37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በመጪው የካቲት ወር መጀመሪያ በመዲናችን አዲስ አበባ ይካሄዳል። የአህጉሪቱ መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶች እና በርካታ የዓለም አቀፍ ተቋማት ድርጅቶች ኃላፊዎችና ሌሎች ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎች በዚህ ስብሰባ ለመሳተፍ ወደ ኅብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ ይመጣሉ።
ኅብረቱ ይህን ጉባኤ ለማስተናገድ ዝግጅቶች መደረጋቸውን አስታውቋል። ኢትዮጵያም በተመሳሳይ ብሔራዊ ኮሚቴዎችን በማቋቋም ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅ በጸጥታና ደህንነት፣ በመስተንግዶ በኩል በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ይፋ አድርጋለች።
ይህ ጉባኤ የልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ዲፕሎማቶች መቀመጫም ለሆነችው ኢትዮጵያ በተለይ ለአዲስ አበባ ከተማ ያለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደሆነ ይታወቃል። እንዳለፉት በርካታ አመታት ሁሉ የሀገሪቱንና የዋና ከተማዋን አዲስ አበባን መልካም ገፅታ መገንባትም ይችላል።
አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ትኩረትን በከፍተኛ ደረጃ የሚስቡ እንደ አፍሪካ ኅብረት ያሉ ስብሰባዎች በተለይ ለሁነት (ማይስ) ቱሪዝም እድገት የጎላ ፋይዳ ያላቸው ስለመሆኑ የዘርፉ ምሁራንም ያመለክታሉ። በእነዚህ መድረኮች የሚገኙ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን፣ ዲፕሎማቶች እና ሌሎች ባለድርሻዎች የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብት እንዲያውቁና እንዲያስተዋውቁ ዕድሉን ከመፍጠሩ በላይ የሆስፒታሊቲው ዘርፍ እንዲያድግና የሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅምም እንዲጨምር እንደሚያስችል የቱሪዝም ዘርፉ የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች ይጠቁማሉ።
የቱሪዝም ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ዩኒት አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ ደርበው እንደሚሉት፤ ሀገሪቱ ካሏት የታሪክ ትሩፋቶች መካከል አንዱ አዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ ኅብረትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ መሆኗ ነው። ይህም የሁነት ቱሪዝምን ለማስፋፋት እንደ ሀገር ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እያስቻለ ነው።
በዚህ ረገድም 37ኛውን የኅብረቱን ጉባኤ ለማስተናገድ እንዲሁም ከጉባኤው በቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ ለመሆን በርካታ እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በተለይም ሀገርን፤ ያሉትን የቱሪዝም ጸጋዎች፤ የቱሪዝም ምርትና አገልግሎቶችን የማስተዋወቅ ሥራዎችን ለመሥራት ዝግጅት እየተደረገ ነው። ሀገሪቱ ለቱሪዝም ልማት፣ ለጉብኝት እና መሰል እንቅስቃሴዎች ያላትን ምቹነት ወይም ተመራጭነት የማስተዋወቅ ሥራ መሥራት ይጠበቃል። በመሆኑም ጉባኤውን በመጠቀም የገጽታ ግንባታ ሥራዎች ይከናወናሉ። የሀገሪቱን (ብራንድ) መለያ (ላንድ ኦፍ ኦሪጅን) ምድረ ቀደምትነት በቀዳሚነት ለማስተዋወቅ ይሠራል።
«የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ተሳታፊዎች በሚኖራቸው ቆይታ ከዋናው አጀንዳቸው ጎን ለጎን ስለ ኢትዮጵያ እንዲያውቁ በአዲስ አበባ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ጉብኝት እንዲያከናውኑ ለመቀስቀስ የሚያስችሉ ሥራዎችን እንሠራለን» የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ ይህም የገበያ (የማርኬቲንግ) እና የማስተዋወቅ ሥራዎችን የሚያጠቃልል እንደሆነ ይናገራሉ። የሚከናወነውም በአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ ውስጥና እንግዶች በሚያርፉባቸው ሆቴሎች መሆኑን ጠቁመዋል። በመለያ (ብራንድ) ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥ፣ የቱሪዝም ጸጋዎችን የማስተዋወቅ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ጠቅሰው፤ ይህም በቅንጅት እንደሚሠራና ሥራውም የቱሪዝም ሚኒስቴር ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል።
የሁነት(ማይስ) ቱሪዝም ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ልማት እጅግ ሰፊ ድርሻ እንዲኖረው ማድረግ ይቻላል የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ ይህንንም ለማድረግ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ብራንድ ሆቴሎች በአዲስ አበባ ተስፋፍተዋል ይላሉ። በቀጣይም ወደ ሥራ የሚገቡ በርካታ ሆቴሎች እንዳሉ ጠቁመዋል። በሌላም በኩል ከዚህ በፊት የተሠሩት እንዳሉ ሆነው በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ የስብሰባ ማዕከላት እየተገነቡ እንደሚገኙ ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአካባቢውና የቀጣናው መናኸሪያ (ሀብ) እንደሆነ ጠቅሰው፣ አየር መንገዱ ወደ ተለያዩ መዳረሻዎች የሚሄዱ ተጓዦች መተላለፊያ መሆኑንም ገልጸዋል፤ አፍሪካን ከተቀረው ዓለም ጋር በማገናኘት እንደሚታወቅም ጠቁመዋል። እነዚህን መልካም ሁኔታዎች ግምት ውስጥ በማስገባት መንግሥት የቱሪዝም ዘርፍ ከኢኮኖሚ መስኮች እንደ አንዱ በማድረግ በርካታ ደረጃቸውን የጠበቁ የቱሪስት የመዳረሻ ስፍራዎች እየገነባ እንደሚገኝ ያስረዳሉ። ይህም የሁነት ቱሪዝምን በኢትዮጵያ ለማስፋፋት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አመላክተዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ለማይስ ቱሪዝም እና ለሀገር ገፅታ ግንባታ ያለውን ፋይዳ በተመለከተ የዝግጅት ክፍላችን ላነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንዳብራሩት፤ ይህ ለ37ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ለሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ዝግጅት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የሚመለከታቸው አካላት ያቀፈ ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ መዋቀሩን አቶ ቴዎድሮስ ደርበው አስታውቀዋል፤ ከእነዚህም መካከል እንግዶቹ የተሳካ ቆይታ እንዲኖራቸው በማድረግ በኩል የቱሪዝም ሚኒስቴር የራሱን ድርሻ ወስዶ እየሠራ እንደሚገኝ ይገልፃሉ።
አቶ ቴዎድሮስ እንዳሉት፤ በጉባኤው በርካታ ቁጥር ያላቸው የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። እነዚህ እንግዶች የሚስተናገዱባቸው ሆቴሎችና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሀገርን ስም በመልካም ሊያስጠራና የሀገርን ገጽታ የሚገነባ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ አቶ ቴዎድሮስ ጥሪ አቅርበዋል።
የሆቴል አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶችም የእንግዶቹን ደህንነት በተጠበቀ መልኩ በኢትዮጵያዊ ሥነ ምግባር፤ ጨዋነትና እንግዳ አቀባበል ማስተናገድ ይጠበቅባቸዋል የሚሉት የስትራቴጂክ ዩኒት አስተባባሪው፤ ሆቴሎች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት የጉባኤው ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ጥሩ ትዝታ እንዲኖራቸው የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው ያሳስባሉ።
