ጠዋት ከእንቅልፌ ነቃሁ፡፡ በሬን ስከፍት አንድ ምንዱባን የምጽዋት አቆፋዳውን ይዞ በሬ ላይ ቆሟል፡፡ “ስለማርያም” አለኝ፤ ፊቱን በማጣት አሳዝኖ፡፡ ቀኑ ማርያም መሆኑን እሱ ነው ያስታወሰኝ፡፡ ከአንድ እስከ ሰላሳ ያሉትን ቀኖች ዝም ብዬ ነው የምኖራቸው፡፡ ሰዎች ነጠላ ለብሰው በሰፈሬ ቀጭን መንገድ ወደ አጥቢያ ሲጎርፉ፣ እዛና እዚህ የተተከሉ የአምልኮ መቅደሶች ጡሩንባቸውን ሲያሰሙኝ ምንም ያልመሰለኝ በዚህ ሰው ደጄ መቆም ብዙ መሰለኝ፡፡ የኖርኳቸውን አርባ ስድስት አመታት እንዴት መጥተው እንደሄዱ እንኳን አላውቃቸውም፡፡ ዝም ብሎ መኖር ይቻላል?
“ስለማርያም!” ማጣት የደቆሰውን ኮሳሳ ድምጹን ደገመልኝ፡፡
አሁን እኔ ምን አለኝና በሬ ላይ ይቆማል? ከዛች እመበለት የባስኩ፣ ከመቀነቴ ፈትቼ የምሰጠው ስሙኒ የሌለኝ መሆኔን ቢያውቅ፡፡ ቦሀቃና ገንቦዬ ዘይትና ዱቄት አጥተው ለዘመናት እንደከረሙ ቢገባው በጠዋት ደጄ አይቆምም ነበር፡፡ ግቢያቸውን በግንብ ያጠሩ የጎረቤቶቼን በር አልፎ እኔ ዘንድ መምጣቱ ሞኝ ለማኝ እንደሆነ እንዳስብ አደረገኝ፡፡ ይሉኝታ ይዞኝ እንጂ እኔም ልመና ልወጣ አንድ ሀሙስ የቀረኝ ነኝ፡፡ “ምን ይሉኝ”ን ፈርቼ እንጂ በህይወቴ ውስጥ ጨርቅ አስጥለው የሚያስኬዱ ብዙ ጉስቁልናዎች አሉ፡፡ እንዳይታዩ ሸፍኜአቸው እንጂ . . . እንዳይገለጡ ደብቄአቸው እንጂ እንዳንተ እና ከአንተ የባስኩ ነኝ አልኩት . . በሆዴ፡፡ ግን ምን ታይቶት ጎበኘኝ?
“ሂድ”ልለው ቃጣኝ፡፡ አይደለም ላንተ ለራሴም የምበላው የለኝ ልለው፣ ሄደህ ከሞላቸው ለምን ልለው አፌን አሞጠሞጥኩ፡፡ ከአንደበቴ ግን ቃል አልወጣም፡፡ ልለው ያሰብኩትን የሻረ ሌላ አመክንዮ ውስጤ ተፈጠረ፡፡ ዝም ብዬ አስተዋልኩት … እስካሁን ያልታየኝን ነገር አየሁ፡፡ ከፊት ለፊቱ ደረቱ ላይ የቤዛይተ ኩሉን ምስል አንጠልጥሏል፡፡ በግራው ቅዱስ ገብርኤል፤ በቀኙ ደግሞ ቅዱስ ሚካኤል ከመስቀልና ጎራዴአቸው ጋር፡፡ በዚህ ማዶ አናኒያና አዛርያ ምሳኤል እሳቱ መሀል ከጸጉራቸው ላይ አንዲት ሳይጎድል . . በዛ ማዶ ትዕቢተኛው ሳጥናኤል በመላኩ ተረግጦ . . . መሀል ላይ አማላጅቱ፡፡ ይሄን ኩነት ማምለጥ አልቻልኩም፡፡ በእምነት የበረቱ ዓይኖቹ ከመላዕክቶች አንዱን መስለው አስፈሩኝ፡፡ እንደምንም አየሁት፡፡ ማጣት ሰው ቢሆን ኖሮ . . . ድህነት