ቴክኖሎጂና አዲስ የፈጠራ ሥራ የሰው ልጆችን ሕይወት በብዙ አሻሽሏል፡፡ ከትምህርት፣ ከጤና፣ ከግብርና እና ከሌሎች ዘርፎች አንፃርም የሚሰጠውን ጠቀሜታና የአጠቃቀም ሂደቱን ብንመለከት እንደ ዘርፎቹ አይነት ጥቅም ላይ የሚውልበት መንገድም ይለያያል፣ የሚጠቀምባቸው መሳሪያዎችም እንዲሁ እንደ አገልግሎቱ አይነትና ስፋት ይለያያሉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላሉና በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ደግሞ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራ ፋይዳው ከምንለው በላይ ትልቅ ነው።
በተለያዩ ዘርፎች ላይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የማደግ ዕድል እንዳላት ሀገር፣ የማኅበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ለመሻሻል፣ ለደህንነት፣ ለትምህርት፣ ለግብርናና፣ ለጤና አገልግሎት፣ በአጠቃላይ በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን በቴክኖሎጂና በአዲስ የፈጠራ ሥራ መታገዝ የግድ ሆኗል፤ ያለቴክኖሎጂ ያለሙበት መድረስ ከባድ እየሆነ መጥቷል። ከእነዚህ ዘመን አፍራሽ የቴክኖሎጂ ዘርፎች መካከል አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቀደሚውን ስፍራ እየያዘ መጥቷል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ዘርፎች ምርታማነትን ለመጨመር እንዲሁም አምራች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ለማስተሳሰር ቁልፍ ቴክኖሎጂ ነው። ሰው ሰራሽ አስተውሎት በአሁኑ ወቅት በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በጤና፣ በደህንነት እና በግብርና ዘርፎች ምርታማነትን እና ቅልጥፍናን ለመጨመር ቁልፍ ቴክኖሎጂ ሆኖ እያገለገለ ነው። በኢኮኖሚው ረገድም መረጃዎች እንደሚያሳዩት የዚህ ቴክኖሎጂ ድርሻ በዓለም ገበያ 350 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል። ይህ ቴክኖሎጂ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን እና ሕይወታችንም ሰፊ ድርሻ እየያዘ መጥቷል።
ያደጉትም ሆነ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ቴክኖሎጂው በሚያስፈልጋቸው ዘርፎች እንደ አስፈላጊነቱ እየተጠቀሙበት ችግሮቻቸውን እየፈቱ ይገኛሉ። ኢትዮጵያም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች። የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የግብርና፣ የጤና፣ የደህንነት፣ እና መሰል ዘርፎችን አቅም ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል።
ወጣት ጄርሚያ ባይሳ ይባላል። ተወልዶ ያደገው በኦሮሚያ ክልል አምቦ ከተማ አቅራቢያ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ከአምቦ በ12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ጉደር ከተማ ተከታትሏል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአምቦ አጠናቋል። በመቀጠልም በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ጥሩ ውጤት በማምጣት የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመከታተል ወደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት በ2008 ዓ.ም በኮምፒውተር ሳይንስ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል።
ከኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርቱ ጎን ለጎን የሲቪል ምህንድስና ትምህርቱን ሲከታተል የቆየው ጄርሚያ በዚህ የትምህርት ዘርፍ ደግሞ በተመሳሳይ በ2010 ዓ.ም በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቋል። በተጨማሪም የመጀመሪያ ድግሪውን ባገኘበት የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት በሁለተኛ ድግሪ በኮምፒውተር ኔትወርኪንግ ተመርቋል። በዚህ ያለበቃው ጄርሚያ ወደ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ በማቅናትም በፕሮጀክት ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪውን ማግኘት ችሏል።
ጅማ ዩኒቨርሲቲ በሚያስተምርባቸው የትምህርት ዘርፎች ሁሉ የተሟላ ግብዓት ያለው መሆኑ በትምህርት ቆይታው የተሳካ ጊዜ እንዲያሳልፍ በእጅጉ እንደረዳው የሚናገረው ወጣት ጄርሚያ፤ የተለያዩ የትምህርት አይነቶችን በመከታተል ክረምትን ጨምሮ በዩኒቨርሲቲው ረዥም ጊዜን በማሳለፉ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመተዋወቅ የትውልድ አካባቢው ናፍቆት ሳያስቸግረው ትምህርቱን በአግባቡ የተከታተለበት እንደነበር ይናገራል።
ባስመዘገበው ጥሩ ውጤትና ምርምር በዩኒቨርሲቲው በመምህርነት ሥራውን የቀጠለው ወጣት ጄርሚያ፤ ከተማሪነት ወደ መምህርነት በነበረው ሽግግር ስለነበረው ሁኔታ ስናገር፤ በዕድሜ ከብዙ ተማሪዎች ጋር ተቀራራቢ መሆኑና በዩኒቨርሲቲ ቆይታውም በሚሰራቸው ሥራዎች በተለያየ መልኩ በግቢው ማኅበረሰብ ዘንድ በስፋት ይታወቅ ስለነበር መምህር ሆኖ ሲመጣ ተማሪዎች እሱን ለመቀበል እንዳልከበዳቸው ይናገራል።
የመምህርና ተማሪ ግንኙነት ከተፈጠረ በኋላ ከተማሪዎቹ ጋር የነበረው ቆይታ በክፍል ትምህርት ሆነ የተግባር ላይ ልምምድ እሱን ስለተማረውና ስለሚሰራው ነገር ስለሆነ እያስተማረ የቀጠለው በሂደቱ ያሳለፈው ቆይታ መልካም እንደሆነ፤ ከተማሪዎች ጋር ተቀራርቦ በመስራት በሚችለው ሁሉ ስለሚማሩት ነገር ተማሪዎች በቂ ዕውቀት ይዘው እንዲወጡ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት እንዳደረገ ይናገራል።
ወጣት ጄርሚያ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበረው ቆይታ ወደ ምርምርና ፈጠራ ሥራው የገባበት አጋጣሚ ምን ይመስል እንደነበር ሲናገር፤ የሁለተኛ ድግሪ ተማሪ በነበረበት ወቅት በጅማ ዩኒቨርሲቲ በሚሰጠው የማኅበረሰብ ተኮር የትምህርት ፕሮግራሙ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር በጋራ በመሆኑ የተለያዩ የማኅበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት እንደነበር ያስረዳል።
በወቅቱ በኮምፒውተር ሃርድዌር ጥሩ እውቀትና ችሎታ ከነበረው አንድ ተማሪ ጋር የተዋወቀው ጄርሚያ፤ ከእርሱ ጋር ወዳጅነት በመፍጠር በተማሩበት የትምህርት ዘርፍ ሁለቱም ባላቸው እውቀት በጅማ ከተማ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ሥራዎችን በጋራ በመስራት ጅማሮአቸውን በማድረግ በሂደትም በሰው ሰራሽ አስተውሎት በመታገዝ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን የሚሰራ ደቦ ኢንጂነሪንግ የተሰኘ የቴክኖሎጂ ኩባንያ በጋራ በማቋቋም የምርምር ሥራቸውን በስፋት ማከናወን ቀጠሉ።
ጄርሚያና ጓደኛው በዚህ ድርጅታቸው አማካኝነት በመስራት ለምረቃ ፅሁፋቸው የሚሆን አንድ የምርምርና የፈጠራ ይዛው ቀረቡ። ይህም በሰው ሰራሽ አስተውሎት አማካኝነት የግብርና ሰብል ላይ የሚከሰት በሽታን መለየት የሚችል ቴክኖሎጂ ነበር። የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በሆነው ግብርና ላይ ለሚያጋጥም ከፍተኛ ችግር የመፍትሔ ሀሳብ ይዛው የቀረቡት ሁለቱ ወጣቶች በዚህ የቴክኖሎጂ ሥራቸው በ2012 ዓ.ም በነበረውና ሁሉም የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በተሳተፉበት ሀገር አቀፍ ውድድር አሸናፊ መሆን ችለዋል።
በዚህ ሀገር አቀፍ ውድድር ቀዳሚውን ሥፍራ ይዘው እንዲያጠናቅቁ ስላስቻላቸው የምርምር ሥራ ወጣት ጄርሚያ ሲናገር፤ የመጀመሪያው ትክክለኛ ችግር በመለየት ለዚህ የሚሆን ትክክለኛ የመፍትሔ ሀሳብ ይዘን መቅረባችን ነው ይላል። በግብርና ውስጥ ትልቁ ችግር በሽታን በጊዜ በመለየት የሚያስፈልጉ ቅድመ ጥንቃቄዎችን በጊዜ መውሰድ ነው። ይህንን ቶሎ መለየት ደግሞ ለአርሶ አደሩ አስቸጋሪ ነው። የሰው ሰራሽ አስተውሎት ደግሞ በሰው የማይታዩ ነገሮችን ቀድሞ በመረዳት ማሳወቅ ይችላል። ስለዚህ በዚህ መንገድ በትክክል መሬት ላይ ወርዶ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ሥራ በመሆኑ ለአሸናፊነታቸው ትልቁ ምክንያት እንደሆነ ይናገራል።
ሌላው ጉዳይ ይህንን ቴክኖሎጂ ማበልፀግ የቻሉት ኢትዮጵያን ባማከለ መልኩ እንደሆነ የሚናገረው ጄርሚያ፤ በኢትዮጵያዊ ባለሙያ አማካኝነት ጥቅም ላይ እንዲውል ከማድረግ ባለፈ፣ በሀገሪቱ በአርሶአደሩ ማኅበረሰብ በአብዛኛው የመፃፍና የማንበብ ችግር ስላለ ይህንን ከግምት ባስገባ መልኩ በተለያዩ ቋንቋዎች በድምፅ በመታገዝ አገልገሎት የሚሰጥ ቴክኖሎጂ ነው ይላል።
በቅርቡ መንግሥት ነዳጅ በቴሌ ብር ብቻ በመክፈል ነው ማግኘት የሚቻለው ብሎ ፖሊሲ እንዳወጣው ሁሉ ይህ ቴክኖሎጂም መሳል የፖሊሲ አቅጣጫ የሚፈልግ ስለመሆኑ የሚናገረው ወጣት ጄርሚያ፤ ግብርና የመጀመሪያ የኢኮኖሚ ዘርፋቸው ያልሆኑ ሌሎች ሀገራት ሳይቀር ሰፊ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩበት እንደመሆኑ፤ በኢትዮጵያም ያለው የፖሊሲ ክፍተት ተቀርፎ የሀገሪቱ ትልቁ የኢኮኖሚ ዘርፍ ተገቢውን ውጤት ማምጣት እንዲችል መስራት እንደሚገባ ይናገራል።
ወጣት ጄርሚያ እንደሚለው፤ በሀገሪቱ በእያንዳንዱ ቀበሌና ወረዳው ላይ ባሉ የግብርና ባለሙያዎች አማካኝነት አርሶ አደሩ በመድረስ በዚህ ቴክኖሎጂ የእርሻ ማሳውን ጤንነት እንዲጠብቅ ማድረግ ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ አሁን እየተስፋፉ ያሉ በክላስተር እርሻ የሚዘሩ አቅም ያለቸው የተማረ የሰው ኃይል የሚጠቀሙ የንግድ እርሻ ጣቢያዎች አሉ፤ እነዚህ ይህንን ቴክኖሎጂ ቢጠቀሙ ውጤታማነታቸው እንደሚጨምር ይገልጻል።
ጄርሚያ እንደሚናገረው፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ማሽን ወይም ኮምፒዩተር የሰው ልጆችን ተክቶ ማመዛዘን፣ መማር፣ ማቀድ እና ፈጠራዎችን ማከናወን እንዲችል የሚያደርግ ነው። በዚህ ሁኔታ ማሽኖቹ አካባቢያቸውን እንዲገነዘቡ፣ የተገነዘቡትን እንዲተነትኑ፤ ችግሮችን እንዲፈቱ ያስችላቸዋል። ይህም በተለይ የሰዎችን ንክኪ በመቀነስ ለምርት መጨመር፣ የጊዜ አጠቃቀምን ለማሻሻል፣ ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ እና ውስብስብ ስራዎችን ያለ ከፍተኛ ወጪ ለመፈፀም ያስችላል። ከጊዜ አንፃርም ያለማቋረጥ እና ያለ ምንም እረፍት ይሰራል። ይህም የኅብረተሰብን ኑሮ የሀገርን ዕድገት እንደሚያቀላጥፍ ያስረዳል።
አሁን ላይ ይህ ቴክኖሎጂ በሁሉም ዘርፎች ሰፊ ተግባራት ያሉት በመሆኑ ከቅንጦት ይልቅ ለኅብረተሰብ ያለው አስፈላጊነት ግንዛቤ እያገኘ እንደመጣ የሚገልጸው ወጣት ጄርሚያ፤ ቴክኖሎጂው ግብርናን በማሳደግ በአህጉሪቱ ለሚታየው የምግብ እጥረት መፍትሔ ከማምጣት ባለፈ በተለይ በአፍሪካ በሽታዎችን ለመቀነስ፣ የጤና እንክብካቤን እና ትምህርትን ለማሻሻል፣ ድህነትን ለመቀነስ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያግዝ ይናገራል።
ቴክኖሎጂ የሚሰጠው ያለው መልካም አበርክቶ እንዳለ ሆኖ ይዞታ የሚመጣው የራሱ የሆነ ጉዳት ይኖረዋል የሚለው ጄርሚያ፤ እርሱ ወደፊት በሚሰራቸው የቴክኖሎጂ ሥራዎች ግለሰብና ሀገርን በማይጎዳ መልኩ ቴክኖሎጂን ለታለመለት ዓላማ ብቻ ጥቅም ላይ በማዋል ሀገረና ሕዝብ ለመጥቀም ትልቅ ሕልም እንዳለው ይናገራል።
ወጣት ጄርሚያ እንደሚያስረዳው፤ በሚመጣው ዘመን ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ለቴክኖሎጂ ሥራና ምርምር ትልቅ ትኩረት ያስፈልጋል። ቴክኖሎጂ የተለያዩ ሀገራት የሰው ሰራሽ አስተውሎትን በተመለከተ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ። በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማሰብ ጥረት እያደረጉ ነው። ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ መንግሥት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ቴክኖሎጂን ከግምት በማስገባት የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ ብሎም በቴክኖሎጂ ላይ ለተሰማሩ ተቋማትና ግለሰቦች አቅም በፈቀደ መጠን ሁሉ የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ መስራት እንዳለበት ያስገነዝባል።
የፋይናንስ ድጋፎች ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራዎችን ለማበረታታት ይሰጣሉ የሚለው ጄርሚያ፤ እነዚህ ድጋፎች በትክክል በዘርፉ ለተሰማሩ ወጣቶች ሊሰጡ ይገባል። አሁን ባለው ሁኔታ ለኩናት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየወጣ ነው። ይህንን ፋይዳ ቢስ አካሄድ በማስወገድ ረገድ የሚመለከታቸው አካለት ተገቢ የሆነ ሥራ መስራት እንዳለባቸው ይናገራል።
ኢትዮጵያ አቅም አላት ብዙ መስራት ትችላለች የሚለው ጄርሚያ፤ ነገር ግን ጉዳዩ የሚመለከታቸውና በቴክኖሎጂ ዘርፍ በተገቢው መንቀሳቀስ ያለባቸው ተቋማት በዛ ልክ እየሰሩ አይደለም። ቢሆንም በዚህ ዘርፍ እየሰራ ያለው ወጣት የሚደግፈኝ አካል የለም ብሎ መንቀሳቀስ ማቆም የለበትም የራሱን ጥረት ማድረግ አለበት ይላል። “እኔ እዚህ ደረጃ እስክደርስ ድረስ መንግሥት ወይም የሆነ ተቋም የተለየ ድጋፍ አድርጎልኝ ሳይሆን ባለመታከት ባደረጉት የግል ጥረት ነው እዚህ መድረስ የቻልኩት ድጋፍ የሚያደርጉ የመንግሥት ተቋማትም ቢሆን የተወሰነ የሚታይ ነገር ማሳየት ሲቻል ነው የሚያበረታቱት ስለዚህ ባለን አቅም የሚታይና ተጨባጭ የሆነ ነገር ለመስራት ጥረት ማድረግ አለብን” ይላል።
በመጨረሻም ወጣት ጄርሚያ ባስተላለፈው መልዕክት፤ አንድ ነገር ለማድረግ ሲታሰብ ሁል ጊዜ ዋጋ መክፈል ይኖረዋል፤ ፀንቶና ተግቶ በመስራት ግን የማይሳካ ነገር የለም፤ የሀገሪቱን ወደፊት መልካም የማድረግ ኃላፊነትና ግዴታ ያለባቸው የዚህ ትውልድ ወጣቶች ለዓላማቸው መሳካት መክፈል ያለባቸውን መስዋዕትነት ሁሉ መክፈል እንዳለባቸውና፤ የነገው ራዕያቸውን ከግብ ለማድረስ ቀን እና ሌሊት ሳይሉ ተስፋ ባለመቁረጥ መትጋት እንደሚገባቸው አስረድቷል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን የካቲት 8 /2016