ይህንን ለማሳካትም ተሳታፊዎቹን ያስተናግዳሉ ከተባሉ ባለ ኮከብ ሆቴሎች ሥራ አስኪያጆች ጋር መድረክ ተዘጋጅቶ ውይይት መካሄዱንም ይገልፃሉ። እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በውይይቱም እነዚህ ሆቴሎች ለሚከፈላቸው ገንዘብ ተመጣጣኝ ክፍያ እንዲያቀርቡና ያለአግባብ ዋጋ እንዳይጨምሩ፣ እንዲሁም ሆቴሎቹ ከጤናና ከድንገተኛ አደጋ ጋር በተያያዘ አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ ከስምምነት ተደርሷል። በቀጣይም በከፍተኛ ኃላፊዎች ደረጃ ሆቴሎቹ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ዝግጅት እያደረጉ ስለመሆኑ በአካል በመገኘት ጉብኝት ይደረጋል። በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩልም ከመብራት፤ ከውሃና ቴሌኮም አገልግሎት ጋር በተያያዘ ችግር የሚገጥም ከሆነ በወቅቱ ለመቅረፍ ክትትልና ድጋፍ ይደረግላቸዋል።
አቶ ይታሰብ ስዩም የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው የሚመሩት ተቋም ከ50 ዓመታት በላይ በሆስፒታሊቲና ቱሪዝም ዘርፍ የሚሠሩ ባለሙያዎችን በማሰልጠን ወደ ኢንዱስትሪው ቀላቅሏል። ባለሙያዎቹ በልዩ ልዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲሁም አገልግሎት ሰጪዎች ውስጥ እየሠሩ ይገኛሉ። የዝግጅት ክፍላችንም በቅርቡ የሚካሄደውን የኅብረቱን ጉባኤ በማስመልከት የኢትዮጵያን ገፅታ እና የቱሪዝም ሀብት ለማስተዋወቅና የማይስ ቱሪዝም ፅንሰ ሃሳብን ለማሳደግ ‹‹ይህን አጋጣሚ በምን መልኩ ልንጠቀመው ይገባል?›› የሚል ጥያቄ አንስቶላቸዋል።
‹‹የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ‹የአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ ነች› በሚል እሳቤ ነው›› የሚሉት አቶ ይታሰብ፤ መስተንግዶው እንደ አንድ ሆቴል አገልግሎት ሰጥቶና ገንዘብ ተቀብሎ መሸኘት ብቻ አለመሆኑን ይናገራሉ። መስተንግዶው ከገፅታ ግንባታ ጋር ቀጥታ ግንኙነት እንዳለው ጠቅሰው፤ ጉዳዩ በጥንቃቄ መያዝ እንደሚኖርበት ያሳስባሉ።
አቶ ይታሰብ ከሳምንት በፊት እርሳቸው በምክትል ዋና ዳይሬክተርነት የሚመሩት የማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ከአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ወደ 80 ለሚደርሱ የተመረጡ ሆቴሎች በሥራ ላይ የማማከር አገልግሎት (consultancy service) መስጠቱን ይገልፃሉ። ይህም ጉባኤው በሚካሄድበት ወቅት እንግዶችን በሚፈለገው የጥራት ደረጃ እንዲቀበሉና እንዲያስተናግዱ ያስችላቸዋል ይላሉ።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲሁም የሆስፒታሊቲ ዘርፉ ተዋንያን የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ሲደርስ ብቻ ሳይሆን ሁሌም ዝግጁ ሆነው መጠበቅ እንዳለባቸው ይመክራሉ። የይድረስ ይድረስ ዝግጅት የኢትዮጵያን የማይስ ቱሪዝም እና የቱሪስት ፍሰቱን እንደማያሳድገው አስገንዝበው፣ ሁልጊዜም ቢሆን ሆቴሎችና የመስህብ ስፍራዎች ለውጥና የማያቋርጥ እድገት ማምጣት እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል። የትምህርትና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል።
አቶ ይታሰብ እንዳሉት፤ የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የጠበቁ ስብሰባዎችን በማዘጋጀት የማይስ ቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ ለመሆን ዕድሉን የሚከፍት ልምድ ለማዳበር ያስችላል። ይሁን እንጂ መሪዎች የሚገኙበት እና በኅብረቱ ጽሕፈት ቤት የሚደረግ ጉባኤ እንደመሆኑ ከደህንነትና ጥበቃ አንፃር ጥበቃ ይደረግለታል። ይህ አጋጣሚ ልክ እንደሌሎቹ ጉባኤዎች ነፃነት የሚሰጥ ባይሆንም ጎን ለጎን በሚካሄዱ ዝግጅቶች መሪዎችን፣ ዲፕሎማቶችን እና ልዑካኑን ስለ ኢትዮጵያ መስህቦች እንዲያውቁ ዕድል መፍጠር ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ከተቻለ የኢትዮጵያን ገፅታ ከመገንባት ባሻገር የቱሪዝም ሀብቶችን ለማስተዋወቅ ያስችላል።
