የአንድ ሰው ስብዕናና ማንነቱ ከሚገነባባቸው መንገዶች አንዱ ቤተሰብና አስተዳደግ ቢሆንም አካባቢ ማህበረሰብና ትምህርት ቤት የየራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ፡፡ ግለሰቡ ከልጅነቱ እስከ ወጣትነቱ በሚያሳልፈው ዕድገት በጊዜው ወይም በዘመኑ የነበረው መንፈስና አስተሳሰብ አስተዋፅኦ አለው፡፡
የዘመኑ አስተሳሰብ የወቅቱን ትውልድ ምርኮኛ ያደርገዋል፡፡ ይህ በብዙ ሀገሮች የነበረ፣ የታየና ያጋጠመ ክስተት ነው፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያም በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የነበረውን አስተዳደርና አገዛዝ በመቃወም በተለይ የተማረው ትውልድ ግንባር ቀደም ነበር። እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ አጋማሽና 1970ዎቹ መጀመሪያ በዓለም ላይ የነበረው የዘመኑ መንፈስ የኢትዮጵያንም ወጣቶች ሽውታው ነክቷቸዋል፡፡ በጊዜው ከነበሩት ወጣቶች አንዱ የሆኑት አቶ ተሾመ እሸቱ ከሽውታው አላመለጡም፡፡ በሥርዓት ላይ ካመፀው ትውልድ ጋር አምጸዋል፤በኢህአዴግ ዘመንም በአራት ምርጫዎች በመሳተፍ ለ21 ዓመታት በምክር ቤት ቆይተዋል። በርካታ የሕይወት ተሞክሮ ያላቸው እኒሁ ግለሰብ የዛሬው የህይወት ገጽታ እንግዳችን ናቸው፡፡
ልጅነት፣ አስተዳደግና ትምህርት
ትውልዳቸው ጎንደር ጠቅላይ ግዛት፣ ሰሜን አውራጃ ሲሆን፤ አውራጃው በስተምዕራብ በኩል ከዳባት ጋር ወሰንተኛ ነው፡፡ ከተከዜ ወንዝ ጋር ግጥም በሆነው በዚህ አውራጃ በ1942 ዓ.ም ለእናታቸው የመጀመሪያ፣ ለአባታቸው ደግሞ አራተኛ ልጅ የሆኑት አቶ ተሾመ እሸቱ ተወለዱ። በወቅቱ ትምህርት ብርቅ ስለነበር እድሉን የሚያገኙትም የአስተዳዳሪና የሹም፣ የፖሊስ አዛዦች ልጆች ብቻ ነበሩ፡፡ በቤተሰብም ጭምር ድጋፍ አግኝተው ትምህርት ቤት የሚሄዱት፤ የሚፈቀድላቸውም እነሱ ብቻ ናቸው፡፡ በሀገሬው በተለይም በገበሬው ዘንድ ትምህርት ብዙ ቁብ አይሰጠውም ነበር።
ይሁንና “ሹም” በሚባሉት ሰዎች፤እንዲሁም በሕዝቡ ዘንድ “አደባባይ መዋል” የሚባል ነገር አለና ልጆቻቸው “የአደባባይ ሰው” እንዲሆኑ ስለሚሹ እንዲማሩ ያደርጉ ነበር። አቶ ተሾመም አያታቸው የአደባባይ ሰው ስለነበሩ እንዲማሩ ግፊት ያደርጉባቸው ነበር። እርግጥ የአማርኛ ትምህርት በተወሰነ ደረጃ እሳቸውና እኩዮቻቸው ይማሩ ነበር። እሳቸው ግን በተለይ ንባብን በተመለከተ ጥሩ ጀርባ ነበረኝ ይላሉ። የቤተክህነትን ትምህርት እንደ “አንቀፀ ብርሃን”፣ “ውዳሴ ማርያምን”፤“ዳዊት መድገም”ን ጨምሮ በመጠኑ ተከታትለዋል። እነዚህን አጥርተው በመዝለቃቸው ለሚቀጥለው የትምህርት ዘመናቸው እምብዛም እንዳልተቸገሩም ነው የሚያስረዱት።
