3ኛው አፍሪካ ዋንጫና የዛሬዋ እለት!!

አፍሪካ የራሷ ትልቅ የእግር ኳስ ውድድር እንዲኖራት ካደረጉ ሶስት አገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ በመሰረተችው መድረክ ደጋግማ መታየት አለመቻሏ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ቁጭት ነው። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ከመጠንሰስ ጀምሮ ታላቁን መድረክ ሶስት ጊዜ በማሰናዳትና አንድ ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ታሪክ ስትሰራ እዚህ ግባ የሚባል የእግር ኳስ መሰረት ያልነበራቸው አገራት ዛሬ ላይ በመድረኩ ሲደምቁ ኢትዮጵያ ዳር ቆማ መመልከት ግድ ሆኖባታል።

ከአስተዳደራዊ ችግር እስከ ዘመናዊ መዋቅርና ጊዜውን የዋጀ የእግር ኳስ ስርአት  ስር በሰደደ ችግር የተተበተበውና ደረጃው ከዓመት ዓመት እያሽቆለቆለ ያለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዛሬ ላይ የሚፅናናበት ነገር ቢኖር ብሔራዊ ቡድኑ በታሪክ የማይረሳውን ገድል ያስመዘገበበት 3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ብቻ ነው። ይህ ታሪካዊ የአፍሪካ ዋንጫ ድል ልክ በዛሬዋ እለት ከ62 ዓመታት በፊት ጥር 13/ 1954 ነበር የተመዘገበው።

ዘመን ተሻጋሪው ታሪክ ሁሌም በሚታወሰው ብሔራዊ ቡድን ጀብድ ሲመዘገብ ዛሬ ላይ እንደቀላል በሚታዩ ነገሮችን ሳይቀር ተፈትኖ ነው። 2ኛው አፍሪካ ዋንጫ በግብፅ ካይሮ ሊደረግ የቀናት ዕደሜ ብቻ እስኪቀረው ድረስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ለጨዋታው ከመጓዙ አስቀድሞ እንደ አሁኑ ጊዜ የተመቸና ደረጃውን የጠበቀ የመጫወቻ ጫማ ወይም ታኬታ እንኳን አልነበረውም። ተጫዋቾቹ ገና የመጀመሪያ ልምምዳቸውን ሲያደርጉ ጀምሮ የመጫወቻ ታኬታቸው እያንሸራተተ ሲያስቸግራቸው እንደነበር በታሪክ ሰፍሮ ይገኛል። ይህም ለቡድኑ ሽንፈት የራሱ ሚና እንደነበረው ይነገራል። የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች በዚህ ቁጭት ውስጥ ሆነውም ነበር ወደ አገራቸው ለመመለስ የተገደዱት።

በሦስተኛው የአፍሪካ ዋናጫ ላይ ለመሳተፍ በተደረገው የማጣሪያ ጨዋታም 12 ቡድኖች ተፋልመው ኢትዮጵያ፣ ቱኒዚያ፣ ግብፅ (በያኔው አጠራሯ የአረብ ሪፐብሊክ) እና ዩጋንዳ ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ለውድድሩ አልፈው በመድረኩ ቀረቡ።

ኢትዮጵያ በእግር ኳስ ታሪኳ ብርቅዬ የሆነውን ብቸኛ ዋንጫ ያገኘችበትና የአንድ ሳምንት ዕድሜ የነበረው ሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጥር 06/1954 በአዲስ አበባ ስታዲየም (በቀድሞ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስቴድየም) በኢትዮጵያ እና በቱኒዚያ መካከል በተደረገ ጨዋታ አንድ ብሎ ተጀመረ።

በውድድሩ ላይም አራቱ ቡድኖች ሁለት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎችን እንዲሁም ለፍፃሜና ለሦስተኛ ደረጃ ሌሎች ሁለት ጨዋታዎችን አደረጉ። በውድድሩ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታም አዘጋጇ ኢትዮጵያ ቱኒዚያን ስትገጥም የሁለተኛው አፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ የነበረችው ግብፅ ከዩጋንዳ እንድትጫወት ተደረገ።

በወቅቱ ኢትዮጵያ ቱኒዚያን፥ ግብፅ ደግሞ ዩጋንዳን በመርታት ለፍፃሜው መብቃት ቻሉ። ኢትዮጵያና ግብፅ ለፍፃሜ መብቃታቸው ሲታወቅም የሁለቱ ቡድኖች የቀደመ የእርስ በርስ ግንኙነትና መሰል ሁኔታዎች በጨዋታው ዙሪያ ያለውን ውጥረት በእጅጉ ጨመረው።

ግብፅ ከአምስት ዓመታት በፊት በ1949 የተደረገውን የመጀመሪያ የአፍሪካ ዋንጫ የወሰደችው ኢትዮጵያን 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ ነበር። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት የሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቁጭት ከሁለቱ አገሮች ታሪካዊ ባላንጣነት ጋር ተደምሮ የ3ኛውን አፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ ስሜት አናረው።

የአዲስ አበባ ስቴድየም በ 25,000 ደጋፊዎች ተሞልቶ በአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክ የምንጊዜውም ልብ ሰቃይና አዝናኙ ጨዋታ ተጀመረ። በጋለ ስሜት በሚካሄደው ፍልሚያ በ35ኛው ደቂቃ ግብፅ አብዱልፈታ በደዊ አማካኝነት ስቴድየሙን በድንጋጤ ፀጥ ረጭ ያደረገች ግብ አስቆጠረች። የፈርኦኖቹ መሪነት መዝለቅ የቻለውም እስከ 74ኛው ደቂቃ ነበር። በጨዋታው ላይ የቡድኑን አጥቂ ግርማ ዘለቀን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው ተክሌ ኪዳኔ የአቻነቱን ግብ አስቆጥሮ ጨዋታውን ዳግም ወደ ውጥረት መለሰው። ነገርግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአቻነት ቆይታ ሽርፍራፊ ሰከንዶችን መሻገር አልቻለም።

