መሆን ወይስ አለመሆን፤ ጥያቄው ይሄ ነው፤
(በሼክስፒር “ሐምሌት” ውስጥ ሐምሌት እንደተናገረው)
ይህ የሼክስፒር 400 ዓመታትን የዘለለ ኃይለቃል የበርካታ መጻሕፍት ርእስ፣ የበርካታ ጸሐፍት ማእከላዊ ጭብጥ፤ የበርካታ ሀሳቦች ማራመጃ፣ የበርካታ ማንነቶች ማንፀባረቂያ ∙ ∙ ∙ በመሆን እዚህ 21ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የዘለቀ ገዥ አስተሳሰብ መሆኑ ግልፅ ነው።
በዚህ በቀሲስ ሼክስፒር፣ ዝነኛ ያንድ ሰው ዘመን ተሻጋሪ ንግግር (soliloquy) እና ዘመንን የዘለለ “ጥያቄ” ውስጥ ያሉት ሁለት እርስ በእርሳቸው የሚቃረኑ ሀሳቦች (“መሆን” እና “አለመሆን”) በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ይዞታ በተመለከተ ከላይ ያልነው እንዳለ ሆኖ፤ በሀገራችንም እራሱ ስራው በራሳችን ሰዎች (ለምሳሌ ጸጋዬ ገብረመድህን፣ ተስፋዬ ገሠሠ …) ተተርጉሞ ከማንበብና ማድነቃችን በተጨማሪ፣ በበርካታ ገጣሚና ጸሐፍቶቻችን ሲነሳ ቆይቷል፤ ለበርካታ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ማጠንጠኛነት ሲውልም ተመልክተናል። በደንብ አልተከታተልኩትም እንጂ አንድ “ከመሆን አለመሆን ካለመሆን መሆን እስራት ነው!″ የሚል አንድ በሃይማኖት ላይ ያተኮረ ቲቪ ፕሮግራምም በክፍሎች ተከፋፍሎ መተላለፉንም አስታውሳለሁ።
መኖር አለመኖር ካለመኖር መኖር ሳይሻል አይቀርም፣
ከመኖር ተስፋ አለ ካለመኖር ምንም።
የሚለውን (ዜማ?)ም ማንሳት፤ አንስቶም ከመሆን/አለመሆን ጋር ምን አንድነት/ልዩነት እንዳለው በማሰላሰል ጉዳዩን ውሃ እንዲቋጥር ማድረግ ይቻላል። በተለይ ከገጣሚያኑ መካከል አንዱም ኤፍሬም ስዩም ነው።
ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም በ“መሆን አለመሆን” ግጥሙ ስር፤
በመሆንና ባለመሆን፣ በማድረግና ባለማድረግ፣
በጣምራ ግጭቶች ውስጥ መውደቅ ነው
ሰው የመሆን ትልቅ ሕግ፡፡
ሊኖሩት በማይወዱት ጽድቅ፣ ሊፈጽሙት በማይሹት ስህተት፣
በጣምራ ግጭቶች መሀል መቆም ነው ሰው የመሆን ሰውነት፡፡
ይሄ ሁሉ ፍጡር፣ በፍጥረት መድረክ ላይ የሚርመሰመሰው፣
ላንዲት ቅጽበት እንኳን ሰው ሆኖ አያውቅም፣ ሰው ሊሆን ጽንስ ነው፣
ሰው እስኪሆን ድረስ አንዳንድ ጊዜ አምላክ አንዳንዴ ሰይጣን ነው።