ከዚህ ሁሉ በኋላ ደግሞ ጎንደር ከተማ ላይ ትምህርታቸውን ሲጀምሩ ቀና ሆነላቸው፣ በወቅቱም እሳቸው ተወልደው ካደጉበት ወረዳ ጎንደር ድረስ መጥተው ትምህርት ቤት የገቡት አራት ልጆች ብቻ ነበሩ። ዘመኑም 1950 ዓ.ም ። የእሳቸው ቤተሰብ ግን የአደባባይ ሰው እንዲሆኑ ይገፋፏቸው ስለነበር ትምህርታቸውን ወደፊት ለመግፋት ስንቅ እንደሆናቸው ያምናሉ፡፡ በ1964 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና (ሚኒስትሪን) ተፈተኑ። ፈተናውንም በማለፋቸው እዛው ጎንደር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቀጠሉ። በ1966 ዓ.ም ግን አብዮቱ በመፈንዳቱ ትምህርት ተቋረጠ። በመካከል ለተወሰነ ጊዜ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ትምህርት ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም በ1967 ዓ.ም “የዕድገት በሕብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ” በመታወጁ እንደገና ተዘጋ።
“….እርግጥ ዘመቻው እኔን አይመለከትም ከአስራ አንደኛ ክፍል ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ተቋማት የነበሩት ናቸው እንዲዘምቱ የተደረገው።ይሁንና ዘመቻው እክል ስለገጠመው ተቋረጠ። የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች የነበሩት እንዲዘምቱ እና ለዚህም ዝግጅት እንዲያደርጉ ሲነገራቸው እኔም ዝግጅት አደረግኩ። በዘመቻው ብዙም ሳንገፋ ዘመቻው ተቋረጠ “ይላሉ፡፡
እንዲህ እንዲህ እያሉ አቶ ተሾመ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው ከፍተኛ ትምህርት በመግባት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ለማግኘት ቻሉ።
አቶ እሸቱ ተምረው ዲግሪ ካገኙበት ሙያ ውጪም የሰላና ቶሎ የሚረዳ አእምሮ ስለተቸራቸው የትኛውም የሙያ ዘርፍ ላይ ያለ ሰው ስለአንድ ጉዳይ ሲናገር ቶሎ የሚረዱና የሚገባቸው ናቸው። ይህንንም በአንደበታቸው እንደሚከተለው ይገልጹታል፡፡
“……ለምሳሌ ኢኮኖሚስቶች ተሰብስበው ሲያወሩ፣ ሲወያዩ፣ የእነሱን ያህል ውስጡ ዘልቄ መተንተን ቢያቅተኝም በደንብ ይገባኛል። በተመሳሳይ ስለ አስተዳደር፣ ኢኮኖሚክስ ወዘተ ሲወሩም ያለችግር እረዳለሁ” በማለት ይናገራሉ።
የፖሊቲካ ንቃትና ተሞክሮ
አቶ ተሾመ እሸቱ በልጅነታቸው ያዩት ለኋለኛው ሕይወታቸው መነሻና መሠረት ሆኗቸዋልም። አምባ ጊዮርጊስ ሲማሩ መውጪያና መውረጂያቸው በፍርድ ቤት በራፍ ነበርና ሁሌም የሚመለከቷቸው ትዕይንቶች ይስቧቸዋል። ከፍርድ ቤቱ በራፍ ላይ በተቸከለ እንጨት ላይ ታስረው መሬቱን እየጎደፈሩ የሚውሉ ፈረሶችን ያስተውላሉ። ከዚያም በላይ አርሶ አደሩ ሥራ ፈትቶ የመጣበት ጉዳይ ሳያልቅ ፋይሉ ወደ ወረዳው ተመልሶ ባለጉዳዮቹ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ያለውንም ስሜት ይረዳሉ ።
