በመሬት አቀማመጥ (በላንድስኬፕ) አርክቴክት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የሆኑት ኢንጂነር ጌታቸው ማህተመስላሴ፤ ከ95 አመት በፊት በ1921ዓ.ም ነበር የተወለዱት፡፡ አባታቸው ብላቴን ጌታ ማህተመስላሴ ወልደመስቀል በፈረንሳይ ሀገር ሶርቦርን ዩኒቨርሲቲ የአፈርና የእርሻ ምርምር ሙያ ትምህርትን በመከታተል በአግሮ ኢኮኖሚ የተመረቁ ሊቅ ነበሩ፡፡ ለሀገርና ለትውልድ ጠቃሚ የሆኑ ከ18 በላይ መጽሐፍትን ለንባብ ያበቁ ሰው ናቸው፡፡
ኢንጂነር ጌታቸው በልጅነታቸው ያደጉት የእናታቸው ታላቅ እህት ከሆኑት ከወይዘሮ ሮማን ወርቅ ጋር ነበር። የቄስ ትምህርታቸውንም የጀመሩት እዚሁ አክስታቸው ቤት ነው፡፡ የአክስታቸው ባል ደጃዝማች አባ ሻውል በጣሊያን ወረራ ጊዜ ሲሞቱ ትምህርታቸውን ለመቀጠል እንዲያመቻቸው ወደ ወላጆቻቸው ቤት ተመለሱ፡፡
በጊዜው ክቡር ብላቴን ጌታ ማህተመስላሴ የልዑል አልጋ ወራሽ እንደ ራሴ ሆነው ይሠሩ ነበር፡፡ ኢንጂነር ጌታቸው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ደሴ በሚገኘው በወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ነበር፤፡፡ ኢንጂነሩ በገቡባቸው ትምህርት ቤቶች ሁሉ የላቀ ውጤት በማስመዝገብ በተደጋጋሚ ክፍሎችን እየዘለሉ አልፈዋል፡፡
ወደ አቃቂ ሚሲዮን ገብተው በመማር ላይ እያሉም የ2ኛ ደረጃ መግቢያ ፈተና ሲመጣ፤ ያለደረጃቸው ፈተናውን ከወሰዱት በእድሜ ትንሹ እርሳቸው ነበሩ። ፈተናውን ያልፋሉ ተብሎም አልተጠበቀም ነበር፡፡ ኢንጂነር ጌታቸውም ፈተናውን ‹‹አልፋለሁ›› የሚል ግምት ቢኖራቸውም፤ ‹‹ እኔን ከእነዚህ ትልልቅ ተማሪዎች ጋር ማን አብሮ ይመለከተኛል?›› ብለው አስበው ስለነበር፤ ፈተናውን ማለፋቸው ሲነገራቸው ማመን ተስኗቸው ነበር።
ኢንጂነር ጌታቸው የአምቦ እርሻ ኮሌጅን የተቀላቀሉት በ17 አመታቸው ነበር፡፡ የአምቦ እርሻ ኮሌጅ ተማሪዎችን የሚቀበለው በጊዜው ከባድ የሚባለውን ፈተና ተፈትኖ እንጂ እንዲሁ ‹‹ተማሪ አጣሁ›› በሚል ማንንም አይቀበልም ነበር። ስለዚህ ኢንጂነር ጌታቸው የመግቢያ ፈተና መውሰድ ነበረባቸው። ፈተናውን የወሰዱት ብዙ ተማሪዎች ቢሆኑም ያለፉት ግን በጣም ጥቂቶች ነበሩ። ኢንጂነር ጌታቸውም ፈተናውን ካለፉ ጥቂቶች ውስጥ አንዱ ሆኑ። ትምህርታቸውንም በ1938 ጀምረው ከ 7 አመት በኋላም በ1944 ለመመረቅ ችለዋል፡፡
ኢንጂነሩ በአምቦ እርሻ ኮሌጅ በነበራቸው ቆይታ ከአስተማሪዎቻቸው የተረዱትን ትምህርት እርሳቸው በገባቸው መሰረት በራሳቸው የቋንቋ አጠቃቀም ለፈተናዎች መልስ መስጠታቸውን አስተማሪዎቻቸው ያደንቁላቸውና ያበረታቷቸው ነበር።
ኢንጂነር ጌታቸው በፈተና ውጤታቸው ከክፍላቸው ውስጥ ብዙውን ጊዜ ከአምስት እስከ ሰባተኛ ደረጃ ይወጡ ነበር። በመጨረሻም ከእርሻ ኮሌጅ በአጠቃላይ የእርሻ ሙያ በተመረቁበት ጊዜ ከ45 ተማሪዎች የ5ኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀቁ። ኢንጂነሩ በነበራቸው ተሰጥኦ በአምቦ የእርሻ ትምህርት ቤት እያሉ ትምህርት ቤቱን ለማደስ ጨረታ ሲወጣ፤ አብሮ በመጫረት ለተደጋጋሚ ጊዜ አሸንፈው ሌሎች ተማሪዎችን ከዛው በመቅጠር ትምህርት ቤቱን ያድሱ ነበር። በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ጄኔሬተሮችን በኃላፊነት ይጠግኑ ነበር።
