የወሳኝ ኩነት መረጃ የሕዝብን ማኅበራዊና ተፈጥሯዊ ኩነት ሰንዶ ለማስቀመጥ አስፈላጊ ነው፡፡ ለአንድ ሀገር ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገትም የሚኖረው ስትራቴጂክ አስተዋጽኦም ከፍያለ ነው።
በሀገራችን የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ከተጀመረ ከ80 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። በዚህ ረጅም እድሜው ግን በሚጠበቀው መልኩ መዘመን የቻለ አይደለም። የዕድሜውን ያህል የሚመዘን አሁናዊ ቁመናም የለውም። በዛሬው እትማችን የዚሁ ሀገራዊ ተቋም አካል የሆነውን፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ አድርጌዋለሁ በሚለው ሪፎርም ምንነት ዙሪያ፣ ሪፎርሙ ይዟቸው ስለሚመጣቸው አዳዲስ አሰራሮች እና ሊፈታቸው ስለሚችላቸው የአግልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ወዘተ ጥያቄዎችን አንስተን ከኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ዓለማየሁ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ መልካም ንባብ፡፡ !!
አዲስ ዘመን፡- ኤጀንሲው ባለፉት ወራት ምን አቅዶ ምን ሰራ?
አቶ ዮናስ፡- ተቋሙ ባለፈው ዓመት ጀምሮ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት አለበት ተብሎ በከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ከተሰጣቸው ተቋማት ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ከዋና መስሪያ ቤት እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ በርካታ ጉዳዮችን ለመቀየር በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፤ በሰው ኃይል አደረጃጀት፤ ምቹ የስራ ከባቢ በመፍጠር ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
እንደ ተቋም፤ ተቋም ሁለት ዋና ዋና ስራዎች አሉት፤ አንደኛው የወሳኝ ኩነት ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ስራን መምራት ነው፡፡ በስድስት ወር ውስጥ የተሰራው ስራ በተለይም በወሳኝ ኩነት ምዝገባ እንደ ከተማ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ትልቁ ምክንያት ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ፤ ከአዲስ አበባ መድሃኒትና እንክብካቤ ባለስልጣን እና ከከተማ አስተዳደሩ በጋር መስራቱ፤ በግልም በመንግስት ጤና ተቋማት ላይ ሞትና ልደትን መመዝገብ የሚያስችል ስርዓት በመዘርጋት መመዝገብ መቻሉ ነው፡፡
አሁን ላይ ከ70 በላይ በሚሆኑ የጤና ተቋማት የልደትና የሞት ምዝገባ በማከናወን የምስክር ወረቀት ይሰጣል። ይህ መሆኑ በከተማዋ ያለውን የልደትና የሞት ምዝገባ ላይ ውጤት አምጥቷል፡፡ ሌሎች ሁነቶችም በተመሳሳይ የጋብቻና ፍች ምዝገባ ቢታይ ከዓለፉት ተመሳሳይ ዓመታት ጋር ሲታይ ከ50 በመቶ በላይ ብልጫ አለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሪፎርሙ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ለዘመናዊ ሀገር ግንባታ አስተዋጽኦው እንዴት ይገለጻል?
