ሀገሪቱ በአስር ዓመቱ መሪ እቅድ ትኩረት ለመሠረተ ልማት ግንባታ ትኩረት ሰጥታለች፡፡ በእዚህም ከሚገነቡት መካከል የመንገድ መሠረተ ልማቶች ይጠቀሳሉ። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው 2015 በጀት ዓመት ባደረገው አንድ መድረክ ላይ እንደተጠቆመው፤ ሀገሪቱ አንድ ትሪሊዮን ብር የሚጠይቁ ከ22 ሺ ኪሎ ሜትር በላይ የአስፋልት ኮንክሪት የመንገድ ግንባታዎችን እያካሄደች ነበር፡፡
ሀገሪቱ የመንገድ መሠረተ ልማትን ጨምሮ ለልማት አስፈላጊ የሚባሉ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት እነዚህ ግንባታቸው በተለያየ ደረጃ ከሚገኙ የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታዎችና በቀደሙት ዓመታት ከተካሄዱ የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታዎች መረዳት ይቻላል፡፡
ሀገሪቱ የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታዎችን ከዚህም በላይ ማካሄድ የምትችል ቢሆንም፣ በዘርፉ በሚታዩ ለመንገድ ግንባታ ተግዳሮት በሆኑ ችግሮች ሳቢያ አፈጻጸም ላይ ክፍተት ይታይባታል፡፡ ከካሳ ክፍያ፣ ከወሰን ማስከበር፣ ከግብአት አቅርቦት እጥረትና ከመሳሰሉት ጋር በተያያዘ የመሠረተ ልማት ግንባታ ስራዋ በእጅጉ እየተፈተነ ይገኛል፡፡ ሰሞኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴርንና የተጠሪ ተቋማቱን የ2016 በጀት ዓመት ያለፉትን ስድስት ወራት ሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባዳመጠበትና እሱን ተከትሎ በተካሄደው ውይይት ላይ የተጠቆመውም ይሄው ነው፡፡
በመድረኩ ላይ እንደተጠቆመው፤ በሀገሪቱ በየክልሉ ግንባታቸው እየተካሄደ ባለ የመንገድ መሠረተ ልማት ሥራዎች ላይ የመጓተት ችግሮች በስፋት ይስተዋላሉ። በየክልሉ ለሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶች በወቅቱ አለመጠናቀቅ የተቋራጮችና አማካሪዎች የማስፈፀም አቅም ችግሮች በተግዳሮትነት ሲነሱ ቆይተዋል። የጥራት መጓደል፣ ለልማት ተነሺዎች የካሳ ክፍያ በወቅቱ አለመፈፀም፣ የፕሮጀክት በጀት ክፍያ በወቅቱ አለመለቀቅ፣ ከዋጋ ንረት ጋር የተያያዙ እንዲሁም የግብአት ችግሮች ሌሎች በዋናነት የሚነሱ ችግሮች ናቸው፡፡
የሚኒስቴሩን ሪፖርት ያዳመጡት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በየከልሉ ግንባታቸው የተጓተተ የመንገድ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችንና የመንገድ ጥገና ስራዎችን የተመለከቱ ጥያቄዎችን አቅርበው ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጥባቸውም ጠይቀዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ፣ ቋሚ ኮሚቴው ክትትል ካደረገባቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው 45 ፕሮጀክቶች ብቻ ናቸው፡፡ 109 ፕሮጀክቶች መጓተታቸውን ጠቅሰው፣ 84 የመንገድ ፕሮጀክቶች ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታቸው የተቋረጠ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የምክር ቤት አባላት የመረጣቸውን ሕዝብ በሚያወያዩበት ጊዜ ሕዝቡ ቅሬታ ካነሳባቸው መካከል አንዱ የመንገድ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
እቅድ ተይዞላቸው ያልተሰሩ መንገዶችን፣ ሥራቸው ተጀምሮ የተጓተቱ የመንገድ ፕሮጀክቶችን፣ በከተሞች ያለው የመሬት አስተዳደር ለብልሹ አሰራር የሚያጋልጥ መሆኑንና በትክክል ካሳ ለተገመተላቸው የመሬት ባለቤቶች በወቅቱ ካሳ እየተከፈለ አለመሆኑንም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አመልክተው፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል ።
ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱት የመንገድ እና ሌሎች የከተሞች መሠረተ ልማት ጥያቄዎች የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒሰትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ የሕዝቡ የአገልግሎት ፍላጎት የመንገድ መሰረተ ልማት ማግኘት መሆኑንና ጉዳዩ በትኩረት እንደሚታይም አስታውቀዋል። የማህበረሰቡ ትኩረት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ትኩረት መሆኑን አስታውቀው፣ የተነሱት ገንቢ ሀሳቦችና ጥያቄዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፤ ሁሉም በእቅድ ተይዘው እየተሰራባቸው መሆኑን አመልክተዋል።
በመንገድ ፕሮጀክቶችን ላይ የሚታየውን ችግር በየደረጃው ለመፍታት እንደሚሰራ ጠቅሰው፣ለእዚሀም ሚኒስቴሩ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ የሚሠሩ በሚል ለይቶ ችግሮቹን ለመፍታት መስራት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
በአዎንታዊነት የሚወሰዱ ስራዎች አንዳሉም ጠቅሰው፣ የተቋሙ የማስፈፀም አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ ለእዚህም በቱሪዝም መዳረሻ አካባቢዎች በርካታ የመሠረተ ልማት ግንባታ ስራዎች መካሄዳቸውን በአብነት ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህ ግንባታዎች በፍጥነት እየተሰሩ መሆናቸውንም ነው ያመለከቱት። ቱሪዝሙም ያለመንገድ እና ያለመሠረተ ልማት እውን መሆን እንደማይችል አስታውቀው፣ ተጨማሪ ፕሮጀክቶች ለመሥራትም መሥሪያ ቤቱ አቅም አየፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ያለውን የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ በፀጥታ ኃይሎች ትብብር እንዲጠናቀቅ የሚደረግበት ሁኔታ እንዳለም ጠቅሰው፤ ለእዚህም እየተከፈለ ያለ ዋጋ ትልቅ ነው ብለዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ችግር ፕሮጀክቶች በሚከናወኑባቸው እና ግብአት የሚወጣባቸው አካባቢዎች ላይ ችግር እያስከተለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ የሙያ እና ከማስፈፀም አቅም እንደተጠበቀ ሆኖ ከግብአት ጋር የተያያዘው በተለይ የሲሚንቶ እጥረት በከፍተኛ ደረጃ ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡ የአስፓልት እጥረት ሌላው ተግዳሮት ሲሆን፣ ይህን ከውጭ ሀገር የሚመጣ ግብአት ችግር መፍታት የሚቻልበትን አማራጭ ለማግኘት የሚያስችል የቤት ሥራ ተወስዶ እየተሰራበት ነው። በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የምርምር ማዕከልም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ የመጣውን የአስፓልት ግብአት መተካት በሚያስችሉ አማራጮች ላይ ምርምሮች እየተካሄዱ ይገኛሉ።
ግንባታ ብቻም ሳይሆን ከግንባታ በኋላም ለግንባታ የሚወጣውን ያህል ወጪ ለጥገናም እንደሚወጣ ሚኒስትሯ ጠቁመው፣ በዚህ ሥራ እያተረፍን ነው ወይ የሚለውን ለመመለስ ከባለሙያዎች እና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የጥናት ማዕከል በጋራ በመፍጠር ሃሳብ ለማፍለቅ ጥረት አየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል። በጥናቱም አንድ መፍትሄ ላይ ሲደርስ የግብአት ችግሮችን በመሠረታዊነት በብዙ ርቀት መፍታት እንደሚቻል ይገልፃሉ።
