መሬትን በተቀናጀና በተናበበ መንገድ ማስተዳደርና መምራት ያስፈለገበት ዘመን

 የሀገሪቱ የመሬት አስተዳደር ነባራዊ ሁኔታ ሲታይ መሬት ላይ ፍላጎት ያላቸው ተቋማት ወይም መሬትን እንዲመሩ የተቋቋሙ መንግሥታዊ ተቋማት በርካታ ናቸው። ይህ አሰራር ተቀናጅቶ መሬትን በማስተዳደር በኩል አለመግባባት እንዲፈጠር፣ የግጭት መንስኤ እንዲሆን እያደረገ መሆኑ እየተጠቆመ ነው። መሬት የሚተዳደርበት ሕግም የከተማና የገጠር የሚል መሆኑ በራሱ ሌላው የልማት ተግዳሮት እንደሆነም ይገለጻል።

የመሬት አስተዳደር ሥራ የከተማ እንዲሁም የገጠር በሚሉ ሁለት አደረጃጀቶች ሲሰራ ቆይቷል። በከተማ የመሬት አስተዳደር ውስጥ ብቻ ብዙ መቀናጀት የማይታይባቸው ተቋማት ይገኛሉ። በገጠርም በተመሳሳይ የመሬት ተቋምን አንድ ላይ ያቀፈ አካል አለመኖሩ ለመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ ለሀብትና ጊዜ ብክነት መነሻ ሲሆን ይታያል የሚሉ ወገኖችም አሉ።

የዘርፉ ባለሙያዎችም በሀገሪቱ ከሚታዩ በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አንዱና ዋነኛው የመሬት አስተዳደር ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይሄንን ችግር ለመፍታት ቢያንስ ተቋማዊ አደረጃጀቱ ላይ መሥራት እንደሚገባም ያስገነዝባሉ።

በኢትዮጵያ መሬት አስተዳደር ባለሙያዎች ማህበር የተቋቋመው እና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች ተካሂዶ በቅርቡ የቀረበ ጥናት እንዳመለከተውም፤ ጥናቱ በመሬት አስተዳደር ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለይቷል፤ በዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ተሞክሮ ላይ የተመሰረተና ለመንግሥትም የፖሊሲ ግብዓት የሚሆን ምክረ ሃሳብም ይዞ ቀርቧል። የሀገሪቱ የመሬት አስተዳደር ሥርዓት መዘመን እንደሚኖርበትም አመላክቷል።

ዶክተር አቻምየለህ ጋሹ በባህር ዳር ዩኒቪርሲቲ የመሬት አስተዳደር ኢንስቲትዩት ተባባሪ ፕሮፌሰር እንዲሁም ኢትዮጵያ መሬት አስተዳደር ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ናቸው። እሳቸው እንዳሉት፤ መሬት በደላሎች እጅ የገባበት አንዱና ዋነኛው ምክንያት መሬትን በአግባቡ ሊመራ የሚችል የተግባባ የተቀናጀ ተቋማዊ አደረጃጀት ስለሌለ ነው። ደላሎች በብዛት ተፅዕኖ እያሳደሩ ያሉት በከተማ እና በከተማ ዙሪያ በሚገኘው መሬት ላይ ነው። በተለይም በከተማ ዙሪያ ባለው መሬት ላይ ችግሩ ተባብሶ ይስተዋላል።

የኢትዮጵያ መሬት አስተዳደር ባለሙያዎች ማህበር በሀገራችን ባለው የመሬት አስተዳደር ላይ የሚታዩ ከፍተኛ ችግሮችን ለማቅለል እንዲሁም የሀገራችን የመሬት አስተዳደር ባለሙያዎች መንግሥትንና ማህበረሰቡን በሙያቸው ለመደገፍ በሚል መነሻነት በ2012 ዓ.ም እንደገና የተቋቋመ ነው። ማህበሩ ሀገር አቀፍ ሽፋን ያለው ሲሆን በርካታ ባለሙያዎችንም ይዟል።

አባላቱም ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት፣ የግል ድርጅቶች እና ከትምህርት ተቋማት የተሰባሰቡ መሆናቸውን ዶክተር አቻምየለህ ጠቁመዋል። ማህበሩ ከተቋቋመ ወዲህ እንደ ሙያ ማህበር ጥናቶችን በማካሄድ መንግሥት ለፖሊሲ ግብዓት እንዲጠቀማቸው የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናገረዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ማህበሩ መንግሥት በሚያካሂደው የመሬት አስተዳደር ፖሊሲ ዝግጅት ላይ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል። በርካታ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችንም እየሰጠ ነው። አንድ የመሬት አስተዳደር ሥርዓት በሚሻሻልበት መንገድ በሰው ኃይል ግንባታው ላይም መሥራት ያስፈልጋል። በቀዳሚነት የአቅም ግንባታ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው።

