የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖችና የውጭ ተጫዋቾች ተፅእኖ

በዘንድሮው የ2023 አፍሪካ ዋንጫ ከ24 ሀገራት 630 ያህል ተጫዋቾች ብሔራዊ ቡድኖቻቸውን ወክለው እየተሳተፉ ይገኛሉ። ከእነዚህ ተጫዋቾች መካከል 200 ያህሉ ተጫዋቾች የተወለዱት ከአፍሪካ ውጪ ነው። ይህም በአፍሪካ ዋንጫ አዲስ ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቧል። ተጫዋቾቻቸው ሙሉ በሙሉ በአፍሪካ የተወለዱ ሀገራት ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽና ናሚቢያ ብቻ ናቸው።

በአፍሪካ ዋንጫው እየተሳተፉ ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል 104ቱ በፈረንሳይ የተወለዱ ናቸው። 24 ተጫዋቾች በስፔን፣ 15ቱ በእንግሊዝ፣ 13ቱ በኔዘርላንድስ፣ 10ሩ በፖርቹጋል የተወለዱ ናቸው። በዴንማርክ፣ አየርላንድ፣ ስዊድን፣ ስዊዘርላንድና በሌሎችም ከአፍሪካ ውጪ የተወለዱ ተጫዋቾች በአፍሪካ ዋንጫው ለተለያዩ ብሔራዊ ቡድኖች ተሰልፈዋል።

ዋንጫውን ለማንሳት ትልቅ ግምት የተሰጣት ሞሮኮ ከሀገሪቱ ውጪ የተወለዱ በርካታ ተጫዋቾችን በብሔራዊ ቡድኗ በማካተት ቀዳሚ ነች። የአትላስ አናብስት ባለፈው 2022 የዓለም ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ የሆነች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሀገር ስትሆን መሠረታቸውን አውሮፓና ሌሎች ሀገራት ያደረጉ 18 ያህል ተጫዋቾች በብሔራዊ ቡድኑ መካተታቸው ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው።

የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጇ ኮትዲቯርን በሦስተኛው የምድብ ጨዋታ 4ለ0 በማሸነፍ አስደናቂ አቋም ያሳየችው ኢኳቶሪያል ጊኒ ከሞሮኮ በመቀጠል 17 ተጫዋቾቿ የተወለዱት ከሀገሪቱ ውጪ ነው። ዲሞክራቲክ ኮንጎ ደግሞ በ16 ተጫዋቾች ተከታዩን ደረጃ ትይዛለች። ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ያላቸው እንደ አልጄሪያ፣ ቻምፒዮኗ ሴኔጋል፣ ናይጄሪያ፣ ኮትዲቯርና ሌሎችም በርካታ ሀገራት ወሳኝ የሆኑ በርካታ ተጫዋቾቻቸው መሠረታቸው ከአፍሪካ ውጪ ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአፍሪካ ዋንጫ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ገንብተው እየታዩ የሚገኙ እንደ ኬፕቨርዴ ዓይነት ሀገራትም በውጭ ሀገራት የተወለዱ ተጫዋቾቻቸውን በመጠቀም ውጤታማ እየሆኑ ይገኛሉ።

እነዚህ ሀገራት በውጭ የተወለዱ ተጫዋቾቻቸውን በብሔራዊ ቡድናቸው መጠቀማቸው ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ብቅ ለማለታቸው ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው በስፖርቱ ባለሙያዎች ተደጋግሞ የተነገረና የሚያስማማ ጉዳይ ነው። ዋናው ቁም ነገር ተጫዋቾቹ በውጭ ሀገራት መወለዳቸው አይደለም። ተጫዋቾቹ የዳበረ የእግር ኳስ ባህል፣ በዘመናዊ ሥልጠናና ሳይንሳዊ መንገድ መገራታቸው ለየቡድኖቻቸው የተሻለ ነገር እንዲያበረክቱ እንዳስቻላቸው የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም። ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ተጠቃሚ መሆን ካልቻሉ ሀገራት አንዷ ነች። ባለፈው አፍሪካ ዋንጫ ከተሳተፉ 24 ሀገራት መካከል አንድም ከአፍሪካ ውጪ የተወለደ ተጫዋች ያላካተተችው ኢትዮጵያ ብቻ ነበረች።