አቶ ዮናስ፡– የወሳኝ ኩነት ምዝገባ መቶ ፐርሰንት ደርሶ መንግስት እነዚህን መረጃዎች ባልያዘበት ሁኔታ ዘመናዊ ከተማና ዘመናዊ ሀገር መገንባት አይቻልም፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ ምን ያህል ሰው ተወለደ፤ ሞተ፤ ተጋባ፤ ተፋታ፤ የሚለው መረጃ እስከሌለ ድረስ የሀገሪቱንና የመዲናይቱን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለመምራት ያስቸግራል፡፡ ይህን መረጃ በሚፈለገው መንገድ ለማከናወን በትምህርት ቤት ጭምር ሕጻናት ስለ ወሳኝ ኩነት እንዲገነዘቡ በማድረግ የልደት ካርድ በትምህርት ምገባ እንደ አንድ ማስረጃ እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት የዲጂታል ምዝገባ አፈጻጸሙ ከመቶ ፐርሰንት ተሻግሯል፡፡ በወረዳና በማዕከል ከተሰጡት አገልግሎቶች ውስጥ በስድስት ወሩ 93 በመቶ የሚሆነው ዲጂታል ነው፡፡ የማንዋል መታወቂያ የተሰጠው 15 ሺ ገደማ ነው፡፡ ይህም የሆነው ወደ ዲጂታል አሰራር ባልገቡ በሶስት ክፍለ ከተሞች የሚገኙ 15 የሚሆኑ ወረዳዎች ላይ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱም የመሰረተ ልማት ችግር ነው፡፡ በተለይም ከሁለት ዓመት በፊት በማንዋል የተሰጠው መታወቂያ 89 በመቶ ገደማ ነበር፡፡ ይህ አሁን ላይ ተቀልብሷል፡፡ በሪፎርሙ በ104 ወረዳዎች ላይ ዲጂታል አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ በእነዚህ ወረዳዎች በምንም መልኩ ማንዋል አገልግሎት የለም፡፡
በሪፎርሙ አንዱ ትኩረት የተሰጠው የሚሰራጩ ህትመቶች መታወቂዎችና አገልግሎቶች ኦዲት መደረግ አለባቸው የሚል ነው፡፡ በ2014 ሪፎርሙ ሲጀመር መታወቂያ ጭምር ኦዲት ተደርጎ ነበር፡፡ የ2015 የግማሽ ዓመት በራሱ አቅም ኦዲት ማድረግ ተችሏል፡፡ በተደረገው ኦዲት ስራ 63 አመራር፣ ቡድን መሪዎችና ባለሙዎች ተጠያቂ ሆነዋል፡፡ የተጠያቂነት ደረጃውም ከዲስፕሊን እስከ ወንጀል ድረስ ነው፡፡
12 ሰዎች በወንጀል፣ 83 የሚሆኑ የተቋሙ ሰራተኞች፣ ደላሎችና ተገልጋዮች በስነ ምግባርና ጸረ ሙስና በተደረገው ክትትል በሕግ እንዲጠየቁ ተደርጓል፡፡ ከነዚህ ውስጥ 34ቱ ሀሰተኛ ሰነድ ይዘው የቀረቡ ባለጉዳዮች ናቸው። ሁለቱ ወረዳ ላይ የተያዙ ሲሆን 32 በማዕከሉ ሰነድ ሲረጋገጥ ሀሰተኛ ማስረጃ ይዘው የቀረቡ ናቸው። ካርዶች እየተሰራጩ ያሉት በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በኩል ሚስጥራዊነታቸው በተጠበቀ መልኩ ነው፡፡ በተተገበረው ቴክኖሎጂ ሀሰተኛ ሰነድን መለየት አስችሏል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ በሪፎርም ስራው ውስጥ የስያሜ ለውጥ ማድረጉ ምን ውጤት አስገኘ? እንደ ከተማ አስተዳደርና እንደ አገር ምን ጥቅም አለው? የነበሩ ችግሮችስ ምን ነበሩ?
አቶ ዮናስ፡- የስያሜ ለውጥ የተደረገው ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታውን ያማከለ እንዲሆን ለማድረግ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እና በተባበሩት መንግስታት ቻርተር እንደተመላከተው ዜጎች የወሳኝ ኩነት አገልግሎት የማግኘት ሰብአዊ መብት አላቸው፡፡ ዓለም አቀፉ ተሞክሮ ሲታይ ወሳኝ ኩነት ተብሎ የተሰየመበት የስያሜ አሰጣጥ ከዓለም አቀፍ ልምዱ ጋር በተወሰነ መልኩ ተዛብቷል፡፡ ወሳኝ ኩነት የሚሉት የሚመዘገቡት ኩነቶች ናቸው፡፡
ሁለት አይነት ወሳኝ ኩነቶች አሉ፤ አንደኛው በተፈጥሮ የሚከሰት እንደ ሞትና ልደት ያሉት ናቸው፡፡ ሌላው ማኅበራዊ የሚባሉ እንደ ጋብቻ ፍቺና ጉዲፈቻ የመሳሰሉት ኢትዮጵያ ተቀብላ የምትተገብራቸው ሰባት የሚሆኑ የወሳኝ ኩነቶች መጠሪያዎች ናቸው፡፡ ስርዓቱ ግን የሲቪል ምዝገባ ስርዓት ወይም ሲቪል ሪጅስትሬሽን ሲስተም ነው፡፡ ስራው የሚመራው በኤጀንሲ ወይም ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ ሳይሆን ዓለም ላይ ባለው መጠሪያ የሲቪል ምዝገባ ተቋም በሚባል ነው፡፡ እንደ ሀገርም ስምምነት ላይ የተደረሰው በዚህ ስያሜ ነው፡፡ በዚህ መሰረት ክልሎች ጭምር ስያሜውን እየቀየሩ ነው፡፡ ስያሜው እንዲቀየር የተደረገው ዓለም አቀፉ እውነታን መሰረት በማድረግ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከወሳኝ ኩነት ጋር በተያያዘ በሕብረተሰቡ ውስጥ ያለው ዕይታ ምን ይመስላል ?
