ከሰባቱ የዓለማችን አህጉራት አንዱን ብቻ ይዞ የተነሳው ርዕሳችን “አንዱን” በሚለው ምክንያት ጠባብ ይምሰል እንጂ ሰፊ ነው። ለስፋቱ ምክንያቶቹ ብዙ ቢሆኑንም፣ አህጉሪቱ ከዓለም በስፋት 2ኛዋ፤ በሕዝብ ቁጥርም ከእስያ ቀጥሎ 2ኛዋ፤ በስፋት የ30.3 ሚሊዮን ኪሎሜትር (km²)፤ ከአጠቃላይ የዓለም መሬት ሃያ በመቶን (20% land area)፤ ከአጠቃላይ ስፋት (total surface area) ስድስት በመቶን (6%)፤ የ1.4 ቢሊዮን ሕዝቦች መኖሪያ (ይህ የ2021 ጥናት ያሰፈረው ነው)፤ ከአጠቃላይ የዓለም ሕዝብ አስራ ስምንት በመቶን የያዘች የጥቁር ሕዝቦች ምድር፤ ከ1250–3000 የሚሆኑ የራሷ ቋንቋ (native languages) ያሏት (አንባቢ የማዕድን ሀብቷን ሊጨምርበት ይችላል) በመሆኗ ከሰባቱ አህጉራት አንዱ ትሁን እንጂ በብዙ ነገሯ ብልጫ ስላላት ርዕሳችንን ጠባብ ከመሆን ይታደገዋል።
ሌላውና ርዕሳችንን ከጠባብነት ወደ ሰፊነት ያዘነብል ዘንድ ግድ የሚለው የዘንድሮው (37ኛው) የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ዐቢይ የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ ትምህርትና ሥልጠናን የተመለከተ መሆኑና የአፍሪካ አህጉር የትምህርት አቅጣጫ 21ኛውን ክፍለ ዘመን እንዲመስል የማድረግና በይዘትም አፍሪካዊ ገጽታን እንዲላበስ፤ በሂደቱም በተለይ ወጣቱን ተደራሽ፤ ተጠቃሚና ተሳታፊ የማድረጉ ሥራ ልዩ ትኩረትን ያገኘ መሆኑ ነው።
በቀጥታ ወደ ርዕሰ ጉዳያችን እንሂድና አህጉሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ እንመልከት። በራቸውን ለበርካታ አሉታዊ ጉዳዮች በርግደው ከሰጡ የዓለማችን አህጉራት ያለ ምንም ተፎካካሪ አፍሪካ ቀዳሚዋ ናት። አፍሪካ በእድገት ኋላ ቀር፤ በሥልጣኔ ጭለማ፤ በኢኮኖሚ ያልበለፀገች፤ ከምርትና ምርታማነት አኳያ ደሃ፤ በዲሞክራሲው (ዝም ነው)፤ በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ (አሁንም ዝም ነው)፤ በተማረ የሰው ኃይል ቁጥር አናሳ በመሆኗ ወዘተርፈ ሁሉ ከመታማትም አልፋ ትወቀሳለች።
እናት አፍሪካ ሁሉ በእጇ፤ ሁሉ በደጇ ሆኖ ሳለ በረሀብ አለንጋ እምትጠበጠብ ብቸኛ አህጉር ነች እየተባለ በውስጥም፤ በውጭም እምትተች ቀዳሚት አህጉር መሆኗ አገር ያወቀው፤ ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነውና ከመሪዎቿ ሁሌም ብዙ ስለ መጠበቁ የሚያከራክር አይደለም። ከትምህርት አኳያ ያለውን ስንመለከትም ያውና ተመሳሳይ እንጂ ሌላ አይደለም። አህጉሪቱ “ትምህርት ሚኒስቴር ምን ያደርግላታል?“ እስከሚለው ዘለፋና ወቀሳ ድረስ ትወረፋለች። በዝርዝር እንየው። ከትምህርት ጋር በተያያዘ ከመነሳት የማያመልጡና በዓለም አቀፍ ደረጃ (ስታንዳርድ) የተቀመጡ በርካታ ጉዳዮች ያሉ ሲሆን፣ ተደራሽነት፣ አካታችነት፣ ጥራት ወዘተ ቀዳሚዎቹ ናቸው።
ትምህርት ከሕግ ማዕቀፍ አኳያም የራሱ የሆኑ መደላድሎች ያሉት ሲሆን ከሰብዓዊ መብት አኳያ መሠረታዊ ትምህርት ማግኘት የሰው ልጅ ሁሉ መብት መሆኑ፤ በአፍሪካ ደረጃ (አጀንዳ 2063) ተግባራዊ ይሆን ዘንድ በሚሊኒየሙ የልማት ግቦች (MDGs) ውስጥ ተካትቶ መገኘቱ፤ በየሀገራቱ ከሕገመንግሥት ሰነዶች ጀምሮ፣ በተቋም ደረጃ መመራቱና የመሳሰሉት ትምህርትን በሚገባውና በሚፈለገው ደረጃ ሁሉ ለማስኬድ የሚያስችሉ ናቸው። ይሁኑ እንጂ ወደ እኛይቱ አፍሪካ ሲመጣ እንቅፋቱ ብዙ ነው።
