የከፍተኛ ትምህርት ዓለም አቀፋዊነት

«ዓለም አቀፋዊነት» እማይገባበት ስፍራ የለም። ከወዝ አደራዊ ዓለም አቀፋዊነት (ዓለምን በሁለት ተቃራኒ ጎራ በሰነጠቀው ማርክሲስት ርእዮተ-ዓለማዊ አገላለፅ «ፕሮሌታሪያን ዓለማቀፋዊነት») ጀምሮ እስከ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ድረስ የጽንሰ-ሀሳቡ አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች ናቸው።

በርካታ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ ዓለም አቀፋዊነት የጋራ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል፤ ዓለም አቀፋዊነት ለጋራ ልምድ እና ተሞክሮ ልውውጥ የተሻለ አጋጣሚን ይፈጥራል። ዓለም አቀፋዊ አስተሳሰብ ፀረ-ቅኝ ግዛት፣ ፀረ-ዘረኝነት፣ የሴቶች እኩልነት፣ ፀረ-ወታደራዊ እና የሰራተኛ መደብ ትግልን («ኢንተርናሲዎናል/ የሰው ዘር ይሆናል» የሚለውን ያስታውሷል) ማካሄጃ ሁነኛ መሳሪያ ነው። ዓለም አቀፋዊነት ከልማዳዊ ድርጊቶችና ኋላ ቀር አሰራሮች ለመላቀቅ መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል። የሰውን ልጅ ሁለንተናዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ያግዛል። ከጠበበ አካባቢያዊ አስተሳሰብ ያላቅቃል።

«በዓለም ሀገሮችና ሕዝቦች መካከል ያሉትን ልዩነቶች በማጥበብ አንድ የጋራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገውን እንቅስቃሴ የሚወክል ቃል» መሆኑ የሚነገርለትን «ዓለም አቀፋዊነት» የድሮና የአሁኑን ለማመልከት በሁለት (ብሉይ ዓለም አቀፋዊነት እና ሀዲስ ዓለም አቀፋዊነትን) ከፍለው የሚያዩ የመኖራቸውን ያህል ሁለቱን ለየብቻ የሚፈትሹ፤ የሚመረምሩ ∙ ∙ ∙ መኖራቸውም ይታወቃል።

ከአንድ መቶ ዓመት በፊት የዓለም የኢንዱስትሪ ሰራተኞች “በአንድ ላይ የሚደርስ ጉዳት በሁሉም ላይ የሚደርስ ጉዳት ነው” በማለት አስቀምጠውታል እንደ ተባለው ዓለም አቀፋዊነት ለጋራ ጥቅም የሚታትር አስተሳሰብ ነው። ዘር፣ ቀለም ∙ ∙ ∙ የማይለይ፣ ሰው ተኮር ነው። ለስልጣኔ ቅርብ ነው። ዓለም አቀፋዊነት ተደራሽነት ነው፤ ጥራት እውን ይሆን ዘንድ አስገዳጅ ነው። ትስስር በመፍጠር ለተቋማት በዓለም አቀፍ ደረጃ እሴት መጨመርም ሌላው ዓለም አቀፋዊነት ፋይዳ ነው።

ትምህርት በባህሪው ከአገር አልፎ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊነት ይዘት ያለው ነው፡፡ በመሆኑም፣ «የትምህርት ዓለም አቀፋዊነት» (Educational internationalization) በትምህርት ዓለም ውስጥ ሁነኛ ስፍራ ያለው፤ ወይም ሊኖረው የሚገባ ጽንሰ-ሀሳብ ሆኖ ቢገኝ ምንም የሚገርም ነገር የለውም። የዛሬው እንግዳችንን ጨምሮ የሚመለከታቸው እንደሚስማሙበት፣ የትምህርት ዓለም አቀፋዊነት፣ ወይም ትምህርትን ዓለም አቀፋዊ ማድረግ የሚከተሉት አበይት ፋይዳዎች አሉ።

ዓለም አቀፋዊ የሆኑ ተወዳዳሪና ተመራጭ ዩኒቨርሲ ቲዎችን ለመፍጠር ያግዛል፤ ዓለም አቀፋዊ አስተሳሰብ ያለው ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት ያግዛል፤ በዩኒቨርሲቲዎች መካከል የተጠናከረ ግንኙነት መፍጠርና ተቋማቱ ችግሮቻቸውን እየለዩ ለችግሮቻቸውም መፍትሄ እየሰጡ የሚሄዱበትን እድል ለማመቻቸት ይረዳል፤ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመቀመር እንደ ዩኒቨርሲቲ የተጠናከረ ዓለም አቀፋዊነትን ያዳብራል፤ ዩኒቨርሲቲዎቻችን የውጭ ተማሪዎችን የሚስቡና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚሆኑበትን እድል ለማመቻቸት ያግዛል፡፡

ከዚህ በፊት «የከፍተኛ ትምህርት ዓለም አቀፋዊነትና የሚኖረው ቀጣይ አቅጣጫ ዙሪያ» በሚል ርዕስ በወቅቱ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ በነበሩት ደላሳ ቡልቻ (ዶ/ር) ቀርቦ የነበረ ሲሆን፤ በዛው ጥናት ላይም ከላይ የጠቀስናቸው ነጥቦች ተካትተው ተመልክተናል።

ጠባብ መልከአ ፖለቲካዊ መዋቅርን ከሚያመለክተው «ብሔራዊነት» በተቃራኒ የቆመው ዓለም አቀፋዊነት እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ መጨረሻ ላይ መጀመሩ የሚነገርለት ሲሆን፣ በምሁራዊ ጥናቶች «ኢኮኖሚያዊ ዓለም አቀፋዊነት፣ ባህላዊ ዓለም አቀፋዊነትና ፖለቲካዊ ዓለም አቀፋዊነት» በማለት በሦስት ከፍለው የሚያዩት ሲሆን፤ እያንዳንዱንም ራሱን በቻለ መልኩ ሲያብራሩት ይታያሉ። ይህም ዓለም አቀፋዊነት ዘርፈ ብዙ ብቻ ሳይሆን ጥልቅ እሳቤ እንደሆነም ያስረዳናል። ወደ ራሳችን እንመለስ።

ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዓለም አቀፋዊነት ጋር የተዛመደውን ተጨማሪ መረጃ በትምህርት ሚኒስቴር የስኮላርሺፕና ዓለም አቀፋዊነት ዴስክ ኃላፊ ዶክተር ኢዶሳ ተርፋሳ ሰጥተውናል:: በገለፃቸውም ፋይዳውንና ያለበትን ሁኔታና ይዞታ ገልፀዋል።

ዶክተር ኤዶሳ እንደ ነገሩን ከሆነ፤ የትምህርት አካሄድና አወቃቀር ወይም ትስስር አድጎ ዓለም አቀፋዊነትን ሲላበስ ለዜጎችም ሆነ ለሀገር ጠቀሜታው የበዛ ነው:: ዓለም አቀፍ ትምህርት ሀገራችን በባሕልና ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ከሌሎች ሀገራት ጋር ዓለም አቀፍ ትብብርን እያሳደገች በመሆኑ ወደ አዲስ ደረጃ ከፍ በማድረግ የአንድነት፣ የወዳጅነት፣ የእኩልነት፣ የወንድማማችነት የእርስ በርስ ግንኙነት ባሕል ስሜት መፍጠር ነው። እየሄድን ያለነውም በዚሁ መንገድ ነው።

ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ፍኖተ ካርታውን መሠረት በማድረግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዓለም አቀፋዊነት እንዲላበሱ የሚያስችል፣ የሚደግፍ፣ የሚከታተል አዲስ መዋቅር መኖሩን የሚናገሩት ዶክተሩ፣ የሀገራችን ትምህርት ከየት ተነስቶ የት መድረስ እንዳለበት የሚያመላክተው የትምህርት ፍኖተ ካርታ አያሌ ማሻሻያዎች አድርጓል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወደ ዓለም አቀፋዊነት ለማሳደግ የሚያግዘውን የስኮላርሺፕና ዓለም አቀፋዊነት ክፍል መዋቀሩ ከማሻሻያዎቹ መካከል የሚጠቀስ ተግባር መሆኑን፤ ክፍሉም ከዚህ ቀደም የነበሩ ልምዶችንና እንቅስቃሴዎችን በማቀናጀት ለስኬታማነትም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ከአጋር ድርጅቶች ጋር እየሠራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

እንደ ዶክተር ኤዶሳ ማብራሪያ፤ ሁሉም የከፍተኛ ደረጃ የትምህርት ተቋማት የየራሳቸ የዓለም አቀፋዊነትና ስኮላርሺፕ ዘርፍ ቢያንስ በዳሬክቶሬት ደረጃ እንዲኖራቸው ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንን ጠይቀን ፀድቆ መጥቶልናል። አፅድቆታል። በመሆኑም ሁሉም በዳሬክቶሬት ደረጃ ይኖራቸዋል ማለት ነው።

እንደ ኃላፊው ገለፃ፤ ዴስኩ ዓለም አቀፋዊነትን ለማስረጽ በአዲስ መልኩ የተቋቋመና የራሱ የሆነ ዕቅድና በጀት ያለው ክፍል ነው:: በፈጠረው ግንኙነት ሳቢያም ብዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ያግዙታል:: በአዲስ አበባ የሚገኙ የአሜሪካን፣ የፈረንሳይ፣ የእንግሊዝ፣ የሩሲያ፣ የቻይና ኤምባሲዎች እና ሌሎችም እገዛ ያደርጉለታል:: ክፍሉ የያዘውን ግብና ዓላማ እንዲያሳካ በርካቶች ከጎኑ መዋል:: ድጋፉም በተለያዩ መንገዶች የሚገለፅ ነው::

ተቋማቱ ተቋማችን ዓለም አቀፋዊነትን ለማስረጽ ሞዴል እንዲያዘጋጅ እያገዙት ነው:: ለተቋማት ሥልጠና እየሰጡልን ነው:: በሁለት ዙር ሁሉንም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች (50 የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችና ምክትል ፕሬዚዳንቶች) ወደ አሜሪካ ሄደው ሥልጠና ወስደዋል:: ሠልጣኞቹም ዩኒቨርሲቲዎች ዓለም አቀፋዊነትን እንዴት አሰረፁ? ዘመናዊ አመራር እንዴት ፈጠሩ? የሚሉትንና ተዛማጅ ጉዳዮችን በመያዝና ሥልጠናዊ ጉብኝት በማድረግ ወደ ተቋሞቻቸው ተመልሰው ለውጥ እያሳዩ መሆኑን ዶክተሩ አስረድተዋል::

እንደ ዶክተር ኤዶሳ ማብራሪያ ተቋማቱ የዓለም አቀፋዊነትና ስኮላርሺፕ ዘርፍ እንዲኖራቸው ያስፈለገበት አንዱ ምክንያት ተቋማቱ ዓለም አቀፋዊነትን ይላበሱ ዘንድ እያሰቡ እንዲያቅዱና እንዲሠሩ፤ ለዚህም ፕሮጀክቶችን አብረው እንዲሠሩ ለማድረግ ነው:: ከዚህ አኳያም፣ እገዛና እርዳታዎችን አብረው እንዲያገኙ፣ ጥናቶችን አብረው እንዲሠሩ እየተደረገ ነው::

ትልልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን እንዲጎበኙና በዚያውም እንዲያግዙን የማድረግ ሥራም እየተሠራ ነው:: ትልልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሲመጡ፣ ፕሮጀክቶችንና እገዛዎችን ማግኘት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው:: የውጭ ምንዛሪ ይገኝበታል:: በየዓመቱም ለዩኒቨርሲቲዎቻችን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገቢ ተገኝቶበታል የሚሉት ዶክተር ኤዶሳ ሀገሪቱ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከማሻሻል አንፃር አዎንታዊ ሚና አለው:: ስለዚህ ዓለም አቀፋዊነትን ባሰረጽን፤ ባሰፈንን ቁጥር ዕውቅናዎች ይሰፋሉ ሲሉም ያብራራሉ።

ዓለም አቀፋዊነት በአህጉር ደረጃ፣ በአፍሪካ ደረጃ እንዴት ይታያል ለሚለው «ዓለም አቀፋዊነት ከቤት፣ ከውስጥ ነው የሚጀምረው። በክልል ውስጥ ያሉ እርስ በርሳቸው፤ በአገር ውስጥ ያሉ እርስ በርሳቸው፤ በአህጉርም ውስጥ ያሉ እርስ በእርሳቸው በመያያዝ፣ በመተሳሰር አንዱ የሌለውን ካለው እየወሰደ እንዲያድግ፣ እንዲያማሏ ነው እሚፈለገው» በማለት አስረድተዋል።

