ፈረስ የጀግንነት ምልክት ብቻ ሳይሆን የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት መሠረት ነው

ሰንዳፋ በኬ፦ ፈረስ ለኦሮሞ የጀግንነት ምልክት ብቻ ሳይሆን የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት መሠረት ነው ሲሉ የጨፌ ኦሮሚያ ምክትል አፈጉባኤ ኤልያስ ኡመታ ገለጹ። 3ኛው የኦሮሚያ ፈረስ ጉግስ ፌስቲቫል በሰንዳፋ በኬ ከተማ ተካሂዷል።

በፌስቲቫሉ ላይ የተገኙት የጨፌ ኦሮሚያ ምክትል አፈጉባኤ ኤልያስ ኡመታ እንደተናገሩት፤ ፈረስ ለኦሮሞ የጀግንነት ምልክት ብቻ ሳይሆን የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት መሠረት ነው። የዓድዋ ድል ያለፈረስ አልተሳካም፤ በዚህም በዓድዋ ላይ የተሳተፉ ጀግኖች አባቶችና ፈረሶች በታሪክ የማይረሳ ድል አስመዝግበዋል ነው ያሉት።

ፈረስ ጠላትን ለመዋጋትና ለማምለጥ እንዲሁም በሠርግ ወቅት የውበት ምንጭ በመሆኑ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ቦታ ያለው ፍጡር ነው፤ ለዚህም እንክብካቤና ክብር ይገባዋል ሲሉ አቶ ኤልያስ ተናግረዋል።

ይህን እሴት የቱሪዝም ምንጭ በማድረግ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል። ይህ ፌስቲቫልም የዚሁ አካል በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም የሚጠበቅበትን በማድረግ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በዚሁ መርሀ ግብር ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ደራራ ከተማ፤ በኦሮሞ ሕዝብ ባህላዊ ክዋኔ ውስጥ ፈረስ ልዩ ስፍራ የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል። ፌስቲቫሉን የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የሰሜን ሸዋ ዞን፣ የሸገር ከተማ እና የሰንዳፋ በኬ ከተማ አስተዳደር ያዘጋጁት ሲሆን ከ4 ሺህ በላይ ፈረሰኞች እንደታደሙ አንስተዋል።

ብዛት ያላቸው ፈረሰኞች መሳተፋቸውን ጠቅሰው፤ ሁነቱ ጥልቅ እሴቶች የተንጸባረቁበት መሆኑን ተናግረዋል። በኦሮሚያ የፈረስ ግልቢያና ትርኢት በርካቶችን ባሳተፈና ባማረ መልኩ በየዓመቱ እየተካሄደ መሆኑን አስታውሰው፤ በቀጣይም በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል ብለዋል።

በመሆኑም የፈረስ ውድድሩ ካለው ባህላዊ እሴት፣ የገጽታ ግንባታና የኢኮኖሚ ጠቀሜታ አንፃር በቀጣይ የተጠናከረ ሥራ ይሠራል ሲሉ አውስተዋል። የሰንዳፋ በኬ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አለማየሁ ተንኮሉ በበኩላቸው፤ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ የፈረስ ግልቢያና ትርኢት ከጥንት እስካሁንም የዘለቀ ነው ብለዋል።

በተለያዩ ባህላዊ ኹነትና የአስተዳደር ሥርዓት አብሮ የኖረ እና ታሪካዊ ትስስርም ጭምር እንዳለው አንስተዋል። አክለውም ፌስቲቫሉ አካባቢው ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ያለውን አመቺነት ለማስተዋወቅና ህብረተሰቡ ለልማትና ለሰላም የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል እድል ይሰጣል ነው ያሉት።

ይህንንም አጠናክሮ ለመቀጠል ዓመታዊ ባህላዊ የፈረስ ጉግስ ፌስቲቫል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል። በፈረስ ጉግስ ውድድሩ ላይ ከ4 ሺህ በላይ ፈረሰኞች የታደሙ ሲሆን፤ ለአሸናፊዎች እንደ ቅደም ተከተላቸው የዋንጫና የሜዳልያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በፌስቲቫሉ ላይ የኦሮሞ ብሔር ባህላዊ ምግብና ቁሳቁስ ለዕይታ የቀረበ ሲሆን፤ የፈረስ ሽምጥ ግልቢያ እና ባህላዊ ጭፈራዎች ለታዳሚዎች ቀርበዋል።

 ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ጥር 27/2016  ዓ.ም

Recommended For You