የአፍሪካ ዋንጫው በአጓጊ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ

በኳታሩ የዓለም ዋንጫ እስከ ግማሽ ፍጻሜ በመጓዝ ድንቅ ቡድን መገንባቷን ያስመሰከረችው ሞሮኮን ጨምሮ በዓለም ዋንጫው አፍሪካን የወከሉ፤ እንዲሁም በወቅታዊው የፊፋ ሃገራት ደረጃ መሰረት ከአፍሪካ ቀዳሚ ቡድኖች መካከል ከአንድ እስከ አምስት የተቀመጡትን ታላላቆቹን ቡድኖች በጊዜ ያሰናበተው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ፤ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎቹን ዛሬና ነገ ያከናውናል። በካሜሮኑ የአፍሪካ ዋንጫ ከሩብ ፍጻሜ መድረስ ያልቻሉት ቡድኖች ኮትዲቯር ላይ ዋንጫውን የግላቸው ለማድረግ የሚያደርጉት ፍልሚያ ውድድሩን እጅግ አጓጊና የማይገመት አድርጎታል፡፡

የእግር ኳስ ቤተሰቡን ባስደመመው ጥሎ ማለፍ የተመዘገቡ ውጤቶች ከአፍሪካ ዋንጫው መጀመር አስቀድሞ በቡድን ስብስባቸው የተፈሩ ቡድኖችን እያንጠባጠበ ወደ ሌላኛው ልብ አንጠልጣይ ደረጃ ተሸጋግሯል፡፡ በዓለም ዋንጫ ታሪካዊ ፉክክር ያስተናገደችው ሞሮኮ፣ ከሁለት ዓመት በፊት ዋንጫውን የወሰደችው ሴኔጋል፣ የአፍሪካ ዋንጫን ለ7 እና 5 ጊዜ በማንሳት ተከታትለው የተቀመጡት ግብጽ እና ካሜሮን በፕሮፌሽናል ተጫዋቾች የተገነባ ቡድናቸው ባልተጠበቀ ሁኔታ ነው የተገኙት፡፡ በአንጻሩ የውድድሩ አዘጋጅና እድለኛዋ ኮትዲቯር ወደ ፉክክሩ ተመልሳ ከዋንጫው ተፋላሚ ሃገራት መካከል አንዷ መሆኗ የእግር ኳስን አይገመቴነት የሚያሳይ ሆኗል፡፡ ብዙም ግምት ያላገኙት ኬፕ ቬርዴ፣ አንጎላ፣ ጊኒና ደቡብ አፍሪካም ከስምንቱ ቡድኖች መካከል ተገኝተዋል፡፡

 ከሁለት ቀናት እረፍት በኋላ ዛሬ እና ነገ በሚከናወኑት ጨዋታዎች ደግሞ ሩብ ፍጻሜውን አልፈው ለግማሽ ፍጻሜው ጨዋታ የሚደርሱ አራት ቡድኖች ይለያሉ። የዛሬ ምሽቱ ቀዳሚ ጨዋታም በናይጄሪያ እና አንጎላ መካከል በፌሌክስ ሆፌት ቡዋኜ ስታዲየም የሚከናወን ነው፡፡ ይሆናሉ ተብሎ በማይጠበቁ ክስተቶች የተሞላው ይህ ውድድር በአፍሪካ ዋንጫ ታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ረጅም ርቀት መጓዝ የቻለችው አንጎላ በአስደናቂነቷ ትቀጥላለች ወይስ ዋንጫውን ለመጨረሻ ጊዜ ከወሰደች 10 ዓመታትን ያስቆጠረችው ናይጄሪያ በዋንጫ ፉክክሩ ትጸናለች የሚለውን ይለያል፡፡ በቁጥር በተቀመጡት ቅድመ ግምት መሰረት የአሸናፊነት ሚዛኑ ለናይጄሪያ ያዘነበለ ቢሆንም፤ ምድቧን እየመራች ከሩብ ፍጻሜ የደረሰችው አንጎላ ቀላል ተፎካካሪ ልትሆን እንደማትችል ግልጽ ነው፡፡

