የኮትዲቯር ብሄራዊ ስታዲየም የሆነው አላሳኔ ኦታራ ከሳምንታት በፊት ያስጀመረውን 34ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ በታላቅ ድምቀት ሊያጠቃልል ቀጠሮ ይዟል። በሰሜናዊው የአቢጃን ክፍል የሚገኘውና ከ60ሺህ በላይ ደጋፊዎችን የሚይዘው የኦሊምፒክ ስታዲየም ዝሆኖቹን ከንስሮቹ ያፋልማል። የሁለት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ቻምፒዮኗ ኮትዲዮቯር፤ ሶስት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ባለድል የሆነችውን ናይጄሪያን በመርታት ዋንጫውን በሀገሯ ታስቀር ይሆን የሚለውም የመላ እግር ኳስ አፍቃሪያን የዕለቱ ትኩረት ነው።
በአስደማሚ ገጠመኞች ታጅቦ ለአንድ ወር የዘለቀው የአፍሪካ ትልቁ የእግር ኳስ ድግስ ዛሬ ፍጻሜውን ያገኛል። ከልብ ሰባሪ ሃዘን ተነስቶ በእግር ኳስ የሚገኘውን ሃሴት የቀመሰው የአዘጋጇ ኮትዲቯር ብሄራዊ ቡድን ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ጋር በነበረው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ በ65ኛው ደቂቃ በሰባስቲያን ሄለር በተቆጠረው ብቸኛ ድል ወደመጨረሻው ምዕራፍ መሸጋገሩ የሚታወስ ነው። ሌላኛዋ የፍጻሜው ተፋላሚ ናይጄሪያ ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ ጋር በመደበኛውና ተጨማሪው የጨዋታ ሰዓት አንድ አንድ ግብ በማስቆጠር በአቻ ውጤት በመለያየት ነበር ወደ ፍጹም ቅጣት ምት ነበር የተሸጋገሩት። በጨዋታው ንስሮቹ 4ቱን ከመረብ ሲያገናኙ በአንጻሩ ባፋና ባፋናዎቹ ያሳኩት 2ቱን ብቻ በመሆኑ ነው ለፍጻሜው የደረሱት።
ሁለቱ ቡድኖች እዚህ የደረሱት በምድብ አንድ ተደልድለው ሲሆን፤ ከሳምንታት በፊት ሁለተኛ ዙር ግጥሚያቸውን እርስ በእርሳቸው ነበር ያከናወኑት። በዚህም ጨዋታ ንስሮቹ ብልጫውን በመውሰድ አንድ ለምንም በሆነ ጠባብ ውጤት መርታት ችለው እንደነበር የሚታወስ ነው። በዛሬው ጨዋታም ኮትዲቯሮች ዋጋ እንዲከፍሉ ያደረጋቸውን የናይጄሪያን ብሄራዊ ቡድን ለመበቀል ወደ ሜዳ እንደሚገቡ አስታውቀዋል። ቡድኑን በመምራት ላይ የሚገኙት አሰልጣኝ ኤምረስ ፋዬ ‹‹ዋንጫውን ማንሳት ካለብን ተቀያሪዎቹን ጨምሮ 27ቱም ተጫዋቾች የራሳቸውን ሚና መጫወት አለባቸው። ከግማሽ ፍጻሜው በኋላ በነበሩን ቀናት የናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድንን እንዴት ማስቆም እንዳለብን ስናቅድ ነው የቆየነው›› በማለት ነው ለድል መዘጋጀታቸውን የጠቆሙት።