የግብፁ የግብ አዳኝ በደዊ አገሩን ወደ 2 ለ 1 መሪነት የቀየረችውን ሁለተኛ ግብ ከመረብ አሳረፈ። የትኛውም የአፍሪካ አገር አንድ ዋንጫ ባላሳከበት ሁኔታም ግብፅ የውድድሩን ሦስተኛ ተከታታይ ድል ለማስመዝገብ መቃረቧ እውን መሰለ። በዚህ ውጥረት ውስጥ ግን ተስፋ ያልቆረጡት የይድነቃቸው ተሰማ ልጆች ወደፊት መግፋታቸውን ቀጠሉ። ከደቂቃዎች በኋላም ሉቺያኖ ቫሳሎ ከወቅቱ የኮተን ተጫዋች ጌታቸው ወልዴ የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ጨዋታውን ወደ 2 ለ 2 አቻነት ቀየረ። ከጎሉ አስቆጣሪ ተጫዋች ማንነት ጋር በተያያዘ በወቅቱ የተፈጠረው የታሪክ ብዥታ ግን አሁንም አለ።

የታሪክ መፋለሱ መነሻም ወሳኟን የአቻነት ግብ ከሉቺያኖ ይልቅ የቡድን አጋሩ መንግሥቱ ወርቁ እንዳስቆጠረ በአፍሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ካፍ ህትመቶች ጭምር መፃፉ ነበር። በሌላ በኩል ግን ሉቻኖ ቫሳሎ የአቻነቷን ግብ ለማስቆጠር ያስቻለችውን ኳስ ከጌታቸው ወልዴ ሲቀበል የሚሳይ የምስል ማስረጃ አለ።

የፍፃሜው ጨዋታም በዚህ መልክ ቀጥሎ መደበኛው የጨዋታ ሰዓት 2 ለ 2 በሆነ አቻ ውጤት ተፈፀመ። በወቅቱም ከጨዋታው ጋር በተያያዘ በመላው አዲስ አበባ የነበረው ውጥረት እስካሁንም ተደጋግሞ ሲነሳ ይደመጣል። ጨዋታው በዚህ መልክ በቀጠለበት ሁኔታ ላይም የጨዋታውን ውጥረት መቋቋም ያልቻሉት ግብፆች በ 101ኛው ደቂቃ የፈፀሙትን የመከላከል ስህተት ተጠቅሞ ኢታሎ ቫሳሎ ለራሱ ሁለተኛውን ለቡድኑ ደግሞ ሦስተኛውን ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው ወደ ኢትዮጵያ የ 3 ለ 2 መሪነት ተቀየረ።

በጨዋታው 117ኛ ደቂቃ ላይም የኢትዮጵያን የማሸነፍ ዕድል ያሰፋች በሌላኛው ፅንፍ የእንግዳዎቹን ፈርኦኖች ልብ የሰበረች ግብ ተቆጠረች። የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች መንግሥቱ ወርቁ ያገኛትን ኳስ በግሩም ሁኔታ እየገፋ ሔዶ አራት የግብፅ ተከላካዮችን በቄንጥ በማለፍ ጨዋታውን ወደ 4 ለ 2 የቀየረች ግብ ከመረብ ላይ አሳረፈ። ከአራተኛው ጎል መቆጠር ደቂቃዎች በኋላም የዋንጫውን አሸናፊ ያበሰረው የጨዋታው መጠናቀቂያ ፊሽካ ተሰማ።

በስቴድየም ተገኝተው ጨዋታውን የተከታተሉት የወቅቱ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በደስታ መንፈስ ተውጠው አንድ ለእናቱ ሆኖ ዘመናትን የተሻገረውን የአፍሪካ ዋንጫ  ለሉቺያኖ ቫሳሎ አበረከቱ።

የዚያ ታሪካዊ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብ ስብ ግብ ጠባቂ ጊላ ሚካኤል ተክለ ማርያም ሲሆን ከአስመራው አዶሊስ ክለብ የተገኘ ነው። ተከላካዮች አስመላሽ በርሄ (ከኢትዮ-ሴመንት፣ ድሬድዋ)፣ አወድ መሀመድ (ከኦሜድላ፣ አዲስ አበባ)፣ በርሄ ጎይቶም (ከቴሌ፣ አስመራ) እና ክፍሎም አራያ (ከቴሌ፣ አስመራ) ናቸው።

አማካዮች  ተስፋዬ ገ/መድህን (ከቴሌ፣ አስመራ) እና ሉቺያኖ ቫሳሎ (ከኮተን፣ ድሬድዋ)፤ አጥቂዎች ግርማ ዘለቀ (ከኮተን፣ ድሬድዋ)፣ መንግስቱ ወርቁ (ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ አዲስ አበባ)፣ ኢታሎ ቫሳሎ (ከኮተን፣ ድሬድዋ) እና ጌታቸው ወልዴ (ከኮተን፣ ድሬድዋ) የተገኙ ናቸው።

የቡድን መሪው ታሪካዊው የአፍሪካ ስፖርት አባት ይድነቃቸው ተሰማ ሲሆኑ፣ አሰልጣኞች ሚሎሶቪች (ከዩጎዝላቪያ)፣ አዳሙ አለሙ እና ፀሐዬ ባህር ኢትዮጵያን ነበሩ።

ቦጋለ አበበ

Recommended For You