የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ቤት!

ኢትዮጵያ ጥንታዊ የዲፕሎማሲ ታሪክ ካላቸው ሀገራት አንዷ ነች::ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በሃይማኖት በባህልና በንግድ እንቅስቃሴ ከበርካታ ሀገራት ጋር የጠነከረ ግንኙነት መሰረት የጣለችና በዲፕሎማሲው መስክም ተጠቃሽ ተሞክሮ ማዳበር የቻለች ሀገር ነች::

ኢትዮጵያ ከዋሻ ዲፕሎማሲ ዛሬ እስከ ደረስንበት እስከ ዘመነኛው የዲጂታል ዲፕሎማሲ ድረስ ዕምቅ ታሪክና ተሞክሮ ያላት ሀገር ነች:: በእነዚህ የዲፕሎማሲ ሂደቶች ኢትዮጵያ በውጭው ዓለም ገናና ሆና እንድትታይና ሉላዊነቷና አንድነቷ ተጠብቆ እንዲቆይ ያስቻሉ ስራዎች ተከናውነዋል::

በየዘመናቱ የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎችም ሀገሪቱን ከውጭውም ዓለም ጋር የሰመረ ግንኙነት እንዲኖራትና አልፎ ተርፎም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር እንድትሆን ዘርፈ ብዙ ግኙኘቶችን ሲመሰርቱ ቆይተዋል:: ጥንታዊ ዲፕሎማሲ ከንግስት ሳባ የእስራኤል ጉዞ ጋር የተያያዘ ሲሆን በዘመነ አክሱም የዲፕሎማሲ ዘመንም የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ መሰረቶች ተጥለዋል:: ከእነዚህ መካከል በንጉስ ኢዛና ዘመን ንግድና ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ግንኙነቶች ተፈጥረዋል::

ወደ መካከለኛው ዘመን ስንመጣ የዲፕሎማሲው ዋነኛ አቅጣጫ የሀገርን ሉአላዊነትና አንድነትን ማጽናት ነበር:: ኢትዮጵያ ከውስጥም ከውጭም የሚመጡባትን የሉአላዊነት አደጋዎች በመጋፈጥና አንድነቷን አስጠብቆ መሄድ የዲፕሎማሲው ቁልፍ አቅጣጫ ነበር:: በተለይም በሃይማኖትና በባህል ታጥሮ የቆው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ወደ ንግድና ወታደራዊ ግንኙነት ያደገበት ጊዜ ነበር::

19ኛው ክፍለ ዘመን የአውሮፓና የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያንሰራራበት ዘመን ነበር:: ዘመኑም አውሮፓውያን የአፍሪካ አህጉርን በተጠናከረ ሁኔታ ማሰስ የጀመሩበት ጊዜ ነበር:: አውሮፓውያን በሳይንስ ምርምር እና በሚሽነሪዎች አማካኝነት የክርስትና ሃይማኖትን ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ነበር:: በተጨማሪም ንግድን ማስፋፋት ሌላው ዓላማቸው ነበር::

በወቅቱ የነበሩት የኢትዮጵያ መሪ አጼ ቴዎድሮስ ሀገራችውን ከዘመነ መሣፍንት ትርምስ በመታደግ አንድነቷን ለማረጋገጥና ለማዘመን ራዕይ ሰንቀው መታገል ቢጀምሩም በሀገር ውስጥ የተጠናከረ አመጽ ስለተነሳባቸው ይህንኑ ለማስታገስ ላይ ታች የሚሉበት ጊዜ ነበር:: በተጨማሪም ከአውሮፓ የመጡ የሃይማኖት ሰባኪዎች ጋር ግብግብ በመግጠም ለሀገራቸው የሚያስፈልጋት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎችን ማስፋፋት እንጂ የሃይማኖት ትምህርትማ እዚህ ያሉት የኔ ሰዎች ምን ይሰራሉ በማለት ይሞግቱ ነበር::

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ጉዳይ ታሪክ ሲታወስ በዓለም አቀፍ ብሎም በአፍሪካ ደረጃ የተከናወኑትን ወሳኝ የዲፕሎማሲ ክስተቶች፣ ከራሷ አልፋ የአፍሪካ ጥቅም አስከባሪ ሆነው ከሚነሱ ሀገሮች ቀዳሚውን ቦታ የሚሰጣት ሀገር ነች::

