የአባጁፋር መናገሻ የሆነችው ታሪካዊቷ የጅማ ከተማ፤ ኢትዮጵያ በስተምዕራብ አሉኝ ከምትላቸው ከተሞች ዋናዋ እና ደማቋ ናት። ከተማዋ ከመንግስት ስርዓት መለዋወጥ ጋር ተያይዞ አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀዝቀዝ ብላ የከራረመች መሆኗ ይታወቃል። እንዲያም ሆኖ ታሪካዊት ከተማ መሆኗ ሊሸፈን የማይችል እውነታ በመሆኑ ዛሬም ድረስ ጅማ ከተማ ስትጠቀስ ቤተ መንግስታቸውን ከከተማዋ አናት ላይ የገነቡት ንጉስ አባ ጁፋርም አብረው መነሳታቸው አይቀሬ ሆኖ ቀጥሏል።
ከቅርብ ዓመት ጀምሮ ደግሞ የጅማን የቀድሞ ታላቅነት ለመመለስ በብዙ ሲሰራ ቆይቷል። አቧራዋም ተራግፎ ድምቀቷ መታየት ጀምሯል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከተማዋ እዚህ ለመድረስና በቀጣይ እየተሰሩ ስላሉ እንቅስቃሴዋን አስመልክቶ አዲስ ዘመን የከተማዋን ከንቲባ አቶ ነጂብ አባራያ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅሮ አቅርቧል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- ጅማ ከተማ በአሁኑ ወቅት ያለችበት ሁኔታ እንዴት ይገለጻል? ባለፉት ስድስት ወራት የተሰሩ አንኳር ሰራዎችስ ምን ምን ናቸው?
አቶ ነጂብ፡- ጅማ ጥንታዊ ከተሞች ከሚባሉት መካከል አንዷ ነች። በኢትዮጵያ ቀድመው ከተመሰረቱት መካከል አዲስ አበባ፣ አስመራ፣ ጅማ እንዲሁም ድሬዳዋ እንደነበሩ ይታወቃል። እነዚህ አራቱ ቀድመው በመመስረት ኢትዮጵያን የመሰረቱ ከተሞች ነበሩ። ከዚህ ጋር ተያይዞ የጅማ ስም ይነሳል። ስሟ መነሳቱ ብቻ ሳይሆን ጅማ ቀድማ የተነቃቃች በእርግጥም ተመራጭ ከተማ ተብላ የምትወሰድ በምዕራብ ኢትዮጵያ የምትገኝ ከተማ ነበረች።
በመሃል ግን በተወሰነ መልኩ የመዳከም እንዲሁም ወደኋላ የመመለስ ነገር ታይቶባት ቆይቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ “ጅማን ወደነበረ ስሟ እንመልሳት” የሚል እቅድ ያዝን፤ ለዚያ ደግሞ በመጀመሪያ ጅማ ምን አላት? የሚለውን ፈተሽን። በመጀመሪያ የተረዳነው ነገር ቢኖር ጅማ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ከተማ መሆኗን ነው። ለምሳሌ ያህል ጅማ፣ በመሃላቸው ወንዞች አቋርጠዋቸው ከሚያልፍባቸው ጥቂት ከተማዎች አንዷ ናት። በአብነት የሚጠቀሰው አዌቱ ወንዝ ወደ 12 ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያህል ከተማዋን አቋርጦ የሚያልፍ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች ትንንሾች ወንዞች ያሉ ሲሆን፣ አንደኛው ኪቶ የሚባል ወንዝ ነው። ትንንሾቹ ወንዞች ከአዌቱ ወንዝ ጋር ተገናኝተው የግቤ ገባር ይሆናሉ፤ ግቤ ቁጥር አንድ ጅማ ከተማን ነክቶ የሚያልፍ ነው። ወንዞቹ ከግቤ ጋር ሲገናኙ ሐይቅ መፍጠር ቻሉ። እንደሚታወቀው ጅማ በተራራዎች የተከበበች ከተማ ናት። ተራራዋም ደን የለበሰ ነው። ከዚህ የተነሳ በተፈጥሮ የታደለች፣ ለምለምና አረንጓዴ ከተማ ናት።
ይህች በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ከተማ፣ ወንዞቿ ክረምት ክረምት ስለሚሞሉ ሕዝቧን ያፈናቅሉ ነበር። ሌሎችም መሰል ችግሮች ይታያሉ። ከዚህ የተነሳ የሕዝብን ችግር እንፍታ በሚል ወንዙ ሞልቶ ሕዝቡን እንዳያፈናቅል እና ንብረት እንዳይጎዳ የማድረግ ስራ ያዝን። “የሚያጋጠመውን ችግር ወደ እድል መቀየር” በሚለው የጠቅላይ ሚኒስትራችን መርህ መነሻነት አካባቢን ለማስዋብ ተነሳስተን ወደስራ ገባን። ከተማችንን መዝናኛ እና ምቹ ለምን አናደርገውም? በሚል ተነሳሽነቱን ፈጠርን። ይህ በመሆኑም የወንዝ ዳርቻ ልማት ላይ ተሰማራን። በአሁኑ ወቅት ወደ አራት ኪሎ ሜትር ገደማ ወንዙ የሚሄድበትን መንገድ ከሶስት ሜትር ወደ 20 ሜትር ማስፋት ቻልን። በአካባቢው የነበሩ ቤቶች እንዲነሱ በማድረግ የእግረኛ መንገድ እንዲሰራ እና አበባ እንዲተከል በማድረግ ለደከመው ማረፊያ እንዲሁም ማንበቢያ እንዲሆን ማድረግ ቻልን። የተለያዩ መዝናኛ ቦታዎችም ለመገንባት በቃን።
ከተማዋ የምትታወቅበት አዌቱ መናፈሻ አለ። ሌላው ደግሞ የወጣቶች ማዕከል ነው። እነዚህ ሁለቱ ሕዝብ የሚገለገልባቸው ሲሆን፣ በመሃላቸው ትልቅ መንገድ አለ። በአካባቢው ሕዝብ መተላለፍ ያስችለው ዘንድ ድልድይ እንዲሰራ የተደረገ ሲሆን፣ ድልድዩም ጅማ በሚታወቅበት የበርጩማ ቅርጽ እንዲይዝ ተደርጎ የተገነባ ነው። ስራው ገና ያላለቀ ሲሆን፣ የሚገነባውም ከከተማዋ ከምንሰበስበው ገቢ ነው።
በአሁኑ ወቅት ምዕራፍ አንድና ሁለትን ጨርሰን ወደምዕራፍ ሶስት የተሸጋገርን ሲሆን፣ በ2017 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ይታሰባል። ከእሱ ጎን ለጎን በከተማ ፓርክ ላይ እየሰራነው ያለው ስራ ተጠቃሽ ነው። ወደ 12 ነጥብ አምስት ሔክታር ስፋት ያለው በውስጡ የህጻናት ማዋያ፣ የባህል ማዕከል፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ሬስቶራንትና ሌሎች ነገሮች የሚኖሩት ይሆናል። ይህም በአሁኑ ሰዓት በጥሩ ሁኔታ እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ስድስት ወራት ከሰራችኋቸው ስራዎች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት የትኞቹ ናቸው ? ለምን ያህሉስ ወጣት የስራ እድል ማመቻቸት ተቻለ?
አቶ ነጂብ፡– የሰራነው የወንዝ ዳርቻ ልማት ነው፤ ከተማዋ ንጹህ፣ ጽዱ፣ አረንጓዴና ውብ እንዲሁ ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትሆን በማድረግ ረገድ እየተሰሩ ካሉ ስራዎች አንዱ እና ዋነኛው ይኸው የወንዝ ዳርቻና የፓርክ ስራ ነው። በሁለተኛ ደረጃ መሰረተ ልማት ነው። በጅማ ከተማ ያለው አስፓልት መንገድ ወደአፈርነት ለመቀየር የዳዳው ነው። ስለዚህ ጅማ ከተማ መሰረተ ልማት እንደማንኛውም ከተማ ይፈልጋል። ስለዚህ ያረጃውን መሰረተ ልማት የማደስ ስራ እየሰራን ነው። በጣም የቆየ እና ወደአፈርነት የተለወጠውን የአስፓልት መንገድ እንደገና ጠርገን አንድ ኪሎ ሜትር አካባቢ እንደአዲስ ሰርተናል። ሁለት ቀበሌዎችን የሚያያይዝ ወደ አምስት ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድም ሰርተናል።
ሌላው የነበሩ መንገዶችን ማስፋፋት ነው። በየመንገዱ ዳርዳር በሼድና በፕላስቲክ ተሸፍኖ የነበረውን አንስተን ወደ አራት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው፤ በሁለቱም በኩል አምስት አምስት ሜትር ስፋት ያለው መንገድ ሰርተናል። ይህም ወደ 30 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበት በዚህ ዓመት እና ባለፈው ዓመት የተሰራ ስራ ነው። ሌላው የመብራት ዝርጋታ ሲሆን፣ እሱም በሰፊው እየተኬደበት ይገኛል። የውሃ ዝርጋታም በተመሳሳይ እየሰራን ነን።
የአስፓልት መንገዱ ወደ 400 ሚሊዮን ብር ገደማ የፈጀ ነው። የዚህ ወጪ ምንጩ የከተማ ገቢ ነው። የወንዝ ዳርቻ ልማቱም እንዲሁ እየተሰራ ያለው በከተማ ገቢ ነው። ይህም ወደ 200 ሚሊዮን ገደማ የፈጀ ሲሆን፣ ይህም በየዓመቱ 40 ሚሊዮን ብር፣ 50 ሚሊዮን ብር እየተባለ 200 ሚሊዮን ብር ላይ የተደረሰ ነው። ይህም ወደ ሶስት ዓመት ገደማ የወሰደ ተግባር ነው። የወንዝ ዳርቻ ልማት ያለው በዚህ ደረጃ ነው። ፓርኪንጉም እንዲሁ ወደ 50 ሚሊዮን ብር ያህል ወጪ ወጥቶበት እየሰራን ነው። አራት ኪሎ መንገዱ ደግሞ ወደ 30 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎ እየተሰራ ነው።
ሌላው የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አኳያ ተነሳሽነቱ በክልል ደረጃ ተቀርጾ ወርዷል። ለምሳሌ ዶሮ እርባታ ላይ በሰፊው እንዲሰራና ክላስተሮችም እየተገነቡ ሲሆን፣ በተያዘው እቅድም ወደ 300 ክላስተር ገንብተን አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶሮዎች ወደዚህ ከተማ ለማስገባት ነው። በአሁኑ ወቅት ወደ 400 ሺ ዶሮዎች መያዝ የሚችል ሼዶች አስገንብተናል።
ሌላው የወተት ልማት ነው። ወደ 67 ክላስተር ተገንብቶ ወደ አንድ ሺ 500 የሚሆኑ ምርጥ ዘር ላሞች መግባት ችለዋል። እያንዳንዱ ሼድ ለ20 ወጣቶች የስራ እድል ይፈጥራል። ወደ ስምንት ሺ የሚሆኑ ከብቶችን አደልቦ ለገበያ የሚያበቃ ማደለቢያም አለ። የፍራፍሬ ክላስተርም በሰፊው እየተሰራበት ሲሆን፣ ንብ እርባታም አለ፤ አጠቃላይ 518 ክላስተር በከተማችን ላይ መሰራት አለበት ተብሎ ከተሰጠን ወደ 340 የሚሆን ክላስተር መስራት ተ ችሏል። ስ ራም ጀምረናል።
በዚህ ዓመት 28 ሺ ወጣቶችን ወደስራ ማስገባት አለባችሁ ተብሎ በስድስት ወር ውስጥ ወደ 20 ሺ ገደማ ወጣት ወደስራ ማስገባት ችለናል። ብዙዎቹ የምንሰራቸው ስራዎች ለወጣቶች ሲሆን፣ በዚህ ውስጥ ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው የሚችል ሁሉት ነገር አለ። አንደኛው የኑሮ ውድነትን መቋቋም የሚያስችል ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለወጣቱ የስራ እድል መፍጠር ነው።
በሌላ በኩል እንደፌዴራል ተይዞ እየተሰራበት ያለ “ብቃት” የሚል ፕሮግራም አለ። በሱ ፕሮግራም አንድ ሺ ያህል ወጣት እንዲሰለጥኑ ይደረጋል። ከስልጠና በኋላ ከባለሀብቶች ጋር ይጣመራሉ። ከእነርሱም ጋር ወደ ስድስት ወር ያሀል እንዲቆዩ ይደረጋል። ከዚያም ራሳቸውን ችለው እንዲወጡ ይደረጋል። “ብቃት” በሚል ፕሮግራም በጎንደር፣ ሐዋሳ እና ጅማ በአብነት ተይዘው እየተሰራባቸው ያሉ ከተሞች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- የከተማዋ ገቢ አሰባሰብ ምን ይመስላል?
