በርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች በሚካሄድበት የውድድር ዓመት ውጤታማነትን ለማስጠበቅ

ያለፈው የውድድር ዓመት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ መልካም ውጤት የተመዘገበበት ሆኖ ነበር ያለፈው። በዚህ ዓመት ደግሞ ኦሊምፒክን ጨምሮ በርካታ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚከናወኑበት ነው። በመሆኑም ለዓለም አቀፎቹ ውድድሮች እንደ ማጣሪያ የሚሆኑ የሃገር ውስጥ ቻምፒዮናዎች በጊዜ መርሃ ግብሩ መሰረት በመካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ካለፈው ዓመት በርካታ ተሞክሮዎችን የቀሰመው ፌዴሬሽኑ በዓመቱ ስፖርቱን በምን መልክ እንደሚመራ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ከነበረው ውጤት የተሻለ ለማስመዝገብ የያዘው እቅድ ይህን ይመስላል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሃንስ እንግዳ፤ የተያዘው የውድድር ዓመት በአትሌቲክስ ስፖርት በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች “የተጨናነቀ ሊባል የሚችል መሆኑን ይጠቁማሉ። በአህጉር አቀፍ ደረጃ በቅርቡ የሚከናወነውን ሃገር አቋራጭ ውድድር ጨምሮ የአፍሪካ ቻምፒዮና እንዲሁም የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ይከናወናሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና፣ የሃገር አቋራጭ፣ የዓለም ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮና፤ እንዲሁም የፓሪሱ ኦሊምፒክ ይካሄዳል። በመሆኑም ኢትዮጵያ ለምትወከልባቸው እነዚህ ውድድሮች ከ10 ያላነሱ የሃገር ውስጥ ቻምፒዮናዎች ይከናወናሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ የነበራትን ውጤት አስጠብቃ እንድትቀጥልም ጥረት ይደረጋል፡፡

አጠቃላይ ለእነዚህ ውድድሮች የሚሆነውን ዝግጅት አስመልክቶም ፌዴሬሽኑ ከወዲሁ ስራዎችን የጀመረ ሲሆን፤ ለአብነት ያህል ለዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና የመጀመሪያ ዙር አትሌቶች ምርጫ ተደርጓል፡፡ በቀጣይ ጊዜያትም በቤት ውስጥ የቱር ውድድሮች በሚመዘገበው ውጤት መሰረት የመጨረሻው የአትሌቶች ምርጫ በማድረግ ከ800 እስከ 3ሺህ ሜትር መሰናክል ባሉት ርቀቶች ዝግጅት የሚደረግ ይሆናል፡፡ የመጨረሻው ምርጫ እስኪታወቅም አትሌቶች ለሚያደርጉት የግል ውድድር ፌዴሬሽኑ ለልምምድ የሚረዳቸውን የማዘውተሪያ ስፍራ በማመቻቸት እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮች ላይ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። ይህ ሁኔታ በሌሎች ውድድሮች ላይም በተመሳሳይ ይቀጥላል፡፡

የዓመቱ ትልቁ ውድድር የፓሪሱ ኦሊምፒክ እንደመሆኑ ኢትዮጵያ በምትካፈልባቸው የአትሌቲክስ ርቀቶች አትሌቶችን አስቀድሞ መለየት ተችሏል፡፡ እስከ መጪው ነሐሴ ወር 2016 ዓ∙ም በሚኖረው ሰፊ ጊዜም ይኸው እየተጣራ የሚቀጥል ሲሆን፤ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችም በመከናወን ላይ ናቸው፡፡ ይህ ውድድር የሚመራው በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እንደመሆኑ ከሁለቱ ተቋማት የተወጣጡ ባለሙያዎችን ያቀፈ የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ ካለፉት ኦሊምፒኮች የተሻለ ውጤት እንዲገኝ ከወዲሁ እየተሰራ ነው፡፡ ሁለቱ አካላት በመግባባትና መናበብም ለጥሩ ተሳትፎና ዝግጅት እየተጉ እንደሚገኙም ነው ኃላፊው ያብራሩት፡፡

ኢትዮጵያ በመላው ዓለም ስሟ በመልካም እንዲነሳ ካደረጉ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው አትሌቲክስ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ይሁንና በብርቱ አትሌቶቿ የተገነባው ይህ በጎ ገጽታ እንዲወይብ የሚያደርጉ ክስተቶች በዚሁ ስፖርት መስተዋሉ አልቀረም፡፡ የስፖርቱን ዓለም እያመሰ የሚገኘውና እንደ ሩሲያ ያሉ ሃገራትን ከየትኛውም ውድድር ያሳገደ እነ ኬንያን ደግሞ በዓይነ ቁራኛ እንዲታዩ ያደረጋቸው የስፖርት አበረታች ቅመሞች ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ታዲያ ይኸው የስፖርቱ ጥቁር ገጽ በኢትዮጵያም መታየት ከጀመረ ዋል አደር ያለ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ኢትዮጵያን እስከመወከል በደረሱ ትልልቅ አትሌቶች ጭምር ተጠቃሚነቱ እየሰፋ መጥቷል። ፌዴሬሽኑም ባለፈውና በተያዘው የውድድር ዓመት አስከፊ ወደሆነ ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን ተገንዝቧል፡፡ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የአበረታች ቅመም ተጠቃሚነት አሳሳቢ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው፤ ፌዴሬሽኑ በጉዳዩ ላይ የማያወላዳ አቋም እንዳለውና የትኛውም አትሌት በዚህ ድርጊት መሳተፉ ከተደረሰበት እርምጃ እንደሚወሰድበት ያረጋግጣሉ፡፡

ፌዴሬሽኑ አትሌቶችን የሚከታተሉ ባለሙያዎች ያሉት እንደመሆኑ ግንዛቤ በመፍጠር የድርሻውን እየተወጣ ነው፡፡ ነገር ግን የአበረታች ቅመም ተጠቃሚ የሆኑት አትሌቶች ካሉበት ደረጃ አንጻር ግንዛቤ የላቸውም ለማለት አዳጋች ነው፡፡ ለዚህም ማስረጃ የሚሆነው የቅመሞቹን ምንነት አውቆ በአንድ ውድድር ላይ ብቻ በከፍተኛ መጠን የመጠቀም ዝንባሌ መኖሩ ነው። ፌዴሬሽኑ በዚህ ላይ ጠንካራ አቋም ያለው ሲሆን፣ መሰል ተግባር ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች ላይም አስተማሪ የሆነ ቅጣት ይወስድባቸዋል፡፡ በዚህም ላይ ፌዴሬሽኑ ከሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ጠንካራ ስራ እያከናወነ እንደሆነም ነው ኃላፊው ያስገነዘቡት፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ጥር 10/2016

Recommended For You