ራስን ማወቅ፡- የሕይወት ዘመን እንቆቅልሽ

በዚህ ዓለም ራስን ማወቅ የሚያክል አቋራጭ መንገድ የለም:: ራስህን ስታውቅ ፍፁም የሚያስቀና ሰው ትሆናለህ:: ራሱን የሚያውቅ ሰው ለምን እንደተፈጠረ፣ ለምን እንደሚማር፣ ለምን እንደሚሠራ ያውቃል:: ማንን ጓደኛ፣ ማንን ፍቅረኛ፣ ማንን የትዳር አጋር ማድረግ እንዳለበት ጠንቅቆ ይረዳል:: በምን አይነት መልኩ ሰዎችን መቅረብ እንዳለበትም ይገነዘባል:: የተረጋጋና ስክን ያለ ሕይወት ይመራል:: አንተም ብትሆን ራስህን ስታውቅ የአዕምሮ ሠላም አለህ:: ለመሆኑ ራስን ማወቅ ሲባል ምን ማለት ነው?

ራስን ማወቅ ማለት ምን አይነት ሰው ነኝ?፣ ምን አይነት ፀባይ አለኝ?፣ ምንድን ነው የሚያስደስተኝ? ምንድን ነው የሚያስጠላኝ? ምንድን ነው ፍላጎቴ? የሚለውን መመለስ ነው:: እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ግን ራስን አውቆ መደምደም ማለት አይደለም:: ይህ በሆነበት ቅፅበት ሌላ ማንነትን አይቶ መደንገጥ ይመጣል:: ስለዚህ ራስን ማወቅ የሕይወት ዘመን እንቆቅልሽ ነው::

እዚህ ጋር ራስህን ካላወክ ዝም ብለህ ትባክናለህ:: የማትወደውን ሥራ ትሠራለህ:: ወይ ትማርና ‹‹ድሮም እኮ አልወደውም ነበር›› ትላለህ:: አልያም ደግሞ የፍቅር ግንኙነት ውስጥ ትገባና ‹‹እኔ ከማልግባባው ሰው ጋር አስከመቼ እዘልቃለሁ›› ትላለህ:: አንተ ራስህን በቅጡ ስላልተረዳኸው ‹‹ሰዎች እኮ አይረዱኝም›› ትላለህ:: መኖር ከተባለ ትኖራለህ:: መሥራት ከተባለም እንዲሁ እየሠራህ ትኖራለህ:: ታዲያ ራስህን የምታውቀው እንዴት ነው?

በዚህ ጽሑፍ ስለ አራት አይነት ሰዎች ይነገርሃል:: ስለአራቱ ሰዎች የሚነገርህ ፀባያቸውን አስመልክቶ ነው:: ከነዚህ አራት ፀባዮች ውስጥ አንዱ ወይ ሁለቱ ያንተ ሊሆን ይችላል:: ‹‹እንዴ! እውነትም ይህ ፀባይማ የኔ ነው›› ልትልም ትችላለህ:: ስለማንነትህ ካወክ በኋላ ምን ማድረግ እንዳለብህም ለመወሰን ጽሑፉ ይረዳሃል:: እነሆ ጽሑፉ ……

የአስራዎቹ የእድሜ ክልል በአብዛኛው በትምህርት ያልፋል:: ሳታውቀው እንደንፋስ ሽው ብሎ ሃያዎቹ ይመጣል:: በሃያዎቹ ደግሞ ትምህርት አለ፤ ሥራ አለ፤ ሕይወት አለ:: በሦስት አቅጣጫ ትበተናለህ:: በርካታ አዳዲስ ነገሮችን ታያለህ:: አንድ ዓመት ስትጨምር ብዙ ዓመት የገፋህ ይመስልሃል:: ያረጀህ ይመስልሃል:: እንደው ጊዜው ቆሞ ቢቀር ብለህ ሁሉ ትመኛለህ:: ሰዎች ስላንተ የሚያስቡት ነገር ያሳስብሃል:: ስለዚህ የምታውቀውንም የማታውቀውንም ሰው ለመማረክ ስትል በውጫዊ ነገሮች ላይ አብዝተህ ትጨነቃለህ:: ገንዘብህን፣ ጉልበትህንና ጊዜህን ታጠፋለህ::

