እግር ኳስ የሚያግባባቸው ዝሆኖች

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አፍሪካ በዓለም የእግር ኳስ ካርታ ላይ “የምርጥ ችሎታ መገኛ” በሚል ተካትታለች። ይህም የሆነው በየጊዜው እየተፈጠሩ ካሉ ምርጥ አቋም ያላቸው ተጫዋቾችና ተፎካካሪ ቡድኖች ጋር ተያይዞ ነው። ከሁሉም በላይ ግን እግር ኳስ በአፍሪካ እጅግ ተወዳጅ ብቻም ሳይሆን አስፈላጊ የስፖርት ዓይነትም ነው። ምክንያቱም እግር ኳስ መግባቢያ፣ ለወጣቶቿ አማራጭ የሥራ ዘርፍ፣ ለትውልዱም ተስፋ የሆነ ስፖርት ነው።

በአህጉሪቷ ከፍተኛ የእግር ኳስ አቅም ካላቸው ሀገራት መካከል ደግሞ 34ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ በማስተናገድ ላይ የምትገኘው ኮትዲቯር አንዷ ናት። እአአ ከ1960 ወዲህ የተቋቋመው ብሔራዊ ቡድኗ በአፍሪካ ዋንጫ እና ዓለም ዋንጫ ተሳትፎ እንዲሁም በአህጉሪቷ ተጽዕኖ ፈጣሪ በመሆን ተጠቃሽም ነው። ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ከተላቀቀች በኋላ ብሔራዊ ቡድን በማቋቋም ውድድሮችን የተቀላቀለችው ኮትዲቯር ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አንጻር የዘገየ ቢሆንም ስሟን በመልካም ለመጻፍ ግን ረጅም ጊዜ አልወሰደባትም።

እአአ ከ1965 የጀመረው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ታሪኳም የዘንድሮውን ውድድር በድምቀት እስከ ማዘጋጀት የዘለቀ ነው። ባለፈው ወር በወጣው የፊፋ ሀገራት የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ ከዓለም 49ኛ ደረጃን የያዘችው ሀገሪቷ፤ የመጀመሪያውን የአፍሪካ ዋንጫ እአአ በ1992፣ ሁለተኛውን ደግሞ በ2015 ማንሳት ችላለች። በዓለም ዋንጫም የውጤታማነት ታሪክ መጻፍ ባትችልም እአአ በ2006፣ 2010 እና 2014 ተሳታፊ መሆን ችላለች።

ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር እንደ እግር ኳስ ሀገርነቷ ለዜጎቿ በቂ የሚባል የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችንና ስፖርቱ የሚጎለብትበትን ዕድል የተመቻቸ ነው ሊባል አይችልም። ነገር ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ በምርጥ ብቃታቸው ስማቸው የገነነ ተጫዋቾችን ማፍራት ችላለች። የቀድሞው የቼልሲ ኮከብ ዲድየር ድሮግባ፣ ያያ ቱሬ፣ ኮሎ ቱሬ፣ ጀርቪኒሆ፣ ሰለሞን ካሉ፣ ዊልፍሬድ ቦኒ ከቀድሞቹ ሊጠቀሱ ይችላሉ። በዚህ ወቅት ደግሞ ዊሊ ቦሊ፣ ሰርጌ ኦሪየር፣ ኤሪክ ቤሊ፣ ኬሲ፣ አክፓ አክፕሮ፣ ዛሃ፣ ኒኮላስ ፔፔ፣ ሰባስቲያን ሃለር የመሳሰሉ ተጫዋቾች በአንጋፎቻቸው እግር ተተክተው ዝሆኖቹን በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ሌሎች ወጣትና ታዳጊ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ደግሞ በተለያዩ የአውሮፓና አረብ ሀገራት ክለቦችና አካዳሚዎች ውስጥ ቀጣይ ሕይወታቸውን ለማሳመር እየተጉ ይገኛሉ። በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ እየተሳተፈ ካለው ብሔራዊ ቡድኗ ከተመረጡት ተጫዋቾች መካከል 96 ከመቶ የሚሆኑት በአውሮፓና ሌሎች ሀገራት ሊጎች በመጫወት ላይ የሚገኙ መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።

እነዚህ ተጫዋቾች በአውሮፓ ክለቦች ውስጥ ተጫውተው የሚያገኙትን ገንዘብ መልሰው በሀገራቸው ልማት ላይ በማዋል ኢኮኖሚውንም ይደጉማሉ። በተለይ ከአንዱ ክለብ ወደ ሌላኛው ሲዘዋወሩ የሚያገኙት ገንዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ ግልጽ ነው። ለአብነት ያህል ኮትዲቯራዊው የክንፍ ተጫዋች ኒኮላስ ፔፔ እአአ በ2019 ወደ አርሰናል የተዘዋወረበት 72 ሚሊየን ዩሮ ሲሆን፤ ከአፍሪካዊያን ተጫዋቾች ከፍተኛው ነበር። ይህንን ተከትሎም በሀገራቸው መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ፤ እንዲሁም በበጎ አድራጎት ላይ በመሰማራት ሕዝባቸውን ይጠቅማሉ። ከእግር ኳስ ባለፈ በተለያዩ የማስታወቂያ ሥራዎች ላይ ባላቸው ተሳትፎና ተፈላጊነትም ከስማቸው ጋር ተያይዞ ሀገራቸው እንድትነሳም ምክንያት ናቸው። ከዚህ ባለፈ ባህልን በማስተዋወቅ፣ ማህበረሰቡን በማነቃቃት እንዲሁም ለታዳጊዎች መልካም ምሳሌ በመሆን ረገድም ያላቸው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው።

ለኮትዲቯር እግር ኳስ ባለውለታዋም ነው። ወጣቶቿ ከአስከፊ ድህነት ተላቀው ለሌሎችም እንዲተርፉ ያደረገ፣ ኢኮኖሚዋን ማንቀሳቀስ የቻለ እንዲሁም ሰላሟን የመለሰ ስፖርት ነው። በርግጥ አፍሪካና እግር ኳስ ሊነጣጠሉ የማይችሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች እስኪመስሉ ድረስ አምባገነን መሪዎቿ ጭምር እጅ የሚሰጡት የፖለቲካ ትኩሳትንም የማብረድ አቅም ያለው ስፖርት ነው። በእግር ኳስ ውጤትን በጸጋ አለመቀበል የጸብ መንስኤ የመሆኑን ያህል እርቅን ለማውረድም ምክንያት እንደሆነ የኮትዲቯርን ያህል አስረጂ አይገኝም። እአአ 2006 በተካሄደው የጀርመኑ ዓለም ዋንጫ ሀገሪቷ ተሳታፊ መሆኗን ተከትሎ ተጫዋቾቿ ከግጥሚያ በኋላ በጉልበታቸው እንደተንበረከኩ በሀገራቸው በሁለት ጎራ ተከፍለው የእርስ በእርስ ግጭት ሲያደርጉ ለነበሩ አካላት ፍጅቱን ያቆሙ፣ በሰላምም ይኖሩ ዘንድ ተማጸኑ። እግር ኳስ ነፍሳቸው ድረስ ሰርጻ የገባችው ሁለቱ ጽንፎችም አለመግባባታቸውን ትተው ግጭቱን ለማብረድ ተስማሙ። ይኸውም በእግር ኳስ ታሪክ ከተጻፉ ወርቃማ ታሪኮች አንዱ ሆኖ ሲዘከር የሚኖር ነው። በርግጥ አለመግባባቱ ከቆይታ በኋላ ማገርሸቱ አልቀረም፤ ነገር ግን በሀገራቸው የሚሰናዳውን ይህንን የአፍሪካ ዋንጫ በማሰብ ልዩነታቸውን ገትተው በአንድነት እንግዶቻቸውን በማስተናገድ ላይ ነው የሚገኙት።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ጥር 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You