አቶ ዮናስ፡- ወሳኝ ኩነት ሲባል ማኅበረሰቡ ወረዳ ላይ በመሄድ የሚስተናገድበት፤ ጥሩ አገልግሎት የሚያገኝበት ሳይሆን ቀበሌ ከሚለው አስተሳሰብ የሚያያዝ ነው። አዲስ አበባ ውስጥ ቀበሌ የሚባል አደረጃጀት የለም። ነገር ግን ወረዳ የሚለው ስም ማኅበረሰቡ ለአገልግሎት ሂዶ የሚንገላታበት አደርጎ ተስሏል፡፡ ይህን አስተሳሰብ ለመቀየር የግድ ከስም ጀምሮ ‹ሪብራንድ› መደረግ አለበት ተብሎ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ጥያቄ ቀርቦ ሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት እንዲሆን ተደርጓል፡፡
ተቋሙ የማንነት አስተዳደር ላይ የሚሰራ ነው፡፡ ይህም ማለት ግለሰቦችን ማንነታቸውን መዝግቦ እውቅና የሚሰጥ ነው፡፡ ”አበበ” የሚባል ሰው ”አበበ” መሆኑን አረጋግጦ ሰነድ የሚሰጠው ይህ ተቋም ነው፡፡ ”አበበ” ይህን ማስረጃ ከወሰደ በኋላ ትክክለኛ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መስተጋብሩን ይጀምራል፡፡ አንድ ሰው ማን ነህ? ሲባል ስለማንነቱ የሚገልጽ ሰነድ የሚሰጠው በዚህ ተቋም ነው፡፡ ሰዎች አሰራርንና መመሪያን ያልተከተለ ሕገ ወጥ ሀብትን ለማካበት ሲሉ ማንነታቸውን ይቀይራሉ፡፡ ከሰላምና ጸጥታ አኳያ የአካባቢን፤ የሀገርን ሰላም ማወክ የሚፈልግ ሰው የመጀመሪያ ዓላማው በዚህ ተቋም የሚሰጠውን መረጃ ማስወገድ ነው፡፡ ይህም በአዲስ አበባ ነባራዊ ሁኔታ ተፈጥሮ ተስተውሏል፡፡
ከሰራተኞች የስነ ምግባር ችግር፤ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ውስንነት፤ ጣልቃ ገብነት መኖር፤ ሕገ ወጥ ደላሎች በቀላሉ አሰራሩን የሚጠልፉበት ሁኔታ መኖርና መሰል ችግሮች ተደምሮ የተቋሙን አሰራር ተፈታትነውታል። በአገሪቱ ተጨባጭ ሰላምና ደህንነት አንጻር አዲስ አበባ ውስጥ ሊፈጠር ለታሰበው የሰላም ችግር እንደ መግቢያ በር የታሰበውም በተቋሙ ያለውን መረጃ በመጠቀም ነበር፡፡ ይህም በጻጥታ መዋቅሩና እንደ መንግስትም የተደረሰበት ስለነበር አገልግሎት መስጠት የቆመበት ወቅት ነበር፡፡ አገልግሎቱ መቆሙ ተቋሙ ራሱን እንዲያይ አድርጎታል፡፡ ካርዶች አሰራረን ተከትለው አለመሰራጨታቸው፤ የታተመ ካርድ ከብርሃንና ሰላም ጀምሮ የሚሰራጭበት ሁኔታ የቁጥጥር ስርዓት አልነበረውም፡፡ በዚህ የስርጭት ሂደቱ ስህተት ነበረበት፡፡ የማንዋልና ዲጂታል መታወቂያም በተመሳሳይ መንገድ በራሱ የሚመዘገበው ሰው ማን ነው ? የሚለው ቁጥጥር ይፈልጋል፡፡
