በማሳጅና በወጌሻነት ለብዙዎች ፈውስ የሆነች -ልበ ብርሃን ሴት

ሕይወት መልከ ብዙ ናት።ለአንዱ ብትመች ለሌላው ጎዶሎ ጎኗ ሊበዛ ይችላል ።ግን ደግሞ ሰው በሕይወት እስካለ ድረስ ሞላለትም ጎደለበትም ኑሮ ይሉትን ገመድ መጎተቱ አይቀሬ ነው።በዚህ የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ደግሞ አካል ጉዳተኝነት ሲታከልበት ምን ያህል ከባድ እንደሚሆን መገመቱ አያስቸግርም።አካል ጉዳተኝነት በራሱ ይዞት የሚመጣው ሰፊ የጤና ችግር ከመኖሩም ባሻገር ሰዎች እንደ ልባቸው ተንቀሳቅሶ መስራት ካለመቻል ጋር ተደማምሮ ችግሩ ብዙ ነው።

አካል ጉዳተኝነት በማንኛውም ጊዜና አጋጣሚ በሁሉም ሰው ላይ ሊከሰት የሚችል ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ችግሩ መከሰቱን አምኖ ሕይወትን በጥንካሬ መግፋት ለውጤት እንደሚያበቃ ብዙዎች ምስክር ናቸው፡፡

አንዳንዶች ብዙ መስራት በሚችሉበት እድሜያቸው ላይ ሆነው በሚያጋጥማቸው ቀላልም ሆነ ከባድ የአካል ጉዳት ምክንያት ቤት ለመዋል፤ ተስፋ ለመቁረጥ፤ ከእኩዮቻቸው በታች የመሆን አልፎ ተርፎም በቤተሰብና በአገር ላይ ተጨማሪ ሸክም ለመሆን ይገደዳሉ። ሌሎች ደግሞ የደረሰባቸውን ጉዳት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀምና በማመን በተሰጣቸው ልክ ሰርተው ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የጠቀሙ በርካቶች መሆናቸውን ማንሳት ይቻላል።

ለዛሬ የሕይወት ገጽታ አምዳችን እንግዳ ያደረግናት ወጣትም ለብዙ ወጣት አካል ጉዳተኞች ተምሳሌት የምትሆን ብርቱ፣ ራዕይ ያላት፤ ጉዳቷን ይዛ ቤት ውላ የሌሎችን እርጥባን ከመጠበቅ በራሷ ተንቀሳቅሳ የምትኖር ለተቸገሩ ሰዎች መፍትሔ የሆነች ናት።

ወጣት ብሌን ሰለሞን ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ከተማ መካኒሳ አካባቢ ነው።ለእናቷ ብቸኛ ልጅ የሆነችው ብሌን በጥሩ እንክብካቤ ነበር ያደገችው።ኋላም እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን ትከታታል ዘንድ በእናቷ አማካይነት መሰረተ ኢትዮጵያ ትምህርት ቤት ገባች።

ብሌን ከእኩዮቿ ጋር እየተማረች፤ እየተጫወተች በጠቅላላው አንድ ታዳጊ ሕጻን ሊያደርገው የሚገባውን ሁሉ እያደረገች በተለይም እናቷ እየተደሰቱባትና ነጋቸውን በእሷ ውስጥ እያዩ ሶስተኛ ክፍል ደረሰች።ከዚህ በኋላ ግን ብሌን ሕይወቷን ወዳልታሰበ መንገድ የቀየረ መጥፎ አጋጣሚ ወደእሷና ቤተሰቧ ጎራ አለ።

“…….እናቴ ብቸኛ ልጇም ስለሆንኩ በጥሩ እንክብካቤ ነው ያሳደገችኝ ፡፡ የምፈልገውን አሟልታ ከሰው እንዳላንስ አድርጋ ትምህርት ቤት አስገብታ ብቻ በጠቅላላው ከእናት የሚጠበቀውን ሁሉ አድርጋና ጎዶሎዬን ሞልታ ነው ያሳደገችኝ።ትምህርት ቤትም ከገባሁ በኋላ ጥሩ የትምህርት አቀባበል ነበረኝ” ትላለች።