አካል ነፍስ ቢለብስ ኖሮ ይሄን ሰው ይሆን ነበር፡፡ ባደፈ ገላ . . . ባልጠራ ደምግባት ረህጦ አገኘሁት፡፡ በሰለለ ገላ . . በከሰለ ሰውነት ይሄን የሚያህል እምነት ይቻላል? ነው፣ ወይስ በእምነቱ የማይጨክነውን ሕዝብ በዘዴ ሊበዘብዝ አስቦ ያደረገው? በየቱም እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ እንደ ምንም ብዬ ሃሳቤን ወደ መጀመሪያው አስጠግቼ “አማኝ ነው” ስል ተቀበልኩት፡፡
በእለተ ማርያም በልመና ከበሬ የቆመን ምስኪን የለኝም ብሎ ማባረር ዳግመኛ የማይመጣን እድል ሂድ ከዚህ ማለት መሰለኝ፡፡ በላኤ ሰብን ሆኜ በዚህ ሰው ችግር እንደ ዳክሮስ ከማንም ቀድሜ ገነት ልገባ ቤዛይተ ኩሉ ይሄን ችግረኛ በጠዋት የላከችልኝ መሰለኝ፡፡ ግን እንዴት መሰለኝ? ትውልድ ሁሉ ብጽእት የሚሏትን ንጽእት፣ ከእብራውያን ቆነጃጅቶች የራቀችውን እመቤት፣ ገብርኤል ያበሰራትን፣ ኤልሳቤት የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እንደምን ይሆንልኛል? ያለቻትን ሴት መራቄ . . መናቄ . . መርሳቴ . . መግፋቴ ከዓለም ወንበዴ ዋነኛው እንደሆንኩ ተገለጠልኝ፡፡
ይሄን ሰው መግፋት ፈጣሪን ከበር ላይ ማባረር ሆነብኝ፡፡ ያ ባለከዘራው እየሱስ በዚህ ሰው ምስል በሬ ላይ ሆኖ ክፈትልኝ እያለኝ ቢሆን በምን አውቃለው? ያ ማንም በሩን ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ ለመግባት ዝግጁ ነኝ ያለው አምላካዊ ቃል በእኔ ላይ ሊገለጥ ይሄን ሰው እንደ ሰበብ ተጠቅሞ ቢሆንስ? ሆነም አልሆነ ከመስጠት ውጪ አማራጭ የለኝም፡፡ ግን ምንም የለኝም፤ ምንድነው የምሰጠው? ወደ ኋላዬ ተመልሼ ለዘመናት የማውቃትን ቤቴን በዓይኔ በረበርኳት፡፡ የሆነ ቦታ የሆነ ነገር ያስቀመጥኩ ይመስል የማውቀውን ታሪኬን እንደማላውቀው ሆኜ መፈተሽ ጀመርኩ፡፡ ምንም አላገኘሁም፡፡ ሰዎች የሚያውቁኝ በሁለት ነገር ነው፡፡ የመጀመሪያው ግዴለሽ በመሆኔ ሲሆን፤ ቀጥሎ ለዘላለም እያፈራረቅሁ በምለብሳቸው ሁለት ሸሚዞቼ ነው፡፡ ግዴለሽነቴን ልሰጠው አልችልም፡፡ ከሸሚዞቼ አንዱን ልሰጠው ግን እችላለሁ፡፡
ለሰባት ዓመታት ያለማቋረጥ የለበስኳትን አንድ ለእናቱ መቀየሪያዬን ሽቶ ነስንሼ ዘረጋሁለት፡፡
ተቀበለኝ . . .
