የዙሪች ሴቪላ ማራቶን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በርካታ ታዋቂ አትሌቶች የሚሳተፉበትን ውድድር ከነገ በስቲያ ያካሂዳል። ከመነሻው አንስቶ እጅግ ጠንካራ ፉክክር ይስተናገድበታል ተብሎ በሚጠበቀው ውድድር ከ250 በላይ የርቀቱ ጠንካራ አትሌቶችን ማፋለሙ የተለየ ትኩረት እንዲሰጠው አድርጓል፡፡ በውድድሩ ተሳትፏቸውን ካረጋገጡ አትሌቶች መካከል ያለፉት ዓመታት የውድድሩ አሸናፊዎች ዳግም በሩጫው መካፈላቸው ደግሞ የአሸናፊነት ፉክክሩን ተጠባቂ አድርጎታል፡፡
ሜዳማ በሆነ ስፍራ ላይ የሚካሄደው ይህ ውድድር ላይ በተለይ አፍሪካውያን አትሌቶች ለመሸናነፍ በሚኖራቸው እልህ አስጨራሽ ፉክክር አዲስ ክብረወሰን ሊመዘገብ ይችላል በሚል ይጠበቃል፡፡ አውሮፓውያንና አሜሪካውያን የውድድሩ ተሳታፊዎች ደግሞ ወራት ብቻ ለሚቀሩት የፓሪሱ ኦሊምፒክ ሃገራቸውን ወክለው ለመመረጥ የሚያስችላቸውን ውጤት ለማግኘት ይጥራሉ፡፡ ከቀናት በፊት በመኪና አደጋ ሕይወቱ ያለፈውን የዓለም ማራቶን ክብረወሰን ባለቤቱን ኬንያዊው ወጣት አትሌት ኬልቪን ኪፕቱም እና ለአሠልጣኙ የሕሊና ፀሎት በማድረግ ውድድሩ እንደሚጀመርም ተጠቁማል፡፡
በወንዶች መካከል በሚደረገው ውድድር በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚካፈሉ ሲሆን፤ ባላቸው ፈጣን ሰዓት መሠረት በቀዳሚነት ተቀምጠዋል፡፡ በዚህ ውድድር እአአ በ2022 እና 2023 አሸናፊ የነበሩት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው፡፡ ይህም ውድድሩ በአትሌቶች በኩል ተመራጭና ምቹ መሆኑን የሚያመላክት ሲሆን፤ ዘንድሮም በድጋሚ ለመፎካከር ተዘጋጅተዋል፡፡ በመሆኑም ከነገ በስቲያ የሚደረገው ውድድርም እንዳለፉት ዓመታት በተመሳሳይ ኢትዮጵያውያን አሸናፊነት ይደመደማል የሚለው የበርካቶች ግምት ነው፡፡ በዚህም መሠረት ካቻምና በዚህ ውድድር ተካፍሎ አሸናፊ የነበረው አትሌት አስራር ሃይረዲን ወደ ውድድሩ መመለሱ ታውቋል፡፡
በ2022 ያስመዘገበው ሰዓት የግሉ ፈጣን ሰዓት ከመሆኑም ባለፈ ከውድድሩ ተሳታፊ አትሌቶች በቀዳሚነት እንዲቀመጥ አስችሎታል፡፡ አትሌቱ በወቅቱ ውድድሩን የፈጸመውም 2 ሰዓት ከ04 ደቂቃ ከ43 ሰከንድ በሆነ ሰዓት ሲሆን፤ በድጋሚ ድሉን ለመቀዳጀት የሃገሩን ልጆች ጨምሮ በቁጥር እጅግ የበዙትን አትሌቶች ተፎካክሮ መርታት ይጠበቅበታል፡፡
የሁለተኛው ፈጣን ሰዓት ባለቤትና የዚህን ውድድር ክብር በድጋሚ የመውሰድ ከፍተኛ ግምት የተሰጠው አትሌት ደግሞ ጋዲሳ ብርሃኑ ነው፡፡ ይህ አትሌት በርቀቱ ከፍተኛ ልምድ ያለውና እንደ ጉዋንዡ፣ ካስቴሎን፣ ሪጋ፣ ዛግሬብ፣… ያሉ ማራቶኖች ላይ ውጤታማ መሆን የቻለ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ደግሞ በዙሪች ሴቪላ ማራቶን ተወዳድሮ አሸናፊ ሲሆን፤ ቀድሞ ከነበረው ሰዓት ደቂቃዎችን በማሻሻል አስደናቂ ብቃቱን አሳይቷል፡፡ በውድድሩ ከፈጣን አትሌቶች ተርታ እንዲሰለፍ ያደረገው 2ሰዓት ከ04 ደቂቃ ከ59 ሰከንድ የሆነ ሰዓትም ከተፎካካሪው አስራር ጥቂት ሰኮንዶችን ብቻ የዘገየ ነው፡፡ ይህም አትሌቱ በቦታው ባለው ልምድ እንዲሁም ተፎካካሪነት የውድድሩ አሸናፊ ሊያደርገው እንደሚችል በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ዕምነት ተጥሎበታል፡፡
በአንድ ደቂቃ በዘገየ ሰዓት የሦስተኛው ፈጣን ሰዓት ባለቤትና የኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆን የሚጠበቀው አትሌት ደግሞ ኤርትራዊው እቁባይ ፀጋይ ነው፡፡ ይህ አትሌት አምና የበርሊን ማራቶንን የሮጠበት 2 ሰዓት ከ05 ደቂቃ ከ20 ሰከንድ ፈጣን ሰዓቱ ነው፡፡ ሌላኛው የሃገሩ ልጅ አፈወርቂ ብርሃኔ ደግሞ ሁለት ሰከንዶችን ብቻ ዘግይቶ አራተኛው ፈጣን አትሌት በሚል በአትሌቶች ዝርዝሩ ሊካተት ችሏል፡፡ በኢትዮጵያውያን በኩል ደረሰ ገለታ፣ ደርቤ ሮቢ፣ ይታያል አጥናፉ፣ ኃይሉ ዘውዱ፣ ልመንህ ጌታቸው፣ አብዲ አሊ ጠንካራ ፉክክር የሚያደርጉ አትሌቶች ናቸው፡፡
በሴቶች በኩል ደግሞ 70 የሚሆኑ አትሌቶች በውድድሩ ለአሸናፊነት ይፋለማሉ፡፡ በዚህም ምድብ በተመሳሳይ በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚካፈሉ ሲሆን፤ በፈጣን ሰዓታቸውም በቀዳሚነት መቀመጥ ችለዋል፡፡ በትልልቅ ማራቶኖች ተሳታፊ በመሆን ከፍተኛ ልምድ ያዳበረችው አትሌት አዝመራ ገብሩ ቀዳሚዋ ናት፡፡ የፓሪስ፣ ቶኪዮ፣ አምስተርዳም፣ ቫሌንሲያ እና ባርሴሎና ማራቶኖች ተሳታፊዋ አዝመራ የዙሪች ሴቪላ ማራቶን አሸናፊ እንደምትሆን ትጠበቃለች፡፡ አትሌቷ ቅድመ ግምቱን ልታገኝ የቻለችበት ምክንያት ደግሞ ባላት 2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ48 ሰከንድ ፈጣን ሰዓት ነው፡፡ ኬንያውያን አትሌቶች እንደሚፎካከሯት ሲጠበቅ፤ ፋንቱ ዘውዴ፣ አስረስ እብስቴ፣ ደራርቱ ኃይሉን የመሳሰሉ አትሌቶች ደግሞ በኢትዮጵያ በኩል ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 8 /2016