በዚሁ ኮሌጅ ባገኙት የቅየሳ ሙያ የአውራ ጎዳና ባለስልጣን ተብሎ በአሜሪካ መንግሥት በተቋቋመው መስሪያ ቤት ውስጥ በረዳት መሐዲስነት ደረጃ በቀያሽነት ተቀጠሩ፡፡ በለቀምት፣ ቀጥሎም በይርጋለም የድልድይ መሐንዲስ ሆነው ከአለቃቸው ከአሜሪካዊው መሀንዲስ ጋር ሲሰሩ ቆዩ፡፡
በመቀጠልም ከኮምቦልቻ አሰብ በሚሰራው መንገድ ላይ የዲስትሪክት ኢንጂነር ሆነው ካገለገሉ በኋላ ወደ እርሻ ሚኒስቴር በግዴታ ተዛወሩ፡፡ ፖይንት ለውሃ ሀብት ልማት የተሰኘ ድርጅት በአሜሪካ መንግሥት ሲቋቋም እርሻ ሚኒስቴርን ወክለው አብረው እንዲሰሩ ስለተመደቡ፤ ከአሜሪካዊው አለቃቸው ጋር በኢትዮጵያ ባሉት በበጋ በማይደርቁ መለስተኛ ወንዞች ላይ በተደረገው ጥናት ላይ አንዱ ተካፋይ ሆኑ፡፡
ኢንጂነር ጌታቸው ፖይንት ለውሃ ሀብት ውስጥ ይሰሩ በነበሩበት ወቅት፤ በኢትዮጵያ ባሉ በተለያዩ ክፍለ ሀገሮች ወንዞች ወዳሉበት የመሄድ ዕድል አግኝተዋል። የቆቃ ግድብና የብሉ ናይል እንዲሁም የሌሎችን ወንዞች የውሃ መጠን፣ የውሃውን ፍጥነት፣ የውሃውን ይዘት የሚሄደውን የአፈር መጠን እንዲሁም ለምን አገልግሎት መዋል እንደሚችል በመመርመር ሥራውን ከሚያጠናው አካል ጋር አብረው ሠርተዋል።
ወደ ዋናው መስሪያ ቤት ተጠርተውም የመስሪያ ቤቱ የተሽከርካሪ ክፍል ምክትል በመሆን እያገለገሉ ሳሉ፤ በ1949 ዓ.ም የነጻ የትምህርት እድል አግኝተው ወደ ምዕራብ ጀርመን ተልከው ከይዘን ሀይም ራይን በሚገኘው የትምህርትና የምርምር ኢንስቲትዩት ተመድበው በላንድስኬፕ አርኪቴክቸር በከተማ ፕላኒንግ በዲግሩ ሰለጠኑ፡፡
በትምህርታቸው ያሳዩትን ጥሩ ውጤትና ትጋት በመመልከት ትምህርት ቤቱ ለአምቦ እርሻ ኮሌጅና ለእርሻ ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ ወደ ጀርመን ሀኖቨር ዩኒቨርሲቲ ተልከው ዶክትሬታቸውን እንዲቀጥሉ ሃሳብ ቀረበ። ኢንጂነር ጌታቸው ግን ‹‹በተማርኩት ትምህርት ሀገሬን ባገለግል ይሻላል፡፡›› ብለው ወደ እናት ሀገራቸው ተመለሱ። የበለጠ ሊሰሩ የሚችሉት ማዘጋጃ ቤት ስለነበር ወደ ማዘጋጃ ቤት ተዛውረው ሥራ ጀመሩ፡፡
ኢንጂነር በአዲሱ ሙያቸው በመጀመሪያ እንዲሰሩ የተመደቡት በማዘጋጃ ቤቱ ውስጥ ፓርክና መናፈሻ በሚባል ክፍል ውስጥ ነበር፡፡ ይህንን ክፍልና ሌሎቹን ጨምሮ ይመሩ የነበሩት ኢጣሊያዊው ኢንጂነር ኮሎምቦ ነበሩ፡፡ ኢንጂነር ጌታቸው ይህን ስራቸውን በጀመሩበት ወቅት የአፍሪካ መሪዎች ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ ተብሎ ከተማይቱ ከፍተኛ ውጥረት ላይ የነበረችበት ጊዜ ነበር፡፡
የህንጻ ግንባታው መንገዱ ጽዳቱ ሁሉም ትኩረት የተሰጠው ነበር፡፡ ነገር ግን በጊዜው የአፍሪካ አዳራሽ ህንጻ አካባቢ ያለው ስፍራ የተጎሳቆለ እና ጽዳት የጎደለው ነበር፡፡ ይህን ቦታ ጽዱ እና ያማረ ለማድረግ ቀደም ብሎ በኢንጂነር ኮሎምቦ እና በኢንጂነር ጌታቸው የተዘጋጀ ፕሮጀክት ነበር። በጊዜውም ኢንጂነር ጌታቸው ወደ ማዘጋጃ ቤት እንዲገቡ የተደረገው ይህን እቅድ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ነበር፡፡ ዕቅዱ ዋናው መሀንዲስ ኮሎምቦና ረዳቱ ጅኦሜትራ ደሩኝ ከሥር ከሥር ጥናቱን እያጠኑ፣ የጥናቱን ዝርዝር ለኢንጂነር ጌታቸው በማስተላለፍ ሥራውን እንዲሠራ ነበር።