ሌላው እያዩ ያደጉት ደግሞ አስተዳዳሪዎች ከትንሿ ዶሮ ጀምሮ የገበሬውን ፍየሉን ሲያርዱበት ነው። ይህ በአይናቸው ያዩትና የሚሰጠውንም ፍርድ እየሰሙ የኖሩበት ነው። አብዛኛው የክሱ ይዘት፣በተከሳሽና በከሳሽ መካከል ያለው ውዝግብ ሲጠቃለል “እወለዳለሁ አትወለድም” የሚል ነው። በአካባቢው ከሞላ ጎደል ክስ የሚከፈተው መሬትን በውርስ ለማግኘት ሲሆን፤ በድንበርና ከእርሻ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ነበር። በተለይ ከሚያስታውሱት የምስክር አቀራረብ አንዱ ችግር ሲሆን፤ ይህም ለአብነት ሊጠቀስ የሚችል ነው። በአንድ የአዝመራ ወቅት ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ከመግባታቸው በፊት ያዩትን ያስታውሳሉ።
አንድ የአባታቸው የቅርብ ዘመድ የሆኑ ሰው ቤተሰባቸው ሁሉ በወባ ታሞ እቤት ውለዋል። በሕመሙ ወቅት ያልተኙት እሳቸውና አንዲት ሠራተኛቸው ብቻ ነበረች።አውድማ ላይ የአተር ክምር ነበር።ጭላዳ ዝንጀሮ ክምሩን እያፈረሰ ሲያስቸግራቸው ልጅቱን ይዘው በመውጣት አተሩን ይወቃሉ።በዚህን ሰዓት ነበር ከምክትል ወረዳ ገዢ በታች የነበሩ አጥቢያ ዳኞች የመጡት። ተሾመ ለምን እንደመጡ እንኳን አያውቁም። ብቻ ሰዎቹ በዚያ ሲያልፉ ያቺን ሴት ልጅ ያዩዋታል። በሬዎቹን አውድማ ላይ እያዞረች ነበር።
አጥቢያ ዳኞቹም “ለምን አውድማ ላይ አስገባሃት?” ብለው የክስ መሰል ጥያቄ አቀረቡላቸው። እሚገርመው “ጉልበት በዝብዘሃል፣ አላቅሟ አሠርተሃታል” አልነበረም ጉዳዩ።“ባህል ጥሰኻል” ነበር። እንግዲህ ባህሉ “ሴት ልጅ አውድማ አትገባም” ነበር የሚለው ኋላ ተሾመ እንደገባቸው። ምክንያቱ ደግሞ በባሕል የነበረውና በጊዜውም ሕግ ሊያስጥብቀው የሚሻው ነገር “ሴት ልጅ አውድማ ከገባች እህል አይበረክትም” የሚል ነበር።
በዚሁ እና መሰል ምክንያቶች እነ መንግሥቱ ኃይለማርያም ንጉሡን ማውረዳቸው ትክክል ነው ብለው ያምናሉ። ይሁንና ያን ሁሉ ወጣት መግደላቸው ግን ትክክል አልነበረም ይላሉ። ይንንም በረሃ የመግባታቸው ምክንያት አድርገው ይወስዱታል አቶ ተሾመ፡፡ አንድም ቀን ጠመንጃ ተሸክመው በረሃ እውላለሁ ብለው አስበው እንደማያውቁ ይናገራሉ። እሳቸው ያው የአደባባይ ሰው እሆናለሁ ብለው ነበር የሚመኙት።ይሄው ዛሬ ከድሃው ከሀብታሙ ጋር እንዲኖሩ ያደረጋቸው ያ ተሞክሯቸው እንደሆነ በኩራት ያስታውሳሉ፡፡