አቶ ነጂብ፡- ከተማችን ቀደም ሲል ገቢ አሰባሰቡ ላይ በጣም ደካማ ነበር። የከተማችን ገቢ ከሁለት ዓመት በፊት 400 ሚሊዮን ብር ብቻ ነበር። ባለፈው ዓመት አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተቻለ። ዘንድሮ ደግሞ ሶስት ቢሊዮን ብር እናስገባለን ብለን በግማሽ ዓመቱ ወደ አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ችለናል። ፕሮጀክቶችንም ሆነ መሰረተ ልማቶችን እየሰራን ያለነው በምንሰበስበው የከተማ ገቢ ነው።
በአሁኑ ወቅት አመራሩ አካባቢ ያለው ስሜት ቁጭት ነው። ብዙዎቹም ከተማዋን የተሻለ ቦታ ለማድረስ ይታገላሉ። ጅማ ከ100 ዓመት በፊት ተመራጭ የነበረች ከተማ ናት። በመካከል ደግሞ ይህ ሁሉ ቀርቶ ተጎሳቁላ ነበር። እንዲያውም ከተማ ሲያረጅ እንደ ጅማ ተብሎም እንደነበር ይታወሳል። አሁን ያንን የቀደመ ተፈላጊነቷንና በምዕራብ ደቡብ ዋናዋ ከተማ የሚያስብላት ሁኔታን ለመመለስ ተነሳሽነቱ ተፈጥሯል። በመጀመሪያም ያነቃቃትና ተመራጭ ከተማ እንድትሆን ያደረጋት ስርዓት ነው። መልሶም ያዳካማት ስርዓት ነው። አሁንም መልሶ እንድትነቃቃ ያደረጋት ስርዓት ነው። ስለዚህ ጅማን ቀደም ሲል ያዳካማትም ሆነ አሁን ያነቃቃት ስርዓት ነው። በአሁኑ ወቅት እኩልነትን የሚያረጋግጥ፣ ዴሞክራሲን የሚያሰፍን፣ ፌዴራሊዝምን በትክክል የሚተገብር መንግስት ተገኘ። ሕዝቡም በዚህ ደስተኛ ነው። ባለን አቅምና እድል ሰርተን መለወጥ እንችላለን፤ ጫና የለብንም የሚል ግንዛቤ ማኅብረሰቡ ዘንድ ተፈጥሯል።
አዲስ ዘመን፡- የከተማዋ ሰላምና ጸጥታ ምን ይመስላል? ከተማዋ ለኢንቨስትመንት ያላት ምቹ ሁኔታንም አያይዘው ቢገልጹልን?
አቶ ነጂብ፡– የጅማ ሕዝብ ሰላም ወዳድ ነው። የጅማ ከተማ ሰው፣ የኢትዮጵያዊነት እሴትን ተላብሶ የሚኖርባት ናት። ጅማ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያዊነታቸው ብቻ ጸንተው፣ ተዋደውና ተከባብረው በአንድነት የሚኖሩባት ትንሿ ኢትዮጵያ ናት። ሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰብ ያለባትና እርስ በእርስም ተዋድደውና ተከባብረው የሚኖሩባት ከተማ ነች።
አባ ጁፋርም በጊዜያቸው ለሰላም ያላቸው ቦታ ትልቅ ነው። ጠዋት ላይ ከሰዎች ጋር ሲገናኙ ቀኑን የሚጀምሩት “ቡና እና ሰላም አትጡ!” በሚል ነው። እንግዳን ሲቀበሉ፤ “ቡና ጠጡ” ብለው ሲሆን፤ ሲሸኟቸው ደግሞ ቡና ሰጥተዋቸው “ቡና እና ሰላም አይለያችሁ!” ብለው ነው። እሱ አባባላቸው ኅብረተሰቡ ውስጥ ባህል ሆኖ እስከዛሬ መዝለቅ ችሏል።
በዚህ ላይ ደግሞ የኃይማኖት አባቶች ያላቸው ስፍራ ትልቅ ነው። ጸሎታቸውንም ሆነ ዱዓቸውን ሲጀምሩ ሰላም ለሰው ልጅ ዋስትናው መሆኑን ጠንቅቀው በማወቅ ነው። ጸሎታቸውንም ዱዓቸውን የሚያደርጉ የእምነት አባቶች ሲገናኙ የሚሰብኩት አንድነትን ነው። የኦርቶዶክስ፣ የሙስሊም እና የፕሮቴስታንት ኃይማኖት መሪዎች አንድ ፕሮግራም ሲኖረን እንዲመርቁ የሚነሱት አንድ ላይ ነው። አንዱ ከቀረ እንኳ ሌሎቹ መነሳት አይፈልጉም። ምክንያቱም ለሕዝብ ሰላምና አንድነት ወሳኝ መሆኑን ጠንቅቀው ያውቃሉና ነው። ከዚህ የተነሳ ሶስቱም አንድ ላይ ተጠራርተውና ተቃቅፈው ወደ መድረኩ መጥተው የዕለቱ መርሃግብር ሳይጀመር ይመርቃሉ።
በተመሳሳይ የአገር ሽማግሌውም ሆነ ወጣቱ ብሔር ከብሔር ሳይለያዩ ሰላሙን በማስጠበቅ በኩል ሚናቸውን እኩል እየተወጡ ነው። አንዱ ከሌላው አይለይም። ጅማ ከተማ እስካሁን ድረስ ሰላሟ ተጠብቆ እዚህ መድረስ የቻለችው ለዚህም ነው። አሁንም ቢሆን ከተማችን ሰላም ነው ብለን አንዘናጋም፤ ሰላማችንን ለማስጠበቅ አሁንም ሕዝባችንን ይዘን እንቀጥላለን። ከሕዝብ ጋር ስለምንሰራም የሰላሙ ጉዳይ አስተማማኝ ነው ማለት ይቻላል።