ብሌን የሶስተኛ ክፍል ትምህርቷን እየተማረች ሳለች በአንዲት መጥፎ ቀን ከመምህሯ ጋር ትጋጫለች። በዛ በለጋ እድሜዋ ያጠፋችው ጥፋትና የተወሰደባት የቅጣት እርምጃ ግን ፍጹሞ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ብሌንን ለዘላላም የአካል ጉዳት ዳረጋት።

ልጆች በትምህርት ቤት ሊያጠፉ ሊሳሳቱ አልፎ ተርፎም ሊረብሹ ይችላሉ። ከቤተሰብ ቀጥሎ ያሉት የቅርብ ቤተሰቦቻቸው መመህራን ደግሞ ለጥፋቱ ይገባዋል፤ ያስተምረዋል፤ ባህሪውን ያንጻል የሚሉትን ቅጣት መውሰድ የተለመደ እና ማንኛውም ወላጅም ሆነ አሳዳጊ የሚስማማበት ድርጊት ነው።ነገር ግን የብሌን መምህር በወቅቱ ብሌን ላጠፋችው ጥፋት ተመጣጣኝ ያልሆነ በትር በመሰንዘሯ ዛሬ ላይ ብሌን ሁለቱም አይኖቿ እንዳያዩ ሆነ።

“……ትምህርት እወድ ነበር፡፡ ሆኖም የሶስተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ማንኛውም ሕጻን የሚያጠፋውን ጥፋት አጠፋለሁ፤ ረብሻለሁ፡፡ ነገር ግን አንድ ቀን ረብሷል በማለት መምህሬ በማስመሪያ ጭንቅላቴን መምታቷ የዓይን ብርሃኔን አስከወዲያኛው ለማጣቴ ምክንያት ሆነብኝ”በማለት ሁኔታውን ታስረዳለች።

በወቅቱ መምህሬ በሰራሁት ወይም ባጠፋሁት ጥፋት መናደዷን ብቻ ነበር ያየችው የምትለው ብሌን የወሰደችው እርምጃ ምን ሊያስከትል እንደሚቸክል አልገመተችም ነበር።ለእኔ ግን እርምጃው የሕይወቴን አቅጣጫ ያዛባብኝ ሆነ በማለት ስለሁኔታው ታብራራለች።

ብሌን ቅጣቱን ተቀብላ ወደቤት ስትመጣ ራሷን ስታ በመውደቋ ምክንያት እናቷ ከጎረቤቶቻቸው ጋር ተጋግዘው ወደሕክምና ጣቢያ ይወስዷታል፡፡ እዛም ያገኘችው እርዳታ ከጉዳት የሚያድን አልሆነም። እንደ እሷ አነጋገር ችግሩን አባብሶታል። ያም ሆነ ይህ ግን እናት የልጃቸው የአይን ብርሃን እስከወዲያኛው እንደጠፋ ባወቁ ጊዜ እጅግ ቢደናገጡም፤ ብዙ ቢያዝኑም፤ ብርሃኗ ሊመለስ የሚችልበት እድል ካለ በማለት ያልሄዱበት የሕክምና ተቋም ያላናገሩት ባለሙያ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ብሌን እስከ ሶስተኛ ክፍል ድረስ አብሯት የነበረውን ብርሃኗን ዳግም ላይመለስ ጠፋ።

ከዛ በኋላ ኑሮ ለብሌንም ሆነ ለእናቷ የተመቸ አልሆነም። ትምህርት መማር እንደልቧ ከእኩዮቿ ጋር መቦረቅ አቃታት፤ ይህንን የሚያዩ እናት ደግሞ እጅግ አዘኑ ልባቸው ተሰበረ።ብሌንም ቤት መዋሉን ተያያዘችው።