ለአብነት እንኳ ከ1960ዎቹ ዓ.ም. መነሻ ጀምሮ ኢትዮጵያ ለበርካታ የአፍሪካ ፀረ ቅኝ ግዛትና ፀረ አፓርታይድ እንቅስቃሴዎች ትልቅ ፖለቲካዊ ድጋፍ በመስጠት የምትታወቅ ሲሆን፣ በቀድሞው ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ዘመን በደቡብ አፍሪካ፣ በዚምባቡዌና፣ በናሚቢያ ለነበሩ ነፃ አውጪ ድርጅቶች ወታደራዊ ሥልጠና፣ ቁሳዊና ዲፕሎማሲያዊ ዕርዳታዎች ያደረገችው አስተዋጽኦ ተሰንዶ ይገኛል::

በተጨማሪም ኢትዮጵያ አፍሪካን በመወከል በቡድን 20 እና ቡድን 8 ስብሰባዎች፣ እንዲሁም ደግሞ በአየር ለውጥ ድርድሮች፣ በአፍሪካና በቻይና የትብብር ፎረም፣ እንዲሁም በአፍሪካ፣ ህንድና ደቡብ ኮሪያ የትብብር መድረኮችና በበርካታ ዓለም አቀፍ መድረኮች ኢትዮጵያንና አፍሪካን ያልወከለችበት ጊዜ አልነበረም::

የውጭ ግንኙነት ዋነኛ ማጠንጠኛ የሆነውና በሥራ ላይ ያለው ኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በሀገር ውስጥ በሚታዩ የፖለቲካ ውይይቶችና የክርክር መድረኮች ውስጥ በብዛት በድክመት ሲቀርብ የማይስተዋል፣ የበርካታ ተዋንያንን ቀልብ የሚስብ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ስለመሆኑም ይነሳል::

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት አጀማመር የረዥም ጊዜ ታሪክ ያለው ሲሆን፤ በተነፃፃሪ በይፋና በተደራጀ መልኩ ከውጭ ዓለም የተጀመረው ግን በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን፣ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ:: በዚህ ወቅትም የመጀመሪያው ሊባል የሚችልና በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ ያተኮረ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሰል ሰነድ ተዘጋጅቶ በተግባር ላይ የዋለ እንደነበር በታሪክ ተመራማሪዎች የተደረሰበት ሲሆን፣ ይኼም በዚያን ጊዜ ሀገሪቱን ከማዘመን ጋር የተሠራ ታላቅ ሥራ ተደርጎ በወቅቱ ተወስዷል::

ከአፄ ቴዎድሮስ በኋላ የመጡት ዮሐንስ አራተኛም ምንም እንኳን በአውሮፓያውያን ተስፋፊነትና በጣሊያን ሰርጎ መግባት የተነሳ ከግራም ከቀኝም የተወጠሩበት ሁኔታ ቢኖርም፣ መለስተኛ በሆነ ደረጃም ቢሆን የአፄ ቴዎድሮስን የውጭ ፖሊሲ ለማስቀጠል ጥረት ማድረጋቸውን ታሪክ መዝግቦታል:: እ.ኤ.አ. በ1889 አፄ ዮሐንስን የተኩትና በ1913 ያረፉት አፄ ምኒልክ ጣሊያንን በወቅቱ የባህላዊ ዲፕሎማቲክ ሥልት በሆነው በምልጃና በሽምግልና ማሳመንና ከሀገር ማስወጣት ባለመቻላቸው፣ አይቀሬው ዘመቻ ተከስቶ እ.ኤ.አ. በ1896 የመጀመሪያውን የዓድዋ የጦርነት ድል ሊያደርጉ ችለዋል::