በማለት ያሰፈራቸው ስንኞች (ወይም ያሰነዘራቸው ሃሳቦች) በቀላሉ የሚታዩ ሳይሆኑ (የራሱ ሃሳብ፣ የሄደበት መንገድ የገጣሚው ሆኖ)፣ ሰው በመሆን እና ባለመሆን መካከል ምን ያህል መዋዥቅ እንዳለና “በጣምራ ግጭቶች″ ስር መውደቅን እንደሚያስከትል፤ ወደ መሆን ለመምጣትም ምን ያህል ስቃይን እንደሚያሳይ የሚያመለክቱ፤ መዋዥቅን በአማራጭነት መያዝ የተሻለ (ወይም የግድ መሆኑን የሚጠቁሙ) ናቸው።
በዚህ አንጓ መሰረት ሰው በሁለት ፅንፎች መሀል ወድቋል፤ በእነዚህ ስንኞች መሰረት (ራስን) የመሆንና አለመሆን ውሳኔ እጅጉን ከባድ ነው ማለት ሲሆን፤ የመሆን/አለመሆን ጉዳይ ግን የሞራል ጉዳይ ነው (“በጣምራ ግጭቶች መሀል መቆም ነው ሰው የመሆን ሰውነት፡፡”) ማለት አይቻልም። የመሆን አለመሆን ጉዳይ የመውደቅ አልያም የመነሳት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የጠንካራ ስብእና ጉዳይም ጭምር አይደለም ማለት ነው።
ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን የሼክስፒርን “To be, or not to be: that is the question” ከምንጬ እንዴት አድርጎ ወደ ሀገራችን እንዳሻገረው ቀጥለን እንመልከት∶-
መሆን ወይም አለመሆን እዚሁ ላይ ነው ችግሩ፣
የእድል የፈተና አለንጋ ሲወናጨፍ ወስፈንጥሩ፣
በሀሳብ ግርፊያ መሰቃየቱ ችሎ ታፍኖ ማደሩ፣
ወይስ የመከራን ማእበል ተጋፍጦ ጦርን ከጦሩ፣
ተጋትሮ ወግቶ ድል መምታት እስኪነቀል ከነስሩ፣
የቱ ነው ለሰው ልጅ ክብሩ።
መሞት መተኛት ማንቀላፋት እስከመቼም ባለመንቃት፣
ከስንቱ ቆሽት መቃጠል ማምለጥ ሰው ከመሆን ስጋት፣
የሚፀለይለት ሲሳይ ነው የምኞት ሁሉ አናት።
ለእንቅልፍ ሲባል መሞቱ፣
በሞት እፎይታን ማግኘቱ፣
የሰላም ህልም ማየቱ።
ሕልም አልኩ እንዴ? እሱ ነው ጉዱ፣
በሞት የእንቅልፍ ዓለም ደሞ የሕልም ወግና ሽርጉዱ።
ቢኖር የሰላምን ድባብ የፀጥታን እሹሩሩ፣
የሚያውክ ዓይነት አይሆንም ይታገዳል መጣረሩ፣
ይኽ ሟች ጉፋያ ስጋ ሲደመደም መቃብሩ፣
እዚያ ላይ ይገታል ክብሩ፣
ኑሮ የሚሉት ውጥንቅጥ እንቅልፍ ላይ ነው ድንበሩ።
(ከሀምሌት የመጨረሻ ህመም በጥቂቱ ዊልያም ሼክስፒር እንደ ጻፈው፤ ሎሬት ፀጋዬ እንደተረጎመው)