ከሰራተኛ ጋር ተያይዞ የሚሰራውን ከማይሰራው መለየት፤ የሚያጠፋውን ማረምና መቅጣት ያስፈልጋል። የተቋሙ አስፈላጊነት በመዲናይቱ እየሰፋ ከመምጣቱ አንጻር የተቋሙ አደረጃጀት አገልግሎት ለመስጠት በቂ ስለመሆኑ፤ ኅብረተሰቡን የሚመጥን የአገልግሎት አደረጃጀት ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆን፤ ዲጂታል መታወቂያ ለኅብረተሰቡ በቀላሉ የማይደርሰው ለምድን ነው? የሚለውን በማየት ችግሮችን መቅረፍና አገልግሎት የማሻሻል ስራ መስራት ያስፈልጋል ነበር፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ የአዲስ አበባን ለየት የሚያደርገው የነዋሪ አገልግሎትን አብሮ ነው የሚመራው፡፡ በጡረታ ከቤታቸው የሚኖሩ ዜጎች አገልግሎት የሚያገኙት በውክልና ነው። በዚህ ወቅት መብታቸውን ለአልተገባ ጥቅም ይውላል ተብሎ ስለሚታሰብ ሰዎቹ በሕይወት ስለመኖራቸው የተመዘገቡበት የመንግስት ተቋም ደብዳቤ እንዲሰጥ ይገደዳል፡፡ ለማኅበራዊ ዋስትናም ደብዳቤ ይጽፋል፡፡
የሲቪል ምዝገባ ስርዓት በዲጂታል ካልሆነ በባህሪው አገልግሎቱ ወደኋላ ይቀራል፡፡ ስለዚህ አሻራ መቀበልና ማስተናገድ አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከዜጎች አሻራ መቀበል የሚያስችል የተደነገገ ሕግ አልነበረም፡፡ ለባንክ ቢፈልግ ማጋራት የሚያስችል መመሪያ የለም፡፡ የዚህ ስልጣንና ተግባር በዚህ በአዲሱ ስያሜ ተግባርና ኃላፊነቱ ተካቷል፡፡ አሁን ላይ በተቋሙ ያለ ሕግና መመሪያ የሚሰራ ምንም ስራ የለም፡፡
የሰው ሀብት መረጃ አያያዝ በኩል መረጃው “ስካን” ተደርጎ በዘመነ መልኩ እንዲያዝ ተደርጓል፡፡ በ104ቱም ወረዳዎች የሚከናወኑ የወሳኝ ኩነትና ሲቪል ምዝገባ አገልግሎት ቀጥታ መረጃው በማዕከል ይመዘገባል፡፡ ምን ያህል፤ ሞት፤ ፍቺ፤ ልደትና መሰል ሁነቶች ይመዘገባሉ፡፡ ይህን ማድረግ የሚያስችል ሶፍት ዌር በተቋሙ ባለሙያዎች ለምቷል፡፡ በፊት የማንዋል ስራዎች በነበሩ ጊዜ አሰራሩ አስቸጋሪ ነበር፡፡ አሁን ግን ቀጥታ ሰነዱን ሲስተም ላይ አስገብቶ ማረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ምንም አይነት የወረቀት ንክኪ የለም፡፡ አሰራሩ እንዲዘምን የተደረገው ደሞዝ በመቀየር ሳይሆን የአስተሳሰብ ለውጥ በመኖሩ ነው፡፡
በፊት በተቋሙ የነበረው አሰራር ችግር ያለበት በመሆኑ አገልግሎት ቆሟል፡፡ ይህ የቆመው በከተማ አስተዳደሩ ሊሆን ይችላል፡፡ የቆመው የቁጥጥር ስርዓት ባለመኖሩ በነበረው ችግር ነው፡፡ ሌብነት፤ ሰነድ ማጭበርበር ነበር፤ ይህን ማስተካከል ከተቻለ የተሻለ ተቋም እንሆናለን በሚል ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ አሁን ላይ በአገልግሎቱ በሕዝቡ ረክቷል ወይ ከተባለ ገና አልረካም፡፡ አሁንም በጣም ብዙ የሚቀሩ ነገሮች አሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ በ1935 ዓ.ም የተሰመረተ እንደመሆኑ መጠን በዕድሜው ልክ ዘምኗል ማለት ያስደፍራል?