ትለብሳለህ፣ ትዘንጣለህ፣ ትዝናናለህ፣ ከሰው ማነስ አትፈልግም፣ የፍቅር ግንኙነት ውስጥ ትገባለህ፣ ገንዘብ በጣም ታጠፋለህ፣ ወጣት ነህ፣ ስሜት አለ፣ ሥራ አለ ብዙ ነገር ትሞክራለህ:: በዚህ ውስጥ አንድ የተለየ ፀባይ ግን አለህ:: በፍጥነት ለውጥ ትፈልጋለህ:: ሠላሳዎቹ እድሜ ደግሞ ከተፍ ይላል:: በዚህ እድሜ ትንሽ ሩጫህን ትቀንሳለህ:: የሚያሳስብህ ቤት መከራየት፣ ማግባት፣ መውለድ … ብቻ ኃላፊነቶች ይበዙብሃል:: መዝናናት ትቀንሳለህ:: ከድሮ ጓደኞችህ ጋር ትጠፋፋለህ:: ትራራቃለህ::

በጣም የሚያስጨንቅህ ነገር ያባንክ አካውንትህ ውስጥ ያለው ገንዘብ ነው:: አንድ ነገር ግን ይቆጭሃል:: ‹‹በሃያዎቹ እድሜዬ ምን ስሠራ ነበር? አይ ልጅነት!›› ትላለህ:: አርባዎቹ እድሜ ደግሞ በተራው ይመጣል:: ወርቃማው ግዜ! ብስለት ከወጣትነት ጋር የሚጣመሩበት ወቅት:: ትረጋጋለህ:: የማይጠቅምህ ነገር ላይ መሮጥ ታቆማለህ:: አብዝተህ የምታተኩረው ሀብት መገንባት፣ ትዳርህን ማሳመርና ልጆችህን ማሳደግ ላይ ነው:: አንድ ነገር ግን ይቆጭሃል::

ሠላሳዎቹና ሃያዎቹ ላይ ‹‹ምን ሳደርግ ነበር፤ ስባክን ነበር?›› ትላለህ:: ሳታስበው ሃምሳዎቹ እየፈረጠጠ ይመጣል:: በዚህ የእድሜ ክልል ይበልጥ ሰከን ትላለህ:: ሕይወትና እድሜ የሰጠህ ብስለት አለ:: ስለዚህ ስሜታዊ ሳይሆን ምክንያታዊ ትሆናለህ:: ያለህን ማስጠበቅ ላይ ነው የምታተኩረው:: ቢያበሳጩህ ራሱ ሥራ መልቀቅ አትፈልግም:: የት እሄዳለሁ፣ የት እወድቃለሁ፣ ማን ይቀጥረኛል፣ ልጆቼን ምን አበላለሁ ትላለህ:: በትዳርህ ደስተኛ ባትሆን እንኳን ለልጆችህ ስትል ታግሰህ ትኖራለህ:: አሁንም አንድ ነገር ግን ያንገበግብሃል:: ብዙ ነገር መሞከር የምችለው ያኔ በሃያዎቹና በሠላሳዎቹ እድሜዬ ነበር፤ አሁንማ አልችልም! ትላለህ::

ስልሳዎቹ እድሜ ይመጣል:: ምንም አዲስ ነገር የለም:: ምን አልባት ልጆችህ ያገባሉ:: የልጅ ልጅ ታያለህ:: ግን አሁንም ወደ ኋላ ሄደህ ስታስብ ወጣቶችን ታይና ‹‹አይ ልጅነት! ያኔ ነበር መቀየር የነበረብኝ›› ትላለህ:: ካደረከው ይበልጥ ያላደረከው ነገር ይቆጭሃል:: በርግጥ ይህ የአብዛኛው ሕይወት ሊሆን ይችላል እንጂ የሁሉም ሊሆን አይችልም:: ይህን ለማወቅ ደግሞ በዙሪያችን ያሉትን ሰዎች ማየት ብቻ በቂ ነው::