በ1966 ዓ.ም ዐመፅ ሲጀመር እሳቸው አምባ ጊዮርጊስ ሰላማዊ ሰልፍ እየመሩ ነበር። በዛን ጊዜ ነበር አውራጃ ገዢው የመጡት።ተሾመ ቀደም ቀደም እያሉ በነበረበት ሰዓት አብረዋቸው የነበሩት የአካባቢው ሰዎች “አንተ ዝም በል፤ ለሱ እኛ እንበቃዋለን” ብለው አከላከሉዋቸው። እሳቸውም እንደተነገራቸው አፋቸውን ከርከም አርገው ዝም አሉ። አውራጃ ገዢውም ንግግራቸውን በሰፊው ጀመሩ።
የመልዕክታቸው አብዛኛው ክፍል በጠላት ዘመን ስለሰሯቸው ተግባራት፣ ጀብዱዎች ወዘተ የሚያትት ነበር። ይሁንና አርሶ አደሩ የጠየቀው “አትንኩን” የሚለውን አጭር ጥያቄ እንጂ የኢጣሊያን ዘመን ታሪክ እንዲተረክለት አልነበረም። እንግዲህ እሳቸው ንግግራቸውን እንዳበቁ በሚገርም ሁኔታ ከተሰብሳቢው መሃል በጣም አጭርና ያን ሁሉ ንግግራቸውን የሚያኮሰምን ምላሽ ተሰጠ።“ቢትወደድ የት ሄዱ?” የሚል ጥያቄ ተነሳ፡፡ መልዕክት አስተላላፊውም “ሁመራ እርሻ”፣ ብለው መለሱ፡፡ ተሰብሳቢውም አስተዳዳሪውም እርሻ፣እኛም እርሻ፣ ታዲያ መች ነው እኛን በቅጡ የሚያስተዳደሩት? የሚል ጥያቄ ቀረበላቸው።
መልዕክተኛው ግን መልስ አልበራቸውም። ተሰብሳቢው ቢሰለቸውም “የኛ በቅሎዎች ተሠርቀው የሚገቡት እርስዎ ዘመዶች ቤት ነው”፤ እኛ በቅሎቻችንን ጠብቁልን ስንል እሳቸው ደግሞ ስለጠላት ዘመን ያወራሉ በማለት ሰዉ አማረረ።
በአጠቃላይ በአጼው ዘመን ገበሬው የበይ ተመልካች ነበር፡፡ ያመረተውን ምርት በገፍ ከመውሰድ ውጪ ብሶቱን እንኳን የሚያዳምጠው አልነበረም፡፡ይህ ሁኔታ አማሮኝ ነበር እንደ አብዛኛው ወጣት ኢህአፓ የሚባለውን ፓርቲ የተቀላቀልኩት ይላሉ። በጊዜው የነበረው ቅስቀሳ የወቅቱን አስተዳደር ለመታገል የሚል ስለነበር እኔም በተሞክሮ ያየሁትና የማውቀው ሥርዓት
ስለነበር አምኜ ተቀላቀልኩ፡፡
ስለሀገር ማውራት፣ ማንበብ፣ መከራከር፣ ስለሕዝብ ጉዳይ ማውራትና የመሳሰሉትን ያስተማራቸው ድርጅታቸው እንደሆነም ነው የሚናገሩት።
የወረዳና ዞን አስተዳዳሪነት
አቶ ተሾመ ኢህአፓን ተቀላለቅለው አጼውን ለመጣል በሚደረገው ትግል ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ነበሩ። በዚህም የፖለቲካ አስተሳሰባቸውን አዳበሩ፤ከህዝብ መቆም ባህርያቸው አደረጉ፡፡ይህ አስተሳሰባቸው እየጎለበተ ሄዶ ኢህአዴግ ከገባ በኋላ በምርጫ ተወዳደሩ፡፡ የጎዛምንን ወረዳ ወክለው ተወዳድረው አሸነፉ፡፡
የጎዛመን ወረዳን አስመልክተው ለሳቸው በሥፍራው ለመመረጥም ሆነ 500 ሰው ማስፈረም አስቸግሯዋቸው አያውቅም። ከወረዳ አስተዳዳሪ ጀምሮ እስከዞን አስተዳዳሪነት የደረሱበት ተሞክሮና ልምድ አላቸው።