የብሌን እናት ብቸኛ ልጃቸው በዚህ መልኩ ከእኩዮቿ አንሳ ማየታቸው እረፍት ነሳቸው፡፡ ግን ደግሞ ሊያደርጉ የሚችሉት አንድም ነገር አልነበረም። ብቻ በጭንቀት በብስጭት በቁጭትና በእልህ ራሳቸውን ጎዱ፡፡ ይህ ጉዳታቸው ደግም መፍትሔ ከማምጣት ይልቅ ቀን በቀን ወደበሽታ እየወሰዳቸው የመኖር እድሜያቸውን እያሳጠረው መጥቶ ገና በጠዋቱ ለልጃቸውም ምርኩዝ ሳይሆኗት ከዚህ ዓለም በሞት እንዲለዩ ምክንያት ሆናቸው።

ይህ ሁኔታ ለብሌን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ሆነባት።የአይን ብርሃኗን ማጣቷ ሳያንስ ተንከባካቢና አሳቢ እናቷንም እስከወዲያኛው አጣች። ሃዘኗም በጣም ተባባሰ። ግን ደግሞ እስትንፋስ እስካለች መኖር አይቀርምና ብሌን ነገም ሌላ ቀን ነው በማለት ለመኖር የሚያስችሏትን መንገዶች መፈላለግ ጀመረች። የእናቷ እህት አክስቷም እሷን የማሳደግና የመንከባከብ ኃላፊነትን ተረክበው ወደቤታቸው ወሰዷት።

“…….የእኔ የአይን ብርሃን ማጣት እኔን በብዙ  ጎድቶኛል፡፡ ተምሬ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ እንዳልደርስ አስቀርቶኛል። ከዛ ሁሉ በላይ ግን እናቴ በእኔ ምክንያት በደረሰባት ሀዘን እርር ብላ እንድትሞትብኝ ሆኗል፤ ይህ በጣም ያሳዝነኛል።ግን ደግሞ የእናቴ ምትክ የሆነችው አክስቴ ምንም እንዳይጎልብኝ አድርጋ ይዛኛለች” ትላለች።

ብሌን የአይን ብርሃኗን ካጣች በኋላ ለአስር ዓመታት ቤት ውስጥ ተቀምጣለች። በእነዚህ ጊዜያት ሰርታ ገቢ ማግኘትን በማሰብ በተማረችው የመጥረጊያና መወልወያ እንዲሁም የቡና ረከቦት ምንጣፍ ስራ ገቢ ማግኘትም ትሞክር ነበር።

“…….አያቴ በነበረችበት ወቅት በተለይም የአይን ብርሃኔን ካጣሁ በኋላ ስራ እንዳልፈታ፤ እንዳላዝን በማለት የመጥረጊያ መወልወያ እንዲሁም የቡና ረከቦት ማስቀመጫ ምንጣፍ ስራን አስተምራኝ ነበር። እሱንም እየሰራሁ መጠነኛ ገቢን አገኝ ነበር” ትላለች።

ብሌን በምትሰራው ስራ ገቢ ማግኘቷ እውን ቢሆንም ለስራው የሚያስፈልገው ቦታ ሰፋ ያለ መሆኑና በሌሎችም ምክንያቶች ስራውን ልትገፋበት ሳትችል ቀረች።እናም ከአስር ዓመት በፊት ወዳቋረጠችው የሶስተኛ ክፍል ትምህርት መመለስን አማራጭ አደረገች። በብሬልና በሰዎች ድጋፍ እየታገዘች ትምህርቱን እንደምንም ስምንተኛ ክፍል ማድረስ ቻለች።