እንዲያውም በሌላ አካባቢ ያሉ ሌሎች ከተሞች ከጅማ መማር አለባቸው የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም በጅማ ከተማ ዋና ጉዳዩ በኢትዮጵያዊነት መጸናቱ ነው። በኃይማኖትና በብሔር አለመከፋፈሉ ነው። ሰላም የሁሉም መሰረት ነው ብሎ መውሰዱ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከሁሉም በላይ ለሰላም ትልቅ ቦታ ሰጥቶ መሰራቱ በመቻሉ ነው እላለሁ።
ሰላሙ አስተማማኝ ከመሆኑ የተነሳ ልማቱ እንደቀጠለ ነው። ጅማ እንደሚታወቀው የአየር ጸባዩ ጥሩ የሚባል ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ለኢንዱስትሪ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ የተፈጥሮ ሀብት ያለበት ነው። ማዕድኑ፣ ቡናው እንዲሁም ፍራፍሬው አለ። እነዚህ ለኢንዱስትሪ ግብዓት ሊሆኑ ይችላሉ። ሌላው ደግሞ ስንዴም በቆሎም ይመረታል። ባለሀብቶች ምንም የሚያሰጋቸው ነገር የለም። ጅማ የሰላም ከተማ ነች። ሕዝቡም ሰው ወዳድ ነው። የአገር ውስጡም ሆነ የውጭ ዜጋው ከተማችንን እንደቤቱ እና ቀዬው ማየት ይችላል። ባለሀብቶችን ስንቀበል ልክ የቤታቸው ያህል እንዲሰማቸው በማድረግ ነው። ደግሞም ያሉበት ድረስ ሔደንም እንቀበላቸዋለን እንጂ ተቀምጠን አንጠብቃቸውም። እዚህ ከተማችን መጥተው ስራ የጀመሩትን ደግሞ ለንብረታቸውም ሆነ ለደህንነታቸው ዋስትና ሊሆን የሚችለው ማኅበረሰቡ ራሱ ነው። ስለዚህም ወደከተማችን መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል ላይ ምን ያህል ተሰርቷል? በከተማዋ የተማሪዎች ምገባ መርሃግብርን በተመለከተስ ምን ታስቧል?
አቶ ነጂብ፡- ለትምህርት ጥራት ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ በሚል በመንግስት የተቀመጠ አቅጣጫ አለ። እናም እሱን መሰረት አድርገን እየሰራን ነው። የመጀመሪያው ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲገቡ አድርገናል። ተማሪዎቹ የትምህርት ሒደቱ ምቹ እንዲሆንላቸው የትምህርት ቤት ደረጃ ማሻሻል ስራ ሰርተናል። ይህ በሕዝብም ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ ሲሰራ ነበር። ወደ 30 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ ሆኖ ትምህርት ቤቶች ማሻሻል ላይ ሲሰራ ቆይቷል።
አጠቃላይ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ እና ደረጃ ማሳደግ የወጣው ወጪ ወደ 115 ሚሊዮን ብር ነው። በዚህ ውስጥ እንደእኛ ክልል “ቡዑራ ቦሮ” የሚባል ወይም መዋዕለ ህጻናት ፕሮግራም ብለን የምንሰራው አለ። ይህንን የኦርቶዶክስ ቤተ እምነት 25 ሚሊዮን ወጪ በማድረግ ሰርቶ ሰጥቶናል፤ የሙስሊሙ እና የፕሮቴስታንት ቤተ እምነትቶች እንዲሁ እየሰሩ ነው። ባለሀብቶችም በየስራ ዘርፋቸው ተደራጅተው በመስራታቸው ወደ 19 ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት ተገንብቷል። ትምህርት ቤቶቹ ሻወር እና መጸዳጃ ቤት፣ መጫወቻ እና ማረፊያ ቦታ ያለው ነው። በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ከተማሪ ምገባ ጋር ተያይዞ ወደ 28 ሺ ተማሪዎችን መመገብ አቅደን በአሁኑ ሰዓት በ25 ትምህርት ቤት ውስጥ 26 ሺ ተማሪዎች እየተመገቡ ናቸው። የምገባ ፕሮግራሙ ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል። ባለፈው ዓመት ስንሰራበት ቆይተናል። የተወሰኑ ክፍተቶች ነበሩ፤ እነዚያን ክፍተቶች በዚህ ዓመት አርመን አሁን አንድ ትምህርት ቤት ብቻ ሲቀር ሁሉም ትምህርት ቤት ምገባ ተጀምሯል። ጉዳዩንም በየጊዜው እየተከታተልንና እየገመገምን እንገኛለን። በመጀመሪያ ደረጃ ለምገባ ፕሮግራሙ የሚሆኑ ግብዓቶች በአይነት ተሰብስበው ማከማቻ መጋዘን አስገብተናል።
ሌላው የተማሪ ውጤትን ከማሻሻል ጋር ተያይዞ አመራር እንዲደገፍ በሚል ስራ እየተሰራ ነው፤ እኔ ራሴ አሁን እንድከታተለው የተሰጠኝ ትምህርት ቤት አለኝ። ይህም፣ “አባ ቡና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” የሚባል ሲሆን፣ አንድም ተማሪ ያላሳለፈውን ትምህርት ቤት መያዝ ያለበት ከንቲባው ነው በተባለው መሰረት ይዤያለሁ። ሔጄም እከታተላለሁ፤ ገምግሜዋለሁም። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አነስተኛ ቁጥርን ብቻ ያሳለፈውን ደግሞ እንዲይዝ የተደረገው የፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ነው። እንዲሁም ምክትል ከንቲባ እያለ አምስት ስራ አስፈጻሚዎች አፈጻጸማቸው የወረደ ትምህርት ቤት ይዘው እንዲደግፉ ተደርጎ ስራ ተጀምሯል።
ስራው የሚሰራው ተማሪዎችን በሶስት ደረጃ በመክፈል ነው። ይኸውም ደከም ያሉ፣ መካከለኛ እና ፈጣን የሆኑ ተማሪዎች በሚል እንዲለዩ ይደረጋል። ተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን መምህራንንም ለየናቸው። በጣም ፈጣን የሆኑ መምህራንን ለብቻ አደረግን፤ መካከለኛ የሆኑትን ደግሞ እንዲሁ ለብቻ ከለየን በኋላ መምህራኑ እርስ በእርስ እንዲደጋገፉ አደረግን። በተለይም ጥሩ ውጤት ለማምጣት የሚችሉበትን ሁኔታ እንዲፈጥሩ አመቻቸን። ይህን ካመቻቸን በኋላ ትንሽ ደከም ያሉ ተማሪዎች ተጨማሪ ሰዓት ተሰጥቷቸው እንዲደገፉ፤ በተመሳሳይ መካከለኛ የሆኑትም ድጋፍ እንዲያገኙ፤ ፈጣኖቹ ደግሞ ይበልጥ እንዲጠናከሩ የተለያዩ የመማሪያ ግብዓት እንዲሰጣቸው አደረግን።
በሌላ ደረጃ ደግሞ 12ኛ፣ 8ኛ እና 6ኛ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎች አገር አቀፍ ፈተና ወሳጆች በመሆናቸው የተለየ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ሁኔታዎችን ማመቻቸት ጀመርን፤ በተለይ ለ12ኛ ክፍል በተለየ መልክ ቤተ መጽሐፍት እንዲመቻችላቸው፣ ሌሎች አስፈላጊ መጽሐፍት እንዲዘጋጅላቸው እና የቀደመው የሰባት ዓመት ዎርክሺት (አገር አቀፍ የፈተና ጥያቄዎች) እንዲቀርብላቸውና ጥያቄዎችን በመስራት ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ የማድረግ ስራ ነው፤ መምህራን ደግሞ ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ፤ የጠዋት ፈረቃ ከሆኑ ከሰዓት አሊያም ማታ ላይ ፕሮግራም ተይዞላቸው በደንብ እንዲሰራ አቅጣጫ አስቀመጥን።
ለምሳሌ እኔ ያለሁበት ትምህርት ቤት ሁለተኛ ደረጃ ነው፤ 12ኛ ክፍል በተለየ መልክ እንዲደገፉ 9ኛ፣ 10ኛ እና 11ኛ ደግሞ ዝቅተኛ፣ መካከለኛ እና ፈጣን ተማሪዎች ለየብቻ እየተደገፉ ወደፊት ለፊት የሚመጡበትን ሁኔታ ፈጥረን በየጊዜው እየገመገምን እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- በጅማ ከተማ ባለፉት ስድስት ወራት የተገኙ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ካሉ ቢጠቅሱልን?