እንደ አብዛኛው ሰው ለመሆን ከፈለክ ራስህን ማወቅ አይጠበቅብህም:: እንዲሁ መኖር በቂ ነው:: የተሻለ ሰው መሆን፣ የተሻለ ቦታ ላይ መድረስና ደስተኛ መሆን ከፈለክ ግን ራስህን ማወቅ አለብህ:: ስለዚህ በቀላሉ በሕይወትህ ተግብረሃቸው መፍትሔ ሊያመጡ የሚችሉ ራስን የማወቂያ መንገዶችን ማወቅ ይኖርብሃል::

አራት አይነት ሰዎች አሉ:: የመጀመሪያዎቹ ‹‹ወረተኞች›› ናቸው:: እነዚህ ሰዎች ምንም ነገር ሲጀምሩ በሚገርም ስሜትና ተመስጦ ነው:: ጉልበታቸው በጣም ደስ ይላል:: ሥራ ሲጀምሩ ከማንም በፊት ማልደው ይገባሉ:: ከማንም በኋላ አርፍደው ይጨርሳሉ:: የፍቅር ግንኙነትንም ሲጀምሩ በሚገርም ተመስጦ ነው:: ትምህርታቸውን ሲጀምሩም እንደነሱ የሚለፋና የሚጥር የለም:: የትኛውንም ለውጥ ሲጀምሩ የት ይደርሳሉ የሚያስብሉ ናቸው:: ምን ያደርጋል እነዚህ ሰዎች በዚህ አይቀጥሉም::

ለውጥ አልመጣ ካለና ነገሮች መበላሸት ከጀመሩ የጀመሩትን ያቆማሉ:: ‹‹በቃኝ! ድሮም እኮ እንደጠበኩት አይደለም›› ብለው ያቆማሉ:: እንደዛ የጓጉለት ሥራ ከልፋቴ አንፃር እኮ ገቢው ትንሽ ነው ብለው ማርፈድ ይጀምራሉ:: አልፎ አልፎ ደግሞ ይቀራሉ:: የድሮውን ጥረታቸውን ያቆማሉ:: በፍቅር ግንኙነትም እንደጠበኳት አይደለችም፤ እኔ እኮ ድሮም ሰው አይወጣልኝም ይልና የድሮ እንክብካቤውን ያቆማል:: ትምህርቱ፣ ቋንቋው፣ ስፖርቱና አዲስ ልማዳቸው ላይ ለውጥ ካላዩ እርግፍ አድርገው ይተውታል:: በጉጉት የተጀመረው ለውጥ በመሰልቸት ይደመደማል:: ሁሌም አዳዲስ ነገሮች ያጓጓቸዋል:: ግን እስከመጨረሻው አይጓዙም::

ሁለተኛቹ ሰዎች ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› ናቸው:: ከመጀመሪያዎቹ ሰዎች ጋር አንድ የሚለያቸው ነገር ቢኖር ውጤቱንና ለውጡን ሳያገኙ ንቅንቅ አለማለታቸው ነው:: አንድ የፈለጉት ነገር እስኪሳካ አብዝተው ያስባሉ:: ትምህርት ጀምረው ተማሪው ሲበተን እነርሱ ወደ ኋላ ቀርተው ከአስተማሪው ጋር ተግባብተው ሲወያዩ ይታያሉ:: ጥረታቸው አስገራሚ ነው:: በጣም ያነባሉ:: ካስፈለጋቸው የማይገዙት የመጽሐፍ አይነት የለም:: ጎበዝ ተማሪዎችን ሁሉ ጓደኛቸው ያደርጋሉ:: ቶሎም ለውጥና ውጤት ያመጣሉ::

