ኢትዮጵያ በሆርቲካልቸር ልማት ከፍተኛ እምቅ ሀብት ካላቸው በቀዳሚነት ከሚጠሩት ሀገሮች ተርታ ትጠቀሳለች። ያላት ሰፊ መሬትና የአየር ንብረት ለሆርቲካልቸር ልማት ተስማሚ እንደሆነም ይነገራል።
ይህን እምቅ ሀብት በመጠቀም አበባ፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ሥራሥር ሰብሎች፣ እጸ ጣዕም፣ ቅመማቅመም፣ ቡና፣ ሻይና ሌሎችንም የሆርቲካልቸር ሰብሎችን አልምቶ ለውጭ ገበያ በመላክ የውጭ ምንዛሪን ከማስገኘት አኳያ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። ሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከምታገኝባቸው የግብርና ምርቶች አንዱ ይኸው የሆርቲካልቸር ልማት መሆኑ ይታወቃል።
የግብርና ሚኒስቴር የሆርቲካልቸር ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብዳላ ነጋሽ ፤ በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት በእንሰትና ሥራሥር ሰብል ልማት 32ሺ 580 ቶን ለማምረት ታቅዶ፤ ከ33ሺ681 ቶን በላይ ማምረት ተችሏል። በአበባ ልማት ከ69 ሺ 341 ቶን በላይ ለማምረት ታቅዶ፤ ከ51ሺ683 ቶን በላይ ተመርቷል። በፍራፍሬ ልማት 26ሺ197 ቶን ለማምረት ታቅዶ፤ ከ25ሺ 273ቶን በላይ ተመርቷል። በአትክልትና እጸ ጣዕም ልማት 115ሺ ቶን ለማምረት ታቅዶ 91ሺ596 ቶን ማምረት ተችሏል።
ለውጭ ገበያ ከተላኩት የሆርቲካልቸር ሰብሎች ውስጥ ከ29ሺ 288 ቶን በላይ የእንሰትና ሥራሥር ሰብል፣ ከ46ሺ 984 ቶን በላይ የአበባ ምርት፣ ከ21ሺ276ቶን በላይ ፍራፍሬ፣ ከአትክልትና እጸ ጣዕም ከ74ሺ 336 ቶን በላይ ምርቶችን ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ ተደርጓል። ከእነዚህ የሆርቲካልቸር ሰብሎች የወጪ ንግድም በአጠቃላይ 298 ሚሊዮን 794ሺ 887ነጥብ 45 የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል።
በሆርቲካልቸር ሰብሎች ከምርት አንጻር ሲታይ በአንዳንድ ሰብሎች በ2015 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ወደ ውጭ የተላከው ምርት መቶና ከመቶ በላይ መላክ የተቻለበት ነው ያሉት አቶ አብደላ፤ ከተላከው ምርት የተገኘው ገቢ ግን ዝቅ ያለ መሆኑን አመልክተዋል። ከተላከ ምርት አኳያም ቅናሽ ያሳየ ምርት እንዳለ ጠቅሰው፣ ለውጭ ገበያ የተላከው የእንሰትና ሥራሥር ሰብል እና የአበባ ምርት መጠን መቀነስ ማሳየቱን ተናግረዋል። ገቢውም የዚያኑ ያህል የቀነሰበት ሁኔታ እንዳለ ነው ያስታወቁት።
እሳቸው እንደሚሉት፤ የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ግምገማ መረዳት እንደተቻለው፤ የሆርቲካልቸር ሰብሎችን ለውጭ ገበያ ከመላክ አኳያ ከታቀደው አንጻር መቶና ከመቶ በላይ አፈጻጸም ታይቷል፤ ከተላከው ምርት የተገኘው ገቢ ግን ቀንሷል። ወደ ውጭ የተላከው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ካለፈው 2015 በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር ሲታይ ጭማሪ አሳይቷል።
የተላከው ምርት ከጨመረ የሚያስገኘውም የውጭ ምንዛሬ ገቢ መጠን መጨመር እንዳለበት ይታወቃል ያሉት አቶ አብደላ፣ ገቢው ግን መቀነሱን ነው ያስታወቁት። ይህ የሆነበት ምክንያት መጠናት እንዳለበት አስታውቀው፣ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር ጥናቶችን በማካሄድ መፍትሔዎች ላይ አቅጣጫ ማስቀመጥ ያስፈልጋል ብለዋል።