“…….መጥረጊያና መወልወያ እየሰራሁ እሸጥ ነበር፡፡ አክስቴም መርካቶ በመሄድ ለመስሪያ የሚሆን ግብዓት ታመጣልኝ ነበር፤ ነገር ግን እኔ አክስቴ ጋር ተጠግቼ የምኖር በመሆኑና ትርፍ ቦታም ስላልነበረን፤ ስራውም ሰፋ ያለ ቦታን የሚፈልግ በመሆኑ ተውኩት። እናም ትምህርቴን ለመቀጠል አስቤ ትምህርት ቤት ሄድኩ፤ ያም ቢሆን ግን ብዙ አመርቂ ውጤት ስላላየሁበት ከስምንተኛ ክፍል በላይ ለመማር ሳልችል ቀረሁ “ ትላለች።

እናቷ በሕይወት ሳሉ ማዕድን ሚኒስቴር ይሰሩ ነበር፤ በትርፍ ጊዜያቸው ደግሞ ቤት ለቤት እየዞሩ ተማሪዎችን የማስጠናት አገልግሎት ይሰጡም ነበር ። ታዲያ ይህ ስራቸው ካለፉ በኋላ ለልጃቸው እንጀራን የከፈተ ሆነ። ምክንያቱ ደግሞ እሳቸው ያስጠኗት የነበረች ታዳጊ አድጋ ከኢትዮጵያ ውጪ ሄዳ ስትመለስ አስጠኚ መምህሯ ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለዩ፤ ልጃቸውም የአይን ብርሃኗን አጥታ ችግር ላይ እንደሆነች መስማቷ ውለታዋን ለመክፈል አነሳሳት።

“ከአንጀት ካለቀሱ እንባ አይገድም” ይሉት የአባቶቻችን ተረት አይነት ልጅቷም የት አለች ብላ ከልቧ ተነሳስታ አፈላልጋ አገኘቻት። ብሌንን ስታገኛት ከማዘን ወይንም ደግሞ የእለት ጉርሷን ትችልበት ዘንድ ገንዘብ ሰጥታ ከመሸኘት ባለፈ ዘላቂ ነገር ኖሯት በምትችለው አቅም ሰርታ ራሷን የምታስተዳድርበትን መንገድ ማመቻቸት አለብኝ ወደሚል ሃሳብ ነበር የገባችው።ወጣቷ አስባም አልቀረች ብሌንን ፍላጎትና ስሜቷን ብሰራው እለወጥበታለሁ የምትለውን ነገር ጠየቀቻት።ብሌንም ከልጅነቷ ጀምሮ ትወደው እንዲሁም ትሞክር የነበረውን ስራ በመናገር የማሳጅ ትምህርት ብትማር ውጤታማ እንደምትሆን ገለጸችላት።

“……..በሚገርም ሁኔታ እንጀራዬ ይሆናል ብዬ ባላስበውም ከድሮ ጀምሮ ግን አያቴ ብርድ ምናምን ትከሻዋን ሲይዛት እሺኝ ትለኛለች ሳሻትም ቶሎ ትድናለች፤ ከዛ ባለፈ ደግሞ በምንኖርበት ግቢ ውስጥ የእግር አቀማመጧ የተበላሸ ሕጻን ልጅ ነበረችና እሷንም ቀን በቀን ዝም አሽቼ ቆማ ሄዳለች፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ ማሳጅ ብማር ውጤታማ እሆን ይሆናል የሚል ሀሳብ ጫሩብኝ።

እናቴ በሕይወት በነበረችበት ወቅት ታስጠናት የነበረች ልጅም ወደ እኔ መጥታ ምን እንዳደርግልሽ ወይም በምን ሙያ ሰልጥነሽ መስራት ትፈልጊያለሽ ስትለኝ በቀጥታ ያልኳት ማሳጅ ነበር” በማለት ሁኔታውን ታብራራለች።

ወጣቷም የብሌንን ሕይወት አንድ ርምጃ ወደፊት ሊያራምድ ይችላል ያለችውንና ባለጉዳዯም የመረጠችውን የትምህርት መስክ ትምህርት ቤት በማስገባት ክፍያውን በመክፈልና አስፈላጊውን ሁሉ በማሟላት በትምህርት የታገዘች የማሳጅና ፊዚዮቴራፒ ባለሙያ ለመሆን በቃች።