በጎዛመን ቆይታቸው የተሠሩት ስራዎች ብዙ ነበሩ ይላሉ። እሳቸው ከመመረጣቸው በፊት የጎዛምን ወረዳ በመንገድ እጥረት ትሰቃይ ነበር፡፡ እርሳቸው የወረዳ ብሎም የዞን አስተዳዳሪ ከሆኑ በኋላ ደረጃ በደረጀ የሕዝቡን ጥያቄ አቅም በፈቀደ መጠን ለመመለስ ጥረት አድርገዋል፡፡በጎዛምን ወረዳ መንገድ በመስፋፋቱ አንድም ቀበሌ መኪና እማይገባበት የለም። ማዳበሪያ በትልቅ መኪና መጥቶ ነው የሚራገፈው።የገበሬ እህል በመኪና ተጭኖ ነው የሚወጣው።ለምሳሌ እሳቸው ዞን አስተዳዳሪ ሆነው ሥራ የጀመሩት በ1986 ዓ.ም. አካባቢ ነበር። በዚህ ወቅት ምሥራቅ ጎጃም 80 ሺ ተማሪ ነበረው። በ1992 ዓ.ም ለቅቀው ሲወጡ ግን 280ሺ ተማሪ በትምህርት ገበታው ላይ ይገኝ ነበር። ቀን ከሌሊት ነበር የምንሠራው ይላሉ፤መጀመሪያ ለጥራት አልነበረም ሩጫቸው፤ ፍላጎታቸው ልጆች ትምህርት ቤት እንዲውሉ ነበርና ባሕር ዛፍ በመቁረጥ የተማሪ መቀመጫ እየሠሩ፣ በጭቃ ምርግ ክፍሎችና ቤቶችን እያዘጋጁ ነው ትምህርት ቤት ያቆሙት ።በሌላውም እንዲሁ ነበር አሠራራችን ይላሉ፡፡
በግብርናውም የእሳቸው 16 ወረዳዎች የሚወስዱት ማዳበሪያ ከ12ሺ አይበልጥም ነበር። በ1983 ዓ.ም ወደ ወረዳዎች ሲገቡና በ1992 ሲወጡ 52 ኪሎ ግራም የነበረውን 59 ኪሎግራም ነበር የደረሰው። 7 ኪሎ ብቻ ነበር ጭማሪው።
አስተዳዳሪ ሆነው አንድም ቀን ፖሊስ አጅቧቸው አያውቅም። እዛው እያሉ ዞን አስተዳዳሪ ሆነዋል። የደበረማርቆስ ዞን አስተዳደሪነትን ከ1985 ዓ.ም.አስከ 1986ዓ.ም ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ሠርተዋል። በ1992፤በ1997፤በ2003እና በ2007 በተደረጉት ምርጫዎች በመሳተፍ አሸንፈዋል፡፡ በመጨረሻም 21 ዓመት ካገለገሉ በኋላ 2013 ዓ.ም ጡረታ ወጥተዋል፡፡
የፓርላማ ቆይታ፣ ክርክርና ውይይት
ፓርላማ እያሉ የገጠማቸውን አስመልክተውም ሲያስታውሱ የማስወረድ ሕግ ሲመጣ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ነበር የሠሩት፡፡ሕጉ ራሱ ሲመጣ ጀምሮ የፖለቲካ ፍላጎትና ስሜት ተጭኖት ስለነበርና ሰብዓዊ መብትን ምክንያት በማድረግ ነበር ጫና የተፈጠረው ይላሉ።
ያልተፈለገ እርግዝናን በመከላከል በኩል የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ቢሠሩ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ቢያስተምሩ፣ ያልተፈለገ እርግዝና ከተከሰተ በኋላ ግን የማስወረድ መብት ይኑር በሚል ብዙ ተሄዶበታል። ከብዙ እልህ አስጨራሽ ሙግትና ክርክር በኋላ ግን ሕግ ሆኖ ወጣ።ይህ የማስወረድ ሕግ ወደ ፓርላማ ሲመጣ የሕግና አስተዳደር ኮሚቴ ነበሩ እሳቸው። በመጨረሻ በተደረገው እልህ አስጨራሽ ጥረት ሕግ ሆኖ በመጨረሻ ወጣ፡፡
አቶ ተሾመ ሃያ አንድ ዓመት በምክር ቤት ሲቆዩ ወደ ስድስት በሚሆኑ ኮሚቴዎች ውስጥ አባልና አመራር በመሆን ሠርተዋል።
