በተለያዩ አበቦችና እፅዋት በተዋበውና በተንጣለለው ቅጥር ጊቢ ውስጥ የሚያማምሩ ሕፃናት ይጫወታሉ፡፡ ከውቡ መናፈሻ ትዕይዩ ተሰድረው የተሰሩት ቤቶች ጥግ ላይ የቆሙ ታዳጊዎች ደግሞ ያወካሉ፤ ይላፋሉ፡፡ አንድ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለበት ጎረምሳ ደግሞ ዊልቸሩን እየገፋ ከወዲያ ወዲህ እየተዘዋወረ ከሚያየው ጋር ሁሉ ለማውራትና ለመጫወት ይሞክራል፡፡ ከፊሎቹ ታዳጊዎች ደግሞ ከሳሎናቸው ሆነው ቴሌቪዥን ይመለከታሉ፤ ዳቧቸውን እየገመጡ ይዝናናሉ፤ አንዳንዶቹም ከትምህርት ቤት መልስ መኝታ ክፍላቸው ሆነው ጋደም ብለው እረፍታቸውን ያጣጥማሉ፡፡
በሌላኛው ጊቢ በኩል ደግሞ ነርሶችና ሞግዚቶች ጨቅላና የጤና እክል ያለባቸውን ሕፃናት በመንከባከብ ስራ ተጠምደዋል፤ ሌሎች የሕፃናቱን ልብስ ያጥባሉ፤ ያጣጥፋሉ፡፡ ከወደ ማዕድ ቤቱ በር ስር ደግሞ እድሜያቸው በግምት 14 ዓመት የሚሆኑ ሁለት ልጃገረዶች አቀርቅረው ምስር ይለቅማሉ፤ እየለቀሙም በለሆሳስ የሆድ የሆዳቸውን ያወጋሉ፡፡
የወጥ ቤቷ እመቤትም ከረዳቶቿ ጋር በመሆን የልጆቹ የመመገቢያ ሰዓት ከመድረሱ በፊት ምግባቸውን ለማድረስ በሚመስል ሁኔታ ጉድ ጉዷን ተያይዛዋለች፡፡ ይህ ሁሉ ማራኪና ቤተሰባዊ ትዕይንት ታዲያ በሩህሩህ እናቶች የታጀበውና በጎ ፈቃደኞች የሚመራው የስለ እናት በጎአድራጎት ድርጅት የዘወትር እንቅስቃሴ ነው፡፡
በማሳደጊያው ድጋፍ ለቁምነገር ከበቁ አምስት ሺ ወላጅ አልባ ሕፃናት መካከል መሃሪ ጉተማ አንዱ ነው፡፡ በሃያዎቹ እድሜ መጀመሪያ ላይ የሚገኘው ይህ ወጣት የተወለደው በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ቢሾፍቱ ከተማ ሲሆን፣ በስምንት ዓመቱ ወላጆቹን በሞት ሲያጣ ነው ከታላቅ ወንድሙ ጋር ማሳደጊያውን የተቀላቀለው፡፡
በ11 ዓመቱ የማሳደጊያው ቆይታ ሲያበቃ አሳዳጊ ቤተሰቦች አግኝቶ ወደ ውጭ የመሄድ እድል ገጥሞትም ነበር፡፡ ይሁንና አጎቱ ኃላፊነት ወስደው ሊፈርሙለት ባለመቻላቸው ጉዞው ተሰናከለ፡፡ በመሆኑም ወደ ሁለተኛውና ግሩፕ ሆም ወደተባለው የተቋሙ የማሳደጊያ መርሃ ግብር በመግባት እሱና ወንድሙ ከሌሎች ታዳጊዎች ጋር በመሆን አብረው ወደ ሚኖሩበት ቤት አቀና፡፡
በዚያም ሁሉም ነገር ተሟልቶለትና አሳዳጊ እናት ተመድቦለት እስከ 10ኛ ክፍል ደረሰ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በዓለምአቀፍ በጎአድራጊዎች ድጋፍ የስነ-ስዕል ስልጠና የወሰደ ሲሆን፣ በሂደት ለጥበቡ ልዩ ፍቅር እያደረበትና ችሎታውን እያዳበረ መጣ፡፡ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ገብቶም በሳይኮሎጂ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ወደተቋሙ ተመልሶ እንደ እናት ተንከባኮቦ ያሳደገውን ተቋም መልሶ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡
ይህ ተቋም የተመሰረተው በ1994 ዓ.ም ወይዘሮ ሃና ብርሃኑ በተባሉ በጎ አድራጊ እናት አማካኝነት ነው። በወቅቱ ግለሰቧ ጥቁር አምበሳ ሆስፒታል በማኅበራዊ ጉዳይ አገልግሎት ዘርፍ ይሰሩ ስለነበር በኤች.አይ.ቪ ቫይረስ የተያዙ ወላጆች ልጆቻችን ጥለው ሲሞቱ የነበረውን አሳዛኝ ሁኔታ በእየለቱ ይመለከታሉ፡፡ በዚህ ችግር ምክንያት አሳዳጊ የሌላቸውን ሕፃናት ወደ ጎዳና ሲወጡ መመልከቱ ልባቸውን በእጅጉ ነካው፡፡
