ሀገርን የሚወክሉ አትሌቶችን የሚያፈራው የኢትዮጵያ ቻምፒዮና ከቀናት በኋላ ይካሄዳል

53ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከቀናት በኋላ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ይካሄዳል። በቻምፒዮናው የተሻለ ብቃት የሚያሳዩ የሩጫ፣ ውርወራ እና ዝላይ አትሌቶችም በአህጉርና ዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ውድድሮች ተካፋይ እንደሚሆኑ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት ከሚካሄዱ ዓመታዊ ውድድሮች መካከል ትልቁ የሆነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ነው። ከ1963 ዓም የጀመረው አንጋፋው ውድድር ዘንድሮ ለ53ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ይደረጋል። ከጥር 21 እስከ 26/2016 ዓ∙ም በሚዘልቀው ውድድር ላይም 5 ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች፤ እንዲሁም 27 ክለቦች 1ሺህ 102 የሚሆኑ አትሌቶቻቸውን፤ ከአጭር እስከ ረጅም ርቀት የመም ሩጫ፣ የውርወራ እና ዝላይ ስፖርቶች ያፎካክራሉ። በተለያዩ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት እና አካዳሚ የሚሰለጥኑ ተተኪ አትሌቶችም የውድድር እድል ያገኛሉ። ውድድሩን ለማካሄድም ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን፤ 160 በሚሆኑ ባለሙያዎች የሚመራም ነው።

ተተኪና ምርጥ ብቃት ያላቸው አትሌቶች የሚካፈሉበት ይህ ውድድር ሀገርን የሚወክሉ ብርቅዬ አትሌቶች የሚፈሩበት ነው። በዚህ ውድድር ላይም የላቀ ብቃታቸውን የሚያስመሰክሩ አትሌቶች በአህጉር እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ይሆናል። በሚያዚያ ወር ይካሄድ የነበረው ውድድሩ ወደ ጥር እንዲመጣ የተደረገውም ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚካሄዱበትን መርሀ ግብር መሰረት በማድረግ እንደሆነም ነው ፌዴሬሽኑ የጠቆመው። በቀጣዩ ወር በጋና (አክራ) በሚካሄደው 13ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ተካፋይ የሚሆኑ አትሌቶች ሚኒማ የሚያሟሉበት ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊያን ከአጭር ርቀት እስከ ሜዳ ተግባራት የሚሳተፉበትም ይሆናል። ሌላው ደግሞ ከወራት በኋላ የሚደረጉት 23ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና እና ለፓሪስ 2024 ኦሊምፒኮች ናቸው።

የሁሉም አትሌቶች መዳረሻ የሆነው ኦሊምፒክ ከወራት በኋላ ፓሪስ ላይ የሚካሄድ፤ አትሌቶች ሀገራቸውን ለመወከል የሚያስችላቸውን ዝግጅት የሚያደርጉ እንደመሆኑ እነዚህን መሰል ሀገር አቀፍ ውድድሮች አቋማቸውን ለመለካት፤ እንዲሁም ለምልመላ ምቹ ናቸው። በመሆኑም ከተተኪ አትሌቶች ባሻገር ከተለያዩ ክለቦች የተወጣጡ አትሌቶች የውድድሩ ተሳታፊ መሆናቸው ተረጋግጧል። ለአብነት ያህል በወንዶች የኦሮሚያ ፖሊስ አትሌቲክስ ክለብ አትሌቶቹ ታምራት ቶላ፣ ሲሳይ ለማ፣ ሌሊሳ አራርሳ እና ለሜቻ ግርማ፤ ከፌዴራል ማረሚያ ያሲን ሃጂ፣ አእምሮ ይሌ እና ሀይለማርያም አማረ፤ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ታደሰ ወርቁን የመሳሰሉ አትሌቶች በሩጫ ይሳተፋሉ። በሴቶችም በተመሳሳይ አሸቴ በከሬ ከኦሮሚያ ፖሊስ፣ ብርቄ ኃየሎም፣ ፎቴን ተስፋይ እና አሪያት ዲቦ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ሃብታም ዓለሙና ሂሩት መሸሻ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ አክሱማይት እምባዬ ከፌዴራል ማረሚያ፣ … በውድድሩ ተካፋይ የሚሆኑ ታዋቂና ውጤታማ አትሌቶች ናቸው።

በኢትዮጵያ አስቸጋሪ የሆነው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ማነስ በአትሌቲክስ ስፖርትም ከፍተኛ ራስ ምታት በመሆኑ ቻምፒዮናው ከወጣቶች አካዳሚው ባሻገር የውርወራ ስፖርቶች ሱሉልታ በሚገኘው የቀነኒሳ በቀለ የአትሌቲክስ ማዘውተሪያ እንደሚደረግም ነው ፌዴሬሽኑ ያስታወቀው።

በተያያዘ ዘገባ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለ2024ቱ የፓሪስ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ንቅናቄ መድረክ ዛሬ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስታውቋል። የቴክኒክና ሕዝብ ግንኙነት ኮሚቴ ካለፈው ዓመት አንስቶ የተለያዩ እቅዶችን በማዘጋጀት ከሀገር ውጪ በአምስተርዳምና ፓሪስ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ግንዛቤ የማስጨበጥና የንቅናቄ ስራዎችን ያከናወነ መሆኑን አስታውቋል። በሀገር ውስጥ ደግሞ የተለያዩ ቴክኒክ ኮሚቴዎች የተዋቀሩ ሲሆን፤ ዛሬ ሀገር አቀፍ ንቅናቄው ይጀመራል። በዚህም ዛሬ በሚኖረው የንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይም በኦሊምፒኩ ላይ ሀገራቸውን የሚወክሉ አትሌቶች የሚለብሱትን መለያ የሚያስተዋውቅ ይሆናል።

የስፖርቱን ቤተሰብ ጨምሮ የባለድርሻ አካላት በሚካተቱበት በዚህ መድረክም መልእክት ይተላለፋል። ከነገ በስቲያ ጥር 18/2016 ዓ∙ም ደግሞ የኦሊምፒክ ችቦ ቅብብል በመቀሌ የሚደረግ ሲሆን፤ ጎን ለጎንም ጉባኤ፣ የብስክሌት እንዲሁም የሩጫና እርምጃ ውድድሮች ይከናወናሉ። በቀጣይ ደግሞ ችቦው ተረኛ ወደ ሆነው ቤኒሻንጉል ክልል፤ ከዚያም ወደ ቀጣዩ ተረኛ ቅብብሎሹ እየተደረገ ሐምሌ 6/2016 ዓ∙ም አዲስ አበባ ላይ በማጠናቀቅ የብሄራዊ ቡድኑ ሽኝት የሚደረግ እንደሚሆንም ኮሚቴው በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ጥር 16/2016

Recommended For You