ናይጄሪያዎች በበኩላቸው 10 ዓመታን የተሻገረ የዋንጫ ጥማቸውን ለማርካት ወሳኝ ሰዓት ላይ መሆናቸው በባለስልጣናቱ በኩል ለተጫዋቾቻቸው አስታውቀዋል። የግማሽ ፍጻሜውን ድል ተከትሎ ሃሳባቸውን ያንጸባረቁት የሃገር ውስጥ ቃል አቀባይ ሚኒስትር ሞሃመድ እድሪስ ‹‹መላው የናይጄሪያ ህዝብ ዋንጫውን በማንሳት ስማችሁን በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ በወርቃማ ቀለም እንደምታጽፉ እምነት አለው። የህዝቡ ተስፋ በጫንቃችሁ ላይ ነው። በመሆኑም የዋንጫ ጥሙን እንድታረኩለት በድጋፍ ከናንተጋር ነው›› ብለዋል። የስፖርት ሚኒስትሩ ጆን ኦዋን በበኩላቸው ‹‹በግማሽ ፍጻሜው ጨዋታ የታየው የንስሮቹ ብቃት የናይጄሪያ ስፖርት ነጸብራቅ ነው፤ ማንም የማያቆማቸው መሆኑን ደግሞ በዛሬው ጨዋታ አስመስክረው ህዝባቸውን ያኮራሉ›› በሚል ተጫዋቾቻቸውን አበረታተዋል።
ንስሮቹ በዚህ ዓለም ዋንጫ እያስመዘገቡ ከነበሩት ውጤት አንጻር እንዲሁም በመድረኩ በነበራቸው ሰፊ ተሳትፎ ልምድ አላቸው። እስካሁን በመጡበት አካሄድም የበላይነቱን የመያዝ ግምቱ ወደእነሱ ያዘነበለ ሆኗል። ይሁንና የአሰልጣኝና የአጨዋወት ስልት ለውጥ በማድረግ በድጋሚ ፉክክሩን የተቀላቀሉት ዝሆኖቹ፤ አዘጋጅ ሀገር እንደመሆናቸው የሜዳ ብልጫውን በመያዝ በደጋፊዎቻቸው ፊት ዋንጫውን ለማስቀረት የማይቆፍሩት ጉድጓድ አይኖርም። ሁለቱ ጠንካራ ቡድኖች ለበርካታ ጊዜያት የአፍሪካ ዋንጫውን ማንሳት ባይችሉም በተደጋጋሚ ግን የፍጻሜ ተፋላሚ በመሆን ቀርበዋል። በዚህም አብላጫውን የምትይዘው ናይጄሪያ ስትሆን አራት ጊዜ ሁለተኛ ደረጃን ስምንት ጊዜ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ነበር ያጠንቀቀችው። ሁለቱ ቡድኖች እርስ በእርሳቸው ከዚህ ቀደም በተገናኙባቸው ጨዋታዎች አንዳቸው ሌላኛቸው ላይ ብልጫውን የወሰዱት እኩል ለዘጠኝ ጊዜ ሲሆን፤ አስር ጊዜ ደግሞ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል።
በአፍሪካ ዋንጫው አሸናፊ በመሆን የሚያጠናቅቀው ብሄራዊ ቡድን 7 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት የተዘጋጀለት ሲሆን፤ ሁለተኛ የሚሆነው 4 ሚሊዮን፣ ለደረጃ ተጫውተው ሶስተኛና አራተኛ የሚሆኑት ቡድኖች ደግሞ የ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ባለቤት ይሆናሉ። በሩብ ፍጻሜው ተሸንፈው የዋንጫ ሩጫቸው የተገታው አራቱ ቡድኖች ደግሞ 1ነጥብ3 ሚሊየን ዶላር ይደርሳቸዋል። ከምድባቸው አልፈው 16ቱን የተቀላቀሉ ቡድኖችም 800ሺህ ዶላር ይበረከትላቸዋል። ከየምድባቸው ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ጥሎ ማለፉን ያልተቀላቀሉና በምድባቸው የመጨረሻውን ስፍራ ይዘው ከውድድሩ በጊዜ የተሰናበቱ ስድስት ቡድኖች ደግሞ 500ሺህ ዶላር ያገኛሉ።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም