
አዲስ አበባ፡- በአማራ ክልል የንጹሕ መጠጥ ውሀ አቅርቦትን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ 43 ትላልቅ የውሀ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑን የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ኤፍሬም ምንሽር ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ክልሉ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ 43 ትላልቅ የውሃ ፕሮጀክቶችን እየገነባ ነው። በአሁኑ ወቅትም የፕሮጀክቶቹ የአፈፃፀም ደረጃ 65 በመቶ ደርሷል። በለጋሽ ድርጅቶችና በመንግሥት በጀት እየተገነቡ የሚገኙት እነዚህ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ አሁን ያለው የክልሉ 73 በመቶ የውሃ ሽፋን ተደራሽነት ወደ 76 በመቶ ከፍ ይላል።
በገጠር ለሚኖረው ማኅበረሰብ ንጹሕ መጠጥ ውሃ ተደራሽ ለማድረግ አነስተኛ የውሃ ጉድጓዶች እየተቆፈሩ መሆናቸውን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ ለከተማው ማኅበረሰብ ደግሞ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ ትላልቅ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ከውጪ ከሚመጡ ግብዓቶች ጋር የተያያዘና የፀጥታ ችግር ካላጋጠመ በስተቀር እየተሠሩ ካሉት 43 ፕሮጀክቶች ውስጥ 35 የሚሆኑት በያዝነው ዓመት ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።
‹‹በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ተበታትነው የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ንጹሕ የመጠጥ ውሃ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው፤ እየተሠራ ባለውም ሥራ አንድ ሺህ 200 የሚሆኑ አነስተኛ የውሃ ጉድጓድ ለመገንባት ጥረት እየተደረገ ነው›› ሲሉ አብራርተዋል።
እንደ አቶ ኤፍሬም ማብራሪያ፤ በክልሉ እየተገነቡ ከሚገኙት የውሃ ፕሮጀክቶች የጥራት ችግር ኖሯቸው በማኅበረሰቡ ላይ የጤና ችግር እንዳያደርሱ የውሃ መገኛ ቦታዎች ላይ ጥናት ይካሄዳል። የተገኘው ውሃ ለመጠጥ የሚውል መሆኑ አለመሆኑ የልየታ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ ፕሮጀክቶች ላይ የክትትልና የቁጥጥር ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
በክልሉ የመጠጥ ውሃ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ባለ ሥራ በርካታ ጉድጓዶች ተቆፍረው የጥራት ጉድለትና ከፍተኛ የሆነ የኬሚካል መጠን በውስጣቸው መገኘቱን በመጥቀስ፤ ማኅበረሰቡም እንዳይጠቀማቸው የማድረግ ሥራ መሠራቱን ጠቁመዋል።
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም