አንድ በእድሜያቸው ጠና ያሉ አባት ታክሲ ለመያዝ ቢሯሯጡም ሊሳካላቸው አልቻለም። ወጣቱ እና ጉልበት አለኝ የሚለው ሁሉ እኚህን አባት ገፍትሮም ይሁን ያደገረውን አድርጎ ወደ ታክሲው ውስጥ ለመግባት ትንቅንቅ ላይ ነው። ጉልበተኞቹ ሁሉ ጥሏቸው ይሄዳሉ።ይህንን ሲያደርጉ ያለ አንዳች መሸማቀቅ እና ሀፍረት ነው። እኔም ላለመጋፋት ፈርቼ ከዳር ቆሜ መገሩን በመጎባ እየተመለከትኩ ነበር ያሉት ሲሄዱ ይቀላል ብዬ ተስፋ ባደርግም ቅዳሜ ስለነበር ይሁን በሌላ ምክንያት የሰው ብዛት እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልሄደም። በዚሁ ሁኔታ ውስጥ ሆኜ እኚህ አባት ድንገት መሬት ላይ ወድቀው ተዘረሩ። ግማሹ ውሃ ለማምጣት፤ከወደቁበት አስፋልት ዳር ወደ አንድ ጥግ ለመውሰድ እና ሌሎችን ርዳታዎች ለማድረግ ይጣጣራል።
ምናልባት እኮ ቀድመው ተሳፍረው ቢሆን ላይወድቁ ይችሉ ነበር? አላውቅም! ግን ቀድሞ መረዳት ይቀል ነበር። ፀሀይ በጣም መቷቸው ይሆን የወደቁት? የስኳር በሽታ ነው ወይስ ግፊት?ብቻ ከትንሽ ደቂቃዎች በኋላ እኚህ አባት ነቁ። መልከመልካሙ አባት ልብሳቸው እንዳልነበር ሆኖ ቆሽሿል። የወደቁበት አቧራ ለፊታቸውም ደርሷል። ከንፈራቸው ትንሽ ደም ይታይበት ነበር። በኋላም አንድ ወጣት ልጅ ወዴት እንደሚሄዱ ጠይቆቋቸው ተጋፍቶ እና የታክሲ ከፍሎላቸው ከዳግም እንግልት ገላገላቸው።
አስከፊ የሚባሉ ነገሮች ሁሌም ከመሆናቸው በፊት መደረግ ያለበት ቢደረግ ችግሮችን መቀነስ የሚቻል ይመስለኛል።ብዙ ጊዜ ግን ከሆነ በኋላ ነው ትብብሩም፣ እርዳታውም እና ከንፈር መምጠጡ የሚስተዋለው። በየቦታው እኚህን መሰል በእድሜ የገፉ አረጋውያን ተመሳሳይ ችግር ያጋጥማቸዋል። በበዓላት ወቅት እና የትራንስፖርት እጥረት በሚስተዋልበት ጊዜ ምነው ከቤታቸው ባልወጡም ያስብላል።
በየቦታው ለታክሲ ተብለው የተዘጋጁ ሰልፎች ምንም እንኳን አሰልቺ ቢሆኑም አቅማቸው ደካማ ለሆኑ ሰዎች፣ለአካል ጉዳተኞች ፣በጀርባቸው ልጅ ለታቀፉ እናቶች እና ለነብሰ ጡር ሴቶች በሚገባ እፎይታን የሚሰጥ ነው። የሚገርመው ግን እኚህን ሰዎች ቀድሞ ለመግባት ሰልፍ የሚጥስ ግዴለሹ ሰው ቁጥሩ ቀላል እንዳልሆነ ያለ አንዳች ጥርጣሬ መግለጽ ይቻላል።
ከዚሁ ሀሳብ ጋር በተያያዘ ጣልቃ መግባትም ሆነ እኔን ብቻ አስቀድሙኝ የሚሉት ሰዎች ነገር ሁሌም እንዳስገረመኝ ነው። ድንገት ከኋላ መጥተው እነርሱ ብቻ እንዲገለገሉ የሚያጣድፉ ሰዎች ካለመሰልጠን እና ካለማስተዋል የመነጨ ችግር ካልሆነ ምን ሊባል ይችላል? ደግሞ ይቅርታ እንኳን አይጠይቁም።
አሁን አሁን ሁላችንም የባለ ብዙ ጉዳዮች ባለቤት ሆነናል።ስለራሳችን እንጂ ስለሌሎች እየገደደን አይመስልም። ምንም እንኳን አስቸኳይ ጉዳይ ያለው ሰው ላይ ፍርድ ለመስጠት ቢያስችግርም ካፌ እና መሰል ቦታዎች ላይ ቁጭ ብሎ ጊዜውን ለማሳለፍ ከአቅመ ደካሞች ጋር የሚጋፋውን ስንመለከት ‹‹ትዝብት ነው ትርፉ›› ብሎ ከማለፍ ውጪ ምን ማለት ይቻለናል?