እ.ኤ.አ. ከ1913 ጀምሮ ብዙም የጎላ ዲፕሎማቲክ ክስተት ሳፈጠር ቆይቶ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት በተለይም የውጭውን ዓለም አሠላለፍ በመቃኘት በአዲስ መልክ የተጀመረው እ.ኤ.አ. በ1930 አፄ ኃይለ ሥላሴ ከነገሡበት ጀምሮ ነው:: በወቅቱም ሀገሪቱ ሥርዓት ያላት፣ ጠንካራና ዓለም አቀፋዊ ሕጎች ተገዢ እንደሆነች በተለያዩ መንገዶች ማሳየት ጀመሩ:: የንጉሠ ነገሥት ዘመናቸውን ሳይጀምሩ እንኳን ገና አልጋ ወራሽ በነበሩበት ወቅት ሀገሪቱ የመንግሥታት ሊግ ( ሊግ ኦፍ ኔሽን) አባል እንድትሆን እ.ኤ.አ. በ1923 ተደራድረው መሥራች እንድትሆን አስችለዋታል::

እ.ኤ.አ. ከ1936 እስከ 1941 ድረስ የጣሊያን ወረራ እክል ሆኖ፣ ባያደናቅፍና ሒደቱን ባይቀለብስ ኖሮ ኢትዮጵያን በዓለም የፖለቲካ አሰላለፍ ጉልህ ሥፍራ እንዲኖራት የጀመሩት ጥረት ይሳካላቸው እንደነበር ብዙዎቹ ይስማሙበታል:: ይህ እውን ባይሆንም ጣሊያን ተሸንፎ ከወጣ፣ እሳቸውም ከግዞት ከተመለሱና እ.ኤ.አ. በ1941 እንደገና የንግሥና መንበራቸውን ከያዙ በኋላ የጀመሩትን ሀገሪቱን ከቀሪው ዓለም ጋር የማስተሳሰሩ፣ አቋሟን የመገንባትና ተሰሚነትን የማግኘት ጥረታቸውን ቀጥለዋል::

አፄ ኃይለ ሥላሴ ከሁለተኛው ጦርነት በኋላ በተለይም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ መታወቅ በመጀመራቸው፣ ከምእራባዊያን ጋርም መቀራረብ በመፍጠራቸውና ለአፍሪካ ሀገሮች ነፃነት ድምፅ ማሰማት በመጀመራቸው በወቅቱ ከአፍሪካ ሀገሮች ሁሉ የተለየ ተደማጭነትንና ተቀባይነትን ማግኘት ችለዋል:: በጋራ ጉዳዮችም ላይ በግንባር ቀደምነት ከሚሰለፉ ተርታ ሀገሪቱን ለማሰለፍ በቅተዋል::

በጋራ የሰላምና ደኅንነት ተሳትፎ እንደ አብነት የሚጠቀሰውም እ.ኤ.አ. ከ1951 እስከ 1953 የኮሪያ ጦርነት ወቅት አትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥላ ሥር ከአፍሪካ አገሮች የመጀመሪያዋ እግረኛ ወታደር ላኪ ሀገር ሆና መሳተፍዋ ነው:: በወቅቱ አሥራ ስድስት ሀገሮች ብቻ ነበሩ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔና ጥሪ ምላሽ የሰጡት። በዚህ ጦርነት ኢትዮጵያ 6,037 ወታደሮች ያሳተፈች ሲሆን፣ በ235 የውጊያ ግንባሮች ተሳትፋ ሁሉንም አሸንፋለች:: በጦርነቱ 121 ወታደሮች የተሰው ሲሆን፣ በመጨረሻ በጦርነቱ ማብቂያ በተደረገው ማጣራት የጦር ምርኮኛና እስረኛ ያልነበራት ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ እንደሆነች በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል:: በተጨማሪም እ.ኤ.አ. በ1960 ለኮንጎ የሰላም ማስከበር የሰላም አስከባሪ ሠራዊት በመላክ ተሳትፎ ተደርጓል::

ከዚህ በመነሳትም በተባበሩት መንግሥታትም ድርጅትም ይሁን በኃያላን ሀገሮች የተገኘውን አዎንታዊ ድጋፍና ትኩረት መሠረት በማድረግም፣ የአፍሪካ ሀገሮች ነፃ የሚወጡበት ሁኔታ የማመቻቸት ሥራ ንጉሡ ሠርተዋል:: በዚህም መሠረት የአፍሪካውያን የነፃነት ጉዳይ በአጀንዳነት ተይዞ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መድረክ ውይይት እንዲካሄድበት ከማስቻል ባሻገር፣ የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ያላሰለሰ ጥረትና ግፊት አድርገዋል:: በዚህም የአፍሪካ ልሳን ተብለው የተጠቀሱ የመጀመሪያ የሀገር መሪ ለመሆን አስችሏቸዋል::

