ሞቃዲሾ ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት የአረብ ኤምሬትስና የባህሬን የጦር መኮንኖች ተገደሉ

በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ በሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና የባህሬን መኮንኖችን ጨምሮ አምስት የጦር መኮንኖች መገደላቸው ተገለጸ።

ያላፈው ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በተፈጸመው ጥቃት ሦስት የኤምሬትስ፣ አንድ የባሕሬን እና የሶማሊያ የጦር መኮንኖችን ጨምሮ ቢያንስ አምስት ሰዎች መገደላቸውን የሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ከዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ መንግሥት የወጣ መግለጫ እንዳመለከተው፤ “የሽብር ድርጊት” ባለው ጥቃት የተገደሉት መኮንኖች የሶማሊያ ኃይሎችን በማሠልጠን ተልዕኮ ላይ ሳሉ ነበር።

ጥቃቱን የፈጸመው ግለሰብ ወደ ወታደራዊ ሠፈሩ በመግባት አሠልጣኞችን ዒላማ በማድረግ ተኩስ ከፍቶ ነው አምስት ሰዎችን ገድሎ ሁለት ሌሎችን ማቁሰሉን አንድ ወታደራዊ መኮንን እና የሆስፒታል ሠራተኛን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ጥቃቱን “አስከፊ የሽብር ድርጊት” በማለት አውግዘው፣ ሶማሊያን ከሽብርተኝነት ነጻ በማውጣት እና ሠራዊቱን መልሶ በመገባት ሂደት መስዋዕትነት የከፈሉ ላሏቸው መኮንኖች አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ጥቃቱን አስመልክቶ መግለጫ ያወጣው የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ የመከላከያ ሚኒስቴር ከተገደሉት መኮንኖች አሃዝ ውጪ ዝርዝር መረጃ ያልሰጠ ሲሆን፤ ጥቃቱን ለመመርመር “ከሶማሊያ መንግሥት ጋር የሚያደርገው ትብብር እንደሚቀጥል” አመልክቷል።

በአረብ ኤምሬትስ በሚመራው የጦር ሰፈር ውስጥ ተኩስ ከፍቶ መኮንኖችን የገደለው እና ጉዳት ያደረሰው አህመድ በሚል ስም ብቻ የተገለጸው አዲስ ሠልጣኝ ወታደር ጥቃቱን በፈጸመበት ጊዜ ተተኩሶበት ተገድሏል።

“ወታደሩ፤ አሠልጣኝ የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና የሶማሊያ ወታደራዊ መኮንኖች በጸሎት ላይ ሳሉ ነበር ተኩስ የከፈተው። በጥቃቱ አራት የኤምሬትስ መኮንኖች ሲቆስሉ፣ አራት የሶማሊያ ወታደሮች ተገድለዋል” ሲል አንድ መኮንን ለሮይተርስ ገልጿል።

መኮንኑን ጨምሮም ጥቃት ፈጻሚው ወታደር በሶማሊያ እና በአረብ ኤምሬት ተመልምሎ ወደ ሥልጠና ከመግባቱ በፊት ከአልሻባብ የከዳ የቡድኑ አባል ነበር።

ከአልቃኢዳ ጋር ትስስር ያለው አልሻባብ ባወጣው መግለጫ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደ ሲሆን፣ ተዋጊዎቹ 17 ወታደሮችን መግደላቸውን ገልጿል።

ከተገደሉት ወታደራዊ መኮንኖች በተጨማሪም አስር የሶማሊያ ወታደሮች ቆስለው ወደ ህክምና መወሰዳቸውን የሆስፒታል ምንጮች ለሮይተርስ ተናግረዋል።

አልሻባብ ሰፊ የሶማሊያ ግዛትን ተቆጣጥሮ በደካማው የሶማሊያ መንግሥት ላይ ዋና ከተማዋን ጨምሮ ከአስር ዓመታት በላይ የሽምቅ ጥቃቶችን ሲፈጽም ቆይቷል።

ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በከፈቱት ተከታታይ ዘመቻ አልሻባብ ከባድ ሽንፈት ገጥሞት ከአንዳንድ ይዞታዎቹ ለመልቀቅ ተገዷል።

ቢሆንም ግን ቡድኑ አሁንም በመንግሥት ኃይሎች እና በሌሎችም ላይ ከባድ ጥቃቶችን እየፈጸመ ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑን ቀጥሏል።

በሶማሊያ መንግሥት ወታደሮች እና በአልሻባብ ታጣቂዎች መካከል ሙዱግ በተባለው በሀገሪቱ ማዕከላዊ ክልል ውስጥ ባለፈው ወር ከባድ ውጊያ መደረጉ የሚታወስ ነው።

በርካታ የሶማሊያ አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ የሚገኘው አልሻባብ የተለያዩ ጥቃቶችን እየፈጸመም ይገኛል። የሶማሊያ መንግሥት በማዕከላዊ እና በደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ሰፊ ቦታዎችን በተቆጣጠረው እስላማዊው ታጣቂ ቡድን ላይ ባለፉት ወራት ጥቃቶችን ሲያካሂድ ቆይቷል።

ባለፈው ዓመት ወደ ሥልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሚሐሙድ ከአል ቃኢዳ ጋር ግንኙነት ባለው ታጣቂው አልሻባብ ላይ ከወራት በፊት ወታደራዊ ዘመቻ ሲከፍቱ ቡድኑን በወራት ውስጥ ለማጥፋት ቃል ገብተው ነበር።

ደካማውን የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት ክፉኛ እየተፈታተነ ያለው አልሻባብ ከባድ የቦምብ ጥቃቶችን በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት በመፈጸም የመንግሥት ባለሥልጣናትን፣ የፀጥታ ኃይሎችን እንዲሁም ሰላማዊ ሶማሊያውያንን ሲገድል ቆይቷል።

መንግሥት በቡድኑ ላይ ባለፉት ወራት ባካሄደው ዘመቻ ጥቂት የማይባሉ ቦታዎችን ማስለቀቅ ቢችልም፣ አሁንም በርካታ የሶማሊያ አካባቢዎች በአልሻባብ ቁጥጥር ስር ይገኛሉ።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን የካቲት 5/2016

 

 

 

 

Recommended For You