ውጤት መቀልበስ ለወጣት ቡድኑ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ

የዓለም ዋንጫ ተሳትፏቸው አጣብቂኝ ውስጥ የገባው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከነገ በስቲያ ወሳኙን ጨዋታ ያከናውናል። የወጣት ቡድኑ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ በሚያደርገው ጨዋታ የሞሮኮን ሽንፈት መቀልበስ ከቻለም አፍሪካን በዓለም ዋንጫው ከሚወክሉ አራት ቡድኖች መካከል ይካተታል። ቡድኑ ዕድሉን ለማቅናት ካዛብላንካ ላይ የታዩ ድክመቶቹን በማስተካከልና ስህተቶቹንም በማረም በሀገሩ አየርና ደጋፊው ፊት የሚኖረውን የ90 ደቂቃ ቆይታ መጠቀምም ይጠበቅበታል።

አራት ዙሮች ያሉትን የማጣሪያ ጨዋታ አልፎ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሰው የአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ቡድን ከሞሮኮ አቻው ጋር ካዛብላንካ ላይ ተጫውቶ 2 ለምንም በሆነ ውጤት ተሸንፎ መመለሱ ይታወቃል። ከጉዞ መልስ በኋላም የአንድ ቀን እረፍት ካደረገ በኋላ ወደ ዝግጅት የተመለሰ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን አስታውቋል። ቡድኑ ከሞሮኮ ጋር ለነበረበት የመጀመሪያ ጨዋታ ለሳምንታት ዝግጅት ሲያደርግ ቢቆይም የስልጠና ቡድኑ የጠየቀው የወዳጅነት ጨዋታ አለመመቻቸቱ በሚፈለገው ልክ እንዲገኝ እንቅፋት እንደሆነበት ተጠቁሞ ነበር። በጨዋታው ዕለትም ከፍተኛ የሆነ ያለመረጋጋት ችግር የተስተዋለበት ሲሆን፤ ይህም ለተጋጣሚያቸው ምቹ ሁኔታን ሊፈጥርላቸው ችሏል። የሰሜን አፍሪካዋ ሀገር ሞሮኮ ተጫዋቾች በኢትዮጵያዊያኑ በኩል የነበረውን ድክመት ተጠቅመውም በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች፤ እንዲሁም ከእረፍት መልስ ባሉት ደቂቃዎች በፍጥነት በማጥቃትና የግብ አጋጣሚዎችን በመፍጠር የበላይነቱን መያዝ ችለዋል።

ከወጣት ቡድን አንጻር የደረሱበት ደረጃ እጅግ አበረታችና መልካም የሚባል ቢሆንም ባለፈው ጨዋታ በታዩት ክፍተቶች በኩል መሻሻል ሳይችል አዲስ አበባ ላይም በተመሳሳይ ብልጫ ከተወሰደበት ከዓለም ዋንጫ ጉዞው ሊገታ ይችላል። በመሆኑም በጥረቱ ከጫፍ የደረሰው ቡድኑ ተረጋግቶና ተናቦ በመጫወት እንዲሁም ተጋጣሚያቸው ልዩነት ለመፍጠር በሚጠቀምበት ወቅት ለይቶ መጠንቀቅና በርካታ የግብ እድሎችን መፍጠር የግድ ነው። ነገር ግን፣ በታዳጊና ወጣት ቡድኖች ለመጫወትና ለማሸነፍ በሚኖር ከፍተኛ ጉጉት የተነሳ ዋጋ መክፈል በተደጋጋሚ የታየ ነው። በመሆኑም ይኸው ሁኔታ በዚህ ጨዋታ ተደግሞ የቡድኑ ጉዞ እንዳይሰናከል በዝግጅት ወቅት ስህተቶችን ማረም ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል ጨዋታው የሚደረገው በለመዱት የሀገራቸው አየርና በደጋፊዎቻቸው ፊት እንደመሆኑ ይህንን ዕድላቸውን በመጠቀም ተፎካካሪያቸው ላይ የበላይነቱን በመውሰድ እድሉን እንደሚጠቀሙም ይጠበቃል።

 ኮሎምቢያ አስተናጋጅ የሆነችበት 11ኛው የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ከወራት በኋላ ይጀመራል። በየሁለት ዓመቱ የሚደረገው ይህ ውድድር ቀድሞ 16 ቡድኖችን የሚያሳትፍ ቢሆንም ከዚህ ዓመት ጀምሮ ግን ቁጥሩን ወደ 24 በማሳደግ ይካሄዳል። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በአራት ቡድኖች የሚወከል ሲሆን፤ በማጣሪያውም 35 ቡድኖችን ሲያጫውት ቆይቷል። በማጣሪያው እስከ አራተኛው ዙር የደረሱ ስምንት ቡድኖች የሚለዩበት ወሳኙን የመጨረሻ ጨዋታቸውን ነገ እና ከነገ በስቲያ የሚያከናውኑ ይሆናል። በዚህም መሠረት ነገ ግብጽ ከካሜሮን እንዲሁም ብሩንዲ ከናይጄሪያ ሲጫወቱ፤ ከነገ በስቲያ ደግሞ ኢትዮጵያ ከሞሮኮ እንዲሁም ሴኔጋል ከጋና በሚኖራቸው የደርሶ መልስ ግጥሚያ አሸናፊ የሚሆነው ቡድን የኮሎምቢያ ቲኬቱን የሚቆርጥ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውጤቱን ቀልብሶ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎውን ማረጋገጥ ከቻለ ከ22 ዓመታት በፊት በአርጀንቲና ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ኢትዮጵያን የወከለውን የወንዶች ብሔራዊ ቡድን ታሪክ የሚጋራ ይሆናል። በዚህ ውድድር እንደ ናይጄሪያ እና ዴሞክራቲክ ኮንጎን የመሳሰሉ ሀገራት ተደጋጋሚ ተሳትፎ ያላቸው ሲሆን፤ የመድረኩ ብርቱ ተፎካካሪ የሆነው የናይጄሪያ ቡድን እአአ በ2004 እና 2006 አራተኛ ደረጃን ይዞ የተጠናቀቀበት ውጤት ቀዳሚው ነው። በርካታ ዋንጫዎችን በማንሳት ቀዳሚ የሆኑት ጀርመንና አሜሪካ ሶስት ሶስት ጊዜ ማሳካት ችለዋል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You