ሌላኛው የዕለቱ ጨዋታ ደግሞ አቢጃን በሚገኘውና 60ሺ ሰዎችን የመያዝ አቅም ባለው አላሳኔ ኦታራ ስታዲየም የሚከናወነው የዴሞክራቲክ ኮንጎ እና ጊኒ ጨዋታ ነው፡፡ ከአፍሪካ ኃያል ቡድኖች መካከል አንዷ የሆነችውን ግብጽን ከጨዋታ ውጪ በማድረግ ለሩብ ፍጻሜው የበቃችው ኮንጎ በምርጥ ሶስተኛነት ዳግም ለተፋላሚነት ከበቃችው ጊኒ ጋር የሚኖራቸው ግጥሚያ በእርግጥም ድራማዊ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ ሁለት ጊዜ ዋንጫ ማንሳት የቻለችው ኮንጎ የተሻለ የውድድር ታሪክ ያላት ሲሆን፤ በዛሬው ጨዋታም በርካቶች የአሸናፊነት ግምቱን ሰጥተዋታል።

ነገ በሚኖረው መርሃ ግብር ማሊ ከውድድሩ አዘጋጅ ሃገር ኮትዲቯር ጋር የምትጫወት ሲሆን፤ ዕድለኛዋ ኮትዲቯር ወይስ እምብዛም ፉክክር ያልታየበትን ምድብ አምስትን ስትመራ የቆየችው ማሊ ትረታ ይሆን የሚለው የስፖርት ቤተሰቡን ቀልብ ይዟል። ዋንጫውን በሀገሯ ታስቀራለች በሚል ስትጠበቅ የቆየችው ኮትዲቯር እንደ አዘጋጅ ሃገር ከምድብ ያለማለፏ ዜና አነጋጋሪ ነበር፡፡ ነገር ግን ምርጥ ሶስተኛ በመሆን ወደ ፉክክሩ በመመለስ ጠንካራዋን ሴኔጋልን ጥላ ማለፍ ችላለች፡፡ ሆኖም ቡርኪና ፋሶ ላይ ድል የተቀዳጀችውና ሳይገመት ጠንካራ ሆና የተገኘችው ማሊ ፈተና እንደምትሆንባት ይጠበቃል፡፡

የመጨረሻው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታም ደቡብ አፍሪካን ከኬፕቨርዴ ጋር የሚያገናኝ ነው። ደካማ አጀማመር አሳይቶ ወደ ጠንካራ ብቃቱ የተሸጋገረው የደቡብ አፍሪካ ቡድን በጥሎ ማለፉ ጨዋታ ሳይጠበቅ ጠንካራዋን ሞሮኮን 2 ለምንም የሆነ ፍጹም የበላይነትን መቀዳጀቱ የሚታወስ ነው። ሳትገመት ውጤታማ ጉዞ እያደረገች ያለችው ደሴቲቷ ሃገር ኬፕቨርዴ በአፍሪካ ዋንጫው ጠንካራ በተባለው ምድብ ሁለት ነበር የተደለደለችው፡፡ የአራት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋን ጋናን 2 ለ 1 በማሸነፍና ከሰባት ጊዜ የውድድሩ ዋንጫ ባለቤት ግብጽ ጋር አቻ በመለያየት፤ እንዲሁም ሞዛምቢክን 3 ለምንም በማሸነፍ ነበር በሰባት ነጥብ የምድቡ ቁንጮ ሆና ነው 16ቱን የተቀላቀለችው፡፡ በጥሎ ማለፉ ጨዋታም ሞሪታኒያን በመርታት በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎዋ ስኬታማ የተባለውን ጉዞዋን በማድረግ ላይ ትገኛለች። በዛሬው ጨዋታም ከሁለቱ ቡድኖች ጠንካራ ጨዋታ ይጠበቃል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ጥር 24/2016

Recommended For You