እነዚህን ሁሉ ስንል በአፍሪካ ደረጃ ጉዳዩ ምን ይመስላል በማለት ለመወቃቀስ ሳይሆን፣ ምን መደረግ አለበት በሚለው ላይ የተወሰኑ ሀሳቦችን ለማከል ነው። ሰሞኑን ጀምሮ በመገናኛ ብዙኃን ደረጃ በተደጋጋሚ ሲሰራጭ እንደ ሰነበተው የዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ መሪ ሀሳብም ሆነ ቀዳሚ የመወያያ አጀንዳ የትምህርት ጉዳይ ሲሆን፤ በተለይም ትምህርትን ለወጣቱ ተደራሽ ከማድረግ፣ ጥራትን ከመጠበቅ፣ ይዘቶችን አፍሪካዊ መሠረት ከማስያዝ፣ በአህጉሪቱ የሚሰጠው ትምህርት ክፍለ ዘመኑን የመሰለ ከማድረግ አኳያ በመሪዎቹ ተገቢው ውይይት እንደሚደረግበትና ውሳኔዎችም እንደሚተላለፉ ይጠበቃል።
በበርካታ ጥናቶች ላይ ስንመለከት እንደኖርነው፣ የአፍሪካ የትምህርት ሁኔታም ሆነ ይዞታ ደረት የሚያስነፋ አይደለም። ከመጀመሪያው ደረጃ ጀምሮ እስከ ላይኛው የከፍተኛ ደረጃ የትምህርት ተቋም ድረስ ክፍተቶች አሉበት። ክፍተቶች ይኑሩበት እንጂ ሁሌም (እየዳኸም ቢሆን) ለውጥ ከማስመዝገብ ቦዝኖ አያውቅም። በተለይ የአፍሪካን የትምህርት ታሪክ በሁለት (ቅድመ እና ድረ ቅኝ አገዛዝ) ከፍለው ያጠኑ ሰዎች እንደሚሉት ከፊተኛው የኋለኛው እንደሚሻልና እየተሻሻለ ነው የመጣው። (ለምሳሌ “Literacy-the World Factbook”፣ 2021ን ተመልከት።)
ለምሳሌ ያህል በ1999 58% የነበረው ሽፋን፤ በ2010 77% ደርሷል። በ1999 19% የነበረው የሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ሽፋን በ2009 26% ደርሷል። ከሥርዓተ ፆታ ተመጣጥኖ (Gender disparity) አኳያ ሲታይ ከሰሐራ በታች ባሉ ሀገራት፣ በ1999 100∶85 የነበረው፣ በ2010 100∶93 ደርሷል። (የTIMSS ጥናት እንደሚያሳየው) ከሴት ተማሪዎች ተሳትፎ አናሳነት የተነሳ የአፍሪካ ሀገራት እዚህ ግባ የሚባል ፕሮግራም እንኳን እንደሌላቸው “most African countries lack programs to empower girls holistically” ተብለው እንደሚወቀሱም ዩኔስኮ እና የአፍሪካ ኅብረት ለመጀመሪያ ጊዜ በጋራ ካጠኑት ጥናት (Education in Africa: placing equity at the heart of policy; continental report) መመልከት ይቻላል።
እንደዚህ ጥናት (ሴፕቴምበር 2023 ወቅታዊ የተደረገ) ከሆነ ከሰሐራ በታች ባሉት ሀገራት ከ58% በላይ ለትምህርት የደረሱ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት አይሄዱም። ወደ ትምህርት ቤት የሄዱትም ቢሆኑ) ጥራት ያለው ትምህርት ከማግኘት አኳያ ዓለም አቀፍ መስፈርትን ያሟላ ትምህርትን አያገኙም። በመሆኑም፣ ማንበብና መፃፍ መቻል ባለባቸው ደረጃ እንኳን ያንን ማድረግ ሲችሉ አይታዩም።