የሆርቲካልቸር ሰብሎች በተለያየ መንገድ ለውጭ ገበያ እንደሚላኩ መሪ ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰው፣ ምርቶቹ በየብስ እና በአየር ትራንስፖርት እንደሚላኩ ተናግረዋል። በየብስ ትራንስፖርት ወደሚላክባቸው አካባቢዎች በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ ከሚመረተው ምርት አንጻር የሚፈለገውን ያህል የምርት የማይላክበት ሁኔታ እንደሚያጋጥም ተናግረዋል። በዚህ የተነሳ የሚፈጠሩ ክፍተቶች እንደ ችግር እንደሚነሱ ጠቅሰዋል።
ሌላኛው ምክንያት ደግሞ አብዛኛዎቹ እርሻዎች ዘር ከውጭ እንደሚያስገቡ ጠቅሰው፣ በዚህም ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት ሊመረት እንደሚችል ይናገራሉ። ምርቱ በሚፈለገው ጥራት ካልተመረተ እና በሚፈለገው መጠን መላክ ካልተቻለ የዚያኑ ያህል ለውጭ ገበያ የሚላከው መጠን ሊቀንስ እንደሚችልም ነው አቶ አብዳላ ያስረዱት።
አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ምርቱ በበቂ ሁኔታ እንደተመረተ የሚያሳይ ሁኔታ እንዳለም ተናግረዋል። በአንጻሩ በአበባ ልማቱ አዳዲስ ዝርያዎችን የመተካት ሥራ እየተሠራ ያለበት ሁኔታ እንዳለም ይጠቁማሉ። ይህ ሁኔታ የመጀመሪያው ስድስት ወር አፈጻጸምን ሊቀንስ እንደሚችል ተናግረው፣ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥ ደግሞ ሊጨምር የሚችልበት ሁኔታ መኖሩን አመላክተዋል።
መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ ምርቶቹ የሚላኩባቸው በርካታ የውጭ ሀገራት የገበያ መዳረሻዎች እንዳሉም ጠቅሰው፣ የአበባ ምርት በአብዛኛው ለአውሮፓ ገበያ እንደሚቀርብ አስታውቀዋል። ከእነዚህ ሀገሮች ቀዳሚዋ የገበያ መዳረሻ ኒውዘርላንድ መሆኗን ጠቅሰዋል።
የእንሰትና የሥራሥር ሰብል ምርቶችን እንዲሁ ወደ ተለያዩ ሀገራት እንደሚላኩ ተናግረው፣ ምርቶቹ በተለይ ከምሥራቅ አፍሪካ ጀምሮ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ገበያ እንደሚቀርቡም አመልክተዋል። አብዛኛዎቹ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾች እና ከአርሶ አደሩ ተረክበው የሚልኩ ላኪዎች ደግሞ ወደ አውሮፓና ሌሎች ሀገራት ይልካሉ ብለዋል።
መሪ ሥራ አስፈጻሚው በሆርቲካልቸር ሰብሎች ልማት በርካታ አልሚዎች መሰማራታቸውን ጠቅሰዋል። ከእነዚህ ውስጥ ከ68 በላይ ባለሀብቶች በአበባ ልማት መሰማራታቸውን አመልክተው፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የተሰማሩ ባለሀብቶች ውስን መሆናቸውን ጠቅሰዋል። የሆርቲካልቸር ምርቱን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡት እነዚህ ብቻ እንዳልሆኑም ጠቅሰው፣ ሌሎች ምርቱን አሰባስበው ወደ ውጭ የሚልኩ ፈቃድ የተሰጣቸው አካላት እንዳሉም ይጠቁማሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ የሆርቲካልቸር ምርቶች በተለያየ መንገድ ለውጭ ገበያ ከሚልኩት ውስጥ አምርተው የሚልኩ እንዳሉ ሁሉ ለአምራቹ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ምርቱን ተቀብለው ለውጭ ገበያ የሚልኩ እንዳሉም አስታውቀው፣ ምርቱን ብቻ በማሰባሰብ የሚልኩ እንዳሉም ጠቅሰዋል።