በክልል ደረጃ ለአብነት የአማራ ክልል የመሬት አስተዳደር ተቋማዊ አደረጃጀቱን ወደ አንድ ተቋም ሲያመጣም ማህበሩ እና በማህበሩ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች ተሳትፎ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፣ ለዚህ ፖሊሲ ግብዓት የሚሆን ጥናት በማካሄድ በዚያ መሠረት የክልሉን የመሬት አስተዳደር ሥርዓት የሚመራ አንድ ተቋማዊ አደረጃጀት በመፍጠር የመሬት ቢሮ የሚል አደረጃጀት ተፈጥሮ እየተሰራበት መሆኑን አመልክተዋል።

ዶክተር አቻምየለህ እንዳብራሩት፤ መሬት የሰው ልጆች ውድ ሀብት ነው፤ የሀብቶች ሁሉ ምንጭ የሆነ ሀብትም ነው። ይህ ውድ ሀብት በአግባቡ ካልተመራና ካልተዳደረ የችግሮች ሁሉ ዋና ምክንያት ይሆናል። የመልካም አስተዳደር፣ የግጭቶች ሁሉ ችግር ከመሬት ጋር ሊያያዝ ይችላል።

የሰው ልጅ አብዛኛዎቹ ግጭቶች ከመሬት ጋር የተያያዙ መሆናቸውን የፍርድ ቤት ኬዞችን ዋቢ በማድረግ ዶክተር አቻምየለህ ገልጸዋል። ከፍርድ ቤት ኬዞች በርካታዎቹ ከዚሁ ጋር የተያያዙ ስለመሆናቸው ጥናቶች እንደሚያመለክቱ አስገንዝበዋል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈንታ ደጀን በበኩላቸው የሀገሪቱ ትልቅ ሀብት የሆነውን መሬት የማስተዳደር ሥራን ለማዘመንና አጠቃቀሙን ለማሻሻል መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራበት አጀንዳ መሆኑን አመላከተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታውም መሬት ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ልማትና እድገት የማይተካ ሚና ያለው የሀብቶች ሁሉ ቁንጮ የሆነ ሀብት መሆኑን አስገንዝበዋል። እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የኢኮኖሚ መሠረታቸው እና ሕዝባቸው በእርሻ ሥራ ላይ ለተመሰረተ ሀገሮች ደግሞ መሬት ማለት የተለየ ትርጉም ያለው ይላሉ።

ይህንን በሚገባ በመረዳትም መሬት በሀገራችን የሕገ መንግሥት አካል ሆኖ ተደንግጓል። በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት ላይ እንደተመለከተው መሬት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረ-ብሔሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ሀብት ነው። ክልሎች በተሰጣቸው የአስተዳደር ወሰን የፌዴራል መንግሥቱ በሚያወጣው ሕግ መሠረት የማስተዳደር ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል።

መሬት ከተፈጥሮ ሀብቶች ሁሉ አንዱና ትልቁ ነው። የሰው ቁጥር ሲጨምር፣ የልማት ፍላጎት ይጨምራል፣ የተፈጥሮ ሀብት ይቀንሳል፣ በዚህም የጥቅም ግጭት ይፈጠራል። የአሁኑና የወደፊቱ፣ አካባቢ እና ልማት፣ የግል እና የሕዝብ የልማት እሳቤዎች ይህንን የሀብቶች ሁሉ መሠረት፣ ለመልካም አስተዳደር መስፈን ወይም መታጣት ምሰሶ የሆነን ሀብት በአግባቡ ማስተዳደር አስፈላጊ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።

መሬትን በአግባቡ ማስተዳደር ማለት የመሬት ይዞታ መብት የሚሰጥበት፣ ዋስትና የሚከበርበት፣ የመሬት ሀብት ዋጋ የሚተመንበት፣ የመሬት አጠቃቀም ዕቅድ የሚተገበርበት በመሬት ተጠቃሚዎች መካከል የሚነሱ ግጭቶች የሚፈቱበትና ግዴታዎች የሚተገበሩበት መሆኑንም አስታውቀዋል። በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ መረጃ በመሰብሰብ የሚተነተንበትና ለተጠቃሚዎች የሚሰራጭበት ሂደትን በአግባቡ በሕግና በሥርዓት መምራትን እንደሚያካትትም ተናግረዋል።