በመሆኑም በአፍሪካ ደረጃ ጥሩ እየሰራን ነው ያሉት ዶክተሩ፤ ከግብፅ፣ ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አልጄሪያ፣ አረብ አገራት ∙ ∙ ∙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር መልካም ግንኙነትን በመፍጠር በመስራት ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ዓለም አቀፋዊነት ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት ከተጀመረ ሁለት ዓመታትን ማስቆጠሩን የሚናገሩት ዶክተር ኤዶሳ፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለው የአጭር ጊዜ ዕቅድ አብሮ የመሥራት፣ ጥናቶችን የማካሔድ፣ ፕሮጀክቶችን የመንደፍ፣ አብሮ አዳዲስ ነገሮች ማምጣት እንደሆነም ይናገራሉ:: በረጅም ጊዜ ዕቅድ ደግሞ ልምድ መለዋወጥ፣ ሦስት አራት ዓመት ሔዶ ሳይንሱን፣ ኢኖቬሽኑን፣ ቴክኖሎጂውን እና አዳዲስ ዕይታዎችን መማር ነው:: የረጅም ጊዜ ውጤቱ የቴክኖሎጂ፣ የዕውቀት ሽግግር ማድረግ ነው:: የተማሯቸውን አዳዲስ ይዘቶች፣ ያገኟቸውን ነገሮች ያመጡና በተቋማቸው ውስጥ እንዲተገብሩት ይደረጋል:: ይህም የሰዎችን ዕይታ ሊቀይር የሚችል ዕውቀትን ያመጣል:: ዕይታና አመለካከት ሲቀየር ሁሉ ነገር እየተቀየረ ይሄዳል ሲሉም ያስረዳሉ።

ዶክተር ኤዶሳ በቅርቡ (በሌላ እትም) ከዚሁ ጋዜጣ ጋር አድርገውት በነበረው ቆይታ እንደተናገሩት ከሆነ የትምህርት ዓለም አቀፋዊነት ጉዳይ በመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን የግሉን ዘርፍም የሚያካትት ነው።

የዓለም አቀፋዊነት ጽንሰ ሃሳብን ስናመጣው ለትምህርት ሥርዓታችን በማሰብ ነው የሚሉት ዶክተር ኤዶሳ፤ የትምህርት ሥርዓታችን ሁለቱንም የግልና የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያጠቃልላል:: ስለዚህ ከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን በአንድ ሃሳብ እንዲሔዱ እያደረገ ነው:: ይህን ስናደርግ የግልና ከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን ቀደም ብለው የጀመሩትን የዓለም አቀፋዊነት ማስፋፋት አለ። ሪፍት ቫሊ፣ አድማስ፣ አልፋ ዩኒቨርሲቲን የመሳሰሉ በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ውስጥ ቅርንጫፍ ከፍተው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውንም ተናግረዋል::

በተለያየ መልኩ ከአቻ ተቋማት የጀመሩት ግንኙነት ቢኖርም መስተካከል የሚገባው ነገር አለ:: በአንድነት የመሥራት አካሄድ አይታይም:: ትብብሩ የለም፤ ውድድሩ ነው የሚታየው:: ዕይታቸው በሙሉ ገቢ ላይ ነው:: በእርግጥ ገቢ ማስገኘት ግድ ነው:: ነገር ግን ገቢን እያስገኙ የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅ አንፃር የሚጎላቸው ነገሮች አሉ:: ወደ ፊት የትምህርት ሥርዓቱ እንደ አጠቃላይ በተሻለ መልኩ የዓለም አቀፍ ሁኔታውን ግንዛቤ ውስጥ ባስገባ መልኩ እንዲሔድ እየተደረገ ነው ያሉት ኃላፊው፣ በተሻለ መልኩ እንዲሠሩ ለመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተሠራ ባለው ልክ ለግሎቹም እየተሠራ እንደሆነ አብራርተዋል::