ሼክስፒር ገና ድሮ አስቀድሞ እንደደረሰበት የሰው ልጅ በ“መሆን” እና “አለመሆን” መካከል ተወጥሮ መከራ-ፍዳውን ሲያይ የሚኖር ፍጡር ነው። ይሁን እንጂ፣ ባለ ቅኔው ከዚህ ከተወጠረ ተቃርኖ ውስጥ በቀላሉ መውጣት እንደሚቻልም ያመለክታል፡፡ ያ ማለት የቀረበው ምርጫ ሁለት ሲሆን ያለው የመምረጥ እድል ደግሞ አንድ ብቻ ሆኖ መጥቷል። እሱም “መሆን″ ወይም ″አለመሆን″ ነው።
የኤፍሬም “መሀል መቆም″ ይሉ ድምዳሜ እዚህ ጋ የሚሰራ አይሆንም ማለት ነው። እሱ ራሱ (ቀሲሱ) “ጥያቄው ይሄ ነው″ እንዳለው፤ ሁለቱንም መሆን አይቻልምና አንዱን መምረጥ የግድ ሲሆን፣ የመረጡትን ሆኖ መገኘት ደግሞ ሌላው ፈተና ነው። ለምሳሌ “አማኝ መሆን” ወይም “አማኝ አለመሆን”፤ እዚህ ጋ ምርጫችን “መሆን” ከሆነ “ሆኖ መገኘት የግድ ይሆናል ማለት ነውና ጉዳዩ አውቶማቲክ በመሆኑ ጊዜ አይሰጥም። (ካስፈለገም፣ “መሆን ወይም አለመሆን″ን “To be or not to be” means “To live or not to live” (or “To live or to die” በማለት የበየኑትንም እዚህ ላይ አስታውሶ ማለፍ ይቻላል።)
አንድ ሰው “ሴት″ ወይም “ወንድ″ እንጂ ሴትም አለመሆን፤ ወንድም አለመሆን፤ ወይም፣ ሴት እና ወንድ የመሆን መብትም አቅምም የለውም። ያለው አቅምም ሆነ ምርጫ ወይ መሆን፤ አልያም አለመሆን ነው። በ“መሆን” እና በ“አለመሆን” መካከል ምንም አይነት “ወርቃማ መንገድ” የለም። ማለትም፣ የአርስቶትል “ወርቃማው መንገድ” (ጎልደን ሚን) ፍልስፍና እዚህ ጋ አይሰራም። እሚሰራው የሼክስፒር “መሆን ወይም አለመሆን፤ ጥያቄው ይሄ ነው” (Hamlet, Act III, Scene I) የሚለው ብቻ ነው።
ከእምነት ወጥተን ወደ ርዕዮት ዓለምም ስንመጣ ጉዳዩ (የምርጫው) ያውና ተመሳሳይ ውሳኔን ሲሻ የምናገኘው ሲሆን፣ “ማርክሲስት መሆን ወይስ አለመሆን?″ የሚለው የ1960ዎቹ እና 70ዎቹ መጀመሪያ ምርጫና ፍጥጫ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።
በዚያ ክፉ ዘመን (ክፉው ዘመኑ አልነበረም) ምርጫዎች ሁሉ ከመኖር እና አለመኖር፣ ከመሞት እና አለ መሞት ጋር የተያያዙ ነበሩና ዝም ተብሎ ብድግ በማለት “ማርክሲስት መሆን″፤ ወይም፣ “ማርክሲስት አለመሆን” የሚባልበት ጊዜ አልነበረም። መሀል ላይ ቆሞም በሁለት ቢላዋ ቁርጥ የሚቆረጥበት፤ ዝልዝል የሚዘለዘልበትም አይደለም። ብቻ መሆን ወይም አለ መሆን የግድና የወቅቱ ጥያቄ ነበር። (“ከኔ በላይ ስለምታውቁት እዚሁ ላይ ትቼዋለሁ″ ያለው ማን ነበር?)