አንድ ቀን ግን “ዝም ብሎ ከመመልከት ይልቅ ለምን የበኩሌን አስተዋፅኦ አላበረክትም?” የሚል ጥያቄ ለራሳቸው ያነሳሉ፡፡ ለተወሰኑ ጓደኞቻቸውን ጉዳዩን ሲጫውቷቸው ቀና ምላሽ አገኙ፡፡ እናም ቤት ፈለጉና ስለእናት የተባለች አንዲት ጨቅላ ሕፃን ከጎዳና ላይ ማሳደግ ጀመሩ፡፡ በዚህች ሕፃን አማካኝነት የበጎ አድራጎት ሥራቸውን አሃዱ ብለው የጀመሩት እኚህ እናት፣ የድርጅቱንም ስም ለልጅቷም ማስታወሻ ምግባሩም እንደእናት ይሆናል በሚል “ስለእናት” አሉት፡፡
ወይዘሮ ሃና በርካታ ችግረኛና ወላጅ አልባ ሕፃናትን ከጎዳና እያነሱ፤ እንዲሁም በያሉበት ቤት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ አስተምረው ለወግ ማዕረግ አብቅተዋል። በብዙ ውጣ ውረድ ሆነው ለዘጠኝ ዓመት ከመሩ በኋላ በወቅቱ በነበረባቸው ቤተሰባዊ ጫና ምክንያት ተቋሙን ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል የሚል ውሳኔ ላይ ደረሱ፡፡ እናም ራዕያቸውን የሚጋራና በጎ ትውልድ የመገንባት ህልም ሰንቆ በራሱ መንገድ ጥረት ሲያደርግ ለነበረው ወጣት ያሬድ አብዱ አስተላለፉ፡፡ ያሬድም የእኚህን እናት አደራና እምነት በከንቱ አላስቀረም፤ ራዕያቸውንም ሆነ ድርጅቱን ተረክቦ ላለፉት 21 ዓመታት በስኬት ጎዳና እየመራ ቆየ፡፡
የድርጅቱ ዋና ስራአስኪያጅ ያሬድ አብዱ ተቋሙን በኃላፊነት ተረክቦ ለመስራት ጥያቄያቸውን የተቀበለው የእሱም የልጅነት ራዕዩ ስለነበር እንደሆነ ያነሳል፡፡ ይሁንና ዋና ምክንያት የሆኑት ግን በኤች አይ ቪ ኤድስ ወላጆቻቸውን ያጡ ያጎቱ ልጆች እንደሆኑ ይጠቅሳል። ‹‹በጎነትን የተማርኩት ከእናቴ ነው፤ አራት የአጎቴን ልጆች የሙት አደራ ተቀብላ ለማሳደግ ሞክራለች፤ ይሁንና ከራሷ ልጆች ጋር ተዳምሮ አቅም ቢፈትናት በእኛ ወትዋችነት ለማሳደጊያ ለመስጠት ተገደደች፤ ያ አጋጣሚ ነው፤ እኔም ወደፊት እንደ አጎቴ ልጆች ወላጅ ያጡ ሕፃናትን ሕይወት መታደግ አለብኝ የሚል ውሳኔ ላይ ያደረሰኝ›› ሲል ያብራራል።
እንደ እድል ሆኖ የሚሰራበትም ዓለምአቀፍ የበጎአድራጎት ድርጅት ስለነበርና በልቡ ለዘመናት ያቆየው ሕልሙን እውን ለማድረግ በግሉ በሚጣጣርበት ወቅት ከወይዘሮ ሃና ጋር ተቀራረበና እቅዱ እንደ ሰመረለት ይናገራል፡፡
ለላፉት 12 ዓመታት ተቋሙን በመምራት ላይ የሚገኘው አቶ ያሬድ በተቋሙ የሚያድጉ ሕፃናት ቁጥር ከመጨመር በዘለለ መሰረታዊ ፍላጎታቸው እንዲሟላ፤ ከሁሉም በላይ ተቋማዊ ቅርፅ ከመያዝ ይልቅ ማኅበረሰቡን መስለውና ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው እንዲያድጉ ጥረት ይደረጋል፡፡ በተለይም ከተቋሙ ሲወጡ የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች በብቃት መወጣት ይችሉ ዘንድ ከ11 ዓመት በኋላ ሁሉም ወጪያቸውን በመሸፈንና ቤት በመከራየት እንዲሁም የምታሳድጋቸው እናት በመመደብ የሚያድጉበትን ስርዓት ማዘጋጀቱን ይገልጻል፡፡