እነዚህ ሰዎች እንደመጀመሪያዎቹ ተስፋ ቆርጠው የጀመሩትን አያቆሙም:: ጥረታቸውን ይቀጥላሉ:: እልኸኛ ናቸው:: ለውጥ ይፈልጋሉ:: ሥራቸውንም በጥሩ ተነሳሽነት ነው የሚሠሩት:: በቶሎ ለውጥ ያያሉ፤ ጥሩ ውጤት ያመጣሉ:: በፍቅር ግንኙነታቸውም እንደዛው ናቸው:: እልህ ጨመር አድርገው የፍቅር ግንኙነታቸውን የተሻለ ያደርጋሉ::

ከባዱ ነገር እንዲህ እየደጋገሙ ለውጥና ውጤት ለማምጣት ቢጥሩም የሆነ ሰዓት ላይ ግን ተስፋ ይቆርጣሉ:: ላስቲክ ተወጥሮ፤ ተወጥሮ የሆነ ሰዓት ላይ ብጥስ እንደሚል ሁሉ የትም ፍጪው ∙ ∙ ∙ ሰዎች በቃኝ ብለው ያቆማሉ:: ብዙ ሞክረው፤ ብዙ ጥረው ያ የጣሩለት ነገር ሳይሳካ ሲቀር በቃኝ ይላሉ:: ለምን? እነዚህ ሰዎች ለውጥ ካላዩ መቆየት አይችሉም:: የለውጥና የውጤት ሱሰኞች ናቸው::

ስለዚህ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ስለሆነ ዱቄቱ ከሌለ እነርሱም የሉም:: በቃኝ ይላሉ:: ሁልግዜ ጥረታቸውን እየጨመሩ ግን የጠበቁትን ያህል ገቢ ካልመጣ ሥራው እንደሞተ ያስባሉ:: ሕይወት በከፍታና በዝቅታ የተሞላች እንደሆነ ይረሳሉ:: እነዚህ ሰዎች ውጤቱ ብቻ ስለሚያሳስባቸው እስከመጨረሻው አይቀጥሉም:: ያቆማሉ::

ሦስተኞቹ ሰዎች ‹‹እንቅልፋም›› ናቸው:: ለውጥ ቢኖርም ባይኖርም ግድ የላቸውም:: ደህንነት ነው የሚፈልጉት:: እንደው ሥራ ያግኙ እንጂ፣ ይቀጠሩ እንጂ፣ ቋሚ ገቢ ይኑራቸው እንጂ ትንሽ ትንሽ በየዓመቱ እየጨመረ ቢሄድና እዛው ተቀጥረው ቢያረጁ ግድ አይሰጣቸውም:: ከሰው አይነሱ እንጂ፣ ትዳር ይኑራቸው እንጂ ደስተኛ መሆናቸው ላይ ችግር የለባቸውም:: እነዚህ ሰዎች በየቤቱ አሉ:: የዛሬ አስር ዓመትም ዛሬም አንድ አይነት ናቸው:: አልተቀየሩም፤ ምንም ነገር አልጨመሩም:: በየእለቱ የሚያደርጓቸው ነገሮች አንድ አይነት ናቸው:: እነዚህን እየደጋገሙ ዓመቱ ይገፋል፤ ይሮጣል:: እነርሱ ግን ተኝተዋል::