የከፍተኛ ትምህርት ራስ በራስ ማስተዳደርን በተመ ለከተም ጠይቀናቸው፤ ያደጉት አገራት ዩኒቨርሲቲዎች በሙሉ ለማለት በሚያስችል ደረጃ ራስ ገዝ ናቸው። ወደዚህ ራስ ገዝነትም ሊመጡ የቻሉት ትምህርትን ዓለም አቀፋዊ በማድረግና በሱው ውስጥ በማለፍ ነው። የጀርመን፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ ወዘተ ዩኒቨርሲቲዎች ለዚህ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው ሲሉ መልሰውልናል።

ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት ራስ ገዝ አስተዳደርን የጀመረች ሲሆን፣ በሂደት ሁሉም ወደ እዚሁ አሰራር ነው የሚገቡት። ለዚህ ሁሉም መዘጋጀትና ከዚሁ አኳያ መስራት ይጠበቅባቸዋል የሚሉት የዴስክ ኃላፊው ተቋማቸው ትምህርት ሚኒስቴርም ከዚሁ አኳያ እየሰራ መሆኑን ይናገራሉ።

አሁን ካለንበት የቴክኖሎጂ እድገት አኳያ ብቻ እንኳን ብናየው ዓለም አቀፋዊነት እጅጉን አስፈላጊ ነው። ምንም እንኳን ያደጉት አገራት ቀድመውን የሄዱ ቢሆንም ቢያንስ ልንከተላቸው የምንችለው በዚሁ፣ ትምህርትን ዓለም አቀፋዊ በማድረግ ነው የሚሉት ዶክተር ኤዶሳ፤ እውቀታችንን በጥቂቱ እንድናስተካክል እና በአገር አቀፍ እና በግል ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ያለው የአቅም ልዩነት ምን እንደ ሆነ እንድንለይ፤ ለአካባቢያችን እድገት ምን ያህል አስተዋፅዖ ማድረግ እንዳለብን እራሳችንን እንድንጠይቅ ያስችለናል ሲሉም የትምህርት ዓለም አቀፋዊነትን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያስረዳሉ።

የዴስክ ኃላፊው ዶክተር ኤዶሳ ተርፋሳ እንደሚሉት፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ዓለም አቀፋዊ ማድረግ፣ ከላይ ከገለፅናቸውም በላይ፣ ፋይዳው ብዙ ሲሆን በተለይ በዚህ፣ ዓለም ወደ አንድ መንደር በተለወጠችበትና በቴክኖሎጂ በተራቀቀ ዘመን በብቸኝነት የሚሰራ ስራ የለም። ያደጉት አገራት የደረሱበት ለመድረስ፤ ለመከተል እንኳን ዓለም አቀፋዊነትን መላበስና ማስረፅ የግድ ይሆናል።

ከላይ እያብራራን እንደ መጣነው፣ ዶክተር ኤዶሳም ሆኑ ሌሎች እንደሚያምኑበት በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የትምህርት ዓለም አቀፋዊነት (ኢንተርናሽናላይዜሽን) አስፈላጊነት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ ነው። ምክንያቱም ተቋማትም ሆኑ ምሁራኑ እውቀቶቻቸውን ወደ አደጉት ደረጃ ከፍ እንዲያደርጉ፤ በአገር አቀፍ እና በግል ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ያለው የአቅምም ሆነ ሌላ ልዩነት ምን እንደ ሆነ እንዲለይ፤ እንዲሁም ለየአካባቢያቸው እድገትና ብልፅግና ምን ያህል አስተዋፅዖ ማድረግ እንዳለባቸው እራሳቸውን እንዲጠይቁ እድል ይሰጣል፤ አለም አቀፍ ምሁራንን ለማፍራት ያስችላል። በአጠቃላይ እድገትምም ሆነ ተጠቃሚነትን፤ እንዲሁም ተደራሽነትን ለተመለከቱ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጠው ትምህርትን ከብሔራዊነት (አካባቢያዊነት) ባለፈ ዓለም አቀፋዊ ማድረጉና መፍትሄውም ዓለም አቀፋዊነት መሆኑ ከዓለም ተሞክሮ እየታየ ነውና ጠበቅ አድርጎ መያዝ የግድ ይሆናል።

 ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ጥር 27/2016  ዓ.ም

Recommended For You