ከመጀመሪያው ጀምሮ ብዙ ዘመን ፓርላማ በመቆየታቸው ተሞክሯቸውን ለአዳዲሶቹ ተመራጮች ማካፈልም ተቀዳሚ ስራቸው ነው። የፓርላማውን ሁኔታም በማሳየትና በማስረዳት አስተዋፅዖ አበርክተዋል። እንደሳቸው አገላለፅ በፓርላማው ብዙ ዓይነት ክርክሮች ይደረጋሉ። ክርክር መልካም ቢሆንም ገንቢነቱ ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ሰው ፍረጃ ወስጥ የሚገባበት አጋጣሚ ሰፊ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ይህ ደግሞ ን ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል ይላሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ያለው የፓርላማ ሂደትም ከዚህ የጸዳ ቢሆን ግቡን ይመታል በማለት አቶ ተሾመ ከልምዳቸው በመነሳት አስተያየታቸውን ይስጣሉ።
በፓርላማ ቆይታቸው የገረማቸውንና በጣም ያሳዘናቸውን ገጠመኝ ሲገልጹም “….በ1996 ወይም 1997 ላይ አንድ ባለስልጣን ለኦዲት ተጠራና በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ ምን እንደሚመስል ተጠየቀ። መልሱ፣- “የኔ መሥሪያ ቤት እኮ የሙያ መሥሪያ ቤት እንጂ የፖለቲካ መሥሪያ ቤት አይደለም” አለ። የኢህአዴግ የፖለቲካ ቢሮ ባልደረባ እና የምክር ቤት አባል ነው።
ሆኖም በፖለቲካ አስተሳሰብ የሴቶች ጉዳይ ዋነኛ የፖለቲካ ጉዳይ መሆን ሲገባው ይህን የመሰለ መልስ መስጠቱና ከገዢው ፓርቲም ጋር የጠበቀ ቁርኝት ስለነበረው ምንም አለመባሉ እስካሁን ያንገበግበኛል፡፡ብዙ ጊዜ የምንናገረውና በተግባር የምንፈጽመው ስለሚለያይ ይቖጨኝ ነበር›› ሲሉ አቶ ተሾመ በምክር ቤት ቆይታቸው የታዘቡትን በጥቂቱ ይናገራሉ፡፡
ምክር ቤቶች የሀሳብ መንሸራሸርያ መድረኮች መሆን ይገባቸዋል፡፡የምክር ቤት አባላት ታማኝነታቸው ለህሊናቸውና ለመረጣቸው ህዝብ ነው፡፡ስለዚህም ሁልጊዜ ለህዝብ ጥቅም መቆም አለባቸው፡፡
አቶ ተሾመ እንደሚያምኑበት የምክር ቤት አባላት
በምክር ቤት በሚቆዩበት ጊዜ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ላይሆንላቸው ይችላል፡፡የሚጎረብጣቸው ጉዳይም ሊከሰት ይችላል፡፡ሆኖም ለህዝብ ጥቅም የቆሙ ናቸውና የሚደርስባቸውን ፈተና በመጋፈጥ ከህዝብ ጎን መቆም እንደሚኖርባቸው ይናገራሉ፡፡
እርሳቸው በቖዩባቸው 21 አመታት ህሊናን የሚፈታተኑ፤በራስም ላይ አደጋ የሚያስከትሉ በርካታ ፈተናዎችን ተጋፍጠው እንዳለፉ ያስረዳሉ፡፡በተለይም ከገዢው ፓርቲ አስተሳብ ወጣ ያሉ ሃሳቦችን መስጠት ወይም በሌሎች አካላት የሚሰጡ አስተያየቶችም መደገፍ ዋጋ ያስከፍል ነበር፡፡ሆኖም ከህዝብ የሚበልጥ ጉዳይ የለምና በርካታ ተጽዕኖዎች ቢኖሩም ሁኔታዎችን እንደአመጣጣቸው እያለፉ 21 አመታትን በትግል መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡
በ21 ዓመታት የምክር ቤት ቆይታቸው ከታዘቧቸው ጉዳዮች መካለል ዋነኛው የምክር ቤት አባለት በህገመንግስቱ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣትና የህዝብን ጥያቄ ለማንጸባረቅ በሚያደርጓቸው ጥረቶች ሁሉ ከተለያዩ አካላት ዛቻዎችና ማስፈራርያዎች ይደርስባቸው እንደነበር ነው፡፡
አንዳንድ የፓርላማ አባላት ዛቻና ማስፈራሪያዎችን በመፍራት ከመናገር ቢቆጠቡም ሌሎች ደፋሮች የህዝብን ጥቅም በማስቀደም የመሰላቸውን ሃሳብ ከመሰንዘር ቦዝነው እንደማያውቁ ያስረዳሉ፡፡በተለይ አዳዲስ የፓርላማ አባላት በምርጫ አሸንፈው ምክር ቤት ሲገኙ ቀድመው የጠበቁትና ሆኖ የሚገኘው ስለሚለያይባቸው ቶሎ ተስፋ የሚቆርጡም እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውይይትና የምክክር ቦታ መሆን ሲገባው መሾም ፤መሸለም ለሚሹ ሰዎች የፖለቲካ ነጥብ ማስቆጠሪያ የሚሆንበት አጋጣሚ እንደሚኖር አቶ ተሾመ ይናገራሉ፡፡
ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳቱን በማራገብ እና በእሰፈጻሚው አካል ዕይታ ውስጥ በመግባት ለመሾም የሚጥሩ በርካታ ሰዎች መኖራችውን ያስረዳሉ፡፡የእነሱን አስተሳሰብ መታገል በራሱ ፈተና ነው ይላሉ፡፡
በሌላም በኩል የምክር ቤት አባላት ህዝብ የወከላቸው እንደመሆኑ መጠን ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ በላይነትን በማስፈን፣ መንግሥትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በመሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መሟላት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያድሱና እንዲተገብሩ ልዩ ትኩረትና ክትትል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ምክር ቤቱ አዋጆችን በማጽደቅ ይጠመድና አስፈጻሚውን ችላ ሲለው ይታያል፡፡ይህ ሲሆን ደግሞ መልካም አስተዳደር ይሰተጓጎላል፤ሌብነት ይንሰራፋል አልፎ ተርፎም ሰብአዊ መብት ጥሰት ይበረክታል፡፡
ስለሆን የተለያየዩ አዋጆችን ከማጽደቅ በላይ ሰው ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ማተኮሩ የበለጠ ውጤታማ ያደርጋል። በየአካባቢው ያሉ የመልካም አስተዳድ ችግሮችን እየነቀሱ እንዲስተካከሉ ማድረግ የእያንዳንዱ ምክር ቤት አባል ኃላፊነት ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ አጥፊዎች ላይ ተገቢው አርምጃ እንዲወሰድ ማመላከትና ህዝብን የሚያንገላቱ አካላት ከቦታቸው እንዲነሱና እንዲጠየቁ ማድረግ የምክር ቤት አባላት ግዴታ ነው፡፡ነገር ግን በወቅታዊ ስራዎች በመጠመድ ህዝቡ የሚማረርባቸው ጉዳዮች ችላ ሲባሉ ይታያሉ፡፡
