ዓ.ም አንጋፋ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ አርቲስቶችና የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በተገኙበት ከአሥር ዓመት መዘጋት በኋላ ዳግም ወደ ሥራ መመለሱ ይፋ ተደርጓል፡፡”የሚል ዜና ተነግሮለት ወደ ነበረው፤ ወደ ሥራ ከተመለሰ በኋላ ከጥር 8 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በየሳምንቱ ረቡዕ ምሽት ልዩ የሆነ የኪነ ጥበብ መሰናዶ ማቅረብ ወደ ጀመረው (ተማሪዎች ግጥሞችን፣ ተውኔቶችንና ሙዚቃን እያዘጋጁ ለታዳሚዎች በማቅረብ ላይ ወዳሉበት)፤ በሀገሪቱ ኪነጥበብ ታሪክ ውስጥ ዘመን የማይሽረው መሠረትን ወደ ተከለው፣ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል (በቀድሞ ስሙ የአፄ ኃይለሥላሴ የባህል ማዕከል) ዳግም ወደ ተግባር መመለስ እንመለስ።
የሀገሪቱን ባህልና ጥበብ ከማበልፀግ አንፃር ከፍተኛ ሚናን ሲጫወትና የድርሻውን ሲወጣ የነበረው የአአዩ ባህል ማዕከል ታሪክ እንደሚያስረዳው፣ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ-መንግሥት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲቋቋም መጋዘን የነበረን ቤት ወደ አዳራሽነት በመቀየር የባህል ማዕከሉን ማቋቋም ተቻለ። ምክንያቱ ደግሞ በወቅቱ በሀገሪቱ የነበሩ የኪነ-ጥበብ ተቋማት ከቁጥር የማይገቡ ስለነበሩ፤ የባህል ማዕከሉ መቋቋም፤ በዩኒቨርሲቲውና ከዩኒቨርሲቲው ውጪ የሚገኘውን ማኅበረሰብ ከጥበብ ማዕድ ተቋዳሽ ማድረግን መነሻ ያደረገ ነው።
ቀድሞ በባህል እና ኪነጥበባዊ ቅርሶች ጥበቃ እና ስነዳ ዙሪያ በርካታ ሥራዎችን ይሠራል ተብሎ በሚጠበቀው የባህል ማዕከል ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ የጥበብ ሰዎች (Alumni) መካከል በርካታ ለሀገርም፣ ለዓለሙም የተረፉና አንቱ የተባሉ የኪ(ሥ)ነጥበብ ሰዎች ያሉ ሲሆን፣ ዐሻራቸውም በባህል ማዕከሉ ላይ ሰፍሮ ይገኛል።
“በዚህ አንጋፋ የጥበብ ማዕከል ከዚህ በፊት እነ ማን ነበሩ?”የሚል ጥያቄ ለሚያነሱ የጥበብ ቤተሰቦችም መልስ ያለ ሲሆን፣ እንደ ማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ እሸቱ ማብራሪያ “የጋሽ ፀጋዬ ገብረመድህን፣ የጋሽ አባተ መኩሪያ፣ የጋሽ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር፣ የጋሽ ዮሐንስ አድማሱ፣ የጋሽ መንግሥቱ ለማ ቤት ነበር።″
ከሰሞኑ፣ ማዕከሉን ከተመለከቱ ዐቢይት ጉዳዮች መካከልም አንዱ እና ምናልባትም ዋና ሆኖ ሲሰማ የነበረው “ማዕከሉ ከመቼውም በላይ የራሱን ዐሻራ ለማሳረፍ ቤቱን ወለል አድርጎ እየጠበቃችሁ ነው። ደራሲያን ኑ፤ ድርሰታችሁን አቅርቡ፤ ፀሐፊያንም ፃፉ፤ አዘጋጆችም ቴአትራችሁን አዘጋጁ፤ መለማመጃ ስፍራ አጥታችሁ በየቦታው ያላችሁ የኪነ ጥበብ አፍቃሪያንና አማተር ተዋንያን እባካችሁ ኑ፤ ማዕከሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ ክፍት ነው”የሚለው የዋና ዳይሬክተሩ ጥሪ ሲሆን፤ ብዙዎችም ጥሪውን በደስታ እንደተቀበሉት ለሚዲያ ሲሰጡት ከነበረው አስተያየት ለማወቅ ተችሏል።
ይህ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰርከስ ማኅበር ጥምረት ጋር በጋራ መሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሥምምነት የተፈራረመው (ኅዳር 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ሰርከስ ማኅበር ጋር በመሆን ታላቅ የኪነ ጥበብ ምሽት አድርጓል) የአአዩ ባህል ማዕከል፣ ልክ ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፣ በ“ሐዲስ ዓለማየሁ የባህል እና የምርምር ተቋም”አማካኝነት፣ “ኢትዮጵያ ያላት ጥንታዊ የታሪክ፣ ሥነጥበብ፣ የእምነት፣ የሥልጣኔ፣ የሥነጽሕፈት፣ ኅብር ያለው የብሔር ብሔረሰቦች ባህል፣ ሀገር-በቀል ዕውቀት፣ የሥነጽሑፍ እና የሥነ ዜማ ቅርስ፣ የሕዝቡ ማኅበራዊ አኗኗር፣ ወዘተ በአግባቡ እንዲጠና፣ ዕውቅና እንዲያገኝ፣ እንዲደነቅ እና ከዘመናዊ ሥርዓተ ትምህርት ጋር ተቀናጅቶ ለመማር ማስተማሩ ሒደት አገልግሎት”መስጠት ላይ እየሠራሁ ነው እያለ እንዳለው ሁሉ፤ እንደ እናት ዩኒቨርሲቲነቱ የበለጠ ይሠራል ተብሎ ይጠበቃልና ይህንንም ከዚሁ ጋር ሰንቆ ሊሄድ ይገባል።
