ሰማያዊው የዳኞች ካርድ!

በየትኛውም የእግር ኳስ ጨዋታ ላይ ቢጫና ቀይ ካርዶች የተለመዱ ናቸው። ከ1970 የሜክሲኮ ዓለም ዋንጫ ጀምሮ የጨዋታ ዳኞች እነዚህን ሁለት ካርዶች ይዘው መመልከትም ለየትኛውም የእግር ኳስ ቤተሰብ አዲስ አይደለም። ከተለመዱት ሁለት አይነት ካርዶች በተጨማሪ ሶስተኛ የሆነውን ሰማያዊ ካርድ መመልከት ግን ለማንም ቢሆን እንግዳ ነው።

የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር ቦርድ (አይ.ኤፍ.ኤ.ቢ) ሰሞኑን በእግር ኳስ ጨዋታ ወቅት ዳኞች ሰማያዊ ካርድ ጥቅም ላይ እንዲያውሉ ፈቃድ ሰጥቷል። የእንግሊዝ የእግር ኳስ ማኅበርም ሰማያዊ ካርድ በ2024-25 የኤፍ.ኤ ዋንጫ ውድድር ላይ እንዲሞከር ፈቅዷል፡፡

ሰማያዊ ካርድ ሆን ብለው ጥፋት ለሚፈፅሙ ተጫዋቾች እንዲሁም በጨዋታው ዳኛ ውሳኔዎች ላይ ያልተገባ ምላሽ ለሚያሳዩ ተጫዋቾች የሚሰጥ መሆኑንም ተገልጿል።

ሰማያዊ ካርዱ ከቢጫ ካርድ ጋር ተመሳሳይ አቅም እንዳለው የተገለጸ ሲሆን፤ በጨዋታ መካከል ሁለት ሰማያዊ ካርድ የተመለከተ ተጫዋች እንደ ሁለት ቢጫ ካርድ ተቆጥሮ ከሜዳ እንዲወጣ ይደረጋል። ሰማያዊ ካርዱ ቢጫ እና ቀይ ካርድ ወደ አገልግሎት ከገቡበት ከ1970 ወዲህ ዳኞች የሚጠቀሙበት የመጀመሪያው አዲስ ካርድ እንደሚሆንም ተነግሯል። ሰማያዊ ካርድ የተመለከተ ተጫዋችም ለ10 ደቂቃ ያክል ከሜዳ ወጥቶ እንዲቆይ ከተደረገ በኋላ ተመልሶ ጨዋታውን እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው ተብሏል። አንድ ሰማያዊ እና አንድ ቢጫ ካርድ የተመለከተ ተጫዋችም በድምር ቀይ ካርድ ተሰጥቶ ከጨዋታ እንዲወጣ ይደረጋልም።

ይሁን እንጂ ይህ ነው የተባለ የሙከራ ጊዜ ያልተቆረጠለት ሲሆን፤ የእንግሊዝ የእግር ኳስ ማኅበር በ2024-25 የወንዶች እና የሴቶች ኤፍ.ኤ ዋንጫ ውድድር ላይ እንዲሞከር ፈቅዷል።

ፊፋ ‘ሰማያዊ ካርድ’ እየተባለ የሚጠራውን አዲሱን ካርድ ማጣራት እንደሚፈልግ እና የእግር ኳስ ደረጃ የተሳሳቱ እና ያለጊዜው የተከሰተ ነው ሲል አጣጥሎታል። ይህ ካርድ የሚሞከር ከሆነም በዝቅተኛ ደረጃ በሚገኙ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ላይ የተገደበ መሆን እንደሚገባው እና ሙከራውም ኃላፊነት የተሞላበት ሊሆን እንደሚገባ አሳስቧል።

በእግር ኳስ ከቢጫና ቀይ ካርድ በተጨማሪ ሌላ ካርድ አገልግሎት ላይ የማዋል ጉዳይ ዛሬ የመጣ ነገር አይደለም። ሃሳቡ በዋናነት የተጠነሰሰው በቀድሞው ፈረንሳዊ ኮከብና የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ፕሬዚዳንት ሚሼል ፕላቲኒ ነው። ይህም ‘sin bin’ ወይም ተጫዋቾች የዳኛን ውሳኔ ተቃውመው ያልሆነ ቃል ሲሰነዝሩ ወይም ምልክት ሲያሳዩ እንዲሁም ዳኛ ሲንቁ ለጊዚያዊ ቅጣት (ለ10 ደቂቃ) የሚመዘዝባቸው ካርድ እንዲሆን የታሰበ ነው። ከዚህ ባሻገር ተጫዋቾች በጨዋታ ወቅት ስፖርታዊ ጨዋነትን እንዳይዘነጉ ለማስታወስና ስፖርታዊ ጨዋነትን ለማበረታታት ዳኞች እንዲመዙት በማሰብ ነው ሃሳቡ የመነጨው።

ይህ ሃሳብ ሲመነጭ ግን ከሰማያዊ ይልቅ ነጭ ካርድ ነበር የታሰበው። ሃሳብ እስካሁን በእግር ኳስ አልተስፋፋም ወይም ተግባራዊ አልሆነም። በፖርቹጋል ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወደተግባር ለመለወጥ ጅምሮች ታይተዋል። በፖርቹጋል የሴቶች አምስተኛ ዲቪዚዮን የስፖርቲንግ ሊዝበንና ቤኔፊካ ጨዋታ ነጭ ካርድን ተግባራዊ ለማድረግ የተሞከረ ሲሆን ተጫዋቾች ስፖርታዊ ጨዋነትን ሲያሳዩ ለማበረታታት ነበር ጥቅም ላይ የዋለው።

ነጭ ካርድ እንደቢጫና ቀይ ካርድ ሁሉ ወጥ የሆነ ሕግ ተደንግጎለት በዓለም አቀፍ ደረጃ በቅርቡ ተግባራዊ ሆነው ከሚተገበሩ አዳዲስ ጉዳዮች አንዱ እንደሚሆን ተነግሮ የነበረ ቢሆንም አሁን ሃሳቡ ወደ ሰማያዊ ካርድ የተለወጠ ይመስላል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን  የካቲት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You