አቶ ዮናስ፡- ዕድሜውን የሚመጥን ተቋም እንዲሆን ባለፉት ዘጠኝ ወራት መሰረት የመጣል ስራ ሰርተናል፡፡ መሰረት ተጥሏል? ብለህ በቀጣይ ሰኔ ወር ላይ ብጠይቀኝ በእርግጠኝነት አዎ ብዬ በልበ ሙሉነት እመልሳለሁ። መሰረት መጣል ማለት አንዱ ሕግ ማውጣት፤ የሰው ኃይል፤ የአሰራር ስርዓት ተቋማዊ ማድረግ ነው፡፡ የሕግ ማውጣት ጉዳይ አልቋል፡፡ ካሁን በኋላ የሚቀየር አሰራር የለም፡፡ የአሰራር ስርዓቱ በሙሉ ወደ ሕግ ማቀፍ ገብቶ መሰረት ይዟል፤ አንዳንዶቹም ትግበራ ላይ ገብተዋል፡፡
ሕጎቹ ወደ እንግሊዝኛና ብሬልም እየተተረጎሙ ነው። በቴክኖሎጂ ትግበራም የተያዙት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ለሌሎች ተቋማት ጭምር የሚተርፍ ነው፡፡ ከወራት በኋላ ወደ ስራ የሚገባ ግንባታው የተጠናቀቀ የዳታ ማዕከል አለ፤ በተደጋጋሚ ሲስተም በመቆራረጥ ለአገልግሎቱ ችግር የሆነው የዳታ ማዕከሉ ማዘጋጃ ቤት ነው ያለው፡፡ ይህ ዳታ ማዕከል ከ15 ዓመት በፊት ውስን ለሆኑ ተቋማት የኢሜልና የዌብሳይት አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡ ከዚህ ዳታ ተነስቶ ወደ ወረዳ የሚደረስ መስመር አልነበረም፡፡ ሁሉም ተቋማት በአንድ የዳታ ማዕከል አገልግሎት ሲሰጡ የመጨናነቅ ሁኔታ ነበር፡፡
አሁን ላይ ይህን መጨናነቅ ለማስቀረት በአንድ ማዕከል ለማከናወን መስመሩ እንዲዘረጋ ተደርጓል። “የወረዳ ኔት” የሚለውን ስያሜ በመተው “ሲአርኔት” በሚል የራሱን የቻለ ሲስተም ተዘርግቷል፡፡ ይህን መሰረተ ልማት የሚያሻሻል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከሁለት ወር በፊት በግማሽ ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት ተጀምሮ ቁሳቁሶች እየገቡ ነው፡፡ ኔትወርክ ሲቋረጥ የት አካባቢ እንደሆነ የሚጠቁም ሲስተም እየተዘረጋ ነው። ከአንድ ወር በኋላ ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል፡፡
ለተቋሙ አገልግሎት በተሰጠው ትኩረት መሰረት የፊትና የአይን አሻራ ከዚህ በፊት አልነበረም፡፡ አሁን ላይ በሁሉም ወረዳዎች ገብቷል፡፡ ምክንያቱም ተቋሙ ካልተሻሻለ ለውጥ ሊመጣ አይችልም፡፡ ስለዚህ ይህን ታሳቢ ያደረገ ሲስተም እየለማ ነው፡፡ ወደ አገልግሎት ሲገባ አገልግሎት በኦንላይን የሚሰጥበት ስርዓት ለመፍጠር ነው። ለዚህ ደግሞ አሻራ ሊቀበል የሚችል ኮምፒውተር መኖር አለበት፡፡
አንዳንድ ወረዳ ላይ ያሉ ኮምፒውተሮች ከእጅ ስልክ አይበልጡም፤ ካሉት ወረዳዎች ብቁ የሆነው ኮምፒውተር ብቁ የሚባለው መቶ አይሞላም፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ከከተማ አስተዳደሩ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ጋር በመነጋር ዘመናዊ የሆኑ ስምንት መቶ ኮምፒውተሮችን ለመግዛት እየተሰራ ነው፡፡ እነዚህ ኮምፕዊተሮች ዋናው መስሪያ ቤት በሚቆጣጠርበትና ክትትል ሊያደርግ በሚችልበት መልኩ ተዘጋጅተው ይሰራጫሉ፡፡ የ80 ዓመት እድሜ ያለው ተቋም ግን በዚህ ደረጃ መገኘት