ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ!

 በዛሬው እለት በመላ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የጥምቀት በዓል በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሥነሥርዓት ይከበራል። በዋዜማውም የጥምቀት ከተራ በዓል የየአድባራቱ ታቦታት አዳራቸውን ባደረጉባቸው ጥምቀተ ባህሮች በታላቅ መንፈሳዊ ሥነሥርዓት ተከብሯል።

መላ የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ! የጥምቀት በዓል በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች በልዩ ልዩ ሥነሥርዓቶች ይከበራል።

እየሱስ ክርስቶስ በልደቱ በትህትና በከብቶች በረት እንደ ተወለደ ሁሉ በጥምቀቱም በዮርዳኖስ ወንዝ ተገኝቶ በሰው እጅ የተጠመቀበትና ለሰው ልጆች ሁሉ በድጋሚ ትህትናና ፍቅርን ያስተማረበት እንደመሆኑ፣ የእምነቱ ተከታዮችም ይህን ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ትውፊት በመከተል በትህትና፣ በመልካም ሰብእናና በፍቅር ፈጣሪን በማመስገን በደማቅ ሥነሥርዓት ያከብሩታል።

የጥምቀት በዓል አካል የሆነው ከተራ በመላ ሀገሪቱ በደማቅ ሥነሥርዓት እየተከበረ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማም በጃንሜዳ እና በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ በርካታ ጥምቀተ ባህሮች እየተከበረ ይገኛል። ልብሰ ተክህኖ የለበሱ የቤተክርስትያኗ አባቶች፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ዜማዎችን በማሰማት በወረብና በሽብሸባ ለፈጣሪ ምስጋና በማቅረብ የሚያከብሩት ሲሆን፤ የእምነቱ ተከታዮችም በልዩ ልዩ አልባሳት አምረውና ተውበው በየጥምቀተ ባህሩ በመገኘት ይህን ሃይማኖታዊ ሥርዓት በጽሞና በመከታተል፣ አብረውም በማዜም ለፈጠሪ ምስጋና በማቅረብ ያከብሩታል።

የጥምቀት በዓል ከመንፈሳዊ በዓልነቱ ባሻገርም ባህላዊና ማኅበራዊ እንዲሁም ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው። የእምነቱ ተከታዮች መንፈሳዊ ዜማዎችን ብቻ ሳይሆን ልዩ ልዩ ባህላዊ ዜማዎችን በማዜምና በመወዛወዝም ጭምር በዓሉን ይበልጥ አድምቀውት ይውላሉ። ለእዚህም ልዩ ዝግጅት አድርገው ነው የበዓሉን መድረስ ሲጠባበቁ የሚቆዩት። ለእዚህ ታላቅ ቀን የማያውሉት የክት ልብስ፣ የማያወጡት ገንዘብ የላቸውም። ‹‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ›› የሚባለውም ከዚህ በመነጨ ነው።

ባህላዊና ማኅበራዊ ትውፊቶቹ ለሰዎች የእርስ በርስ ትስስር መጠናከር ሚናቸው ከፍተኛ ነው። ባህላዊ ዜማዎች ብቻ ሳይሆኑ ባህላዊ አልባሳትም የበዓሉ ታዳሚዎች መድመቂያ ናቸው። የባህላዊ አልባሳትና ባህላዊ ጨዋታዎች አይነት በስፋት የሚታይበት፣ በዓል እንደመሆኑም ለባህላዊ ትውፊት መጠበቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል።

በበዓሉ የሚታደመው የኅብረተሰብ ክፍል በርካታ እንደመሆኑም፣ በዓሉ የእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያውያን በዓልም ነው ያሰኛል። በዓሉ በድምቀትና በሰላም እንዲከበር በማድረግ በኩል ከእምነቱ ተከታዮች በተጨማሪ የተለያዩ እምነቶች ተከታዮች ታቦታት የሚጓዙባቸውን ጎዳናዎችና የሚያድሩባቸውን ስፍራዎች በአጠቃላይ በዓሉ የሚከበርባቸውን አካባቢዎች በማጽዳት የሚያደርጉት ርብርብ ይህንኑ ያመለክታል።

የጥምቀት በዓል በዓለም አቀፍ ደረጃም በዩኔስኮ ትልቅ ስፍራ የተሰጠው ነው። በድርጅቱ በዓለም የማይደሰስ ቅርስነት የተመዘገበ እንደመሆኑም የዓለም ሕዝብ በዓልም ጭምር ነው።

የጥምቀት በዓል ለምጣኔ ሀብት ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ አንጻር ሲታይም ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል። ይህን በዓል ብለው በርካታ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች እና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዚህ ወቅት ወደ ሀገሪቱ ይተማሉ። የሀገር ውስጥ ቱሪዝም በከፍተኛ ደረጃ ከሚንቀሳቀስባቸው በዓላትና ወቅቶች መካከልም የጥምቀት በዓል ይጠቀሳል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ትህትናና ፍቅር የተገለጸበትና የትህትናና ፍቅር ፋይዳ በሰፊው የሚሰበክበት እንደሁም በርካታ ፋይዳዎች ያሉት ይህ ታላቅ በዓል በድምቀትና በሰላም እንዲከበር ማድረግ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው። በዓሉ በድምቀትና በሰላም እንዲከበር ቤተክርስቲያኗና የእምነቱ ተከታዮች እንዲሁም መንግሥት አስቀድመው ልዩ ዝግጅት አድርገውበታል።

ይህ የእምነቱ ታላቅ ሥነሥርዓት የሚካሄድበት፣ ከሕፃን እስከ አዋቂ መላ ቤተሰብ፣ የውጭ ሀገር ቱሪስቶችና በውጭ ሀገሮች የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን፣ መላ ዓለም በአንክሮ የሚከታተለው በዓል በድምቀትና በሰላም እንዲከበር ለማድረግ የእምነቱ ተከታዮች የቤተክርስቲያኗ እና የጸጥታ አካላት ጥረት ብቻውን አይበቃም። እንደተለመደው መላ ኢትዮጵያውያንም ለበዓሉ በሰላምና በድምቀት መከበር የበኩላቸውን ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል።

ከዚህ በዓል በሰላምና በድምቀት መከበር የሚያተርፉት የእምነቱ ተከታዮች ብቻ አይደሉም፤ መላ ኢትዮጵያውያንና. መንግሥትም ሀገርም ዓለምም ናቸው። ፍቅርና ትህትና በእጅጉ የሚሰበክበት፣ የኢትዮጵያውያን ወንድማማችነትና እህትማማችነት የተጠናከረ መሆኑ የሚመሰከርበት፣ የመንግሥትና ሕዝብ አንድነትና ጥንካሬም የሚታይበት ነው።

ስለሆነም መላ ኢትዮጵያውያን የከተራ በዓል በድምቀት እንዲከበር የበኩላችሁን ሚና እንደተጫወታችሁ ሁሉ የጥምቀት በዓል ተከብሮ እስከሚጠናቀቅ የሚጠበቅባችሁን መወጣታችሁን አጠናክራችሁ ቀጥሉ። በድጋሚ ለመላ የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ!

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You