እነዚህን ተግባራት በአግባቡ ለማከናወን፣ ከመሬት አስተዳደር ጋር የተያያዙ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ወይም ለመቀነስ፤ ሀገር ከመሬት ማግኘት ያለባትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ሁለንተናዊ ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ መሬትን በተቀናጀና በተናበበ መንገድ ማስተዳደርና መምራት ለነገ የማይባል ወሳኝ ሥራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በሀገሪቱ የገጠርንም ሆነ የከተማ የመሬት አስተዳደር ሥርዓትን ለመገንባትና ዘርፉንም በተሻለ ሁኔታ ለመምራት እንዲቻል የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸው ይታወቃል። ነገር ግን በዘርፉ በመደረግ ላይ ያሉ ጥረቶች የሚፈለገውን ያህል ርቀት ያልተጓዙና በተበታተነ የተቋም ቅርጽና አደረጃጀት ላይ የተመሰረቱ በመሆኑ ዘርፉንም ሆነ ውጤቱን በዘላቂ መንገድ ላይ እንዲገኝ አላስቻሉትም።

በተለይም በመሬት ዙሪያ ያለው የአደረጃጀት ችግር ለዘመናት ሳይፈታ በመቆየቱ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበና ስር እየሰደደ መጥቷል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ይህ ተቋማዊ ሁኔታ የዘርፉን ባለሙያዎች፣ ተግባሩን የመምራት ፖለቲካዊ ኃላፊነት ያለባቸውን ወገኖች እንዲሁም የዘርፉን መዘመን የሚሹና ለመልካም አስተዳደር መስረጽና ለኢኮኖሚ ዕድገት ያለውን ሚና የሚረዱ ወገኖችን ሁሉ በከፍተኛ ደረጃ እያሳሰበ እንደሚገኝም አመላክተዋል።

በሌላ በኩል እስካሁን የተገኙ ውጤቶችን ለመጠበቅና ስር እንዲሰዱ ለማድረግ የሚቻለው፣ የመሬት አስተዳደር ሥርዓት ግንባታውም በዘላቂ መሠረት ላይ ሊቆም የሚችለው፣ እስካሁን እንደመጣንበት መንገድ በዘመቻ ወይም በአንድ ወቅት በሚገኝ የውጭ የድጋፍ አጋጣሚ ሳይሆን ወጥ የሆነ፣ ሩቅ የሚያይና ዘርፉን በሚገባ የተረዳ፣ የሚናበብ ተቋማዊ አደረጃጀት ሲኖር መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው አስገንዝበዋል።

በዚህ እሳቤና በመሬት ዘርፉ ዙሪያ የሚታየውን ችግር በመረዳት፣ በተለያየ ጊዜና አጋጣሚ በዘርፉ የሥራ ተሞክሮ ያላቸው ባለሙያዎች ተቋማዊ አደረጃጀቱን ለማሻሻልና ወጥ በማድረግ ሃሳቡን ባልተደራጀና በተበታተነ ሁኔታ ሲያቀርቡት መቆየታቸውንም አስታውሰዋል። በተለያዩ ባለሙያዎች የተደረጉ ጥረቶች መልካም ቢሆኑም፣ ሃሳቦቹ በተለይም ለውሳኔ ሰጭ አካላት ግልጽ በሆነና የችግሩን ጥልቀት ማመልከት በቻለ ሁኔታ የቀረቡ አልነበሩም ብለዋል።

ይህንን ሁኔታ በመረዳትና ዘርፉም ያለበትን የተቋምና አደረጃጀት ተግዳሮት በዘላቂነት ለመቅረፍ እንዲያግዝ ጉዳዩ ያስጨነቀው የኢትዮጵያ የመሬት አስተዳደር ባለሙያዎች ማህበር የተለያዩ ጠቃሚ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱንም ጠቅሰዋል። ከበርካታ ጥረቶቹ መካከል አንዱና ዋናው የመሬት አስተዳደር ዘርፉ ተቋማዊ አደረጃጀት ያለበትን ሁኔታ መረዳት፣ የሚታይበትን ተግዳሮት መለየትና ሀገራዊ ሁኔታውን ከዓለም አቀፍ ልምዶችና ለተግባሩ ምቹ ከሆኑ መርሆዎች ጋር በማዛመድ ሀገራዊ የምክረ ሃሳብ ሰነድ ማዘጋጀት መሆኑንም አስታውቀዋል።

በዚህም መሠረት የመጀመሪያ የምክረ ሃሳብ ረቂቁን በማዘጋጀትና በዘርፉ ከሚገኙ የተለያዩ ባለሙያዎች ጠቃሚ ግብዓት ሲያሰባስብ ቆይቷል ይላሉ። በዋናነትም የመጀመሪያው ሰነድ ከተዘጋጀ በኋላ ሶስት መድረኮች ላይ በማቅረብ ግብዓቶችን በማሰባሰብና በማካተት የማዳበር ሥራ መሠራቱን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ የመሬት አስተዳደር ባለሙያዎች ማህበር አባል እና የጥናት ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ዘርፉ ኃይሉ በበኩላቸው ሙያዊ ግብዓት የታከለበት አንድ ወጥ የመሬት አስተዳደር አደረጃጀት መፈጠር አለበት ይላሉ።