ብሌንም ምንም እንኳን የአካል ጉዳቷ እንደምትፈልገው ተንቀሳቅሳ ለመስራት እክል ቢሆንባትም በተማረችው ሙያ ግን ለመታወቅ፤ ሰርታም ለኑሮዋ የሚያስፈልጋትን ሁሉ ለማሟላት ጥረት ማድረጓን አላቋረጠችም። በዚህ ጥረቷ ደግሞ በተለይም በሰፈሯ አካባቢ በርካታ ሰዎች የተለያዩ ጉዳቶች ሲያጋጥሟቸው ወዳለችበት በመምጣት አልያም ቤታቸው ድረስ መጥታ እርዳታ እንድታደርግላቸው በመጥራት አገልግሎት እያገኙ ከሕመማቸውም እየዳኑ ሲሆን ብሌንም በምትሰራው ስራ በምታገኘው ገቢ ምግቧን ልብሷን እንዲሁም አንዳንድ አስፈላጊ ወጪዎቿን ከሞላ ጎደል እየሸፈነችበት ስለመሆኑ ታስረዳለች።

“……እውነት ለመናገር የማሳጅ ስራ በውስጤ የነበረ ነው፤ በትምህርት ሲታገዝ ደግሞ የበለጠ ሙያውን እንዳወቀው ብሎም የመስራት ፍላጎቱ እንዲያድርብኝ ሆኗል፤ ዛሬ ላይ ሰዎች ሲጠሩኝ ዘይቴን ይዤ ቤት ለቤት በመሄድ አሻለሁ፡፡ አስፈላጊውን ምክርም እለግሳለሁ፤ ለሰጠሁት አገልግሎት በሚከፍሉኝ ክፍያ ደግሞ ወጪዎቼ ለመቻል እሞክራለሁ “ በማለት ትናገራለች።

ብሌን የአቅሟን ያህል ትሞክር እንጂ ራቅ ያለ ቦታ ሄዳ እንደልቧ ተንቀሳቅሳ ለመስራት አብሯት የሚሄድ ረዳት ሁሌ አታገኘም፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሰዎች በሰፈሯ አካባቢ ስራዋን ቢያውቁትና ቢለምዷትም ሰፋ ባለ ሁኔታ ለመታወቅ አልቻለችም፤ ያም ቢሆን ግን እጇን አጣጥፋ ቁጭ ብላ ተመጽዋች መሆንን አታስብም እንዲሁም እየተንቀሳቀሰች ሰርታ ራሷን መቻል ነው ፍላጎቷ።አሁን ላይ በምታገኘው ገንዘብ ልብስና ጫማዋን ቀለቧን ከመቻል አልፉ የኮንደሚንየም ቤት ባለእድል የሚያደርገውን ቁጠባ እንደ አቅሟ ሳታቋርጥ ትቆጥባለች።

ብሌን በማሳጅ ስራዋ የነርቭ፣ የኩላሊት፣ የልብ የስኳርና የደም ግፊት፣ እንዲሁም አስምና ሳይነስ ሕመሞችን ለማስታገስ የሚጠቅሙ የማሳጅ አይነቶችን የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን በመነካካትና በማሸት ታስታግሳለች፤ ይህንንም በትምህርቷ መሰረት በርካታ ሰዎች ላይ ሞክራው ውጤትም እንዳገኘችበት ነው የምትናገረው።

በሌላ በኩል ደግሞ የወገብ በሽታ፤ ወለምታ፤ ውልቃትን በማሸት መፍትሔ ትሰጣለች።ብሌን ከስብራት ውጪ የማትሰራው ስራ እንደሌለም ነው በአንደበቷ የምትናገረው። ብሌን በወር እስከ ሶስት ሰው ድረስ እሰራለሁ ትላለች፡፡