የዛሬው ርእሰ ጉዳያችንን ሰፋ ባለና አስረጂ በሆነ መግቢያ ስንጀምረው ወደ አንድ ዐቢይ ጉዳይ እየመጣን መሆኑን እንደሚያስታውቅብን በማወቅ ሲሆን፤ እሱም የአሁኑ ዘመን “መሆን/አለመሆን”ን፤ በተለይም “ራስን መሆን″ን አጥብቆ የመፈለጉ ጉዳይ ነው። (እዚህ ላይ የ“አለመሆን″ን ሌላኛ ገፅታ፣ ለምሳሌ “ሌባ አለመሆን″ን ዘንግተን አይደለም።)
ዛሬ ዛሬ የብዙዎቻችን መሰረታዊ ችግር “ራስን መሆን” ወይም “ራስን አለመሆን” (ወይም፣ መምሰል) እንደ ሆነ ከራሳችንም አልፎ ለማንም ግልፅ ነው። ይህ ደግሞ የአንድ ሰው፣ የአንድ አካባቢ ወይም ሀገር ችግር ሳይሆን (ምናልባትም ግሎባላይዜሽን ይዞት የመጣው ጣጣ ሊሆን ይችላል) የብዙዎች ነው።
“ለመሆኑ ራስን በመሆን እና ባለ መሆን መካከል ምን ልዩነት አለ?” የሚል ጋራገር የሚመስል፣ ግን ደግሞ በጣም ከባድ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። እውነት ነው፣ ይነሳ ዘንድም ተገቢ ነው። ይነሳ ዘንድ ተገቢ ይሁን እንጂ መልሱ ጥያቄውን የማንሳት ያህል ቀላል አይደለም። ቀላል ላለመሆኑ ምክንያቱ ደግሞ ችግሩ ወይም ጥያቄው ከ400 ዓመት በፊት ጀምሮ የነበረና ሼክስፒርን በሚያካክሉ የሰማይ ስባሪ ጸሐፍት ዘንድ ከመነሳቱም በላይ፣ አሁንም ድረስ አጥጋቢ ምላሽን ሳያገኝ እዚህ ድረስ መዝለቁ ነው።
ብዙ ጊዜ ሲባል እንደሚሰማው ቢያንስ በሁለት ሰዎች መካከል በሚደረግ ክርክር መሀል “እራስህን ሁን” የሚል ወቀሳ አከል አስተያየት ሲሰነዘር ይሰማል። ይህም ቀላል “አስተያየት” አይደለም። ምክንያቱ ደግሞ ያ አስተያየት የተሰጠው ሰው በመሆን እና አለመሆን ዳይሌማ ውስጥ ተዘፍቋል ማለት ነውና አስተያየቱ ከዛ ይወጣ ዘንድ የተሰነዘረ ነው።
“ራስህን ሁን” ማለት “ራስህን አይደለህም” ማለት ነው። “ራስህን አይደለህም” ማለት ደግሞ ሌላ አካል ከጀርባ ሆኖ ይነዳሃል፤ ይዘውርሀል፤ እየተመራህ ያለኸው በራስህ አስተሳሰብ፣ አመለካከት፣ እውቀት ∙ ∙ ∙ ሳይሆን በሌላ ሰው (ምናልባትም በማታውቀውና በተቃራኒህ) ሀሳብ ነው ማለት ነው።
ይህ ደግሞ በየትኛውም መስፈርት የሚያዋጣም፤ የሚመከርም ባህርይ አይደለም። “ከራስህ ጋር ሁን” ሰውየው ከራሱ ጋር አይደለምና ከዚህ የማንነት ቀውስ ውስጥ ይወጣ ዘንድ የስነባህርይ ተመራማሪዎች ሳያሰልሱ ይመክራሉ።
ከላይ በስሱም ቢሆን “ራስን አለመሆን” ማለት “መምሰል ማለት ነው” ብለናል – ሌላውን፣ ራስ ያልሆነን አካል መምሰል። ይህ ደግሞ እንኳን በእውኑ ዓለም በትያትርና ድራማው ዓለምም የሚመከር አይደለም። በመሆኑም ነው “ተዋናይ(ት) እከሌ(ሊት) እኮ ሲ(ስት)ተውን መስ(ላ)ሎ ሳይሆን ሆ(ና)ኖ ነው” የሚል አስተያየት በአድናቆት መልክ በኪነጥበብ ቤተሰቦች ዘንድ ሲሰነዘር የሚሰማው።
የሰዎች የህይወት ተሞክሮም ሆነ ጤነኛ የህይወት ኡደት /ሳይክል/ እንደሚያሳየን፣ “መሆን” ምንም ጊዜ አዋጭ ነው፤ ይዘገይ ይሆናል እንጂ አያከስርም። ዜማው፤
እንደኮራ ሄደ እንደተጀነነ
ጠጅ ጠጣ ሲሉት ውሃ እየለመነ
ሊጋባው በየነ
እንዳለው፤ እንዳማሩ መኖር የሚገኘው፣ እንደ ተጀነኑ መሄድ የሚቻለው በመሆን እንጂ ባለመሆን አይደለም። በመምሰል ጠጅ ሊገኝ ይችላል እንጂ ሌላ ምንም አይገኝም፣ በመሆን ግን ንፁህ ውሃን ከነ ሙሉ ጤንነቱ የሚከለክል ማንም የለም – ልክ እንደ ሊጋባው!!!