‹‹የማይስ ቱሪዝም ፅንሰ ሃሳብን ለማስረፅ እና ለማሳደግ እንደ ሀገር ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል›› የሚሉት አቶ ይታሰብ፤ ሚሊኒየም አዳራሽን የሚያክሉ አሊያም ከዚያም የላቀ ግዝፈት ያላቸው አዳራሾች (convention center) በመገንባት፤ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን፣ ኤክስፖዎችን ወደ ሀገር በማምጣት ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንደሚያስፈልግ ይመከራሉ። ለዚህ እንዲረዳ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲናና ታላላቅ ስብሰባዎች (እንደ አፍሪካ ኅብረት ጉባኤ) የሚዘጋጅባት እንደሆነች በስፋት ማስተዋወቅና ከዚያ ዕድል ተጠቃሚ መሆን እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።
በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ትላልቅ ኤክስፖዎች (trade fairs) እንደሚካሄዱ የሚናገሩት አቶ ይታሰብ፤ ይህን መሰል ዝግጅት ለሀገራቱ በርካታ ዕድል ይዞ እንደሚመጣ ይናገራሉ። ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ ከሚመጡት ጋር የእውቀት ሽግግር ይደረጋል፤ የሥራ ዕድል ይፈጠራል፤ የሆቴል ዘርፉ፣ ግብይቱ፣ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ይነቃቃል፤ የቱሪዝም መስህቦች መነቃቃት ይፈጠራል ሲሉ ያብራራሉ።
ይህንን ዕድል ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት በትኩረት መሥራት እና የመሰናዶ ስፍራዎችን ማዘጋጀት እንደሚገባ የሚናገሩት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ አኳያም ጅምር ሥራዎች እዚህም እዚያም እንደሚታዩ ጠቅሰዋል፤ ወጥ በሆነ መንገድ ስኬታማ ለመሆን ግን በርካታ ጥረቶችን በማድረግ ውጤቶች መመዝገብ እንደሚኖርባቸው አስረድተዋል።
ከአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ተጠቃሚ ለመሆን በርካታ ሆቴሎች በጉጉት ይጠብቁታል ያሉት አቶ ይታሰብ፤ ይሁን እንጂ በኅብረቱ ጉባኤ ላይ ብቻ ጥገኛ የሆነ የሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪ መኖር እንደሌለበት ይናገራሉ። ይልቁኑም መሰል ታላላቅ ዝግጅቶች በማይስ ቱሪዝም ዘርፍ እንዲዘጋጁና በየወቅቱ ገበያ እንዲፈጠር፣ የኢትዮጵያ የመስህብ ሀብቶች እንዲተዋወቁ እንዲሁም ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ ተከታታይ ሥራ በመንግሥትም ሆነ በግሉ ዘርፍ መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ማይስ ቱሪዝም በዓለማችን ላይ ከፍተኛ ገቢን የሚያንቀሳቅስና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተመራጭ እየሆነ የመጣ የቱሪዝሙ ንዑስ ዘርፍ ነው። ያደጉ ሀገራት ከመስህብ ቱሪዝም በተጨማሪ ምጣኔ ሀብታቸውን በሚደግፈው በእዚህ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ላይ ትኩረታቸውን አድርገው እየሠሩ ይገኛሉ።
ማይስ ቱሪዝም በሆቴልና ሆስፒታሊቲ፣ ዓለም አቀፍ ስብሰባ፣ ለማበረታቻና ሽልማት የሚካሄዱ የተቋማት ስብሰባዎች እንዲሁም ወቅትን ጠብቀው የሚካሄዱ የንግድ ኤግዚቢሽን ላይ የሚያተኩር የቱሪዝም ዓይነት ነው።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2017 የተካሄደ ዓለም አቀፍ ጥናት እንደጠቆመው፤ ማይስ ቱሪዝም አንድ ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያንቀሳቅስ ግዙፍ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ነው። ይህ አሃዝ እስከ 2025 (ከሁለት ዓመታት በኋላ) ወደ አንድ ነጥብ 5 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያደግ ጥናቱ ቅድመ ግምቱን አስቀምጧል። ከዚህ መረዳት የምንችለው የሆቴል፣ ኮንፍረንስ፣ ኤግዚቢሽንና ባዛር እንዲሁም ልዩ ልዩ የማይስ ቱሪዝም ንዑሶችን የሚይዘው ይህ ኢንዱስትሪ የዓለማችን የምጣኔ ሀብት ምንጭ እየሆነ መጥቷል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥር 26/2016