አቶ ነጂብ፡– ከኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል ጅማ ላይ ትንሽ የመቀዛቀዝ ሁኔታ ታይቶ ነበር። ይሁንና ለማነቃቃት የሰራነው ስራ አለ። ካለፈው ዓመት እስካሁኑ ሰዓት ድረስ 120 የሚሆኑ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ለማሳያ ሆቴል፣ ሪል ስቴት፣ ማኑፋክቸሪንግ እና በተለያየ የስራ ዘርፍ ላይ የተሳተፉ አሉ። እነርሱም የአስራ አምስት ቢሊዮን ብር ካፒታል አስመዝግበው በከተማ ደረጃ መሬት ተለይቶ መሟላት ያለባቸው ነገሮች ታይተው የኢንቨስትመንት ኮሚቴው እንዲወስን ተደርጓል። ይህም በክልሉ የኢንቨስትመንት ቦርድ ይመራል። ከቦርዱ ጸድቆ የተመለሰው ወደ 120 ፕሮጀክት ነው። ከእነዚያ ውስጥ ወደ 94ቱ ወደስራ አስገብተናቸዋል።
ከእነዛ ውስጥ ደግሞ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ያላቸው አሉ። ለምሳሌ ኃይሌ ሪዞርት ግንባታውን በስምንት ወር ውስጥ ሊጨርስ ደርሷል። ወደ 120 መኝታ ክፍል ያለውን ሪዞርት በአሁኑ ወቅት አጠናቅቆ ቀለም በመቀባት ላይ ነው። ሴንትራል ሆቴልም ደረጃውን ወደ አምስት ኮከብ ለማሳደግ በአራትና አምስት ወራት ውስጥ የመጨረሻውን የቆርቆሮ ክዳን በማልበስ ላይ ይገኛል። ከእነዚህ ሌላ ደግሞ አጠናቅቀው ስራ የጀመሩም አሉ። ለምሳሌ ኮፊ ፕሮሰሲንግን ኤልያስ ጀበል የሚባል ባለሀብት በአራት ወራት ውስጥ ግንባታውን አጠናቅቆ፣ ማሽን ከቻይና አስገብቶ ቡናውን አንድ ጊዜ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ችሏል። ለውጭ ገበያ ያቀረበውም ወደ ሶስት ሺ ኩንታል ቡና ገደማ ነው። አሁን አሁን ከበፊቱ የተሻለ ነገር እያየን ነው። ከዚህ የተነሳ በአሁኑ ወቅት መነቃቃት አለ ማለት ይቻላል። ይህ ሁሉ የሆነው በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ውስጥ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከተማዋ ለኢንቨስትመንት ምን አይነት ምቹ ሁኔታን ፈጥራለች? ምንስ አማራጮች አሏት?
አቶ ነጂብ፡- ለምሳሌ መሬት ለከተማ ግብርና፣ በተመሳሳይ ለሆቴል ኢንዱስትሪ አዘጋጅተናል። እንዲሁም ለኢንዱስትሪም የተዘጋጀ መሬት አለ። በማኑፋክቸሪንግ እና በኮፊ ፕሮሰሲንግ እንዲሁም ማርን ፕሮሰስ ለሚያደርጉ እና ከአቡካዶ ዘይት ለሚጨምቁ፣ ከፍራፍሬም እንዲሁ የተለያየ ነገር ለሚያዘጋጁ፤ ስንዴው ላይ አለ፤ ከዚህ በተጨማሪ ማዕድናትም አሉ። ለእነዚህና ለመሰል ኢንቨስትመንት መሬት አዘጋጅተናል። ለዚህ ያዘጋጀነው መሬት ከ200 ሔክታር መሬት በላይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከከተማዋ ጋር በቅንጅት እየሰራ ያለው ስራ ይኖር ይሆን?
አቶ ነጂብ፡- ጅማ ዩኒቨርሲቲ ትልቅ ተቋም ነው። በከተማችን የሚሰራውን የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት ከዲዛይን ጀምሮ እስከ መስከ ምልከታ እና ክትትል ድረስ ያለው ከእኛ ጋር ነው። ሌላው ከከተማ ግብርና ጋር ተያይዞ ጥናት ከማድረግ እስከ ቦታ መረጣ ድረስ አብረውን እየሰሩ ነው። ለከብት እና ለዶሮ ርባታ ቦታው መሆን ያለበት የቱ ነው? ከሚለው ጀምሮ የቤቱ ግንባታ ድረስ ምን አይነት መሆን አለበት? የሚለውን ጭምር በጉዳዩ ገብተው ጥናት ያደርጉልናል።
ሌላው ቀርቶ እንስሳቱ የሚገዙበት ድረስ በመሄድና ስለጉዳዩ በማጥናት እንዲሁም አይነቱን በመለየት ተገቢውን መረጃ በመስጠት አብረውን እየሰሩ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ስልጠና ይሰጣሉ፤ ድጋፍም ያደርጋሉ። የተሰሩ ፕሮጀክቶችን ከማማከር ጀምሮ አፈጻጸሙንም በመከታተልና ክፍተቶችን ለይተው በመጠቆም አብረውን አሉ። በጥቅሉ በሁሉም አቅጣጫ በከተማው ልማት ውስጥ ተሳትፎ እያደረጉ ነው። እንዲህ ስል ክፍተቶች የሉም ማለት አይደለም። ያለው ስራ በዚህ ደረጃ የሚገለጽ ከሆነ ክፍተቶች ሲፈጠሩም እየሄድን ያለነው በጋራ እያየንና እየፈታን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሱማሊላንድ ጋር በባህር በር ዙሪያ ስምምነት መፈጸሟ ይታወቃል። ይህንንም ተከትሎ የተለያዩ አገራት በተቃራኒ የሚመስል መግለጫዎች ሲያስደምጡ ቆይቷል። ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያኑም በጉዳዩ ዙሪያ ተቃራኒ ሐሳብ ሲሰነዝሩ ቆይተዋል። እንደ አንድ የከተማ ከንቲባ ይህንን ሁኔታ እንዴት ይረዱታል?
አቶ ነጂብ፡- ኢትዮጵያ የባህር በር በማግኘቷ እንደ አንድ የጅማ ከተማ እና የኢትዮጵያ ዜጋ የተሰማኝ ትልቅ ደስታ ነው። የባህር በር ማግኘት የሚያስችለን ስምምነት መደረጉ የተበሰረ ዕለት የከተማችን ሕዝብ እና ወጣቱ ወጥቶ ደስታው ሲገልጽ ነበር። ስለዚህም ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት ማድረጓ ትልቅ ደስታ ፈጥሮብኛል።
ከዚህ በኋላም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ መጠናከር የሚያስችላት ከመሆኑም በተጨማሪ በተለይ ለወጣቱ ሰፊ የስራ እድል መፍጠር የሚያስችል ይሆናል። ስምምነቱ ከኢኮኖሚ መጠናከር አልፎ ከኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ጭምር የሚያያዝ ነው ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ አገሬ ይህንን እድል በማግኘቷ እንደ አንድ ዜጋም ይሁን አመራር ትልቅ ተስፋ እና ደስታ ይሰማኛል። ከዚህም የተነሳ በራሴ በኩል ማድረግ የተገባኝ ነገር ሁሉ ለመፈጸም ፈቃደኛ ነኝ።
ሌሎች ኢትዮጵያ ያገኘችውን የባህር በር እድል ለማጣጣል የሚሞክሩ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የተዳፈሩ ያህል የሚቆጠሩ ናቸው። እንዲሁም ጉዳዩ ተቀባይነት እንደሌለው አድርገው ለመሳል የሚጥሩ የኢትዮጵያ ሕዝብን የናቁ እንደሆኑ ማወቅ መቻል አለባቸው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የተከበረ ሕዝብ እንደመሆኑ ሕዝብን ማክበር መቻል አለባቸውም። ይህ የባህር በር ስምምነት የአንድ ቡድን ወይም የአንድ ፓርቲ ጉዳይ ሳይሆን የአገር ሉዓላዊነት ጉዳይ ነው። ስለሆነም በዚህ ደረጃ ተረድተው በተለይ በተቃራኒው የቆሙ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ክብር ቢጠብቁ መልካም ነው ለማለት እወዳለሁ። የፖለቲካ ልዩነት ሁሉ እንዳለ ሆኖ የአገር ጉዳይ ላይ ወደአንድ በመምጣት አንድ አቋም መያዝ ይኖርብናል የሚል አተያይ አለኝ። ስለሆነም እኔ በበኩሌ ከሚቃወሙት ጋር ለመፋለምም ሆነ ስምምነቱን ከሚደግፉት ጎን ቆሜ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ ለመክፈል ፈቃደኛ እንደሆንኩ መግለጽ እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ነጂብ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ጥር 23/2016