ሚኒስትሯ እንዳብራሩት፤ ሌላው የዘርፉ ችግር ከወሰን ማስከበር ጋር የተያያዘው ነው፡፡ የወሰን ማስከበር ጉዳይ የመንገድ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም መሠረታዊ ተግዳሮት መሆኑ ቀጥሏል። በፌዴራል እና ክልሎች ለተመሳሳይ የመሠረተ ልማት ግንባታ ለተመሳሳይ ቦታ ክልል ለያዘው ፕሮጀክት እና የፌዴራል መንግሥቱ ለያዛቸው ፕሮጀክቶች የተለያየ አገር ውሳኔ የሚመሥሉ የካሳ ጥያቄዎች ይቀርባሉ። ይህን ችግር በተለመደው መንገድ ብቻ በመሄድ መፍታት አይቻልም፤ ሁሉም ሰው በየአካባቢው ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት እገዛ ማድረግ ይጠበቅበታል፤ በተለይ ክልል አካባቢ ያሉትን ችግሮች በምን መልኩ በመሠረታዊነት መፍታት እንችላለን የሚል ትልቅ ሰነድ አዘጋጅተናል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ሰነዱ ለእዚህ ምክር ቤት እንደሚቀርብም አስታውቀዋል፡፡
አሁን እየተሰራበት ባለው መንገድ የአንድ የመንገድ ፕሮጀክት ዋጋ አንድ ቢሊዮን ብር ከሆነ ለካሳ ክፍያ የሚጠየቀው ሁለት ቢሊዮን እየሆነ መምጣቱ እንደማይቀርም አስገንዝበዋል፡፡ ይህም ትርፍ ነው ወይስ ኪሳራ የሚለውን በሕዝብ ሀብት አተያይ በማየት ስራውን ማስተዳደር የሚቻልበት ውሳኔ እንደሚፈለግ ጠቅሰው፤ ይህም የዘርፉ አንዱ መሠረታዊ ችግር መሆኑን አንስተዋል።
የካሳ ክፍያው በትክክለኛ መንገድ ተገምቶ የመጣ ሆኖም ተቋሙ ጋ ሲደርስ በተለያየ ምክንያት በተለይም ከበጀት እጥረት አኳያ ክፍያው በወቅቱ እየተፈጸመ ያልሆነበት ሁኔታ እንዳለ ጠቅሰው፣ ከዚህ ውጪ መንግስት የሚቻለውን ሁሉ ለመንገድ መሰረተ ልማት ዘርፉ ክፍያ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም ተቋሙ የሚጠይቃቸው የካሳ ክፍያ በጊዜ ከመክፈል ጋር የተያያዙ ችግሮች በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በኩል እንደ ክፍተት የሚወሰዱና መፈታት ያለባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፤ ችግሮቹ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ሲንከባለሉ የመጡና ችግሮቹን መፍታት እንደ ተቋም የሁሉንም አካላት ድጋፍ የሚጠይቅ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል ለፕሮጀከቶች መተግበሪያ ከሚለቀቀው ክፍያ መዘግየት ጋር የተያያዙ መሠረታዊ ችግሮች መኖራቸውንም ሚኒስትሯ አመልክተዋል፡፡ የተቋራጮች፣ የአማካሪዎች፣ የማስፈጸም አቅም ችግር እንዳለም ጠቅሰው፣ ለሰሩት ስራ በመሠረታዊነት መክፈል ሲቻል ብቻ ፕሮጀከቱን ወደፊት ማስኬድ እንደሚቻልም ይገልፃሉ። መንግሥት የተቻለውን ያህል ክፍያ ለመሠረተ ልማት ዘርፉ ቅድሚያ እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቀው፣ አሁንም ያሉበትን መሠረታዊ እጥረቶች ለመፍታት መረዳዳት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በተለይ ከመንገድ መሠረተ ልማት ጉዳይ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር በመሠረታዊነት ለመፍታት ባለፈው ዓመት የተፈጠሩት የአደረጃጀት እና የአሰራር ማዕቀፎች እገዛ ወሳኝ ነው። ይህ አሰራር በየአካባቢው የሚገኙትን 188 የመንገድ ፕሮጀክቶች ለመቆጣጣር አስችሏል።
ከማዕከል ብቻ ሆኖ እነዚህን ሁሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች መቆጣጠር እንደማይቻል ሚኒስትሯ አስታውቀው፣ በአካባቢው ያለው የፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ማኔጀመንት ፀሐፊ ውሳኔ ማሳለፍ በሚችልበት መንገድ በሰው ኃይል እና በአደረጃጀት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ይህም በሂደት የሚያመጣቸውን ለውጦች በመወሰድ ችግሮችንም በአደረጃጀት ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ከከተማና መሠረተ ልማት ውጪ በሆኑና የሌላ ዘርፍ ተሳትፎን እና የመንግሥትንም ድጋፍ በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት እና ስራዎችን ስትራቴጂከ በሆነ መንገድ በመምራት ከመንገድ ጋር የተያያዙ ፈተናዎችን ለመፍታት መልካም አጋጣሚዎችን መጠቀም እንደሚያስፈልግም ሚኒስትሯ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሐመድ አብዱራህማን በበኩላቸው፤ ከመንገድ መሠረተ ልማት ፐሮጀክቶችና ከጥገና ስራዎች ጋር ተያይዞ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። እሳቸው እንዳብራሩት፤ የዓለም ገና ቡታጀራ መንገድ ፕሮጀክት አካል የሆነው የሆሳዕና ከተማ መንገድ እና የፍሳሽ መሄጃ ስራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ መሆናቸውን ይገልፃሉ። ፕሮጀክቱ በግል የሥራ ተቋራጭ ይሰራ እንደነበረ አስታውሰው፣ የመንገድ አስተዳደር መስሪያ ቤቱ በአፈፃፀም መጓደል በታዩ ክፍተቶች በተቋራጩ ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቀዋል።
የመንገድ አስተዳደር መስሪያ ቤቱ እርምጃዎችን የመወሰድ እና ማሰተካከያዎችን የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ጠቅሰው፣ በዚህ መሰረትም እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑንም አስታውቀዋል። የአፈፃፀም ጉድለት በሚታይባቸው የሥራ ተቋራጮች ላይ ኮንትራቱን እስከማቋረጥ የሚደርስ እርምጃ የመውሰድ ሁኔታዎች እንዳሉም ጠቅሰው፤ ለእዚህም በማሳያነት በሆሳዕና ከተማ በሚሰራው የአምስት ኪሎሜትር መንገድ ሥራ ተቋራጭ ላይ የተወሰደን እርምጃ ገልጸዋል፡፡ የተቋራጩ አፈፃፀም አመርቂ ባለመሆኑ ኮንትራት በማቋረጥ በራስ አቅም እንዲሰራ መደረጉን ጠቁመዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ የመንገድ አስተዳደሩ በስድስት ወራቱ ለመከወን ካቀዳቸው 54 የዲዛይን ፕሮጀክቶች መካከል 21 ያህሉን በጸጥታ ችግር መተግበር አልቻለም። የስድስት ወራቱ የዲዛይን ስራዎች አፈጻጸም 57 በመቶ መሆኑም ሌላው ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛነት በምክንያትነት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በውጭ አማካሪ ድርጅት ለተሰራ ሥራ ክፍያ ለመፈጸም የውጭ ምንዛሪ መዘግየት ማጋጠሙን ጠቅሰው፣ በዚህ የተነሳ የተጓተቱ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። በተለያዩ ምክንያቶችም 84 ፕሮጀክቶች መቋረጣቸውን እና ሙሉ በሙሉ የኮንትራት ውላቸው መሰረዙንም ይናገራሉ። የግብዓት እጥረት፣ የወሰን ማስከበር ችግር እና የተጋነነ የካሳ ተመን ችግሮች መቀጠላቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በመንገዶች ጥገና እና ግንባታ በስድስት ወራቱ የተሻለ አፈጻጸም የታየበት ሁኔታ መኖሩንም ይጠቁማሉ። በአሁኑ ሰዓት አጠቃላይ የመንገድ ሽፋን በኢትዮጵያ 169 ሺህ 450 ኪ.ሜ መድረሱን ኢንጂነር መሐመድ አብዱራህማን አስታውቀዋል፤፤ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የተቋረጡ 64 የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከልም 15ቱን ማስጀመር መቻሉን አስታውቀዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የመንገድ ፕሮጀክቶች ስኬቶች፣ መሠረታዊ ተግዳሮቶች እንዲሁም ቀጣይ ስራዎች በምን መልኩ መከናወን ይገባቸዋል በሚሉት ላይ በልዩ ሁኔታ መነጋገር እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ከካሳ ክፍያና ከሥራ ተቋራጮች ጋር የሚያያዙ ጉዳዮች እንዲሁ ተቋም ውስጥም ያሉ ጉዳዮችና ተግዳሮቶችን መነሻ በማድረግም በቀጣይ በምን መልኩ ማስኬድ እንደሚገባ በጥናት በመለየትና የሌሎች ሀገራት ተሞክሮዎችን በመጠቀም በሁሉም አካባቢዎች ያሉ የመንገድ መሠረተ ልማት ችግሮችን በመሠረታዊነት መፍታት እንደሚገባ አስታውቀዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 25 ቀን 2016 ዓ.ም