ዘመናችን በመምሰል እንጂ በመሆን በኩል የተሳካለት አይመስልም።“አስመሳዮች በዙ” የሚለው አስተያየት የትም ቢኬድ የሚሰማ መሪር አስተያየት ነው። “ሰው ከአምላኩ ተጣላ“ የሚለውም እንደዛው ሲሆን፣ የዚህ አስተያየት ክፋቱ የጥፋቱ ወሰን-ዲካ ከዚህ መለስ ሊባል የሚቻል አለመሆኑ ነው። እስከ ጭካኔዎች ጥግ ድረስ ሁሉ ይዘልቃል።
ጉዳዩ እንዲህ በቀላሉ እዚህ አንስተን እዚሁ ልንጥለው የምንችለው አይደለም። ብዙ ያስኬዳል። አቶ አማረ ማሞ እንዳሉት ያመራምራል፤ ያወያያል፤ ያነጋግራል። ይሁን እንጂ፣ እኛ በማጠቃለያ አንቀፆቻችን የሚከተለውን እንላለን።
የዛሬዋ ዓለም ለድሮ ሰዎች የምትመች አይደለችም የሚሉ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። “ምክንያት?” ሲባሉ ያኛው ራሱን የነበረ፣ ራሱን የሆነ እና ራሱን የወከለ ነበር፤ ተጋላቢ ጌኛም ሆኖ አያውቅም።
የአሁኑ ራሱን ያልሆነ፤ ሌላውን የመሰለ፤ በመሆን እና ባለ መሆን መካከል እየዋዥቀ ያለ፤ የሚጋልበው ፈረስ ከመብዛቱ የተነሳ ለቁጥር ማታከቱ፤ አቋሙ ሁሉ “እናቴን ያገባ ሁሉ አባቴ ነው“ የሆነ በመሆኑ ነው የሚል ነው።
ይህ ከላይ ባለ ምክንያቶቹ የሰጡት ምክንያት እውነት ከሆነ፣ እኛም እንላለን ራስን መሆን ራስን ሆኖ ለመኖር ያስችላል። ራስን አለመሆን ያለ ራስ መኖርን ያስከትላል፤ ወይም፣ ያመጣል። መምሰል ከራስ መነጠል ሲሆን፤ መሆን ከራስ መታረቅ ነው። መሆን ተፈጥሮን ማጣጣም ሲሆን አለመሆን ከተፈጥሮ መጋጨት፤ ፀጋዋን መነፈግ ነው። ከተፈጥሮ መጋጨት ከአካባቢ መነጠል ሲሆን፣ በአውጋር አድባሩም መገፋት ነው።
“ስለ ሁለቱም ግዴለኝም ማለት ደግሞ ከሁለቱም ባለ መሆን መሀል መንገድ ላይ በመቅረት መሀን መሆን ነው። ከ“አለመኖር” መጽሐፍ ከምንገነዘባቸው እውነታዎች መካከልም አንዱ ይሄው ነው። በመሆኑም፣ ብቸኛውና አዋጪው መንገድ መሆን እንጂ መምሰል አይደለም።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ጥር 18/2016