እንደዋና ስራ አስኪያጁ ማብራሪያ፤ ስለእናት በተለያዩ የሕፃናት እንክብካቤ አማራጮች ሁሉ የሚሰራ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ሕፃናቱ በቤተሰባቸው ውስጥ እያሉ ወጪያቸውን በመሸፈን፤ በተለያየ ምክንያት ከቤተሰባቸው የጠፉ ሕፃናትን በማቀላለቀል ከኅብረተሰቡ ጋር እንዲኖሩ ማድረግ፤ የሕፃናቱ ቤተሰቦች ራሳቸውን እንዲችሉና ልጆቻቸውን እንዲረዱ መልሶ ማቋቋም፤ ሕፃናት የጉዲፈቻ ቤተሰብ እንዲያገኙ ማድረግ፤ አማራጭ ሲጠፋና ሌሎች እድሎች እስኪገኙ ድረስ በተቋም ውስጥ አስፈላጊውን ድጋፍና እንክብካቤ የማድረግ ሥራ ይሰራል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሺ 560 በላይ ሕፃናት እንደሚደግፍ ጠቅሶ፣ ከእነዚህ ውስጥ ከአንድ ሺ 300 በላይ የሚሆኑት በውጭ ሆነው የትምህርት ቤት ወጪያቸው የሚሸፈንላቸው መሆኑን ያስረዳል። በተቋሙ ውስጥ ሆነው የሚያድጉት ደግሞ 59 መሆናቸውን ገልጾ፣ ከእነዚህ ውስጥ ከፊሉ የአዕምሮ እድገት ውስንነት እንዳለባቸው ነው የጠቆመው፡፡
‹‹ይህ ተቋም ጊዚያዊ ማረፊያቸው እንጂ የዘላለም መኖሪያቸው እንዲሆን አይፈልግም›› የሚለው አቶ ያሬድ፣ ይልቁንም ትክክለኛ ትውልድ ማፍራት ይቻል ዘንድ ከተቋማዊ አስተሳሰብ የተላቀቀ፤ ማኅብረሰቡን መስሎና ወዶ የሚኖር፤ በውጣ ውረዶች የማይፈተን ጠንካራ ትውልድ እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግም ያብራራል። ‹‹በተቋሙ ከሁሉም በላይ ትኩረት የሚሰጠው ሕፃናቱን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው በመኖር ማኅበራዊ ሕይወት ኖሯቸው፤ ተግዳሮትን በራሳቸው መጋፈጥ የሚችል አቅም አዳብረው እንዲያድጉ ማድረግ ላይ ነው›› ይላል፡፡
እንደ ስለእናት በመሰሉ ተቋማት ትክክለኛ ሃገር ተረካቢ ትውልድ ማፍራት የሚቻለውም ሕፃናቱ የመጡበትን መንገድ በማየትና የቱ አማራጭ ለእነሱ ይሻላል? ብሎ በመለየት ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣውን መምረጥ ሲቻል እንደሆነም ያስረዳል። በዚህ ረገድ እሱ የሚመራው ይህ ተቋም ከሌሎቹ በተለየ ጤነኞቹን ብቻ ሳይሆን ከተለያየ አይነት ሕመም ጋር የሚኖሩትንም አብሮ የሚያሳድግ እንደመሆኑ ለእያንዳንዱ ልጅ እንደየእድሜውና የጤና ሁኔታው የሚበጀውን የድጋፍ አማራጭ በመለየት እንደሚሰራ ነው ያስታወቀው፡፡
‹‹አቅም እስካለ ድረስ የተሻለ ነገር ማበርከት እንችላለን ብለን እናምናለን፤ መርዳት ስለሚለው ሃሳብ ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው እንፈልጋለን›› የሚለው አቶ ያሬድ፣ በዚህ ረገድም ትልቅ ኃላፊነት ያለባቸው የመንግስት ተቋማት በሚገባቸው ልክ እያገዙ አለመሆኑን አስታውቋል፡፡ በተለይ የእነሱ ድርጅትም ሆነ ሌላው የሚሰራውን በጎ ስራ በመረዳት ውስብስብ አሰራሮችንና ቢሮክራሲዎችን በማስቀረት ረገድ ድጋፍ ሊያድርጉልን ይገባል የሚል እምነት አለው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ያጋጠመውን ችግር አብነት ሲጠቅስም ‹‹በጉዲፈቻ ወደ ውጭ የሄዱ ሕፃናት አዋጥተው እዚህ ላሉት ሕፃናት ሁለት ዊልቸርና ከ50 በላይ ካርቶን የሚሆን የተለያየ ችግር ላለባቸው ሕፃናት የሚውል የአዋቂዎች ዳይፐር ልከውልን ነበር፤ ይሁንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢተባበረንም ጉምሩክ በነፃ ሊያስገባልን ባለመቻሉ ምክንያት ብዙ መንገላታት እየደረሰብን ነው›› ሲል ያመለክታል፡፡