ለምርቃት ከጭንቅላቱ አጎነበሰ፡፡ ያስደሰትኩት አልመሰለኝም፡፡ እርካታን ከሳቅ ጋር ስመትር የኖርኩ አለሌ ነኝ፡፡ በዳመነ ፊቱ ላይ ሳቅን ሳጣ ጊዜ ስጦታዬ መናኛ እንደሆነ እንዳስብ አደረገኝ፡፡ ደማቅ ሆነ ፈዛዛ ሰው ያለውን ከሰጠ ሰጠ ነው ስል ራሴን ለማበረታት ሞከርኩ፡፡ ህይወቴን እንደሰጠሁት ቢያውቅ፡፡ ታሪኬን . . . ማንነቴን እንደሰጠሁት ቢረዳ ተመኘሁ፡፡
የህይወት ታሪኬ ቢጻፍ ግዴለሽነቴና እነዚህ ሁለት ሸሚዞች ጥሩ መታወሻዬ እንደሚሆኑ አምናለሁ፡፡ ከመታወቂያ ስሜ እኩል ‹ያ ግዴለሹ› መለያዬ ነው፡፡ በብዙ ንፉግ ባለጸጎች መሀል ቆማ ትዳሯን እንደሰጠችው እንደዛች እመበለት ህይወቴን ሰጠሁት . . . ታሪኬን ዘረጋሁለት፡፡ ትዝታዬን . . . ትውስታዬን እነሆ አልኩት፡፡
ልክ እንደ ሸሚዞቼና ግዴለሽነቴ ሰው በመኖር ውስጥ የተለማመደው በእድሜ ሃዲድ ስር የተገኘ የህይወት ታሪክ አለው፡፡ በጨሌና በቅቤ እንደምንካድመው ባዕድ አውለያ የምንካድመው ባዕድ ማንነት፡፡ ከለበስኳት ሸሚዜ ጋር ብቻዬን ቀረሁ፡፡ ምስኪኑ ታሪኬን ይዞብኝ ሲሄድ ቆሜ አየሁት፡፡ ከእግሩ አንከስ ይላል፡፡ አቆፋዳውን ያዘለ ትከሻው ወደ አንድ ጎን አጋድሏል፤ ምስቅልቅል ሰውነት፡፡ ለረጅም ሰዓት አየሁት . . . ጀርባው ላይ ያላስተዋልኩትን አስተዋልኩ፡፡ እንደፊትለፊቱ ጀርባውም በጎለጎታው እየሱስ ስዕል ያጌጠ ነበር፡፡ ሳልሰጠው ሰድጄው ቢሆን በዚህ ምስል ፊት እንዴት እጸና ነበር? ካለመኖር የከፋው ሞት ይሄ አይደል . . . በትልቅ እምነት ውስጥ ቦታ ማጣት?
እንኳንም ሰጠሁት፡፡ በህይወቴ ከሰራሁት በጎ ሥራ ሁሉ ለዚህ ሰው መስጠቴ ልክ ሆኖ ተሰማኝ፡፡ እየሱስን በመስቀል ላይ ጀርባው ላይ አየሁት፡፡ እናቱ ማርያም በሀዘን ወደ ላይ አንጋጣ፣ የቆሎጲያ ሚስት ማርያም፣ ሌላኛዋ መቅደላዊት ማርያም ከዮሀንስ ጋር በአንድ ወደ ጌታ ሞት አንጋጠው ሲያነቡ . . . ሌንጊኖስ ጎኑን ሲወጋው . . . በጦሩ በኩል እውር አንድ አይኑ ስትበራ፣ አይሁዶች በለው፣ በለው ሲሉ፣ ጲላጦስ ከደሙ ንጹህ ነኝ ሲል በዛ ጀርባ ላይ አየሁ፡፡ ሳልሰጠው ቀርቼ ቢሆን . . .
