የ‹‹ሿሿ›› ዘመቻ

አንዳንድ ምኞቶች ወይም ‹‹እንዲህ ቢደረግ›› ብለን ያሰብናቸው ነገሮች ተሳክተው ሲታይ ደስ ይላል፡፡ ከዓመት ፊት ይመስለኛል፤ በተለምዶ ‹‹ሿሿ›› እየተባለ ስለሚጠራው የስርቆት አይነት አንድ ትዝብት እዚሁ ገጽ ላይ አስነብቤ ነበር፡፡ ጥቅል ሀሳቡ፤ ፖሊስ የሆነ የመጠቆሚያ አድራሻ ሰጥቶ ቢሰራበት የሚል ነበር፡፡ ሰዎች አጠራጣሪ ምልክት ሲያዩ ወይም የዚህ ስርቆት ሰለባ ሲሆኑ ወዲያውኑ ተሽከርካሪውን ማስያዝ የሚችሉበት አጋጣሚ ቢኖር የሚል ነበር፡፡ ይህን ለማድረግ የፀጥታ አካል የጥሪ ማዕከል ቢኖር የሚል ነበር፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ ፖሊስ በተደጋጋሚ የሚወጡ ዜናዎች ያንን ምኞቴን አስታወሱኝ፡፡ ሰሞኑን ልብ ብላችሁ ከሆነ ፖሊስ በተከታታይ የሚለቀው ዜና በተለምዶ ‹‹ሿሿ›› የሚባለውን የስርቆት አይነት የፈጸሙ ሰዎችን የሚያጋልጥ ነው፡፡ የሰረቁትን ንብረት (በዋናነት ሞባይል ስልክ) እና የሌቦችን ምስል በግልጽ በማሳየት መቀጣጫ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ከማስፈራራት ባለፈ በተግባር ተደረገ ማለት ነው፡፡ ይህ የአንድ እና የሁለት ቀን አጋጣሚ ብቻ አይደለም፤ እስከ ቅርብ ቀናት ድረስ የሰማነው ዜና ነው፡፡ ፖሊስ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት ነው ማለት ነው፡፡

በነገራችን ላይ ፖሊስ ከፍተኛ ዘመቻ የሚጠበቅበት ለጥቂት ጊዜያት ብቻ ነው፤ ከዚያ በኋላ ጭራሹንም ይጠፋሉ፡፡ ምክንያቱም እንደማይሳካ እና እንደማይቻል አወቁት፡፡ ይህ ማለት ፖሊስ አርፎ ይቀመጥ ማለቴ አይደለም፤ ዳሩ ግን ሌሎች ይጠፋሉ። ከቅርብ ቀናት ወዲህ በተከታታይ የሚሰሙት ዜናዎች የስርቆት ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ምስላቸው በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲዘዋወር ነው፡፡ ይህ ፎቶ ወላጆቻቸውና ዘመድ አዝማድ ያየዋል፡፡ ‹‹የእገሌ ልጅ ሰርቆ ተያዘ›› መባል በባህላችን እጅግ በጣም ነውር ነው፡፡ እነዚህ ወጣቶች ምስላቸው ሲዘዋወር ስለነበር የትኛውም ቦታ ቢሄዱ በሌብነት ነው የሚታወቁት። ከአንድ ቦታ የሰረቁትን ንብረት ሸጠው ሌላ ቦታ ሲዝናኑበት ቆይተዋል፡፡ አሁን ግን እንዲህ አይነት ወጣቶች ሲዝናኑ የተመለከተ ሁሉ ‹‹እነዚህ ሌቦች›› ይላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ውርደት በመፍራት ከዚህ በኋላ ስርቆትን እንደ አማራጭ የሚሞክር አይኖርም፡፡

አይኖርም ብለን እንዘናጋ ማለት አይደለም፤ ፖሊስም ክትትሉን ያቁም ማለት አይደለም፡፡ ዳሩ ግን አሁን ላይ እየተደረገ ያለው ይህ የ‹‹ሿሿ›› የክትትል ዘመቻ እጅግ ሊመሰገን የሚገባ እና ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የሚችል ነው፡፡ በፖሊስ ባህል አንድ አሰራር አለ፡፡ ‹‹ፓትሮል›› የሚባለው ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ፖሊስ በአንድ አካባቢ እየዞረ መታየት ማለት ነው፡፡ ፖሊስ በዚያ አካባቢ ሲዞር ታየ ማለት በአካባቢው አለ ማለት ነው፡፡ ይህ ለዜጎች ምን ያህል ሰላምና መረጋጋት እንደሚፈጥር፣ ለሌቦች ደግሞ ምን ያህል የስርቆት ተስፋ መቁረጥ እንደሚፈጥር ከተጨባጭ ማሳያዎች ማየት እንችላለን፡፡

በአካባቢያችሁ ስርቆት ባይሆን እንኳን የሆነ ህጋዊ ያልሆነ ነገር ለማድረግ ያሰቡ ሰዎን ልብ በሉ፡፡ ለምሳሌ፤ በህገ ወጥ መንገድ የሚሸጥ ነገር አለ እንበል። እነዚህ ሰዎች ምን ሲሉ ትሰማላችሁ? ከወዲያኛው አካባቢ የሚመጣውን ሰው ‹‹እኔ እምልህ? እዚያ ጋ ስትመጣ ፖሊሶች አሉ እንዴ?›› ብለው ይጠይቃሉ። ‹‹አዎ›› ብሎ ከመለሰ ተስፋ ቆረጡ ማለት ነው፡፡ ፖሊስ በአካባቢው አለ ማለት ይደረስብናል ብለው ይፈራሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ፖሊስ አለ ሲባል የግድ በእያንዳንዱ ግቢ በር ላይ አለ ማለት አይደለም፤ በአካባቢው ካለ ሌቦች ይፈራሉ፡፡ ስለዚህ ‹‹ፓትሮል›› የሚደረገው በአካባቢው አለን ለማለት ነው፡፡