በተለይ ዳይፐሩ ገንዘቡም ቢኖርም እንኳን እዚህ ሃገር እንደልብ የማይገኝ በመሆኑ እጅግ እየተንገላታን ስለመሆኑ አስታውቋል፡፡ በተመሳሳይ በርካታ ተቋማት ከአንድ ብር ጀምሮ ድጋፍ የሚያደርጉበት፤ ስምና ዝናቸውን በመያዝ ሥራቸውን ማስተዋወቅ የሚችሉበት እድል እንዲፈጥሩላቸው ጠይቋል፡፡
‹‹በተለይም የመንግስት ተቋማት ኃላፊዎች ስለእናትን እንዲጎበኙና ስራውን ተረድተው እገዛ እንዲያደርጉለትም ጥሪ አቀርባለሁ›› ያለው አቶ ያሬድ፣ በተመሳሳይ የሚዲያ ተቋማት ድልድይ በመሆን ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝቧል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ብዙ የግል ተቋማት መስጠት ቢፈልጉም አስገዳጅ ሕግና ደንብ ባለመኖሩ ምክንያት ከድጋፍ የሚታቀቡበት ሁኔታ መኖሩን ዋና ስራአስኪያጁ አመልክቷል፡፡ ‹‹ከትርፍ ላይ የተወሰነ በመቶኛ ለማኅበራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስገድድ ሕግ ቢኖር የበርካታ ሕፃናትን ሕይወት መታደግ ይቻላል›› ሲልም ይገልጻል፡፡
‹‹እንደ ማኅብረሰብ እኛ ኃላፊነታችንን እየተወጣን ነው፤ ያገባናል ብለን በርካታ ችግረኛ ሕፃናትን እየረዳን ነው፤ ከችግሩ ስፋት አንፃር እንደኛ ያሉ ተቋማት ብቻቸውን የሚወጡት አይሆንም›› ይላል፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮቴሌኮም ያሉ ትልልቅ ተቋማት የድጋፍ እቅዳቸውን ከባዕላት ባለፈ ቀጣይነት ያለው፤ የሚታይና የሚዳረስ ስርዓት ቢያበጁለት መልካም ባይም ነው፡፡
ወይዘሮ እመቤት ክብረት ልጆቻቸው በድርጅቱ ድጋፍ ከሚያገኙ ወላጆች አንዷ ናቸው፡፡ ባለቤታቸው የልብ ሕመምተኛ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የማይሰሩ በመሆናቸው ልጆቻቸውን ለማስተማርም ሆነ ለማሳደግ እንደሚቸገሩ ይናገራሉ፡፡ ችግራቸውን ያየ የቀበሌያቸው አመራርም ከስለእናት በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር እንዳገናኛቸው ይጠቅሳሉ፡፡ ድርጅቱ በየዓመቱ ለትምህርት የሚያስፈልገውን ወጪ የሚሸፍንላቸው ሲሆን፣ በየወሩም አራት መቶ ብር ድጎማ እንደሚያደርግላቸው ነው ያስታወቁት፡፡
ሌላዋ እናት ወይዘሮ ታደለች አየለም ሴት ልጃቸውን የሚያስተምርላቸው ይኸው ድርጅት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እሳቸው የአስም በሽተኛ በመሆናቸው እንደልባቸው መስራት አይችሉም፤ ባለቤታቸውም በሕይወት የሉም፤ በእዚህ ሁሉ የተነሳም ከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቀው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በድርጅቱ ድጋፍ ማግኘት ከጀመሩ ወዲህ ግን በተለይ ስለ ልጃቸው የትምህርት ወጪ እንደማይጨነቁ ያስረዳሉ።
እንደ እሳቸው በበሽታ ውስጥ ሆነው ብቻቸውን ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ወላጆች ድጋፍ በማጣታቸው ሳቢያ ልጆቸውም ሆነ እነሱ ወደጎዳና የሚወጡበት አጋጣሚ መኖሩን ጠቅሰውም ሌሎች አቅሙ ያላቸው ግለሰቦች እንደ ስለእናት ያሉ በጎ አድራጊ ድርጅቶችን በመደገፍ የሃገርን ሸክም እንዲያቃልሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ጥር 24/2016