ወጣት ጡረተኞች

ጡረተኝነት መልኩ ብዙ ነው፤ ሰዎች ረጅም እድሜ ከኖሩ፣ ከተማሩ፣ ከሠሩና የቻሉትን ያህል በጉብዝናቸው ዘመን ከሮጡ እና ከታተሩ በኋላ እድሜ ሲገፋ ወደ ጡረተኝነት ይሸጋገራሉ፡፡ ታዲያ ይህ ማለት ሁሉም በእድሜ ዘመኑ የሚያገኘውና በተፈጥሮ ዑደት ውስጥ የሚጎናጸፈው ከእግዜሩ የተቸረ ጸጋ ነው፡፡

ይህ የጡረተኝነት ዘመን ምንም እንኳን እንከን የሌለበት ሂደት ቢሆንምና የራሱ የሆነ ጣዕም እና ሂደት ቢኖረውም፣ ምናልባት የጡረተኝነትን ዘመን በጥቂቱ ጎዶሎ የሚያደርገው ጡረተኞቹ ከዚህ በፊት ራሳቸውን ችለው ተንቀሳቅሰው ማድረግ የሚችሉትን ነገር እየቀነሱ በመሄዳቸው መደገፊያ ምርኩዝ የመሻታቸው ጉዳይ ነው፡፡

ይህ የሚሆንበት ዋነኛ ምክንያት ቀድሞ የነበራቸው አቅም በአሁን ወቅት ስለማይኖራቸው እንዳሻቸው መሆን የማይችሉ በመሆኑ ነው፤ ታሪክ ራሱን ይደግማል እንደሚባለው ሰዎች ልክ እንደ ልጅነታቸው ጊዜ ለመዳህ፣ ለመብላት፣ ለመጠጣት እና አያሌ ተግባራትን ለማከናወን የእናትና የአባታቸው ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ የሌሎችን ሰዎች ድጋፍ የሚሹበት ወቅት ሲሆን፤ ይህም ጸጋውና ምሕረቱ ከበዛው ከእግዜሩ የሚቸር ነው፡፡

በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከግልና ከመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች አያሌ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች በተለያዩ የትምህርት መስኮች በብዙ ልፋትና መከራ ይመረቃሉ። ታዲያ ከእነኝህ ወጣቶች መካከል ወደ ሥራ የገቡት ምን ያክሎች ናቸው? በሥራ ማጣት፣ላይ ታች እየዳከሩ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉትስ? የሚለው የዘወትር ጥያቄዬ ነው። ምስጋና ይግባትና ይሄን ጽሑፍ እንድፅፍ በማነሳሳት ሀሳቤን እንድገልጽ በር ለከፈተችልኝ ለአንዲት ውድ ወዳጄ።

ወላጅ ከተረፈው ሀብቱ ቀንሶ ሳይሆን ከእለት ጉርሱ አሳንሶ ልጆቹን ሲያስተምር ልጄ ተምሮ፣ እውቀት ቀስሞ ሰው ይሆንልኛል የሚለውን በጎ እሳቤ በመያዝ ነው፡፡ ከምንም በላይ ወላጅ ልጁ በደከመበት እና ባረጀበት ወቅት ምርኩዝ እንደሚሆንለት ያስባል፤ ታዲያ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ በብዙ መስዋዕትነት የተማረው ልጅ ገና በለጋነቱ ከወላጆቹ ጥገኝነት መላቀቅ ተስኖት የእናቱን መቀነት ያስፈታል፡፡ ነገር ግን በሩብ፣ በመንፈቅና በበጀት ዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሥራ አስያዝን የሚሉ ሪፖርቶችም በየወቅቱ መውጣታቸው አልቀረም፡፡

ብዙ በመሥራት ራስን፣ ቤተሰብን እና ሀገርን መቀየር በሚቻልበት በዚህ የብርቱነት ወቅት ቁጭ ብለው ጊዜያቸውን በማባከን የኋሊት የሚጓዙ ወጣቶችን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ ወጣቶች ገና በለጋነት እድሜያቸው በቤተሰቦቻቸው ጫንቃ ላይ ጥገኛ በመሆን የወጣት ጡረተኞች ሆነዋል። ኢትዮጵያ ካሏት ዜጎች ውስጥ አብዛኛው ወጣት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህም በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰው ሀይል ከበለጸጉ ሀገራት አንዷና ተጠቃሽ ናት፡፡

ዜጎቿም በሥራ አጥነት እና በድህነት መኖሩን ለመሸሽ በሕጋዊም ሆነ በሕገወጥ መንገዶች ባሕር ማዶ በመጓዝ በተለያዩ ሀገራት እንጀራ ፍለጋ ተሰማርተዋል፡፡ በዚህም ምንም እንኳን ተሳክቶላቸው ሕይወታቸው የተቀየረላቸው ጥቂት ዜጎች ቢኖሩም ነገር ግን ቤተሰቦቻቸው ረብጣ ዶላር ሲጠብቁ አስከሬናቸው የተላከላቸው ብዙ ናቸው። ይህ ጉዳይ እስከ መቼ ይቀጥል ይሆን? ኃላፊነቱስ የማን ይሆን?

