
ባለፉት ሳምንታት በቀይ ባሕር በኩል በመርከቦች ጭነት ማጓጓዝ ፈታኝ ሆኗል። በኢራን የሚደገፉት የየመን ሁቲ አማጽያን በሰው አልባ አውሮፕላን እና በሚሳኤል መርከቦች ላይ ጥቃት እየፈጸሙ ነው።
ታጣቂዎቹ በተጨማሪም በጀልባ እና በሄሊኮፕተርም ጥቃት አድርሰዋል። አብዛኛውን የመን የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች “በጋዛ እና በዌስት ባንክ ላሉ ፍልስጤማውያን ወንድሞች” ድጋፍ እንደሚሰጡ ገልጸዋል።
ወደ እስራኤል የሚጓዙ የንግድ መርከቦችን ዒላማ እንዳደረጉ ሲሆን፤ ቢቢሲ ባጣራው መረጃ መሠረት ሁቲዎች ጥቃት የሰነዘሩት በደቡባዊ ቀይ ባሕር ነው። ይህም በየመን ባሕር ዳርቻ በባብ ኤል-ማንዳብ መተላለፊያ ላይ ነው።
ወደ ኤደን ባሕረ ሰላጤ የሚጓዙ መርከቦች ላይም ጥቃት ተሰንዝሯል። ነገር ግን በጥቃቱ ዒላማቸውን የመቱት የተወሰኑት ብቻ ናቸው። ከእነዚህም መካከል እአአ ጥር 17 የተፈጸመው ጥቃት ይገኝበታል።
በዚህም በአሜሪካ መርከብ ላይ ነበር ጥቃቱ የተቃጣው። ነገር ግን መርከቡ በሁቲዎች ድሮን ጎኑ ላይ ቢመታም ጉዞውን ቀጥሏል።
ጥቃቱን የሚያሳይ ምሥል ያነሳው የሕንድ የባሕር ተዋጊ መርከብ ነበር። ይህም የሁቲዎችን ጥቃት ለመመከት ያለውን ትብብር ማሳያም ነው።
ሁቲዎች ትናንሽ ጀልባዎችን በመጠቀም መርከቦች ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ። ሄሊኮፕተር በመጠቀም መርከብ ላይ ጥቃት የሰነዘሩበትም ወቅት ነበር።
በሄሊኮፕተር መርከብ ላይ የወረዱት ጥቃት አድራሾች አንድ መርከብን አግተዋል። ጋላክሲ ሊደር የተባለው መርከብ አሁንም በየመን ባሕር ዳርቻ እንደተያዘ ነው።
የየመን የእርስ በእርስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ከሀገሪቱ መንግሥት የተወሰዱ መሣሪያዎች በሁቲዎች እጅ ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው፣ ከምሥራቅ እስያ በሲቪሎች አማካይነት የተገኙም መሣሪያዎች አሏቸው።
አብዛኞቹ ዘመናዊ ድሮኖች እና ሚሳኤሎች ግን ከኢራን እንደተገኙ በስፋት ይነገራል። አሜሪካ እንዳለችው፣ ከየመን ወደ ኢራን በዓሣ ማስገሪያ ጀልባ ተጭኖ እየተጓዘ የነበረ የሚሳኤል እና የአየር መቃወሚያ ይዛለች።
ወታደራዊ ተንታኞች እንዳሉት ኤምቪ ቤሻድ የተባለ የኢራን መርከብ ሁቲዎች ዒላማ እንዲመቱ እያገዘ ነው። ቀድሞ ማጓጓዣ የነበረው መርከብ አሁን የደኅንነት መቆጣጠሪያ መሆኑን ያስረዳሉ።
በቀጣናው የደኅንነት ቡድን የመሩት ክሪስ ፋረል እንደሚሉት፣ የተለያየ ቁሳቁስ የጫኑ መርከቦች ጥበቃ የሚደረግላቸው ቢሆንም ከአየር የሚደረግ ጥቃትን መከላከል የሚያስችል መሣሪያ ግን የላቸውም። ይህ በቀይ ባሕር በኩል የሚያቋርጡ “የንግድ መርከቦች ከረዥም ጊዜ በኋላ የገጠማቸው ከባድ ችግር ነው” ይላሉ።
ዓለም አቀፍ ምላሽ ከመጠናከሩ ጋር በተያያዘ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም በጋራ በየመን የሁቲ አማጽያን ይዞታዎች ላይ የአየር ጥቃት ፈጽመዋል።
በዚህም ሁለቱ ሀገራት የአማጽያኑን ወታደራዊ አቅም ለማዳከም ያለመ ጥቃት ነበር የሰነዘሩት። ሆኖም ግን የየመንን ሰፊ ተራራማ አካባቢዎች ሁቲዎች ይቆጣጠራሉ። መደበቅ የሚችሉትም በዚህ ምክንያት እንደሆነ ወታደራዊ ተንታኞች ይናገራሉ።
ባለፈው ታኅሣሥ በአሜሪካ የሚመራ ወታደራዊ ጥምረት የንግድ መርከቦችን ለመጠበቅ እንደሚሠራ ተገልጿል። በዚህም ቀይ ባሕርን የመቆጣጠር ሥራ የሚሠሩ ሲሆን ዩናይትድ ኪንግደም ለዚህ ተግባር መርከብ እንደምታቀርብ አስታውቃለች።
ከአሜሪካ ጥምረት ውጪ እንደ ፈረንሳይ ያሉ ሀገራትም በቀጣናው መቆጣጠሪያ ጣቢያ አላቸው። የአሜሪካ የባሕር ኃይል ካፕቴን ብራድሊ ማርቲን እንደሚሉት የተለያዩ ዓለም አቀፍ አጋሮችን ማስተባበር ፈታኝ ነው።
ባሕሩ ላይ የሚከናወነውን ጥበቃ የሚያካሂዱትን መርከቦቹ ነዳጅ ሞልቶ መሣሪያ ማስታጠቅም ከፍተኛ ወጪን ይጠይቃል። ከሁቲዎች የሚተኮሱትን እንደ ሲ ቫይፐር ያሉ ሚሳኤሎችን መከላከል በሚሊዮን ዶላር የሚያስወጣ ነው።
በተቃራኒው ሁቲዎች የድሮን ጥቃት ለመፈጸም የሚያወጡት በሺዎች የሚቆጠር ዶላር ነው። በርካታ ተቋማት መርከባቸው በቀይ ባሕር እንዳይጓዝ እያደረጉ ነው።
ይህ ማለት ደግሞ ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ በተባለው የአፍሪካ ዳርቻ መንገድ ለመጓዝ ከፍተኛ ወጪን ያወጣሉ ማለት ነው። ረጅሙን የውቅያኖስ ላይ ዙሪያ ጥምጥም መንገድ በማስቀረት በቀይ ባሕር ለመጓዝ የመረጡ ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ አማራጮች እየተጠቀሙ ነው።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 15 ቀን 2016 ዓ.ም