በአራስ ጀምበር ፊት ታሪኬን ቀምቶኝ በሚሄድ ድሃ ዳና ላይ በሬን ተደግፌ እንደቆምኩ ከርቀት ኃይለኛ ጩኸት ሰማሁ፡፡ ወደ ቤቴ ሳልገባ ወደ ጩኸቱ ተራ ተጣደፍኩ፡፡ ታሪኬን የወሰደብኝን ድሀ ሲንደፋደፍ ከመንገድ ቀድሜው ወደ ላይ ሰፈር ፈጠንኩ፡፡ በአራቱም የሰፈራችን አቅጣጫ ወደ ጩኸቱ ቦታ ሰዎች ሲተሙ አደገኛ ነገር መፈጠሩን ልቤ ጠረጠረ፡፡ ቦታው ላይ ደረስኩ . . . ቀድመውኝ ከደረሱ ከማውቃቸውና ከማላውቃቸው የሰፈሬ ሰዎች ጋር ተደባለኩ፡፡ በእድሜ ገፋ ያሉ የሰፈራችን አባት በጎረምሳ የፊጥኝ ወደ ተያዘችው ሴት ጠጋ ብለው “ምን ሆነሽ ነው?” አሉ፡፡
“ሽበቴን ነቅሎብኝ፡፡ እርጅና እንደምጠላ እያወቀ እንዴት ሽበቴን ይነቅላል? ይሄ ውሻ! ልቀቀሉኝ ልዘልዝለው” ስትል ከጎረምሶቹ ለማምለጥ ታገለች፡፡
“የምን ሽበት?” ሽማግሌው ጠየቁ፡፡
“ሽበት ነዋ! ያለ እድሜዬ እንዳረጅ፣ ይቺ አሮጊት እያሉ ጎረምሶች እንዲጠቋቆሙብኝ . . . ቆሞ ቀር ሆኘ እንድቀር ፈልጎ አይደል የነቀለብኝ?”
“እረ ባክሽ ተይ! ይሄ አንድ ፍሬ ልጅ ስለምታወሪው ምን ያውቅና ነው እንዲህ የምትይው?” አሉ ልጁን ሸሽገው የያዙት አንድ እናት፡፡
ወደ ልጁ እየጠቆመች “ይሄ ነው የማያውቀው? የልደት ካርዱን አስፍቆ እንጂ የሰፈሩ የእድሜ ባለጸ ጋ ነው፡፡ እንዳውም እናገራለሁ፤ አብረሽኝ ካልተኛሽ እያለ እያስቸገረኝ ነው” ስትል ምራቋን ቱ አለችበት፡፡ ምራቋ ኢላማውን ስቶ ካሰበችበት ሳይደርስ ሌላ ሰው ደረት ላይ አረፈ፡፡
‹አበስ ገበርኩ› አሉ የቅድሟ ሴት፡፡
“እብድና ዘበናይ የልቡን ይናገራል” አድራሻው ከየት በኩል እንደሆነ ያላወኩት ድምጽ ወደ ጆሮዬ ተወናጨፈ፡፡
‹የገዛ ልጇን ነው እንዲህ የምትለው?› አጠገቤ የቆመ ወጣት ፊት ፊቴን እያየ ጠየቀኝ፡፡
እኔ በተጠየኩት ጎረቤቷ ናት መሰል ጓዳ ጎድጓዳዋን የምታውቅ በሚመስል አኳኋን ‹ለዛውም የመጀመሪያ ልጇ ነዋ! እሱን ከወለደች በኋላ ነው እንዲህ እቅሏን የሳተችው› ስትል ከነማብራሪያው ከበስተኋላዬ መለሰችለት፡፡ መልኳን ላየው ወደ ኋላዬ ስዞር በነጠላ ተከናንባለች፡፡
ከዚህ ንግግሯ በኋላ አብዛኛው ሰው እየተዋት ሄደ፡፡ ቀስ በቀስ ግቢው ርቃኑን ቀርቶ እኔና አንቀዋት የያዟት ሶስት ሰዎች ከአንድ አሮጊት ጋር ቀረን፡፡
እኔም መሄድ ስላለብኝ ግቢውን ለቅቄ ስወጣ የቅድሙን ድሀ ጎዳናው ላይ አገኘሁት . . . እያነከሰ፡፡ ከመቼው ሸሚዜን እንደለበሳት እንጃ ታሪኬን አዳፋ ገላው ላይ አየሁት፡፡ አልፎኝ ሲሄድ ቆሜ አየሁት . . .
……….
አንዳንድ ጊዜ ሰው አለመሆን ቢኖር፡፡ የሆነ ነገራችንን ረስተንበት የምንመለሰው ሌላ ተፈጥሮ ቢኖር፡፡ እንደ ንስር ለአፍታ ተሰፍረን በብርታት ለምን ጊዜም ሰው ብንሆን፡፡ በማስተዋል ነጻነትን ማምጣት ሲያቅተኝ እንዲህ በማሰብ በነጻነት መኖር ያምረኛል፡፡
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን የካቲት 1 ቀን 2016 ዓ.ም