እንደ አህጉር ከታየ ደግሞ በአጠቃላይ አፍሪካ ከአምስት ልጆች አንዱ ወደ ትምህርት ቤት አይሄድም። ከአስር ወጣቶች ስድስቱ የትምህርት ቤቶችን ደጃፍ መርገጥ አልቻሉም። ለእነዚህ እና ሌሎችም ምክንያቶቹም መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ሥርዓተ-ፆታዊ (ኢ)እኩልነት፣ የከፋ ድህነት፣ አካል ጉዳተኝነት፣ ቅጣንባሩ የጠፋ ቀውስ፣ የከፋ የእርስ በርስ ግጭት፣ መፈናቀል ወዘተርፈ በማለት ይኸው፣ የላይኛው ጥናት ያስቀምጣል።
እነዚህ፣ የላይኛዎቹ ሰው ሠራሽ እንቅፋቶች ደግሞ የአህጉሪቱን መሪዎች ጠንካራ አሠራርና ውሳኔን የሚፈልጉ በመሆናቸው በዘንድሮው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ተገቢውን የውይይት መድረክ ያገኛሉ ተብሎ በጉጉት ይጠበቃል። የአፍሪካ ኅብረትም ከዩኔስኮ ጋር በመሆን ጥናቱን ያቀረበው ያለ ምክንያት አይደለምና ለውጥ ይኖራል የሚለው ሚዛን ደፍቶ ይገኛል።
እንደዚሁ ጥናት የአፍሪካ ትምህርት አካታችነትን በነቢብ ሳይሆን በተግባር (inclusion through action) የማሳየት ችግር አለበት። በመምህራን ልማት በኩልም የከፉ ችግሮች አሉ። ደረጃቸውን የጠበቁ የትምህርት ተቋማት የመገንባት ችግሮችም በብዛት ይስተዋላሉ። ሥርዓተ ትምህርት ቀረፃው በራሱ በተገቢው መንገድ የተሠራ አይደለም። የፋይናንስ አቅም የሌላቸውን ወገኖች የረሳ ነው፤ ምንም አይነት እገዛ አይደረግላቸውም። በመሆኑም፣ ባለ 256 ገፁ የጋራ ጥናት (WWW.UNESCO.ORG ላይ ያገኙታል) የአፍሪካ መሪዎች ለጉዳዩ ትኩረትን በመስጠት በአፋጣኝ ችግሩን ሊፈቱት ይገባል።
ይህ፣ መሪዎቹ በ2016፣ በ26ኛው መደበኛ ጉባኤያቸው ያፀደቁትን ሰነድ (“The Continental Education Strategy for Africa 2016-2025 (CESA 16-25)) የሚያስታውሰው ጥናት፣ ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር መቀየር ያስፈልጋል። በተለይ አዲስ የለውጥ ኃይል መፍጠር ካስፈለገ፤ አዲስ ተነሳሽነት የግድ ከሆነ፤ የምትፈለገውና አፍሪካውያን የሚፈልጓት አፍሪካ እውን ትሆን ዘንድ ፍላጎት ካለ ይህንን ሰነድ ወደ መሬት በማውረድ ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይሆናል። ዓለም አቀፍ አጀንዳ 2030፣ Sustainable Development Goal on Education (SDG 4) የሚለውን ለማሳካት፤ Pan-African High-level Conference on Education (PACE) ውሳኔዎች ለመተግበር ያለው ምርጫ ወደ ሥራ መግባት ከመሆኑ አኳያ ጉዳዩ የአፍሪካ መንግሥታትን እንቅልፍ ሊነሳ ይገባል።
እንደ ሌላኛው የዩኔስኮ (UNESCO, 2020a: 21) ጥናት ከሆነ፣ በዓለም ላይ ያለ ምንም ተወዳዳሪ ከመጀመሪያ ደረጃ 18.8%፤ ከመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ 36.7%፤ ከመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ 57.5% ትምህርት ቤት ውጪ የሆኑ ወጣቶች (OOSY) ያሉባትን ከሰሐራ በታቿን አፍሪካ የያዘች አህጉረ አፍሪካ፤ ጥናት በተደረገባቸው 25 የአህጉሪቱ ሀገራት ለሙያ ትምህርት የተመዘገበው ከ5% (ከ25ቱ በአብዛኞቹ ከ1% በታች) በሆነባት አፍሪካ የትምህርትን ጉዳይ ቸል ብሎ የትም ሊደርስ አይቻልም እና ጊዜው አሁን እና አሁን መሆኑን ደግሞ ደጋግሞ ማስታወስ፤ አላርሙን ደግሞ ደጋግሞ (መንቃት ያለበት እስኪ ነቃ ድረስ) ማጮህ ይገባል።