በመሬት አጠቃቀም ላይ ቀደም ብሎ የታቀደ ወጥ አሠራር ከሌላ ተገቢውን የመሠረተ ልማት ግንባታ ለማከናወን ተግዳሮት እንደሚሆን ዶክተር ዘርፉ ጠቅሰው፣ ይሄ ቦታ ለመንገድ፣ ይህ አካባቢ ለመኖሪያ፣ ይህ ደግሞ ለፓርክ ይሁን፣ ወዘተ. የሚል የመሬት አጠቃቀም እንዲኖር አንድ ወጥ እና ተመሣሣይ የማኔጅመንት አሠራር ሊኖር እንደሚገባም አስታውቀዋል።

እሳቸውም በዓለም መሬት ትልቅ ሀብት እንደሚመነጭበት ተናግረዋል። ለኢንዱስትሪ እና ለከተማ ማስፋፊያ መሬት በሚወሰድበት ወቅት ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግን ይጠይቃል ሲሉም ጠቅሰው፣ አሁን ባለው ሁኔታ ለሰብል ምርታማነት በጣም ተመራጭ የሆነው መሬት የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ አኳያ ያለው ጠቀሜታ ሳይታይ ኢንዱስትሪ ሲገነባበት ይታያል ብለዋል። በዚህ ሚዛን ሳይታይ በዘፈቀደ የሚሰሩ የመሬት አስተዳደር ክፍተቶች መኖራቸውም ጠቁመዋል።

ጥቅሞቻችን እና ፍላጎታችን ሰፊ ናቸው ያሉት ዶክተር ዘርፉ፤ ከተማ ለማስፋፋት ሲፈለግ ወደ ከተማ የሚገባው መሬት የምግብ ሰብል ሊመረትበት የሚችለውን መሬት እያሳጣና እየቀነሰ ይገኛል ብለዋል። በየዓመቱ ምን ያህል ሄክታር መሬት ወደ ከተማ እንደሚገባ በጀት መያዝ እንደሚገባም አስታውቀው፣ ከምርት ውጭ የሆነው መሬት በምግብ አቅርቦት ላይ ያለው ተፅእኖ መታየትና መጠናት እንዳለበትም አስታውቀዋል።

በተመሣሣይ የዱር እንስሳት ባሉባቸው ፓርኮች አካባቢ ከተሞችን መመሥረት ወይም እርሻ ማስፋፋት እንደማይቻልም ጠቅሰው፣ ከተማውንም እርሻውንም የዱር ብዝሀ ሕይወት እንስሳቱን እንፈልጋቸዋለን ብለዋል። ለእነዚህ ሁሉ በእውቀት ላይ የተመሠረተ የመሬት አጠቃቀም አሠራር መኖር እንዳለበት ጠቁመዋል።

ለምሳሌ የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ላይ የአፋር እና የከረዩ አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ በኩል የሚታየው ወደ ፓርኩ የመግፋት ሁኔታ፣ ለስኳር ፋብሪካ ሸንኮራ አገዳ ለመትከል የሚደረገው መሬት መግፋት በፓርኩ ህልውና ላይ ፈተና መደቀኑን ጠቁመዋል። ይህም ለከብቶች ግጦሽ፣ ለዱር እንስሳት፣ ለኢንዱስትሪ መስፋፋትና ለመሳሰሉት በጥናት ላይ የተመሠረተ የመሬት አጠቃቀም ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የበለጸጉት ሀገራት መሬታቸውን ቆጥረው በአግባቡ በመጠቀማቸው ነው እድገት ያሳዩት ያሉት ዶክተር ዘርፉ፣ የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት በከተማና ገጠር መሬት አደረጃጀት አዋጆች ላይ የሕግ ማሻሻያዎችን እስከ ማድረግ የሚደረስ ሥራ መሥራትን ይጠይቃል ሲሉም ገልጸዋል። አዋጆችን ወደ አንድ የማምጣት አስፈላጊነትንም ጭምር ጠቁመዋል።

ከፖሊሲ ጋር የተያዙትን በክልሎች የሚታዩ የተዘበራረቁ አሠራሮችንም ወደ አንድ ዘመናዊ አሠራር መቀየር እንደሚገባ አመልክተዋል። ለማሻሻያውም የመጨረሻ ግብዓት መሰባሰቡን የተናገሩት ባለሙያው፣ ከተማ ልማትም ለጉዳዩ ወቅታዊና ተቋማዊ ምላሽ ለመስጠት በ10 ዓመት እቅዱ ላይ ማስቀመጡን አስታውቀዋል።

 በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You