ሰው ሲለወጥ በጣም ይገርማቸዋል:: እድለኛ ካልሆነ ሰው የሚለወጥ አይመስላቸውም:: ሕልመኛ መሆን ይፈራሉ:: የሆነ ነገር መጠየቅ ይፈራሉ:: ምክንያቱም ጠይቀው የማያገኙ ስለሚመስላቸው ከመጀመሪያውኑም አይጠይቁም:: ጥንቁቅ ናቸው፤ የራሳቸውን ደህንነት ነው የሚፈልጉት:: እንቅልፋም ናቸው:: አዲስ ነገር መሞከር እንደ ጦር ነው የሚፈሩት:: በነገራችን ላይ አንተ በሁሉም ፀባይህ አንድ ምድብ ላይ ላትወድቅ ትችላለህ:: በሥራህም፣ በትምህርትህም፣ በፍቅር ግንኙነትህም፣ በገንዘብ ጉዳይም እንቅልፋም ላትሆን ትችላለህ:: ምን አልባት በትዳር ጉዳይ እንቅልፋም ሆነህ በሥራህ ጉዳይ ግን ወረተኛ ወይም የትም ፍጪው ልትሆን ትችላለህ:: ዋነው ነገር ያንተ ፀባይ በዚህኛው በኩል የቱጋር እንደሚወድቅ ማወቅ ነው:: ዋናው ዓላማ በሽታህን እንድትለይ ነው:: ቀጥሎ መድኃኒቱን ማግኘት በጣም ቀላል ነው::

አራተኞቹ ሰዎች ‹‹ንቁዎች›› ይባላሉ:: እነዚህ ሰዎች እንደማንኛውም ሰው ለውጥ ይፈልጋሉ:: ግን በአንድ ግዜ ካልሆነ አይሉም:: ከውጤቱ በላይ እንደውም ሂደቱን ይወዱታል:: ስፖርት ሠርተው ክብደታቸው መቀነሱና ቅርፅ በቅርፅ መሆናቸውን ሳይሆን ስፖርት መሥራታቸውን በራሱ ይወዱታል:: ሥራው ከሚያመጣው ገቢ በላይ ስራውን ራሱ ያጣጥሙታል:: ሂደቱ ደስ ይላቸዋል:: ስለዚህ ለውጥ አልመጣም ብለው ጥረታቸውን አያቆሙም:: እንደውም ለውጥ አልመጣ ሲል ነገሮች ሲበላሹና ድብልቅልቅ ሲሉ ረጋ ብለው ያስባሉ:: ‹‹ምንድን ነው ያጠፋሁት፣ ምን ላስተካክል›› ብለው ይማሩበታል::

እነዚህ የሕይወት ዘመን ተማሪዎች ናቸው:: ብቁ ነኝ፤ ብዙ ነገር አውቃለሁ ብለው አይዘናጉም:: እንደንቁዎች ሕይወት የገባው የለም:: ሕይወት በከፍታና በዝቅታ ውስጥ የተሞላች እንደሆነች ያውቃሉ:: ምንም ነገር የሚመጣው ሊያልፍ እንደሆነ ይረዳሉ:: ችግር ቢመጣ እንኳን ሊያቆማቸው ሳይሆን ሊያስተምራቸው እንደሆነ ይረዳሉ:: ነግደው ቢከስሩ ይማሩበታል እንጂ እኔ ለንግድ አልተፈጠርኩም ብለው ተስፋ አይቆርጡም:: ምንድነው ያጠፋሁት ብለው ጥረታቸውን ጨምረው ይቀጥላሉ:: በፍቅር ግንኙነታቸውም እንደዛው:: ሁልግዜ ኃላፊነት ይወስዳሉ:: ሰው ላይ ችግሩን አይጥሉም፤ ሰበበኛም አይደሉም::

እንተም እንደንቁዎቹ በአንዴ ላትሆን ትችላለህ:: ነገር ግን ምን እንደሆንክ ካወክ፣ የራስህን ምድብ ከለየህ በኋላ ንቁ ለመሆን ጥረትህን መቀጠል አለብህ:: አንድን ነገር አጥብቀህ የምትፈልገውና የምትወደው ከሆነ ለውጥ ሲጠፋና ነገሮች ሲበላሹ ማቆም አይደለም ያለብህ:: ረጋ ብለህ ምን ላስተካክል ነው ማለት ያለብህ::

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን  የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You