አልነበረበትም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ በ1935 በሰርተፊኬት ጋብቻ ስታስፈጽም ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች በቅኝ ግዛት ስር ነበሩ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ነዋሪው በተለይም በልደት ካርድ ስርጭት ላይ ውስንነት እንዳለ ከፍተኛ ቅሬታ ያሰማልና እርሶ ይህን እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ዮናስ፡– የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እዛው ተመዝግቦ ወዲያውኑ ሰርተፊኬት ይዞ የሚሄደው አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ሌሎች ክልሎች ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሀገሮች የምስክር ወረቀት ይቆያል፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ ላይ ህጻን በጤና ጣቢያ እንደተወለደ ለአገልግሎት መስሪያ ቤቱ መረጃ ይሰጥና የምስክር ወረቀቱ ቆይቶ ይደርሳል፡፡
ኤጀንሲው የሚሰጠው የወሳኝ ኩነት የምስክር ወረቀት የሚታተመው ብርሃንና ሰላም ማተሚ ድርጅት ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የሚታተመው በሚስጥራዊ ህትመት ከፍል ነው፡፡ ሀገሪቱ ውስጥ የሚከናነወኑ የወሳኝ ኩነትና ሌሎች ሚስጥራዊ ካርዶች በሙሉ የሚያትመው ይህ ድርጅት ነው፡፡ ስለሆነም ተቋሙ እንደማንኛውም ተቋም የማተሚያ ማሽን ብልሽት ይገጥመዋል፡፡ በዚህ ወቅት በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ጫና ይፈጠራል፡፡
የልደት ሰርተፊኬት በትምህርት ቤቶች በንቅናቄ ለመስጠት ሞክረን ነበር፤ ነገር ግን የካርድ እጥረት አጋጠመን፡፡ ማተሚያ ቤቱም ሕትመቱን በወቅቱ ማድረስ አልቻለም፤ የዲጂታል ማንነት ምዝገባ በባህሪው ውድ ነው፡፡ የማሽን ብልሽት በሚገጥምበት ወቅት እስከ ዱባይ ድረስ በመላክ ጥገና ይደረግ ነበር፡፡ የአጭር ጊዜ መፍትሄ የተወሰደው ክፍለ ከተሞች እንደየአቅማቸው እንዲገዙ ነው፡፡ ምክንያቱም ያለ ካርድ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡
አሁን ላይ ከካርድ ሕትመት ጋር በተያያዘ ብዙም ችግር የለም፡፡ ምን ያህል ካርድ ተላከ? ምን ያህል ታትሞ ለተገልጋይ ተሰጠ? የሚለው ማዕከል ላይ ባለው መቆጣጠሪያ መከታተል ተችሏል፡፡ ነገር ግን ቴክኖሎጂው የሚፈጥረው ችግርም አለ፤ ፕሪንተሩ ከተበላሸ አገልግሎት ይቆማል፡፡ አንድም ሰው የወረቀት መታወቂያ መያዝ የለበትም በሚል ወደ ዲጂታል መታወቂያ እየተቀየረ ነው፡፡ በዚህም እስካሁን አንድ ነጥብ 52 ሚሊዮን ሕዝብ ዲጂታል መታወቂ የያዘ ሲሆን 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ ደግሞ ተመዝግቧል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሪፎርም ስራው የሰራተኛው ደሞዝ አሁን ካለው የኑሮ ውድነት ጋር እንዲጣጣም የተደረገ ነገር አለ?