“በባህል፣ በሥነ ጥበብ፣ በቋንቋ፣ በሥነጽሑፍ፣ በቅርጻ ቅርጽ፣ በቤተ መዘክር (ሙዚዬም)፣ በሥነ-ሙዚቃ፣ በግዕዝ ምርምር ዘርፎች ላይ ፍላጎቱ፣ ችሎታው እና ሙያዊ ክሂሎቱ ላላቸው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አባላትና ለአካባቢው ሕዝብ ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችን”መስጠትን ዓላማው አድርጎ እንደ ተነሳው ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ (በጉዳዩ ላይ እየተጋ ያለውን፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ)፣ አአዩም የበለጠ በማድረግ ይወጣዋል የሚለው የብዙዎች አስተያየት ነው። የባህል እና የሥነጥበብ ቅርስ ጥበቃ እና ስነዳንም በተመለከተ እንደዚያው።
የኅብረ-ባህል (የሰው ልጆችን ሁሉ የጋራ ቅርስ የያዘ) መገለጫ የሆኑት የባህል ማዕከላት፣ በተለይም የከፍተኛ ትምህርት የባህል ማዕከላት ለከፋ የፖለቲካ ሸመታ መሣሪያ (አንዳንድ ጸሐፍት “የፖለቲካል ቁስ”ሲሉ ነው የሚገልጿቸው) እና ለእርስ በእርስ ግጭት የዋሉትን፣ “ባህል”እና “ቋንቋ”ን መሠረት ያደረጉ ግንዛቤዎችን ለኅብረተሰቡ በማስጨበጥ ሁሉም አደብ እንዲገዛና ወደ ቀልቡ እንዲመለስ በማድረግ በኩል የሚያደርጉት አስተዋፅኦ ከዚህ በመለስ የሚባል አይደለም። ከዚህ አኳያ የአአዩ የባህል ማዕከልም በዚሁና ሌሎች መሰል ተግባራቱ ብዙዎችን ወደ ቀልባቸው ይመልሳል ተብሎ ይጠበቃል።
ወደ ፊት በኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ታሪክ ብቻ ሳይሆን በዓለምአቀፍ ደረጃ በፈጠራ ሥራዎቻቸው፣ በዲፕሎማሲ ችሎታቸው፣ በሀገር አስተዳደር ብቃታቸው፣ በጦር ሜዳ ውሎና የአርበኝነነት ተጋድሏቸው እጅግ ከፍተኛ ክብር፣ አበርክቶ ያላቸውና ስመ ገናና ሰብዕናዎች ስምና ሥራዎቻቸው ይነሱበታል ተብሎ የሚጠበቀው የአአዩ የባህል ማዕከል በጀትና የሰው ኃይሉ በይፋ ተወስዶበት ተቋማዊ ማንነቱ በጠራራ ፀሐይ ተነጥቆበት አመታትን ቢያስቆጥርም (መቼም ግፍ ነው የተሠራው)፤ ከዚያ ሁሉ በማገገም፣ በፍጥነት ወደ ነበረበት በመመለስ ታሪክ እንደሚሠራ ቀደም ሲል በማዕከሉ ያገለገሉ ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም የጥበብ፣ ባህል፣ እውቀትና እውነት አድናቂዎች ሁሉ ተስፋና ምኞት ነው።
የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ እንደሚሉት የባህል ማዕከሉ በኪነ ጥበብ ዘርፍ ዘመን ተሻጋሪና የማይረሱ ሥራዎችን በማከናወን አስተዋጽኦው የላቀ ነው።
በ1956 ዓ.ም የተቋቋመውና በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ የኪነ-ጥበብ ማሰልጠኛ ማዕከል መሆኑ የሚነገርለት ማዕከሉ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ባልተስፋፉበት ጊዜ ድንቅ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ያኖረ መሆኑን ያስታወሱት ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ፥ የማዕከሉን የኪነ-ጥበብ ምሽቶች እንደገና ማስጀመሩ ለዘርፉ እድገት ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።