በአንድ ሀገር (ማሊ) ብቻ ከ51,000 በላይ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎችን በማኅበረሰብ አቀፍ ማስተማሪያ ማዕከላት አማካኝነት መድረስ እንደተቻለው ሁሉ፤ ሌሎች የአፍሪካ አገራትም ተመሳሳይ ተግባራትን ሊያከናውኑ ይገባ ዘንድ በጥናት (2018) ተመልክቷል። ይህን መሰል እርምጃ በመላዋ አፍሪካ ስለ ማስፈለጉ እዚህ መጠያየቅ አያስፈልግምና እንቀጥል።
መሪዎች ቃላቸውን፣ በተለይም በ2030 እናሳካዋለን ያሉትን፣ የትምህርት ተደራሽነት፤ ጥራት፣ ተሳትፎ ወዘተ እናረጋግጣለን በማለት ቃል የገቡትን ለአፍታም ሊረሱት የሚገባ ባለ መሆኑ፣ እንደ አንድ የዓለም አካል ሁሉ የአፍሪካ መሪዎችም ዳግም ቃላቸውን ሊያድሱና ተግባራዊ ሊያደርጉ ይገባል።
ምንም እንኳን፣ የአፍሪካ ሀገራት ከነጭ የበላይነት ነፃ ሲወጡ ከነበሯቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ተማሪዎቻቸው አኳያ ሲታይ (ለምሳሌ በ1961 ኬኒያ 400 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ፤በ1963 ታንዛኒያና ዛምቢያ እያንዳንዳቸው 300 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ብቻ ነበሩ የነበሯቸው) አሁን በማይገናኝ መልኩ ያደጉ ቢሆንም፤ ጥራት፣ ተደራሽነትና አካታችነት ላይ ምንም የሠሩት ሥራ እንደ ሌለ ነው የተመራማሪዎችን የጥናት ይሁንታ አግኝተው በመረጃነት እያገለገሉ ያሉ ጥራዞች የሚያመለክቱት።
የአፍሪካ የትምህርት ተደራሽነት ችግር የትምህርት ተቋማት በከተሞች ብቻ የመታጨቃቸው ጉዳይ ሲሆን፣ ትምህርትን ለሁሉም እኩል ተደራሽ ማድረግ ላይ ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ ሁሌም እንደ ተመከረ ነውና በዚሁ የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይም በለሆሳስ ሊታለፍ እንደማይገባ ጉዳዩን ከስሩ አስምሮ ማለፍ ይገባል።
እንደ ተመራማሪዎች ምሑራዊ ምክር ከሆነ የአፍሪካ ሀገራት መንግሥታት መሥራት ያለባቸውን ሁሉ አሁኑኑ መሥራት ካልቻሉ መጪው ዘመን ለሀገራቱ (በተራዛሚው ለአህጉሪቱ) የከፋ ይሆናል። በተለይም በፈጣን ሁኔታ እያሻቀበ ያለውን የሕዝብ ቁጥር በተመለከተ ጊዜ ወስደው፣ ከሌላ ሌላው ነገር ሰብሰብ ብለውና አስበው እማይሠሩ ከሆነ አደጋው የከፋ ይሆናል። ለዚህ ስጋታችን ደግሞ በ2020 ያለውን ብቻ እንኳን ብንወስድ ጉዳዩን ግልፅ ያደርግልናል።
እዚህ እንደተጠቀምንባቸው መረጃዎች በ2020 በአፍሪካ ከ25 ዓመት እድሜ በታች ያው ወጣት ብቻ 800 ሚሊዮን ሲሆን፤ 677 ሚሊዮኖች ደግሞ እድሜያቸው ከሦስት እስከ 24 ያሉ ናቸው። ይህንን ይዘን የአሁኑን፣ የ2024ን ስናክልበት ውጤቱና ስጋቱ የት ሊደርስ እንደሚችል ለማንም ግልፅ ነውና ጥናቶቹ Africa’s population is not only young but also growing fast ያሉትን በመጥቀስና በመግቢያ አንቀፃችን ላይ ያሰፈርነውን በማስታወስ እዚሁ ላይ እናቆማለን።
መልካም የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 4 ቀን 2016 ዓ.ም