በደምበል ሐይቅ ዙሪያ በ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጪ ሆቴሎችና ሪዞርቶች እየተገነቡ ነው

ባቱ፦ በደምበል ሐይቅ ዙሪያ በሦስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ወጪ ሆቴሎችና ሪዞርቶች እየተገነቡ እንደሆነ የባቱ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

የባቱ ከተማ ከንቲባ አቶ አህመዲን እስማኤል ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ የባቱ ከተማን የቱሪዝም ከተማ ለማድረግ በደምበል ሐይቅ ዙሪያ በርካታ የልማት ሥራዎች ታቅደው ወደ ተግባር ተገብቷል። አሁን ላይ ስድስት ባለሀብቶች በሦስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ወጪ በደምበል ሐይቅ ዙሪያ ሆቴሎችና ሪዞርቶች እየገነቡ ይገኛሉ።

የባቱ ከተማን የቱሪዝም መዳረሻና ከተማ ለማድረግ የከተማውን ተፈጥሮ፣ ታሪክ፣ ባህል፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታን፣ የንግድ እንቅስቃሴን ከጎብኚዎች ጋር የማጣመር ሥራ እየተሠራ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አህመዲን፤ በዚህም በደምበል ሐይቅ ዙሪያ በርካታ ሆቴሎች እንዲገነቡ ከተማ አስተዳደሩ ባለሀብቶችን እየደገፈ ይገኛል ብለዋል።

ግንባታው ሁለት ምዕራፍ ያለው ሲሆን የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ መጀመሩን ገልፀዋል። ይህም በአንድ ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አስረድተዋል፡፡ ይህም ፕሮጀክት «ደምበል የቤተሰብ ባሕር ዳርቻ» የተሰኘ ሲሆን ስድስት ባለሀብቶች እያንዳንዳቸው ለግንባታው 600 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

እንደ አቶ አህመዲን ገለፃ፤ ከተማ አስተዳደሩ ለስድስቱ ባለሀብቶች የመሥሪያ ቦታ፣ የአካባቢውን ደህንነት የማረጋገጥ እና አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። ባለፉት 60 ዓመታት ወደ ከተማዋ 21 ባለሀብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ መጋበዝ ተችሏል። ነገር ግን ከዚህ ውስጥ ስድስቱ ብቻ ወደ ሥራ መግባት ችለዋል።

ቀሪዎቹ 15 ኢንቨስተሮች በተሰጣቸው ጊዜ ማልማት ባለመቻላቸው የወሰዱት መሬት ለመንግሥት ተመላሽ ተደርጓል ያሉት አቶ አህመዲን፤ ከለውጡ መንግሥት በኋላ ግን በአንድ ዓመት 36 ኢንቨስተሮችን መጋበዝ መቻሉን ጠቅሰዋል። ከ36ቱ ውስጥ 30ዎቹ ኢንቨስትመንቶች የከተማዋን መሠረተ ልማት የሚያሻሽሉ፣ ለከተማዋ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ እና የከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻነት የሚያጠናክሩ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በሐይቅ ዳርቻ ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል ለመገንባት የሚፈልጉ ባለሀብቶችን እያወያየና እየደገፈ ነው። ይህም ወደከተማዋ የሚመጣውን የቱሪስት መጠን እንደሚጨምርም ተናግረዋል። ኢንቨስተሮች ወደ ከተማዋ መጥተው በልማት ሥራ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You