ዘርፉ ለምን ያህል ሰዎች የሥራ ዕድል እንደፈጠረ እስከ አሁን በጥናት የተለየ መረጀ እንደሌለ ጠቅሰው፣ ‹‹የሆርቲካልቸር ሰብል ልማት ዘርፍ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይታመናል›› ሲሉም አቶ አብደላ አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ በአብዛኛዎቹ የአበባ እርሻዎች፣ አትክልትና እጸ ጣዕም በብዛት በሚያመርትባቸው አካባቢዎች እስከ 200 /ሁለት መቶ/ ሺ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል ስለመፈጠሩ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህም ከ10 እስከ 15ሺ ሄክታር በማይበልጥ መሬት ላይ የሚካሄድ የሆርቲካልቸር ልማት የፈጠረው የሥራ ዕድል ነው። እስካሁን ያለው መረጃ በአግባቡ ያልተያዘ ቢሆንም፣ በእያንዳንዱ የሆርቲካልቸው ልማት በአማካኝ በሄክታር ከ18 እስከ 30 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይገመታል። ይህን ደግሞ ከለማው ሄክታር አኳያ ሲታይ ልማቱ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እየፈጠረ ስለመሆኑ መረዳት ይቻላል።
መሪ ሥራ አስፈጻሚው የዘርፉ ዋንኛ ተግዳሮት ያሉትንም ጠቅሰዋል። ለኢንቨስትመንቱ በሚያስፈልጉት የቴክኖሎጂ አቅርቦቶች ላይ ክፍተቶች እንዳሉ አስታውቀው፣ ለዘርፉ ከሚያስፈልገው ቴክኖሎጂ አብዛኛው ከውጭ እንዲገባ ተደርጎ እንደሚሠራ አንስተዋል። ከኬሚካል ማዳበሪያ ጋር ተያይዞ ያለውን ተግዳሮት ለመቀነስ በሀገር ውስጥ ባዮሎጂካል የሆኑ ምርቶችን በማምረት ለመጠቀም የሚያስችሉ ጥሩ ሥራዎች መጀመራቸውንም ይገልጻሉ።
ለዘርፉ የሚያስፈልጉ ኬሚካሎችን ለማስገባት እና የተለያዩ ለኢንቨስትመንቱ ወሳኝ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ለማቅረብ ከውጭ ምንዛሪ ጀምሮ ችግሮች ሲያጋጥሙ እንደነበር አስታውሰው፣ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በመንግሥት በኩል ጥረቶች መደረጋቸውንም አስታውቀዋል። በዚህም ችግሮቹን ሊቀርፍ የሚችል የአሠራር ሥርዓት መዘርጋቱን ገልጸዋል።
ሌላኛው ተግዳሮት አምራች የሰው ኃይል ከማፍራት ጋር ተያይዞ የሚነሳው መሆኑንም መሪ ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ዘርፉ በሚጠይቀው ልክ ክህሎትና እውቀት ያለው የሰው ኃይል አብቅቶ ማቅረብ ላይ እጥረት ይታይ ነበር። ይህንንም ተግዳሮት ለመፍታት በግል በተከፈተ አንድ የቴክኒክና ሙያ የሆርቲካልቸር ኮሌጅ በኩል ጥረቶች እየተደረጉ ናቸው። በተመሳሳይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚያስፈልጋቸውን ክህሎትና እውቀት ይዘው እንዲወጡ ሰፊ ሥራ መስራት እንዳለበት የሚያሳዩ ነገሮች መኖራቸውንም ነው አቶ አብደላ የሚገልጹት።
ሌላው በተግዳሮትነት መሪ ሥራ አስፈጻሚው የጠቀሱት የደህንነትና ሰላም ጉዳይ ነው። ለማንኛውም ኢንቨስትመንትና ልማት የሰላምና ደህንነት ጉዳይ ወሳኝ ነው ያሉት አቶ አብደላ፤ በልማቱ ላይ የተሰማሩ አካላት በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ ለማድረግ በመንግሥት በኩል ኃላፊነት ተወሰዶ መስራት እንዳለበት አመላክተዋል። ለእዚህም በየደረጃው ያለው የመንግሥት አካል የሚገጥማቸውን ችግር በፍጥነት የመፍታት እና ችግር እንዳይገጥማቸው መከላከል ላይ መስራት እንደሚጠበቅበት አስታውቀዋል። ችግሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ቀደሞ ተንብዮ ከመስራት አኳያ መሠራት ያለባቸው ተግባሮች እንዳሉም አስታውቀዋል።