አቶ ዮናስ፡– እኔ የማልስማማበት አንድ ነገር አለ፡፡ ይህም አንድ ባለሙያ ጥሩ አገልጋይ ሆኖ በተመደበበት ቦታ ላይ እንዲያገለግል ደሞዝ ወሳኝ ነው የሚል እምት የለኝም። ከእኛ ተቋም የተሻለ ደሞዝ የሚከፈላቸው ተቋማት አሉ። ነገር ግን አሁንም ሌብነትና በርካታ ችግሮች አሉባቸው። የተሻለ ገንዘብ እያገኙ በስነ ምግባር የማያገለግሉ አሉ። ስለዚህ በአግባቡ አገልግሎት ለማግኘት ከደሞዝ ጋር የሚያገናኘው አስተሳሰብ በልኩ መታየት አለበት፡፡
የተሻለ መከፈሉ ያነሳሳል ነገር ግን የሚከፈለኝ ደሞዝ ትንሽ ነውና ልስረቅ የሚለው አስተሳሰብ በተለይም ኢትዮጵያ ውስጥ አይሰራም፡፡ ይች ሀገር በምንሰራው ልክ ሙሉ ለሙሉ እየከፈለች ለማሰራት የምትችልበት አቅም አልደረሰችም፡፡ እንደ ሀገር ሰነድ ለሚሰጡ ተቋማት ያለው ትኩረት አነስተኛ ነው፡፡
በሪፎርም ስራው ግን ሰራተኛውን ጥቅም ለማስከበር የተጀመረ ስራ አለ፡፡ በእርግጠኝነት በቅርቡ ውጤት ላይ ይደርሳል፡፡ ቢያንስ እንኳን ደረጃቸው ሊሻሻል የሚችልበትና የሚወደው ተቋም ለማድረግ በቅርቡ አዲስ የሰራተኛና ደንብ ልብስ ይተዋወቃል፡፡ ይህም ለብሶ ለመስራት ብቻ ሳይሆን ሰራተኛው ኃላፊነት አውቆ በአግባቡ እንዲወጣ እንዲቻል ደረጃቸውን የጠበቀ ሁለት አይነት ሙሉ የደንብ ልብስ ይፋ ይደረጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኤጀንሲው ከዚህ በፊት በ2016 በጀት ዓመት የወረቀት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ይቆማል የሚል መረጃ ሰጥቶ ነበር፡፡ አሁን ላይ በ15 ወረዳዎች የወረቀት አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡ ለምን በእቅዱ መሰረት አልተከናወነም?
አቶ ዮናስ፡- እስካሁን የተቋማችን የወሳኝ ኩነት አገልግሎት ወደ ዲጂታል ያልገባው 6 በመቶ ብቻ ነው። እነዚህ ወረዳዎች የመሰረተ ልማት እና ሌሎች ተጨማሪ ችግሮች ያሉባቸው ናቸው፡፡ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ሲደረግ የጣት አሻራ ከሲስተሙ ጋር የሚናበበው ከአንድ የሕንድ ኩባንያ ጋር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሲስተሙን በኩባንያው ተቆልፏል፡፡ ይህ ማለት ድርጅቱ መጥቶ ‹‹ኢንስቶል›› ካላደረገው በቀር በራስ አቅም “ኢንስቶል”ማድረግ አይቻልም፡፡
ከድርጅቱ ጋር ቀድሞ የነበረው ውል በትብብር ነበር፤ አሁን ላይ ዶላር ካልከፈላችሁ የሚል ሀሳብ በማንሳቱ ድርድር ተደርጎ 170 የሚሆን ፈቃድ በቅርቡ ይገዛል፡፡ አሁንም እርግጠኛ መሆን የሚቻለው የወረቀት አገልግሎት በዚህ ዓመት ያበቃል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በመሸኛ የሚመጡ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡ ነገር ግን ከመጡ በኋላ በወረዳዎች ከሶስት እስከ ስድስት ወር ጠብቁ እየተባሉ ለተለያዩ እንግልት እየተዳረጉ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ መታወቂያ ከሌላቸው ለችግር የሚጋለጡበት ሁኔታ ከፍተኛ ነውና ይህ እንዴት ይታያል?
