ታሪክ አዋቂ፣ አንደበተ ርቱዕም ነው፡፡ በርካቶች ያለምንም ማስታወሻ በቀደመውን ዘመን የተፈጠሩ ጉዳዮችን አዋዝቶ ሲተርክ ያውቁታል። ላለፉት ዓመታት በራዲዮና ቴሌቪዥን መስኮቶች ከሚያዘጋጃቸው መርሀ ግብሮች ባለፈ እግር ኳሳዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን እንዲተነትን እንዲሁም ባለፈው ጊዜ የሆነውን እንዲያስታውስ በበርካቶች ይጋበዛል። መረጃ ለሚጠይቀው የትኛውም ባለሙያ ተባባሪና በዘመናት የካበተ ዕውቀቱን ሳይሰስት ይሰጣል፡፡ በዕውቀት በተሞላ ማንነቱም በርካቶች ‹‹የኢትዮጵያ ስፖርት ቤተመጽሃፍት›› ይሉታል፡፡ ይህ ሰው ሰው ከቀናት በፊት በህወት የተለየን በተባ አንደበቱና ብዕሩ የኢትዮጵያን ስፖርት ለትውልዱ እንካችሁ የሚለው ጋዜጠኛው፣ የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋችና ሙዚቃ ወዳጁ ገነነ መኩሪያ ‹‹ሊብሮ›› ነው፡፡
የኢትዮጵያ ስፖርት እጅግ ከሚፈልጋቸው ሰዎች መካከል ሁለገብ ባለሙያው ገነነ በህመም ምክንያት ቢለየንም፤ በህይወት ሳለ አሻራውን ያሳረፈባቸው መጽሐፍትና ተረኮች ስሙን ከመቃብር በላይ ያውሉታል። በዛሬው የስፖርት ማህደር እትምም ይህንን የታሪክ ባለውለታ እናስታውሳለን። ገነነ የተወለደው መጋቢት 5/1957 ዓም ይርጋለም ከተማ ይሁን እንጂ ያደገው በሻሸመኔ ከተማ ነው፡፡ እግር ኳስን በሰፈር ቡድኖች የግብ ጠባቂ በመሆን ነበር የጀመረው፡፡ በአስደናቂ ጉዳዮች የታጀበ የተጫዋችነት ዘመኑን ገጠመኞች ሲያስታውስ ጥርስ የማያስከድነው ገነነ፤ በ1974 ዓም ከግብ ጠባቂነቱ በመውጣት የሜዳ ተጫዋች በመሆን አውራ ጎዳና ለተባለ ቡድን የወቅቱ ከፍተኛ ተከፋይ ሆኖ ተቀጠረ።
በአውራጃዎች ውድድር ያደገበትን የሻሸመኔን መለያ ለብሶ ሲሰለፍ፤ የሸዋ ውድድር ላይ ደግሞ ሀይቆችና ቡታጅራን ወክሎ ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል። ይህ ችሎታው የ12ኛ ክፍል ተማሪ እያለ ለረጅም ጊዜ ለተጫወተበት ሜታ ቢራ እንዲፈርምም አድርጎታል። የክለቡ ተጫዋች ሆኖም 3 ጊዜ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና እንዲሁም አንድ ጊዜ የብር ሜዳልያ ተሸላሚም ነበር። በተጫዋችነቱ ወቅት ግብ ጠባቂውን ጨምሮ አራት ተጫዋቾችን አልፎ ያስቆጠረው ግብ ተከትሎም እስከ እለተ ሞቱ ስሙን ተከትሎ የሚጠራበትን ‹‹ሊብሮ›› የሚል ቅጽል አትርፏል፡፡ ፈገግታን ከሚያጭሩና ለየት ካሉት የእግር ኳስ ገጠመኞቹ መካከልም በአንድ ዓመት ብቻ በራሱ ክለብ ላይ አምስት ግቦችን ያስቆጠረ ተጫዋች ነው፡፡