አቶ አብደላ እንዳሉት፤ የሆርቲካልቸር ዘርፉ ገና ብዙ አልተሠራበትም። ብዙ መስራት ከተቻለ የምግብ ዋስትናን በሚገባ ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አጠቃላይ በሀገር ደረጃ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ጋር ተያይዞ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። ለዚህ ደግሞ ስትራቴጂዎች ተቀርጸው ለመተግበር ጥረት እየተደረገ ነው።
የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት ረገድ ዘርፉ እንደሀገር ካለን እምቅ አቅም እስካሁን እያስገኘ ያለው ገቢ ብዙ እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ በቡናና የሻይ ተክል ምርት ላይ በስፋት እየተሠራ እንዳለው ሁሉ በሆርቲካልቸር ሰብሎች ላይም በርካታ ሥራ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
መሪ ሥራ አስፈጻሚው እንዳብራሩት፤ ሆርቲካልቸር ሲባል ብዙ ጊዜ አበባ ብቻ አድርጎ የመመልከት ሁኔታዎች አሉ። ሆርቲካልቸር ሲባል አበባ ብቻ አይደለም፤ የአትክልት፣ የሥራሥር ሰብሎች፣ የፍራፍሬ፣ የእጸ ጣዕም ፣ የቅመማቅመም፣ የቡና፣ ሻይና ሌሎችንም ሰብሎች የሚያካትት ነው።
‹‹እንደ አገር በሆርቲካልቸር ዘርፍ ለማልማት የሚያስችለው አቅም ከፍተኛ ስለሆነ ማንኛቸውንም በዓለም ላይ ሊመረቱ የሚችሉ የዘርፉን ሰብሎች አምርቶ ወደ ውጭ በመላክ መጠቀም ይቻላል›› ሲሉ አስታውቀው፣ ከዚህ አንጻር ብዙ አልተሰራም ይላሉ። ወደፊት በፖሊሲና ስትራቴጂዎች በመደገፍ የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ ሀገር በተሻለ መልኩ ተጠቃሚ መሆን የሚያስችላትን ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻልም አመልክተዋል።
መሪ ሥራ አስፈጻሚው እንዳብራሩት፤ በግብርናው ዘርፍ ገቢን በማስገኘት ረገድ ከቡና ቀጥሎ የሆርቲካልቸር ሰብሎች በሁለተኛ ደረጃ እንደሚገኙ ይታወቃል። እንደ ሀገር ያለው አቅም ከዚህም በላይ ማምጣት እንደሚቻል ይጠቁማል። አሁን በአንድ ሺ 892 ሄክታር መሬት ላይ እየለማ ካለው የአበባ ተክል ብቻ ነው 255 ሚሊዮን በላይ ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የተቻለው።
ይህን ልማቱ የሚካሄድበትን መሬት በእጥፍ ማሳደግ ቢቻል፣ ገቢውንም በእጥፍ ማሳደግ ይቻላል። የልማቱን ስፍራ ከዚህም በላይ እጥፍ ማድረግ ቢቻል ሦስት አራት እጥፍ ገቢ ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል። በመሆኑም ከአበባ ብቻ ከአንደ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ ይኖራል ሲሉ አቶ አብደላ አስገንዝበዋል።
ይህንን ለማሳካት ስትራቴጂክ ሆኖ መስራት እንደሚያስፈልግ አስታውቀው፣ ከክልሎች ጋር ተናብቦ የሚያስፈልገውን መሬት ለይቶ መስራትን እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፤ ችግሮችን መፍታት ከተቻለ ዘርፉ በአጭር ጊዜ ዘርፉ ለውጥ ማምጣት የሚችል ፣ ለዜጎችም፣ ለሀገርም ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።
ለውጭ ገበያ በርካታ የሆርቲካልቸር ምርት ለውጭ ገበያ ቀርቦ፣ ዝቅተኛ ገቢ እየተገኘ ያለበትን ሁኔታ በጥናት ላይ ተመስርቶ መቀየር፣ ዘርፉ ያለውን እምቅ አቅም በሚገባ ለይቶ መጠቀም መቻልና የአልሚዎችን፣ ሀገርንና ዜጎችን ተጠቃሚነት በሚገባ ማረጋገጥ ቀጣይ የዘርፉ የቤት ሥራዎች ናቸው።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 15 ቀን 2016 ዓ.ም