ይህ አካሄድ ያልጣማቸው ኢንጂነሩ በመጀመሪያ ስለ አጠቃላይ ፕሮጀክቱ ለመረዳት የተዘጋጀው ፕሮጀክት እንዲሰጣቸው ጠየቁ፤ ይህ ፕሮጀክት ደግሞ ለወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉስ ቀርቦ ሊጸድቅ ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርቶት ነበር፡፡ ኢንጂነር ጌታቸው ግን ፕሮጀክቱን ሲመለከቱት ከብዙ አቅጣጫ ብቁ ሆኖ አላገኙትም ነበር።
ስለዚህ በጊዜው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ለነበሩት ዘውዴ ገብረሥላሴ፤ ‹‹ይህ ፕሮጀክት ልክ አይደለም አንደኛ የግንብ ብዛት አለው፤ ሁለተኛ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል፣ ሶስተኛ ለመኪና ማቆሚያ የተከለለው ቦታ የተዘጋጀው 250 መኪና ብቻ ማስተናገድ እንዲችል ተደርጎ ነው፡፡ ይህንን ቦታ ከዛ በተሻለ ዘመናዊ በሆነ መልኩ በመገንባት ለብዙ መኪናዎች ማቆሚያ ጭምር ማድረግ ይቻላል፡፡ ስለዚህ `እኔ ላጥናው፡፡›› በማለት ይጠይቃሉ።
ከንቲባው የጊዜው መቃረብ ያሳስባቸው ስለነበር ‹‹ጊዜ የለንም፤ ይህ ጥናት ብዙ ጊዜ ፈጅቷል በፕሮጀክቱ መሠረት ቶሎ ተብሎ ወደ ተግባር መግባት ይኖርብናል›› ቢሉም ኢንጂነር ጌታቸው ግን በሃሳባቸው በመጽናት ‹‹እኔ ሌትና ቀንም ቢሆን ሠርቼ በቶሎ አደርሳለሁ፡፡›› በማለት ትንሽ ቀን እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ፤ ከንቲባውም ኢንጂነሩ ለፕሮጀክቱ የሰጡትን ከፍተኛ ትኩረት በማስተዋል ጥያቄያቸውን ተቀብለዋቸዋል።
ኢንጂነር ጌታቸው በገቡት ቃል መሠረት ቀንና ሌት በመስራት በጥቂት ቀናት ውስጥ ንድፉን ሠርተው ለከንቲባው አቀረቡ። ከንቲባው የቀረበላቸውን ንድፍ ሲመለከቱ በንድፉ በእጅጉ ተሳቡ፤ ሲመለከቱም ለ250 መኪና ማቆሚያ ታስቦ የነበረው ቦታ ወደ 525 መኪና ለማስቆም መቻሉን ተገነዘቡ። በበፊቱ ፕሮጀክት ላይ የነበሩ አላስፈላጊ ግንቦች ቀርተው፤ ሁሉ ነገር መልክ መያዙን በመረዳት ክቡር ከንቲባው በኢንጂነር ጌታቸው በቀረበው ንድፍ ተደስተው በቶሎ እንዲያልቅ ባዘዙት መሠረት ኢንጂነሩ ፕሮጀክታቸውን በፍጥነት በመጨረስ ለከንቲባው አቀረቡ። ይሄው ፕሮጀክት በኢንጂነር ጌታቸው አስረጅነትና በከንቲባው አማካኝነት ለንጉሱ ቀርቦ ሥራ ላይ ዋለ። ኢንጂነር ጌታቸውም ፕሮጀክቱ ለመሥራት ጨረታ ካሸነፈው የጣሊያን ኩባንያ ጋር የሥራው ተቆጣጣሪ መሀንዲስ በመሆን፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አደራሽ እውን ማድረግ ቻሉ።