ሌላው እና ዋነናው ጉዳይ ሙስና ነው፡፡አንድ ሰው በምርጫ አሸንፎ ምክር ቤት ሲገባ ከተጣሉበት ኃላፊነቶች መካከል የሀገርና የህዝብን ሀብት መጠበቅ አንዱ ነው፡፡አስፈጻሚው አካል ያገኘውን አጋጣሚ ተተቅሞ ሲዘርፍና የሀገርና የህዝብ ሃብት ሲያባክን የምክር ቤት አባላት ለምን ብለው መጠይቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡አንዳንድ ጊዜ እኮ የሚሰርቁ ሰዎች ሲሾሙና ለበለጠ ኃላፊነት ሲታጩ እታዩ ዝም ተብለው ሲታለፉ ይታያል፡፡እነዚህ ሌቦች የበለጠ እንዲዘርፉና የሀገርና የህዝብ ሀብት እንዲየባክኑ እድል ሲሰጣቸው የምክር ቤት አባላት ታግለው ሹመታቸውን ማስቀረት ይጠበቅባቸዋል፡፡ግዴታቸውም ጭምር ነው፡፡
አቶ ተሾመ የምክር ቤት አባላት በነበሩባቸው አራት የምርጫ አመታት በተለያዩ ወቅቶች ከሕግ ውጪ የተፈጸሙ ግድያዎች፣ ከመጠን ያለፈ የኃይል አጠቃቀም፣ የዘፈቀደና ከፍርድ ወይም ክስ በፊት ያለ የተራዘመ እስር፣ በጋዜጠኞችና በፖለቲካ ተቃዋሚዎች ላይ ያነጣጠረ እስራት እና የአንዳንድ እስር ቦታዎች አያያዝ ሁኔታ አሳሳቢነት እየጨመረ በመምጣቱ የምክር ቤቱን ልዩ ትኩረት አግኝቶ ውይይት ሲካሄድባቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በጦርነትና በግጭት እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች የተጎዱ የመሰረተ ልማት አውታሮችን መልሶ ከማቋቋም ጎን ለጎን ሀገራዊው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታና የኑሮ ውድነት፤ እንዲሁም በልዩ ልዩ ማህበራዊና መንግሥታዊ አገልግሎቶች አሰጣጥ የሚሰማው የሕዝብ ቅሬታ ለሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ አደጋና ስጋት በመሆኑ የቅርብ ክትትል የሚሹ ጉዳዮች መሆቸውንም ለአስፈጻሚው በየጊዜው ሲያሳስቡ እንደቆዩ ተናግረዋል፡፡ አንዳንዶቹ ውጤት ሲያመጡ ሌሎቹ በአስፈጻሚው አካል ቸልተኝነት ሳይፈቱ መቅረታቸውን ያስታውሳሉ፡፡
የግል ሕይወት
አብራቸው በትግል ከነበረች ጓደኛቸው በ1983 ዓ.ም ትዳር መስርተው አራት ልጆች አፍርተዋል።በጣም የሚያስደስታቸው ራሳቸውን ሆነው መገኘታቸው ነው። ሰው ለማስደሰት ወይ ለማስከፋት ያደረጉት ምንም ነገር እንደሌለ ይናገራሉ። የእርሳቸው መርህ “ለሚስቴ ወይም ለልጆቼ የማልነግራቸው ሀብት ሊኖረኝ አይገባም” የሚል ነው። በንፅሕና መኖራቸው ደስ ያሰኛቸዋል። ይህንን ባላደረግሁ የምለው አንድም ነገር የለኝም ይላሉ። በመታገላቸው ደስተኛ ናቸው። ከህዝብ የተረከቡትን አደራ በተቻላቸው አቅም ሁሉ ለህዝብ ጥቅም አውያለሁ ይላሉ። የሰው ግዴታው መጀመሩ ነው። ይህ ባይሆን ኖሮ የትዳር አጋርህ እንኳ አትመሰክርልህም የሚለው መዝጊያ ቃላቸው ነበር፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥር 19 ቀን 2016 ዓ.ም