የባህል ማዕከሉ በሀገሪቱ በርካታ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን በማፍራት ባለውለታ መሆኑን፤ ከሌሎች የኪነ ጥበብ መፍለቂያዎች የሚለየው ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ ባለተሰጥኦዎች ገጣሚዎች፣ ዘፋኞችና ሌሎችም የኪነ ጥበብ ዝንባሌ ያላቸው ተማሪዎች በኅብረት የሚገኙበት መሆኑን የሚናገሩት የባህል ማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ እሸቱ (ረዳት ፕሮፌሰር) እንደሚናገሩት ከሆነ፣ በማዕከሉ የሚቀርበው ሳምንታዊ ፕሮግራም በጉጉት የሚጠብቁትና የሚናፍቁት ምሽት እየሆነ መጥቷል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስመጥር እንዲሆን ካደረጉት ተቋማት መካከል ፈር ቀዳጁ የባህል ማዕከሉ ነው የሚሉት ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ እሸቱ ለዘርፉ እድገት አሁንም የራሱን ዐሻራ በማኖር አስተዋጽኦ ለማድረግ በየሳምንቱ ማክሰኞ፣ ሐሙስና ቅዳሜ ፊልም የሚያሳይ ሲሆን በቀረቡት ፊልሞች ላይ በወር አንድ ጊዜ ውይይት ይደረጋል።
በማዕከሉ በቋሚነት የሚስተናገዱ ፕሮግራሞች ያሉ ሲሆን፣ አንዱም ‹‹የአንድ ግጥም የአንድ ወግ እንግዳ›› የሚለውና፣ አንጋፋ የኪነ ጥበብ ሰዎች በየሳምንቱ የሚጋበዙበት፣ እውቅ አርቲስቶች ሥራቸውን የሚያቀርቡበት ፕሮግራም እንደሆነ ከኃላፊዎቹ ማብራሪያዎችና ካለፉት ፕሮግራሞች ለማወቅ ተችሏል። ከሰላሳ በላይ ባሉ የዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከላት የሚገኙ ተማሪዎች በአንድነት ሆነው የየራሳቸውን ሥራዎች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተሰባስበው የሚያቀርቡበት ፌስቲቫል እንዳለም እንደዚያው።
እስካሁን ባለው ሁኔታ፣ ታዋቂ የኪነጥበብ ሰዎች (አዜብ ወርቁ፣ ገነት ንጋቱ፣ ግሩም ዘነበ፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ሰለሞን ቦጋለ እና ሌሎችም) “የአንድ ግጥም የአንድ ወግ እንግዳ”በሚለው የወሩ የኪነ ጥበብ ምሽት መድረክ ላይ በመገኘት ሙያዊ ምክርና አስተያየታቸውን የሰጡ መሆኑን ከባህል ማዕከሉ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሪፖርተር ጋዜጣ እንደዘገበው፣ የአዲስ አበባ የተማሪዎችና የአስተዳደር ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አብዱራዛቅ መሃመድ (ዶ/ር) በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፣ በኢትዮጵያ መደበኛ የባህል ፖሊሲ ከመርቀቁ በፊት ሀገራዊ ውክልና ያለው ተቋም እንደሆነ መስክረዋል፡፡ ፈር ያለው የቋንቋ ፖሊሲ ከመታሰቡ በፊት የቋንቋዎች እኩልነት ሲቀነቀንበት የነበረ፣ የሐሳብ እኩልነትና ነፃነት እምብርት ከመሆኑ ባሻገር፣ መልክ ያለው የኪነ ጥበብ እንቅስቃሴ ከመስፋፋቱ በፊት ተፅዕኖ ፈጣሪ ጠቢባን ያፈራ የባህል ማዕከል መሆኑንም በደማቁ አስምረውበታል።
እንደ ዶ/ር አብዱራዛቅ የወቅቱ ንግግር ማዕከሉ ሀገራዊ እሴቶችን ከፍ የሚያደርጉ፣ የትውልድን አካዳሚያዊና ሥነ ምግባራዊ ሰብዕና የሚያድሱና የሀገር ፍቅር ስሜትን የሚያላብሱ፣ ልዩነትን በወል እሴቶች የሚያስተሳስሩ፣ እያዝናኑ የሚያስተምሩ ሀገራዊ ግጥሞች፣ መዝሙሮች፣ ሙዚቃዎችና ቴአትሮች ሲቀርቡበት ቆይተዋል። አሁንም አድማሱን በማስፋት በመላ ሀገሪቱ ተደራሽ ለመሆን እየሠራ ይገኛል፤ በሂደትም ወደ ዓለም አቀፍ መድረኮች።
በቅርቡ በሀገራችን የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ የሆነው፤ ለብዙ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች መነሻ በመሆን ለበርካታ አሠርት አመታት የኪነ ጥበብ መፍለቂያ የሆነው፤ ለኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከተው፤ ዕውቅ ከያኒያን የማይፋቅ ዐሻራቸውን ያሳረፉበት፤ ከ“እንኳን ደስ አላችሁ!!!”ጀምሮ የማይደበዝዝ ትዝታቸውን ያኖሩበት የአአዩ ባህል ማዕከል ዳግም ወደ ሕይወት፤ ካለ መኖር ወደ መኖር እንዲመጣ ላደረጉት ሁሉ ምስጋናችንን እያቀረብን “ከባህል ማዕከሉ ጋር ወደ ፊት!!!”በማለት የዛሬውን ዝግጅታችንን እናጠቃልላልን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም