ጌዴኦ-የማኅበረሰቡ እሴቶች

የጌዴኦ ማኅበረሰብ ውብ ባሕል፣ ተፈጥሮ ታሪክና ልዩ ልዩ እሴቶች ካላቸው የኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል አንዱ ነው። በያዝነው 2016 ዓ.ም ባሕላዊ መልከዓ ምድሩን ጨምሮ የማኅበረሰቡን ጥንታዊ እሴቶች በዩኔስኮ ማስመዝገብ ተችሏል። ከቀናት በፊት ደግሞ ዓመታዊው የደራሮ በዓል በደመቀ ሁኔታ በዞኑ ተከብሯል። በወቅቱ የቱሪዝም ሚኒስቴር አምባሳደር ናንሲሴ ጫሊን ጨምሮ በርካታ እንግዶች ታድመው የማኅበረሰቡን እሴቶች ለዓለም ለማስተዋወቅና የቱሪዝም ፍሰቱን ለመጨመር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የጌዴዮ ማኅበረሰብ በየዓመቱ ከሚያከብረው የደራሮ የዘመን መለወጫ በተጨማሪ እጅግ በርካታ እሴቶች ያሉት ማኅበረሰብ መሆኑን ምሁራን ይገልፃሉ። ከእነዚህ ውስጥ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀብታሙ ተመስገን አንዱ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት የጌዴኦ መልካ ምድር የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ዲላ ዩኒቨርሲቲ የድርሻውን ሲወጣ ቆይቷል፡፡ በአካባቢው የሚገኙ ባሕላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የሆኑ የማኅበረሰቡን ሀብቶች ጠብቆ፣ አልምቶና አስተዋውቆ ማቆየት እንደሚገባ ይናገራሉ። የማኅበረሰቡ እሴቶች የኢትዮጵያ አልፎም የዓለም ሕዝብ ሀብት በመሆናቸው ከባሕላዊ መልከዓ ምድሩ በተጨማሪ በየዓመቱ የሚከበረውን የደራሮ የአዲስ ዘመን መለወጫ በዓል በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እንደሚሰሩ አስረድተዋል።

የጌዴኦ ሕዝብ በአካባቢ ጥበቃ ባሕሉ ደንና አካባቢን እንደ ልጁ በመንከባከብ ከአረንጓዴ አሻራ ልማት ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው ባሕላዊ እውቀት ያለው ሕዝብ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ሕጋዊ ሰርተፍኬት አግኝቷል። ማኅበረሰቡ በባሕላዊ መልከዓ ምድሩ ብቻ የሚታወቅ አይደለም፤ ይልቁኑ እጅግ በርካታ እሴቶችን የያዘ ማኅበረሰብ ለመሆኑ አያሌ ማስረጃዎች ማንሳት ይቻላል። የዝግጅት ክፍላችንም ከዚህ ቀደም በባሕላዊ መልከዓ ምድሩና በደራሮ ዓመታዊ የዘመን መለወጫ በዓል ዝርዝር መረጃዎችን መስጠቱ የሚታወስ ሲሆን፤ ለዛሬ በሌሎች የማኅበረሰቡ እሴቶች ላይ ለማተኮር ወድዷል።

የዝግጅት ክፍሉ የዕለቱን አገርኛ አምድ በጌዴኦ የጋብቻ ስነ ስርዓት፣ የቤት አሰራር እና ባሕላዊ ምግቦች ላይ በማተኮር የሚከተለውን ዳሰሳ አቅርቧል። መረጃውን የጌዴኦ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መመሪያ ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ማሩ አድርሰውናል፡፡

የጌዴኦ የጋብቻ ስነ-ሥርዓት

በጌዴኦ ብሔረሰቡ ዘንድ ተግባራዊ የሚደረጉ የተለያዩ የጋብቻ ዓይነቶች ያሉ ሲሆን እነዚህም “ካጃ”/ሕጋዊ ወይንም የስምምነት ጋብቻ/፣ ቡታ፣ ጃላ፣ ኪንቾ፣ አደባና፣ ሀዋዴ፣ ዋራዬ ኦልታ፣ ሰባ እና ጊንባላ በመባል ይታወቃሉ። ከእነዚህ መካከል “ካጃ” እና “ሀዋዴ” የተሰኙት የጋብቻ ዓይነቶች በብሔረሰቡ ውስጥ በስፋት ተቀባይነት ያላቸው ሲሆን “ቡታ” እና “ዋራዬ ኦልታ” የተሰኙት በአፈፃፀማቸው በሕገ ወጥነት ይፈረጃሉ። እንደነዚህ ያሉ የጋብቻ ዓይነቶች ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ ቢፈፀሙም በመጨረሻ ውስጥ ለውስጥ በሚደረግ ስምምነት እና ባሕላዊ አስተዳደርና እምነት ፍራቻ ሕጋዊነታቸው ይፀድቃል።

“ሰባ” የሚባለው ጋብቻ በወንዱና በሴቷ ወላጆች ይሁንታ ወይንም መፈቃቀድ የሚከናወን ሲሆን “ሀዋዴ” የሚባለው ደግሞ በሌላ ሶስተኛ ሰው አግባቢነት ወንዱና ሴቷ ስምምነት ላይ የሚደርሱበት ከዚህም በኋላ ወደ ሴቷ ቤተሰቦች ሽማግሌ በመላክ የሚፈፀም የጋብቻ ዓይነት ነው።

ብሔረሰቡ በሕጋዊነት የተቀበላቸው የጋብቻ ዓይነቶች ከመፈፀማቸው በፊት ከጥንት ጀምሮ በዓይነት የሚተገበር የጥሎሽ ሥርዓት ይኖራል። በጥንታዊ የጋብቻ ሥርዓት ጥሎሽ ይሰጥ የነበረው ለአባትና እናት ሲሆን ከሚቀርቡ ስጦታዎች መካከል ለአባት ጠገራ፣ ድርብ ቡልኮ፣ ሂቶ / መቀነት/ በዋናነት የሚሰጡ ሲሆን ለእናት ደግሞ ነጠላ ቡልኮ /ዱዳ/ ይሰጣል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባሕላዊ የጥሎሽ ስጦታ ወደ ገንዘብ ተለውጦ ከፍተኛ የገንዘብ ክፍያ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል። የጥሎሽ ገንዘብ ከፍ ማለት በብሔረሰቡ ዘንድ ሕጋዊ ጋብቻን እያመነመነ በመምጣቱ በገዳ ሥርዓት ጠቅላላ ጉባኤው /ያኣ/ ለአባት ቡልኮ መግዣ ስድሣ ብር፣ ለእናት ደግሞ ሃያ ብር በድምሩ ብር ሰማኒያ እንዲሰጥ ቢወሰንም አንዳንድ የብሔረሰቡ አባላት በገዳ ስርዓቱ የተወሰነውን የጥሎሽ መጠን በመተላለፍ ከብር አንድ ሺህ እስከ አንድ ሺ አምስት መቶ የሚደርስ የጥሎሽ ገንዘብ ሲሰጡ ይስተዋላሉ።

በቤተሰብ ስምምነት በሚፈፀመው ሕጋዊ ጋብቻ ወቅት ተጋቢዎች በተጋቡ በሶስተኛው ቀን የሙሽራው ወላጆችና ቤተዘመድ በወንዱ ቤት ተሰባስበው የጉርሻ / ጊጫ/ ሥነ ሥርዓት በማከናወን ለሙሽሪት የተለያዩ ስጦታዎችን የሚሰጥበት ሥርዓት አለ። በዚህን ዕለት የሙሽራው ዘመድ አዝማድ በተገኘበት ሙሽራዎች /ወንዱ በስተቀኝ ሴቷ በስተግራ በመሆን/ ከተሰብሳቢዎች ፊት ለፊት ቁጢጥ ብለው የሚከናወነውን የጉርሻ /የስጦታ/ ሥነ ሥርዓት ለመፈፀም ይጠባበቃሉ።

የጉርሻው /ስጦታው/ የሚጀመረው ከሙሽራው አባት ወይንም አባት ከሌለ ከተሰብሳቢዎች መካከል አንጋፋ ከሆነው ሰው ስለሆነ ሙሽሪት ቀደም ብላ በተዘጋጀችበት መሠረት ጉርሻውን /ስጦታውን/ ለመቀበል ወደ አባት ወይንም አንጋፋው ሰው ተጠርታ ትሄዳለች። በዚህ ሥነ ሥርዓት ወቅት ሙሽሪት ከወንዱ ቤተሰብ የምትፈልገውንና የምትጠብቀውን ስጦታ እስከምታገኝ ድረስ የሚሰጣትን ጉርሻ አትቀበልም። ስለዚህ በጥሪው መሠረት የልጁ አባት ወይንም አንጋፋው ቤተዘመድ አጉራሽ “ይህን ያህል ብር ሰጠሁሽ ይላታል።” እሷም “አይበቃኝም” ትላለች። በመቀጠል “ይህን ያህል መሬት ሰጠሁሽ” ይላል። አሁንም መልሳ “አይበቃኝም” ትላለች። ከዚያም “ይህንን ያህል ከብት ሰጠሁሽ” ሲላት አይበቃኝም አይበቃኝም” እያለች ከቆየች በኋላ ከአጉራሹ /ከስጦታ ሰጪ/ ዘንድ የምትፈልገውን ያህል ስጦታ ስታገኝ ጉርሻውን ትቀበላለች። በዚህ መልኩ የተሰበሰበውን ቤተ ዘመድ በሙሉ በማዳረስ ለጎጆ መውጫ የሚሆናትን በቂ ሀብትና ንብረት ታገኛለች።

የቤት አሠራር

በጌዴኦ ብሔረሰብ ቤት የአንድን ግለሰብ ወይም ቤተሰብ ማኅበራዊ ደረጃ መገለጫ ስለሆነ ትልቅ ግምትና ክብር አለው። በብሔረሰቡ ባሕል መሠረት አንድ ልጅ ካገባ በኋላ እስከ አንድ ዓመት ድረስ በአባቱ ወይም ወላጆቹ ቤት መቆየት ይችላል። ከአንድ ዓመት በኋላ ግን ደረጃውን የሚያስጠብቅ ቤት ሠርቶ መውጣት የግድ ነው። ጌዴኦዎች ቤት የሚሠሩት በአንድ አካባቢ ተሰባስቦ በመንደር መልክ ነው። በጌዴአዎች የተለያዩ የቤት ዓይነቶች ያሉ ሲሆን ዓይነታቸው የሚወሰነው በቅርፅ፣ በግንባታ፣ ቁሳቁስ፣ በክዳን ዓይነትና በሚሰጠው አገልግሎት ነው። ከቤት አሰራራቸው መካከልም ዶጎዶ፣ ፎቃ (ፎቆ)፣ አዲቻሞና ሸካ የሚባሉ የቤት አሰራር አይነቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ዶጐዶ

ዶጐዶ ለአጭር ጊዜ ለሚቆይ ዝግጅት የሚሆን ጊዚያዊ ቤት ነው። አገልግሉቱ ለጫጉላ ቤት፣ እህል ለመጠበቅ ባሕላዊ በዓላት ለማክበር እና እንሰት ለመፋቅ ነው። ቅርፁ ክብ ሆኖ ከአራት ካሬ ሜትር የማይበልጥ ስፋትና ከሁለት ሜትር የማይበልጥ ቁመት ያለው ቤት ነው። ቤቱ ከቀጫጭን ጭራሮ እንጨት፣ ከወፊቾ ገመድና በእንሰት ቅጠል ሊሠራ ይችላል።

ፎቃ (ፎቆ)

የዚህን ዓይነት ቤት የሚሠሩት ሰዎች በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ፣ አዲስ ጐጆ ወጪዎች እና ከዋናው ቤት በተጨማሪ ለከብት ማደሪያነት የሚጠቀሙ ናቸው። ቤቱ ከቀርከቀሃ፣ ከሸምበቆ ከወፊቾና ከሰምበሌጥ ሊሠራ ይችላል። የቤቱ የውስጥ አደረጃጀት በአብዛኛው ሁለት ክፍል ያለው ሲሆን በር ኖሮት መስኮት አይኖረውም።

አዲቻሞ (መደበኛ ቤት)

የዚህ ቤት ዓይነት ረጅም ጊዜ ዝግጅት የሚጠይቅ ነው። ዝግጅቱ የመሥሪያ ቁሣቁስ በጥንቃቄ ይዘጋጃል፣ ለቤት ሠሪዎች ምግብ፣ እና በተለይ ከቁሳቁስ የምሰሶ መረጣ ትልቁን ጊዜ የሚወስዱ ተግባራት ናቸው። የዚህ ቤት የውስጥ አደረጃጀት ሲታይ ከሁለት በላይ ክፍሎች ሊኖሩት ይችላሉ፣ መስኮትና የጓሮ በር ይኖረዋል። የአዲቻሞ ቤት ሥራ ልዩ ባለሙያ ለምሰሶ መረጣ፣ ለሣር ክዳን ሥራ፣ የመሥሪያ ቦታ ማዘጋጀትና የምሰሶ ቅርፅ ማውጣት እንዲሁም ጣራ ማዋቀር የተለየ ባለሙያ ይፈልጋል።

ሸካ

ሸካ (የቀርከሃ ቤት) ሲሆን፤ የቤቱ ዓይነትና አሠራር ከዲቻሞ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ልዩነቱ ከቀርቀሃ ልባስ (ጳሻ) እና ከቀርከሃ የሚሠራ በመሆኑ ብቻ ነው። ቤቱ የሚታወቀው የደገኞች ቤት በመባል ነው። የቤቱ መዝጊያም ጭምር ቀርከሃ ሲሆን ከፍተኛ የቀርከሃ ጥበብ የሚታይበት ባሕላዊ የቤት አሰራር ነው።

ባሕላዊ ምግብና የአሠራር ሥርዓት

የብሔረሰቡ ዋነኛ ባሕላዊ ምግብ «ዋሳ» በመባል የሚታወቅ ነው፡፡ ‹‹ዋሳ›› ከዕለታዊ ምግብነቱ በተጨማሪ ለደስታም ሆነ ለሀዘን በተለያየ ዓይነት እየተዘጋጀ ከሌሎች የማባያ ዓይነቶች ጋር ይበላል። በስምንት የተለያዩ ባሕላዊ አዘገጃጀት የሚዘጋጅ ሲሆን፤ ከሚቆይበት ጊዜ አንፃር፣ ከማበያው ዓይነት፣ እና ከሚጠቀመው ሰው አኳያ እንደሁኔታው እየታየ ይዘጋጃል። ከባሕላዊ ዋሳ ምግብ ዓይነቶች አንዱ «ወእረሞ» የሚባል ሲሆን ብዙውን ጊዜ በኳስ ቅርጽ ተድበልብሎ ከገብስ ወይም ከበቆሎ ዱቄት ጋር በመደባለቅ የሚዘጋጅ፣ ለማንኛውም ዓይነት ዝግጅት የሚውል ከጐመን ወይንም ከስጋ ጋር የሚበላ ጣፋጭ ምግብ ነው።

ሌላው ተወዳጅ ምግብ «ኮፎ» በመባል የሚታወቅ ሲሆን አዘገጃጀቱ እንደ ዱቄት ሆኖ የተዘጋጀ ቆጮ ከገብስ ዱቄት ጋር በመደባለቅ የሚነኮር፣ በቅቤ እና ሌሎች ቅባት ነክ ነገሮች እንዲለሰልስ ተደርጐ የሚዘጋጅና፣ የተለየ ክብር ለሚሰጠው እንግዳ ወይንም ትላልቅ ሰዎች የሚቀርብ ነው። አንዳንዴም ይህን ምግብ ከአደንጓሬ ጋርም በመደባለቅ አዘጋጅተው ይጠቀሙታል። «ጣልታ» እና «ኬቦ» የምግብ ዓይነቶች የመጠን ልዩነት ካልሆነ በስተቀር ጠፍጠፍ ወይንም ሞልሞል ተደርገው በቀላሉ በአምባሻ መልክ የሚዘጋጁ ናቸው። «ሆጨቆ» ብቻውን በማድበልበል በመጠን አነስ ተደርጐ የሚዘጋጅ ከጐመን ጋር የሚቀቀል ጣፋጭ ምግብ ነው። «ቁንጭሣ» ደግሞ የቆጮ ዱቄት በምጣድ ላይ ተደርጐ ሲበስል እንደ እንጀራ እየተቆረሰ የሚበላ ብዙ ማገዶ የማይፈጅ የዘወትር ባሕላዊ ምግብ ነው። ኦጣ ርሞጦ የሚባለው ደግሞ ለረጅም ጊዜ ሳይበላሽ እንዲያገለግል በተለይም ለረጅም ጉዞና በጦርነት ወቅት ስንቅ እንዲሆን ታስቦ የሚዘጋጅ እንደ ድፎ ዳቦ ዓይነት ነው። ኮሣ /ጉንጃ/ በማድበልበል ጠቅለል ተደርጎ በእሣት ፍም ወይንም ትኩስ ረመጥ ላይ ተደርጎ ሲበስል የሚበላ ተዘውታሪ ምግብ ነው።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን የካቲት 8 /2016

 

Recommended For You