ኢንጂነር ጌታቸው በመቀጠል የተረከቡት የጽዳትና ፕላን ክፍል ኃላፊነትን ነበር፡፡ ይህንን የሥራ ኃላፊነት እንደተረከቡ ካከናወኑት ሥራውን ለማቀላጠፍና ውጤታማ ለማድረግ የተወሰኑ ማሻሻያዎች አድርገዋል። ከእነዚህ መካከል ዋና ዋናዎቹ፦ ሥራዎች በሥራ ጣቢያቸው መልክ አስይዘዋል፡፡ ለየሥራውም በተለያዩ ቦታዎች ብቃት አላቸው ብለው የሚያምኑባቸውን ሙያተኞችና ሠራተኞች መደቡ፣ ተከማችቶ ለነበረው ሥራ የሠራተኛ ኃይል መደቡ፣ ከውዝፍ ሥራ የዕለት ተዕለት ሥራ ቅድሚያ እንዲሰጠው አደረጉ።
ኢንጂነር ጌታቸው በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ክለሳ የተለያዩ ሥራዎችን ሰርተዋል፡፡ ዘጠኝ መቶ ሺህ ነዋሪዎችን ታሳቢ አድርጎ የተዘጋጀውን ፕላን የህዝብ ቁጥሩ ዕድገቱን ባማከለ መልኩ እንዲዘጋጅ አድርገዋል። ዋናውን የከተማ እምብርት ወደ ብሔራዊ ትያትርና ወደ ፖስት ቤት እንዲወርድ አድርገዋል። በዚህን ወቅት ቤት ሰሪዎች ቤታቸውን ሲሠሩ በፕላኑ መሠረት እንዲሰሩ ውል እንዲገቡ አድርገዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በከተማዋ መሀል የሚገኙ ወንዞች የሚያስከትሉት መጥፎ ጠረን ለማስቀረት ወደ ፊት የሚገነቡ ህንፃዎች ወንዞችን እየሸፈኑ ማለፍ እንዳለባቸው ኢንጂነር ጌታቸው ባጠኑት የአሥር ዓመት ማስተር ፕላን ላይ ተቀምጧል።
ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ወደ ውጭ ልከው ካስተማሯቸው አርክቴክቸሮች አንዱ የሆኑት ኢንጂነር ጌታቸው፤ የአንበሳ አውቶቡስ ሞዴል ያመጡ ፣ የአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻዎችና የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ፕላን ሠርተው ያቀረቡ ባለሙያ ናቸው። በህይወት ዘመናቸው የካ ተራራ ጫፍ የሚገኘውና እየፈራረሰ ያለው ዋሻ ሚካኤልን ከመፍረስ ለመታደግ ብዙ ጥረት አደርገዋል።
ከ10 አመት በላይ በማዘጋጃ ቤት ካገለገሉ በኋላ ወደ መንግሥት ንብረት ድርጅት የተዘዋወሩት ኢንጂነር ጌታቸው፤ ቀጥለውም የብሔራዊ ሀብት ልማት ኮርፖሬሽን ኃላፊ በመሆን እየሰሩ የማስፋፋት ስራቸውን ተያያዙት፡፡ ነገር ግን እንደፈለጉት አልቀጠሉም። ምክንያቱም አብዮቱ ፈነዳ፤ ደርግ ለስምንት አመት አሰራቸው፡፡ ኢንጂነር ጌታቸው ደርግ ለስምንት አመት ቢያስራቸውም ታላቅ ወንድማቸውን ያለ ምንም ፍርድ ቢገድልባቸውም ተሰደው ወደ ውጭ መሄዱን አልፈለጉትም፡፡ ይልቁንም በልዩ ልዩ የግል ወይም ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ በሀገራቸው ለማገልገል ወሰኑ፡፡
ኢንጂነር ጌታቸው ወይዘሮ የሺሀረግ ዋዠጎን አግብተው ሁለት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን፤ የህይወት ታሪካቸው መጽሐፍ ከ12 አመት በፊት በ156 ገጽ ታትሞ የወጣ ሲሆን ፤ የራሳቸውን ሰነድ በመያዝም ለብዙዎች አርአያ ሆነዋል፡፡ ኢንጂነር ጌታቸው ህዳር 30 2016 በተወለዱ በ95 አመታቸው ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸውም በቅድስት ስላሴ መንበረ ጸባኦት ቤተክርስቲያን ታኅሣሥ 1 ቀን 2016 ተፈፅሟል። እኛም እኚህን የሀገር ባለውለታ ነፍስ ይመር እንላለን።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 15 ቀን 2016 ዓ.ም