ይህ አሁን የተጀመረው የ‹‹ሿሿ›› ሌቦችን የማደን ዘመቻ ልክ እንደ ‹‹ፓትሮል›› ማለት ነው። ከዚህ በኋላ አታመልጡም ማለት ነው፡፡ ‹‹አሁን ሲሰለቻቸው ይተውታል›› ብሎ የሚገባበት ሌባ ካለ ራሱንም ቤተሰቡንም ውርደት ላይ ይጥላል ማለት ነው፡፡ ይህኛውን ወንጀል እጅግ የከፋ የሚያደርገው መታሰሩ ብቻ አይደለም፡፡ ምስሉ በማህበራዊ ገጾች እና በቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ እንዲታይ ይደረጋል። ይህ ሰው በሄደበት ሁሉ አንገቱን ደፍቶ ይኖራል ማለት ነው፡፡ ቀና ብሎ የመኖር ሞራል አይኖረውም። ታማኝነት የለውም፤ ይህ ሰው ታማኝነት የለውም ማለት ምንም አይነት ሥራ እንኳን አምኖ የሚያሰራው አይኖርም ማለት ነው፡፡ ዕድሜ ዘመኑን በሥርቆት ሊኖር አይችልም፡፡ ስለዚህ ሰርቶ መብላት እንኳን የማይችልበትን ሁኔታ እየፈጠረ ነው፡፡

በነገራችን ላይ የ‹‹ሿሿ›› ሌቦች የዕለት ጉርስ የቸገራቸው ናቸው የሚባሉ እንኳን አይደሉም፡፡ ሰርተው መብላት የሚችሉ ወጠምሻ ጎረምሶች ናቸው። ምቹ አጋጣሚ ካገኙ ሰዎችን በሃይል (በድብደባ) የሚነጥቁ ናቸው፡፡ ስልኩን ከኪሱ ሲያወጡ የደረሰባቸው ሰው ግብ ግብ ቢገጥም ለመደባደብ የተዘጋጁ ጡንቸኞች ናቸው፡፡ ስለዚህ ወንበዴዎች ናቸው፡፡ እንኳን ምስላቸውን ማሳየት ቢገረፉ ራሱ አያሳዝኑም፤ ምክንያቱም ጨለማን ተገን አድርገው የስንቱን አንገት የቆለመሙ ናቸው፤ የስንቱን ሕይወት የቀጠፉ ናቸው፡፡

እነዚህ ሰዎች ለአገር የሚጠቅም የፈጠራ ሥራ በመስሪያ ዕድሜያቸው የድሃ ንብረት እንዴት እንደሚዘርፉ ነው ሲያውጠነጥኑ የሚውሉት፡፡ ሀገር የሚገነባ ጉልበታቸውን የሰው አንገት ለመቆልመም ተጠቀሙበት፡፡ ስለዚህ እንዲህ አይነት ወንበዴዎችን ለመቆጣጠር ማንም ሰው ተባባሪ እና ጠቋሚ ሊሆን ይገባል፡፡

እንኳን በተጨባጭ በምስል ማስረጃ የተያዙ ሰዎችን አሳይተው፤ ማስፈራሪያ ማድረግ በራሱ ዋጋ አለው፡፡ በሌቦች ላይ ፍርሃት ይፈጥራል፡፡ ፖሊስ ‹‹ፓትሮል›› ሲያደርግ ጥይት እየተኮሰ እና ሰዎችን እየገረፈ አይደለም፡፡ እንደማንኛውም መንገደኛ ነው የሚሄድ፤ ዳሩ ግን የፀጥታ አስከባሪ ስለሆነ ለምን ዓላማ እንደሚንቀሳቀስ ስለሚታወቅ ሌባ በዚያ አካባቢ ዝር አይልም ማለት ነው፡፡

የ‹‹ሿሿ›› ሌቦች ላይ የሚሰራው ተከታታይ ዘገባ ራሱን የቻለ ሌባን የማጽዳት ዘመቻ አካል ነው፡፡ በአንድ በኩል ራሳቸው ሌቦች ከፖሊስ እንደማያመልጡ ስለሚያውቁ ከድርጊታቸው ይቆጠባሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡ ለፖሊስ መጠቆምን እና አጠራጣሪ ነገር ሲያይ ለፀጥታ አካላት አሳልፎ መስጠትን ባህል ያደርገዋል፡፡ እስከ ዛሬ የምናየው ወቀሳ ብቻ ነበር። ሕዝቡ ራሱ ‹‹ብንናገርም መፍትሔ አይመጣም›› በሚል ሰበብ አጠራጣሪ ነገሮችን የማጋለጥ ልማድ አልነበረውም፡፡ አሁን ግን ለውጡን በተጨባጭ ሲያይ ለመጠቆም ይነሳሳል፡፡

በእንዲህ አይነት የጋራ ደህንነትን በሚያውኩ ድርጊቶች እና የሰዎችን ገንዘብና ሕይወት በሚቀጥፉ ሌቦች ላይ ፖሊስና ሕብረተሰብ የጋራ ትብብር ሊያደርግ ይገባል፡፡ የፀጥታ አካላት በሚሰጧቸው የመጠቆሚያ አድራሻዎች የመጠቆም እና እኛም የጋራ ደህንነቱ አካል መሆን ይልመድብን!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን የካቲት 6/2016

 

Recommended For You