ገና በጠዋቱ ከስነ ጽሑፍ ጋር የተዋወቀው ገነነ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህር ቤት አንስቶ ስፖርታዊ ጉዳዮች ላይ መጻፍ ያዘወትር ነበር፡፡ ጋዜጣ በማዞር የሚያነባቸውን ታሪኮች መልሶ ለጓደኞቹ በመተንተንም ነበር ችሎታውን ያጎለበተው። ተጫዋች ሳለ በተግባረ ዕድ በጄነራል መካኒክነት ተምሮ የተመረቀ ሲሆን፤ ከዚሁ ጎን ለጎንም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ይጽፍ ነበር። ለሙያው ካለው ፍቅር የተነሳም ሌሎች በርካታ ጋዜጦች ላይ ያለ ክፍያም ነበር የሚጽፈው፡፡ ቆይቶም ሊብሮ ጋዜጣን አስጀመረ፡፡ በወቅቱ የስፖርት ቤተሰቡ በጉጉት ጠብቆ ከሚያነባቸው ተወዳጅ የስፖርት ጋዜጦች መካከል አንዱ በቅጽል ስሙ የተሰየመው ይኸው ጋዜጣ ነበር፡፡ ለ13 ዓመታት ለአንባቢያን ካደረሰ በኋላም የጋዜጣ ስራውን መጽሃፍ ወደማዘጋጀት ቀይሮታል። ከ30ዓመት በላይ በቆየበት የስፖርት ጋዜጠኝነት ህይወቱም ከጋዜጣ ባለፈ በሬዲዮ እንዲሁም በቴሊቪዥንም ሰርቷል፡፡
በጽሑፍ ችሎታው በርካቶችን ያስደመሙ መጽሐፍትን ባለፉት ዓመታት አሳትሟል፡፡ እውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ‹‹ኢህአፓና ስፖርት›› በሚል ርዕስ ከክፍል 1እስከ 3 ለአንባቢ ያደረሰው ገነነ በደርግ ዘመነ መንግስት ስፖርት(እግር ኳስ)፣ ወጣቶችና ፖለቲካ የነበሩበትን ሁኔታ በዝርዝር ያሳየበት ተወዳጅ መጽሃፍት ናቸው፡፡ የወቅቱን ሁኔታ ዋቢ ለማድረግ ከማስቻሉ ባለፈ ‹‹የነገን አልወልድም›› በሚል መጽሃፉን መነሻ ያደረገ ፊልምም እንደተሰራበት ይታወቃል፡፡ ሌላኛው በርካታ ፊልሞችን ሊያሰራ የሚችል ጉዳዮችን ያጠቃለለው መጽሃፉ ደግሞ ‹‹ፍትሃዊ የጠጅ ክፍፍል›› በሚል የታተመ ሲሆን፤ በአንባቢ ዘንድም የተወደዱ ናቸው፡፡ በንጉሳዊው ስርዓት ወቅት ታዋቂ ስለነበረውና ከንጉሱ ጋር የሚታየውን መኩሪያ የተባለ አንበሳ ታሪክ ያወሳበት ‹‹መኩሪያ›› የተባለ መጽሐፉም ታሪክን የኋሊት ዳሰሰበት ነው፡፡ ሊብሮ የራሱ የሆነ የእግር ኳስ ፍልስፍና ያለው ሲሆን፤ ‹‹ኢትዮጵያዊ ስልጠና›› በሚል ኢትዮጵያዊያን ታዳጊዎችን መሰረት ያደረገ የእግር ኳስ አሰለጣጠን ቴክኒክ ሊኖረው ይገባል በሚለው መልክ ያሳየበት ነው፡፡
ለዘመናት ለእግር ኳስ ስፖርት ላበረከተው ታላቅ አስተዋጽኦም በአዲስ አበባ ተሰናድቶ በነበረው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የረጅም ዘመን አገልግሎት ሜዳሊያ ተበርክቶለታል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 19 ቀን 2016 ዓ.ም