የኢትዮጵያውያን አትሌቶች የበላይነት የተንጸባረቀባቸው ውድድሮች

በአህጉረ እስያ በግዝፈታቸው ተጠቃሽ ከሆኑ የጎዳና ውድድሮች መካከል አንዱ የሕንዷ ሙምባይ የምታዘጋጀው ማራቶን ነው። ይህ ማራቶን በርካታ ቁጥር ያለው ሯጭ በማሳተፍ፤ እንዲሁም ከፍተኛ መጠን ያለው የገንዘብ ሽልማት በማቅረብም ነው የሚታወቀው። በሩጫው በርካታ ታዋቂ አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተደጋጋሚ የሆነ የበላይነትን በማስመዝገብም ይታወቃሉ። የስፍራው ክብረወሰንም በሁለቱም ጾታ የተያዘው በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ነው።

ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ በተካሄደው በዚህ ማራቶንም በተመሳሳይ በሁለቱም ጾታዎች ፍጹም የበላይነትን በመያዝ አጠናቅቀዋል። ሞቃታማ በነበረው የአየር ሁኔታ አትሌቶቹ እርስ በእርሳቸው ጠንካራ ፉክክር ማድረግም ችለዋል። በወንዶች በኩል በተደረገው ውድድር የአምናው አሸናፊና የሩጫው ክብረወሰን ባለቤት የሆነው አትሌት ለሚ ብርሃኑ በድጋሚ አሸናፊ ሊሆን ችሏል። አትሌቱ በሀገሩ ልጅ ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን ከዓመት በኋላ አሻሽሎ ሊጨብጥ የቻለው 2:07:32 በመሮጥ ሲሆን፤ ይህም ከቀድሞው ሰዓት በአንድ ደቂቃ የፈጠነ ነበር።

ነገር ግን አትሌቱ እአአ በ2016 የዱባይ ማራቶንን የሸፈነበት 2:04:33 የሆነ ሰዓት የግሉ ምርጥ ሰዓት ነው። የቦስተን፣ ዙሪክ፣ የዱባይ እና የዚመን ማራቶን አሸናፊው ለሚ ብርሃኑ እአአ ከ2019 በኋላ ከውድድር ርቆ ቢቆይም ባለፈው ዓመት በምርጥ ብቃት ዳግም ወደ ውድድር ሊመለስ ችሏል። በዚህም ለሁለተኛ ጊዜ በተሳተፈበት የዘንድሮ የሙምባይ ማራቶን ከቀድሞ ሰዓቱ 19 ሰከንዶችን ብቻ ዘግይቶ በመግባት 2:07:50 የሆነ ሰዓት አስመዝግቧል።

 እስከ 39ኛው ኪሎ ሜትር ድረስ በፍጥነት ሲሮጥ የቆየው አትሌቱ የራሱን ክብረወሰን ያሻሽላል በሚል እንዲጠበቅ ያደረገው ቢሆንም በስፍራው በነበረው ሙቀት የተነሳ ሊሳካለት አልቻለም። ውጤቱን ተከትሎም አትሌቱ ‹‹አስደናቂ ውድድር ነበር፤ ሰዓቴን ለማሻሻል ብጥርም የመጨረሻዎቹ 3 ኪሎ ሜትሮች አስቸጋሪ ነበሩ›› ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል። የ29 ዓመቱ አትሌት ለሚ ብርሃኑ የሙምባይ ማራቶን አሸናፊነቱን ተከትሎም 50ሺህ ዶላር ወደ ኪሱ አስገብቷል። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሃይማኖት አለው ደግሞ ለሚን ተከትሎ በመግባት ሁለተኛ ደረጃን መያዝ ችሏል። አትሌቱ የገባበት ሰዓትም 2:09:03 ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፤ ሌላኛው አትሌት ምትኩ ጣፋ ደግሞ ሰከንዶችን ዘግይቶ ውድድሩን በሦስተኛነት ሊፈጽም ችሏል፡፡

በሴቶች በኩል በተካሄደው ውድድርም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከ1 እስከ 9 ባለው ደረጃ ተከታትለው መግባት ችለዋል። የሀገሯን ልጆች አስከትላ በመግባት የውድድሩ አሸናፊ የሆነችው ደግሞ ለማራቶን እንግዳ የሆነችው አትሌት አበራሽ ምንሰዎ ናት። የ22 ዓመቷ ወጣት አትሌት በረጅም ርቀት የመም ውድድሮች ስትሳተፍ ቆይታ የመጀመሪያ ማራቶኗን በመሮጥም ነው አሸናፊ ልትሆን የቻለችው። የገባችበት ሰዓትም 2:26:06 ሆኖ ተመዝግቧል። 45 ሰከንዶችን ዘግይታ የገባችው ሌላኛዋ አትሌት በርቀቱ ልምድ ያላት ሙሉሃብት ጸጋ ናት። መድህን ደጀኔ ሦስተኛ ስትሆን፤ አይናዲስ ተሾመ፣ አበራሽ ደምሴ፣ አንቺዓለም ሃይማኖት፣ አያንቱ ገመቹ፣ ፋንቱ ገላሳ እና ሙሉጎጃም ብርሃን ደግሞ ቀጣዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል። አሸናፊዋ አትሌት አበራሽ ከውድድሩ በኋላም ‹‹የመጀመሪያውን የማራቶን ውድድሬን በአሸናፊነት በማጠናቀቄ ተደስቻለሁ›› ስትልም ስሜቷን አንጸባርቃለች።

ሌላኛው ማራቶን በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ የተሰጠው የሆንግ ኮንግ ማራቶን ሲሆን፤ 70ሺህ ሰዎች የተሳተፉበትም ነበር። በሴቶች በኩል በነበረው ውድድር አሸናፊ የሆነችው አትሌት መዲና ደሜ 2:28:47 በሆነ ሰዓት መግባት ችላለች። ኬንያዊቷ አትሌት ባትሪስ ቼፕቶ ስትከተላት፤ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ጋዲሴ ሙሉ እና ሙሉዬ ደቀቦ ደግሞ ሦስተኛና አራተኛ ሆነዋል። በወንዶች በኩል በተካሄደው ውድድርም ኬንያዊው አትሌት አንደርሰን ሴሮይ አሸናፊ ሲሆን፤ ደቡብ አፍሪካዊው ስቴፈን ሞኮካ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። በአፍሪካውያን አትሌቶች የበላይነት በተያዘው ውድድር ሦስተኛ በመሆን የፈጸመው አትሌት ደግሞ ኢትዮጵያዊው መኳንንት አየነው 2:13:09 የሆነ ሰዓት አስመዝግቧል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ጥር  14/2016

Recommended For You