ወጣትነት ሲደመር ጡረተኝነት ውጤቱ ከባድ ነው፤ እኔም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቄ ከወጣሁ በኋላ ለጥቂት ጊዜያት ወጣት ጡረተኝነትን በሚገባ አጣጥሜዋለሁ፤ በወቅቱም ነገሮችን የማድረግ ፍላጎቱና ምኞቱ እያለኝ አቅም የማጣት ስሜት ይጫጫነኝ ነበር፡፡

አባቴ ለበርካታ ዓመታት በመንግሥት ሠራተኝነት ጊዜውን አሳልፏል፤ አሁንም በዚሁ ሥራ ላይ ይገኛል፤ ተማሪ እያለሁ ሁሌም አንድ የሚናገረኝ ነገር ነበር ‹‹እኔ የማወርስህ ጋሻ መሬትም ሆነ ሀብት የለኝም፤ አንተን አስተምሮ ለቁምነገር ከማብቃት በስተቀር ስለዚህ ጎብዘህ ተማር›› ይለኝ እንደነበር እስካሁን ይታወሰኛል፤ እኔም ቁርጤን አውቄ ከመመረቅ በዘለለ ያለኝን አቅም አሟጥጬ በመጠቀም ተወዳዳሪ ዜጋ መሆን እንዳለብኝ ይሰማኝ ነበር፡፡

የሆነው ሆኖ ትምህርቴን በከፍተኛ ማዕረግ ካጠናቀቅኩ በኋላ ምንም እንኳን ስሜቱ መራርና ከባድ ቢሆንም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳልል የአንድ ዓመት ከመንፈቅ ጊዜዬን የወጣት ጡረተኛ በመሆን አሳልፌያለሁ፡፡

በአሁኑ ወቅት ምንም እንኳን እራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ለመቀየር ቀን ከሌት የሚታትሩ ጥቅት ወጣቶች ቢኖሩም፤ በሌላ በኩል ስለነገ ዓላማና ራዕያቸው ከማሰብና ከማቀድ ይልቅ ቁጭ ብሎ ስለ ትናንትናው ታሪክ በማሰብና በመጸጸት መኖሩን የተያያዙም አልጠፉም፡፡ ይህንን ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት የወጣቱን ዕጣ ፈንታ ከመቀየር ይልቅ ያለፈን ታሪክ ስቦ አውጥቶ ለወጣቱ በማቀበል የግጭት ነጋዴ የሆኑም አልጠፉም፡፡

በሀገራችን የፍላጎት እና የአቅርቦት አለመመጣጠንን ተከትሎ የኑሮ ውድነቱ እያደገ ቢሄድም፤ ሀይ ባይ በማጣቱ በቀን ሶስት ጊዜ መመገብ ቅንጦት እየሆነ በመጣበት በዚህ ወቅት ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ የመጣውን ሥራ አጥ የሰው ኃይል ቁጥር ከመንግሥትም ሆነ ከግሉ ዘርፍ መፍትሔ የሚሻ አንገብጋቢ ጉዳይ እንደሆነ እስካሁን ቀጥሏል።

ምንም እንኳን እኔም ከእናንተ ያልተሻልኩ ሰነፍ ቢጤ ወንድማችሁ ብሆንም ይህንን የወጣትነት ዘመን በፍጹም ዳግም የማታገኙበት ዓመታቶች ሩቅ አይደሉምና ካላችሁበት የጭንቅ ጊዜያቶች ውስጥ በመውጣት ተንቀሳቀሱ አስቡ አቅዱ ሥሩ ከማንም ሰው ውጪ መኖር እንደምትችሉ ራሳችሁን በማሳመን በፈጣሪችሁ እርዳታ ራሳችሁን አሳድጉ እንጂ አትዳከሙ፡፡

ራስን መምራት የሚጀምረው ራስን ከማወቅ፣ ማንነታችንን ከመገንዘብ፣ ያለፉት ልምምዶቻችን በእኛ ላይ ያስከተሉትን ተፅዕኖዎች በመለየት እና ያሉንን መልካም ዝንባሌያችን ምን እንደሆኑ አውቆ ከማዳበር ነው፡፡ ስለራሳችን በሚገባ በማወቅና ፍላጎታችንን በመለየት ለሕይወታችን ግብ ካላስቀመጥን የመጣውንና ያጋጠመንን ነገር ሁሉ እንደግብ በመቁጠር እድሜያችንን እናባክናለን፡፡

ሕይወት የምርጫና የውሳኔ ጉዳይ ናት፤ አሁን ያለንበት የእያንዳንዳችን የኑሮ ሁኔታ የቀደም ውሳኔዎቻችን ውጤቶች ናቸው፤ ካሳለፋችሁት ዓመታቶች ይልቅ ገና ያልኖራችሁባቸው ዓመታቶች ይበዛሉና ወደ ፊት እያያችሁ በብርታት ተራመዱ እላለሁ፡፡

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 4 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You