ብሌን ከአክስቷና እንደ እናት ከምታያቸው የእናቷ ጓደኛ በስተቀር ማንም የላትም፤ የኑሮን ውጣ ውረድ ከአካል ጉዳቷ ጋር ደምራ የምትወጣው እሷው እራሷ ናት።በተለይም ራቅ ወዳለ ቦታ ስትጠራ ቦታው ላይ ለመድረስ ትቸገራለች፤ ያም ቢሆን ግን ብሌንን ከመሄድ ሰርቶ ከመብላት አላገዳትም።

“…..እንደነገርኩሽ በስራ ቦታዎቼ ሁሉ አብሮኝ የሚንቀሳቀስ ሰው የለኝም፤ ነገር ግን ስራ አግኝቼ እዛ ድረስ እንዴት እሄዳለሁ ብዬ ደግሞ የቀረሁበት ስራም የለም፤ በዚህ አጋጣሚ የአዲስ አበባ ነዋሪ ሲበዛ ጨዋና ደግ ሕዝብ መሆኑን ለመግለጽ ፈልጋለሁ። ይህንን ያልኩበት ዋናው ምክንያቴ ደግሞ ታክሲ ልሳፈር ስል ቦታውን ይጠቁሙኛል፤ ከመጠቆምም አልፈው ታክሲ ከፍለው ያሳፍሩኛል፤ መንገድ ለማቋረጥ እንኳን ስቆም ተሻምተው ነው የሚያሻግሩኝ፡፡ ይህ ለእኔ ከድጋፍ በላይ የሆነ ትልቅ ነገር ነው።በጣምም ነው የምደሰትበት። በዚህ አጋጣሚ በመንገዴ ሁሉ ለሚያግዙኝ ምስጋናዬ ይድረስልኝ” በማለት ሃሳቧን ትገልጻለች።

ደስ ያሰኘኝ የስራዬ አጋጣሚ በማለት ብሌን ይህንን ትላለች፤”…….ታካሚዬ ሰፈራቸው አየር ጤና አካባቢ ነው፤ ወድቀው እግራቸው ላይ ነው ጉዳት የደረሰው፤ እናም በሕክምና ሲረዱ ቢቆዩም ነገር ግን ውጤት አላመጡም ነበር፤ ችግሩ ተባብሶ በተለይም ባታቸው አካባቢ ስጋቸው ጠፍቶ ቆዳቸው ቀርቶ ነበር፤ እኔም ሁኔታቸውን አይቼ ስብራት አለመሆኑን ካረጋገጥኩ በኋላ የማሻ ድንጋዮቼን በመጠቀም የጉዳቱን ቦታ ማሸት ጀመርኩ፡፡ እየተመላለስኩ አገልግሎት ከሰጠሁ በኋላም አሁን ላይ ሕመምተኛው ቆመው መራመድ ጀምረዋል “በማለት ስራዋ ውጤታማ ሲሆን የሚሰማትን ላቅ ያለ ደስታ ትናገራለች።

ሙያዬ የተከበረና ትልቅ ለብዙ ሰዎች የችግራቸው መፍትሔ ቢሆንም እኔ ግን መስሪያ ቦታ ማጣቴና ሰዎችን በሰፊው ማገልገል አለመቻሌ በጣም ያሳዝነኛል የምትለው ብሌን ዛሬ ላይ እኔን አይቶ ማድነቅ፤ አልያም ከንፈር መጦ መሄድ ጥቅም አልባ ነው ትንሽም ብትሆን ሰርቼ ለመለወጥ የሚያስችለኝ ቦታ በመንግስትም ይሁን በግለሰቦች ቢመቻችልኝ ለብዙዎች መፍትሔ መሆን እችላለሁ በማለት መልዕክቷን ታስተላልፋለች።