ለዚህም ጥምር ዜግነት አለመፍቀዷ ዋነኛው ምክንያት ሆኖ ሲያከራክርም ቆይቷል። ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ባልተናነሰ በአውሮፓና ሌሎች የተሻለ የእግር ኳስ ደረጃ ያላቸው ሀገራት ውስጥ ተወልደው በትልቅ ደረጃ የሚጫወቱ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በርካታ ናቸው። እነዚህ ተጫዋቾች በርካቶቹ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጫወት ፍላጎታቸውን ሲያሳዩ በተደጋጋሚ ታይቷል። ይሁን እንጂ ከኢትዮጵያ ውጪ ያላቸውን ፓስፖርት ቀደው ለመምጣት ፍላጎት የላቸውም።

እነዚህ ተጫዋቾች ለኢትዮጵያ የመጫወት ፍላጎት የሚያሳዩት ሀገሪቱ እንደ አፍሪካ ዋንጫ ያሉ ታላላቅ መድረኮች ላይ ስትሳተፍ እንጂ በማጣሪያ ውድድሮች ላይ ፍላጎት የላቸውም ተብለው ይወቀሳሉ። በዚህ ሃሳብ የማይስማሙ አሰልጣኞች ተጫዋቾቹን ወደብሔራዊ ቡድኑ የመጥራትና የመመልከት ፍላጎት እንደሌላቸው ሲናገሩ ይደመጣሉ።

የኢትዮጵያ ሕግና የተጫዋቾቹ ፍላጎት ለየቅል መሆኑ ብሔራዊ ቡድኑ ይህን ዕድል መጠቀም እንዳልቻለ ፌዴሬሽኑ በተለያየ ጊዜ ሲገልጽ ይደመጣል። በውጭ የሚጫወቱ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ከያሉበት በመመልመል ለዋልያዎቹ እንዲጫወቱ ትልቅ ጥረት በማድረግ የሚታወቀውና ለኢትዮጵያ ቡና የተጫወተው ትውልደ ጀርመናዊው ዴቪድ በሻህ ግን ይህ ምክንያት ሊሆን እንደማይገባ ደጋግሞ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይህን ዕድል መጠቀም እንዲችል በሚዲያና በሌሎች የስፖርቱ ባለሙያዎች አማካኝነት ከብዙ ውትወታ በኋላ በቅርቡ በውጭ የተወለዱ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን መጠቀም የሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ጥረት እንደጀመረ ይታወቃል።

እነዚህ ተጫዋቾች የውጭ ፓስፖርታቸውን ሳይቀዱ የኢትዮጵያን ጥምር ዜግነትም ሳያገኙ ለብሔራዊ ቡድኑ መጫወት የሚችሉበት ተስፋ ከወደ ፊፋ ተሰምቶ ነበር። ይህም ተጫዋቾች መጀመሪያ የያዙትን ፓስፖርት ሳይቀዱ በስፖርት ፓስፖርት (ስፖርት ቪዛ) የሚጫወቱበት መንገድ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ጉዳይ በራሱ ውስብስብና አሳሪ ሂደቶች ያሉት በመሆኑ ብዙ ርቀት ሳይጓዝ ተደፋፍኖ ቀርቷል።

ፊፋ እአአ 2014 ባወጣው አዲስ መመሪያ መሠረት አንድ ተጫዋች በእናቱና በአባቱ አሊያም በአያቶቹ ኢትዮጵያዊ ከሆነና ላደገበት ሀገር ዋና ብሔራዊ ቡድን ካልተጫወተ ለኢትዮጵያ የመጫወት መብት እንዳለው ያስቀምጣል። ይህም ቢሆን እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ጥምር ዜግነት ለማይፈቅዱ ሀገራትና የውጭ ፓስፖርታቸውን ለመቅደድ ፍቃደኛ ላልሆኑ ተጫዋቾች ጉዳይ መፍትሔ ሆኖ እየታየ አይደለም።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ጥር 18/2016

Recommended For You