በወቅቱም የፓን አፍሪካኒዝም ጽንሰ ሃሳብና መርህ ውስጥ ለውስጥ ሲሠራበትና ሲመከርበት የነበረ በመሆኑ፣ ይኼንን በተደራጀ መንገድ ለማካሄድና ለማስተባበር እንዲረዳ የአፍሪካ አንድነት ጽሕፈት ቤትን ማቋቋም አስፈላጊ እንደሆነ የማስተማር ሥራን ንጉሡ ሠሩ:: ከፍተኛ የማሳመን ተግባራትን በማከናወን የአፍሪካ አንድነት ደርጅት ጽሕፈት ቤት (OAU) በአዲስ አበባ እ.ኤ.አ. በ1963 ተመሠረተ:: ይኼም የንጉሡን ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች ብቃትና ውጤት አረጋገጠ:: በአፍሪካ መሪዎች በኩል ተቀባይነትንና ከበሬታን፣ በዓለም መሪዎች በኩል ደግሞ አድናቆትንና ዕውቅናን እንዲያገኙ አስቻላቸው።

በአጠቃላይ በባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ታሪካችን በጥንካሬ የሚታወሱ የስኬት ታሪኮች እንዳሉን ሁሉ ከባድ ፈተናዎችንም የተጋፈጥንበት በርካታ ጊዜያት አልፈዋል። ከላይ እንደተገለፀው የፋሽስት ጣሊያን መንግሥት ለሁለተኛ ጊዜ ኢትዮጵያን በኃይል በወረረ ጊዜ የሀገራችን የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት እንዲከበር የዓለም መንግሥታት ከጎናችን እንዲቆሙ ለማድረግ በመንግሥታቱ ማህበር የኢትዮጵያ ዋና ፀሐፊነት በተወከሉት በአቶ አክሊሉ ሀብተወልድ እና በኢትዮጵያ የጄኔቫ ዴሊጌሽን መሪ ፊትአውራሪ ተክለሐዋሪያት ተክለማርያም አማካኝነት ሰፊ የዲፕሎማሲ ተጋድሎ ተደርጓል።

ሆኖም ኢትዮጵያ የተፈፀመባት ግፍ በዓለም ሀገራት በቂ ትኩረት ካለማግኘቱም በላይ የመንግሥታቱ ማህበርም የመበታተን እጣ ፈንታ ገጥሞታል። ድርጅቱ የሞተው ኢትዮጵያ ላይ በያዘው ፍርደ ገምድል አቋም ነበር:: እዚህ ላይ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ የጄኔቭ ንግግር ይታወሳል:: በወቅቱ የድርጅቱ ዝም ብሎ ተመልካችነት፣ የጣሊያን ተወካዮች ግብረ ገብነት የጎደለው ተግባርና የንጉሱ የሁኔታ አያያዝ ብልሃት አንገትን ቀና የሚያስደርግ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ነበር::

ከንጉሡ በኋላ የመጣው ወታደራዊው የደርግ ሥርዓት ኢትዮጵያን በአድኃሪያን የአረብ ሀገራትና ሶማሊያን በመሰሉ ተንኳሽ ጎረቤቶች የተከበበች ደሴት ናት ብሎ ስለሚያስብ፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የነበራት ግንኙነት በትብብርና በወዳጅነት መንፈስ ሳይሆን በጥርጣሬ፣ በፉክክርና በጣልቃ ገብነት ላይ የተመሰረተ ነበር።

በሶሻሊስታዊ ርዕዮተ ዓለምና በሶሻሊስት ጐራ አጋርነት የተቃኘው የደርግ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከሶሻሊስት ሀገራት ወታደራዊ ድጋፍን በማስገኘት ረገድ የተሳካ ነበር ማለት ቢቻልም፣ ጉልህ የሆነ የኢኮኖሚ ድጋፍ በማስገኘትና የኢትዮጵያን ልማት በመደገፍ ረገድ ግን ስኬታማ ነበር ለማለት አያስደፍርም:: በዚህም ኢትዮጵያ ከአሜሪካና ከምዕራብ አውሮፓ ሀገሮች ጋር የነበራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እጅግ የተዳከመበትና ከአንዳንዶቹ ጋርም ግንኙነቱ ሙሉ በሙሉ የተቋረጠበት ነበር::