ብሌን በማሳጅ ሙያ በሰርተፍኬት ደረጃ ተመርቃለች፡፡ ለምን ተቀጥረሽ አትሰሪም የሚል ጥያቄ ከብዙዎች እንደሚመጣላት ትናግራ ነገር ግን እሷ ይህ እንደማይሆን ነው የምትናገረው ምክንያቷ ደግሞ “……… ማሳጅ ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡ የዛኑ ያህል ደግሞ ለእኩይ ተግባር የሚጠቀሙበት ብዙዎች ናቸው፤ እኔ ደግሞ አካል ጉዳተኛ ነኝ፡፡ ጉዳቴ ደግሞ ማየት መሳኔ ነው፤ ስለዚህ ምንም ዓይነት ጾታዊ ጥቃት ቢደርስብኝ መቋቋም ስለማልችል መቀጠር አልፈልግም።አንዳንድ ቦታ ስጠራ እንደውም አክስቴን ሁሉ አስከትዬ የምሄድበት አጋጣሚ አለ “በማለት ተቀጥራ ላለመስራቷ ምክንያቷን ትናገራለች።

ብሌን አካል ጉዳተኛ በመሆኑ የተለያዩ የአካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበርን ለማነጋገር በእነሱም በኩል አንዳንድ ድጋፎችን ለማግኘት ያደረገችው ጥረት አለመሳካቱን ትናገራለች።በተለይም ወደ አይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር ሄዳ ያቀረበችው ጥያቄ እንደውም አስከፊ ምላሽ ይዞባት ስለመምጣቱም ነው የምትገልጸው።

“…….እውነት ለመናገር በተለያዩ አካል ጉዳቶች ስያሜ የሚቋቋሙ ብሔራዊ ማኅበራት ብዙ ናቸው፤ በእርግጥ የሚጠቀምባቸው የተሻለ ነገርን የሚያገኝባቸው አካል ጉዳተኛ ሊኖር ይችላል።እኔ ግን የአባልነት ምዝገባን ባደርገም ከእነሱ ያገኘሁት አንድም ድጋፍ የለም።እንደውም የአይነ ስውራን ብሔራዊ ማኅበርን ሳናግራቸው አባል አድርገው ከመዘገቡኝ በኋላ አንቺ ማየት ትችያለሽ የሚል ነውረኛ ምላሽ ነው የሰጡኝ።እኔም ብትፈልጉ በሕክምና አረጋግጡ ብዬ ተውኳቸው።በእጄ የምይዘውን ብትር እንኳን የገዛችለኝ የእናቴ ጓደኛ ናት።እኔ ስም ካልሆነ በቀር ያገኘሁት አንዳችም ድጋፍ የለም አሁን ላይ ስለሰለቸኝ ወደ እነሱም አልሄድም “በማለት ሁኔታውን ታስረዳለች።

መልዕክት

አካል ጉዳተኛ ሁሉ የተሰጠውን ተቀብሎ ራሱን የሚችልበትን መንገድ ነው መፈለግ ያለበት፡፡ በልመና አልያም በእርዳታ የሚያልፍ ችግር የለም።ከዛ ይልቅ በሚቻለው መጠን ጥሮ ተጣጥሮ መኖርን ምርጫ ማድረግ ያስከብራል።

አካል ጉዳተኝነት በየትኛውም አጋጣሚ በማንም ሰው ላይ ሊከሰት የሚችል መሆኑን አምኖ ለምን እኔ ላይ ከሚል ሃሳብ በመላቀቅና ራስን ነጻ አድርጎ በመኖር ሕይወትን መግፋት ያስፈልጋል።

በሌላ በኩልም በአካል ጉዳተኞች ስም የተቋቋሙ ድርጅቶችና ሌሎችም ለቆሙለት ዓላማ ታማኝ በመሆን በእውነትና በሀቅ የተቸገሩት የሚረዱበት ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን ችለው ለሌሎች የሚተርፉበትን ሁኔታዎች ቢያመቻቹ በማለት መልዕክቷን አስተላልፋለች።

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን  የካቲት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You