አቶ ዮናስ፡- እንደ ሀገር ቀድሞ ቴክኖሎጂዎችን አስገብታ ብትሰራ ኖሮ እንዲህ አይነት ችግሮች አይከሰቱም ነበር፡፡ ለመታወቂያ አሰጣጥ መሰረታዊ ችግር የሆነው ዘመናዊ የሆነ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የአሰራር ስርዓት አለመዘርጋቱ ነው፡፡ አንድ ሰው ከተወለደ ጊዜ ጀምሮ እሱን የሚመለከት መረጃ ይቀመጣል፡፡ ይህ መረጃ እንደ ሕግ ለሁሉም መረጃ የሚያጋራ ቢኖር መሸኛ አምጥቶ አዲስ አበባ አበበ ነኝ ብሎ መዝግቡኝ ቢል ለዚህ ችግር አይዳረግም ነበር፡፡ ችግሩ ወጥ የሆነ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አለመኖሩ ነው፡፡
አዲስ አበባ መታወቂያ አሰጣጥ የሚታገድበት አንዱ ምክንያት ሰላማዊ ያልሆኑ ሰዎች ወደ ከተማዋ በመግባት የተዛባ ማንነት ይዘው ስለሚገቡ ነው፡፡ ለምሳሌ “ዮናስ” በአንድ ክልል ነዋሪነት ተመዝግቦ መሸኛ ይዞ የአዲስ አበባ መታወቂያ ሲጠይቅ የሚያመጣው አንድ ነጠላ ወረቀት “ዮናስ” ነው ብሎ ሲሰጥ በትክክልም “ዮናስ” ስለመሆኑ የሚረጋገጥበት አንዳችም መንገድ የለም፡፡ የያዝነው ማንነት በመተማመንና በፈጣሪ ጥበቃ እንጂ ደቡብ ኦሞ ያለ አንድ የቀበሌ ሊቀመንበር የሚሰጠው የመሸኛ ወረቀት ትክክለኛ ስለመሆኑ ምንም አይነት ማረጋገጫ የለም፡፡ ይህም አዲስ አበባ ላይ ችግር ፈጥሯል፡፡ ከዚህ የተነሳ ወደ ከተማዋ የሚመጣውን ሰው ማጥራት አለብን፡፡ ከዚህ አንጻር መዝግበን የምናቆይበት ጊዜ ረዝሟል፡፡
ከሌሎች ክልሎች በመሸኛ መጥተው አዲስ አበባ ነዋሪ መሆን በግማሽ ቢዘጋም 70 በመቶው ክፍት ነው፡፡ በስራ ዝውውር፤ በሕመም አዲስ አበባ ምቹ ነው ከተባለ፤ ትምህርት ዕድል ለማግኘት አዲስ አበባ ሆኖ ለመከታተል፤ የሚፈልጉ አካላት በማስረጃ መታወቂያ እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ በአንድ ቤት 20 ሰው ብቻ መታወቂያ መውሰድ ይችላል የሚለውን መመሪያ ያወጣን ስለተቸገረን ነው። በፊት በአንድ ቤት እስከ 180 ሰው ይመዘገብ ነበር፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በፊት መመሪያው ገደብ አልነበረውም። አሁን ግን 20 ሰው የሚል ገደብ ተበጅቶለታል፡፡ ይህ ገደብ ሲመጣ ጫጫታ ተነሳ፡፡
ለምሳሌ በድሮው ኮልፌ 13 በአሁኑ አዲስ ከተማ 13 የሚኖር አንድ ሰው በውስጡ 78 ሰዎችን አስመዝግቦ ተገኝቷል፡፡ ይህ ሰው መሸኛ የያዙ ሰዎችን እያመጡ መዝግቡልኝ ይላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ጌታዬ በእርስዎ ቤት 78 ሰዎች ተመዝግበዋል፡፡ እንዴት ተጨማሪ ይጠይቁናል? ተብለው በባለሙያዎች ሲጠየቁ ፤ “ምን አገባችሁ! ይህን ያህል ብቻ ነው ማስመዝገብ የሚል መመሪያ አላችሁ? አሳዩኝ!” የሚል ምላሽ ሰጡ፡፡ በእዚህ እና መሰል ችግሮችን ተከትሎ እንደመፍትሔ በአንድ ቤት ከ20 በላይ ሰዎች ማስመዝገብ አይቻልም የሚል መመሪያ ልናወጣ ተገደናል። ልጅ ከሆነ ግን 21ኛም ሆኖ መመዝግብ ይቻላል። መመሪያው ይህንን አይከለክልም፡፡ በነገራችን ላይ የዚህ መስሪያ ቤት ችግር ለዘመናት ሲንከባለል የመጣ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በበርካታ ወረዳዎች የልደት ካርድ እጥረት አለ የሚል ቅሬታ ይነሳሉ፤ እዚህ ላይ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው ?
አቶ ዮናስ፡– ከልደት ካርድ ተያይዞ የህትመት ችግር አለ፡፡ ችግሩን ለመፍታት ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት ለሚያደርግልን ትብብር እውቅና እንሰጣለን፡፡ አሁን ከልደት ካርድ ጋር ተያይዞ ትልቁ ችግር የካርድ ስርጭት መሆኑን ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።
አቶ ዮናስ፡- እኔም መአሰግናለሁ፡፡
ሞገስ ተስፋና ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2016