ዛሬ ላይ ብዙዎቻችን ልባችን ደንድኗል መሰለኝ። ሰው ሲደባደብ ጉዳት እንዳይደርስ ከመገላገል ይልቅ ገላጋይ ላይ ምን ሊመጣ እንደሚችል ቀድሞ በመረዳት ጎመን በጤና ብለን ምርጫችን ሽሽት ሲሆን ይታያል። መንገድ ላይ ወድቆ የተለመከትነው ሰው ቀርቦ ከመርዳት ይልቅ ፍርሃታችን ከሰብአዊነታችን ልቆ ዝምታን አስመርጦናል።አንድ ሰው እርዳታችንን ፈልጎ ሲጠይቅ ‹‹ከነገሩ ጾም እንደሩ።››ብለን ያለንን ከማዋጣት እንሸሻለን።ለመርዳትም ቅድመ ሁኔታዎችን እናስቀምጣለን።
በየቦታው የሚሠሩ እና የሚቆፋፈሩት መንገዶች አይደለም ለአካል ጉዳተኛው ለጉዳት አልባው ፈታኝ ናቸው። ልብ ብለን ካየን እንዲህ አይነቱን ችግር ዓይነ ስውራን እና ሌሎችንም በየዕለቱ ሲፈትናቸው እንመለከታለን። እነርሱ አስፋልት ለመሻገር ይሁን በሌላ ነገር ሲቸገሩ እያየን ዝምታን እንመርጣለን።
አንዳንድ ልምምዶች መጥፎ ናቸው። ሲባል ከሰማነው እና ሲሆን ከተመለከትነው ነገር በመነሳት መርዳት ያለብንን ሰዎች ሳንረዳ እንቀራለን። ከመርዳት ይልቅ ቢያጭበረብሩንስ ብለን እንድናስብ ብዙ ድርጊቶች ተፈጥረው ይሆናል። እንደ አሁኑ የራይድ ትራንስፖርት አገልግሎት ሳይስፋፋ በፊት የቤት መኪናም ይሁን ኮድ ሦስት ተሽከርካሪዎች ሰዎችን በተለይም አቅማቸው ደካማ የሆኑትን ይሸኙ ነበር። ዛሬ ግን የሥራ መኪና ሆነው ብር የሚያገኙበት ሥርዓት ተዘጋጅቶላቸው እንዲህ ዓይነቱን በጎ ሥራ ወደ ጎን አድርጎታል ማለት ይቻላል። ደግሞም አይፈረድባቸውም።አንዳንድ ከሠማው እና ከደረሰበት ተነስቶ በእድሜ የገፉትንም ይሁን ሌሎች ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ሰው ጭኜ ሌላ ችግር ቢደርስብኝስ ብሎ በመፍራት ራሱን ከበጎ ሥራ እንዲርቅ አድርጎታል።
ዛሬ ላይ ከሰብአዊነት የፍርሃት፣ የግዴለሽነት፣ የራስ ወዳድነት ሚዛን ከፍ ብሎ ይታያል።ከዚህ በፊት በከተማም ይሁን በገጠር የመሸበት ‹‹የእግዜር እንግዳ›› ውጭ አድሮ ክፉ እንዳይገጥመው ብሎ በማሰብ የማያውቀው ሰው ያለውን አብልቶ አጠጥቶ እና ተንከባክቦ ይሸኛል።በከተማ ላይ እንዲህ አይነቱ ነገር በስፋት አይታይም። ምክንያቱ ብዙ ሊሆን ይችላል። ባስጠጋው አንዳች ጉዳት ሊደርስብኝ ይችላል ብሎ በማሰብ እንዲህ አይነቱ ነገር አይደለም ማድረግ፤ ማሰብ እንኳን አይፈልግም።አንዳንዱ ደግሞ እንኳን ለሌላው ሊተርፍ ለራሱም መሆን አይቻለውም።ብቻ በእነዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች ይመስለኛል አንዳንድ ሰዎች የከተሜ ሰው በሩን ዘግቶ ነው የሚበላ ብለው የሚያሙት።
የስነ ልቦና ባለሙያዎች ደጋግመው እንደሚሉት አንድ ሰው ራሱን መውደድ እንዳለበት ሲናገሩ ይደመጣል።ለምን ከተባለም? እርሱ ሌላውን ሊወድ የሚችለው ራሱን ሲወድ እንደሆነ ያስረዳሉ። ከሃሳቡ ጋር ተቃርኖ የለኝም። ግን ከመጠን በላይ የበዛ ራስን ወዳድነት፣ግዴለሽነት እና ለራስ የሚሰጥ የተጋነነ ግምት ሌላውን በመጉዳት እና በማኮሰስ ከሆነ ፍጹም ስህተት ነው።
ሰብአዊነት መርጦ መርዳት አይደለም። ማንም ከማን ሳይወግኑ መርዳት ማገዝ እና ማከፈልን ይጠይቃል። ያለምንም ክፍያ ሰውን የሚረዱ አቅመ ደካሞችን የሚደግፉትን ሰዎች በመመልከት ቢያንስ እንኳን የነሱን ያህል ማድረግ ባንችል እንኳን በጥቂቱ ተባባሪ እንሁን።
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 11 ቀን 2016 ዓ.ም