በተጨማሪም ከአብዛኞቹ ጎረቤት ሀገራት ጋር በአለመተማመን መንፈስ፣ በግጭትና በጣልቃ ገብነት የታጀበው ግንኙነት ውጤቱ ለሁሉም አክሳሪ እንደነበር ከደርግ አስተዳደር ውድቀት ማግስት የታዩ ቀጣናዊ ክስተቶች አመላካች ናቸው። በአጠቃላይ ደርግ የተከተለው ርዕዮተ ዓለማዊ ጎራ የለየ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ የቀዝቃዛው ጦርነት ባስከተለው ዳፋ እና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ከምዕራባውያኑ በተለይ ከአሜሪካ ጋር የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መቋረጥን ተከትሎ ሀገራችን የውክልና ጦርነቶች መቆራቆሻ ሜዳ በማድረጉ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቀሞቿን እንድታጣና ብዙ መከራና ችግርን እንድታሰተናግድ ሆኗል::

የኢህአዴግ ወደ መንግሥት ስልጣን መምጣት ከዓለም አቀፍ ሥርዓት መቀየር ማለትም የሶሻሊስት ጎራው መበታተን፣ የቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም እና አሜሪካ መራሹ የዓለም ሥርዓት ጅማሮ ጋር መገጣጠሙ ለኢህአዴግ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እንደ አንድ መነሻ ግብዓት መሆኑ አይቀሬ ነው:: ስለሆነም ኢህአዴግ የቀረፀው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ ዓለማዊ ፖለቲካው በነጻ ገበያ/ካፒታሊዝም መንሰራፋት፣ በክልላዊ ውህደት መስፋፋት፣ በሉአላዊ የኢኮኖሚ ትስስር መጠናከርና በመልክአ-ፖለቲካ ፍላጎቶች (Geopolitical interests) ፉክክሮች ጎልቶ መውጣት ዓውድ ውስጥ የተቃኘ ነው ለማለት ይቻላል።

በ 2010 ዓ.ም የመጣው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት “የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ብሔራዊ ጥቅምን ባስጠበቀ መልኩ እንዲካሄድ እየሰራ እንደሆነ ይናገራል። ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፣ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ፣ ዲጂታል ዲፕሎማሲና የሀገር ውስጥ ዲፕሎማሲ በዋናነት በለውጡ መንግሥት የሚተገበሩ የዲፕሎማሲ መርሆዎች ናቸው።

አዲሱ ዲፕሎማሲ በ2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ አዲሱ መንግሥት ተለዋዋጭ ለሆነው ዓለም አቀፍ ግንኙነት የሰጠው ዲፕሎማሲያዊ ምላሸ ነው:: በዚህም መንግሥት በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ውስጥ ከሚገኙ ወዳጅ እና ጠላት ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ሰላምን ማዕከል በማድረግ ትልቅ እና ተምሳሌታዊ የዲፕሎማሲ ሥራ የተሰራበት ሲሆን፤ በዚህም በቀጣናው ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ግንኙነቷን በዋናነት ያሻሻለችበት የዲፕሎማሲ ሥራ ነበር::

ከላይ የተዘረዘሩ የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት የሚመለከቱ ጉዳዮች በዋነኝነት የተከናወኑት ከተመሰረተ 116 ዓመታትን ባስቆጠረው የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አማካኝነት ነው። ከዘመንና ጊዜ ጋር አብሮ የሚራመድ ሆኖ የዘለቀው የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ሀገር መንግሥት ግንባታ የነበረው ሚና ጉልህ ሆኖ የሚታይ ነው።

በዘመናት መካከል ለሀገርና ለህዝብ ትልቅ ትርጉም ያላቸው የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት ሥራዎች ሲከወኑበት ቆይተዋል። እኛም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለሀገር ያበረከተውን እጅግ ከፍ ያለ አበርክቶ ከግምት ውስጥ በማስገባት በዚህ ለሀገርና ለህዝብ የሰሩ ግለሰቦችና ተቋማት በሚወደሱበት የባለውለታዎቻችን ገፅ ሥራዎቹን በማንሳት አመሰገንን።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You