ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ…

ዜና ሐተታ

የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን ባህላዊና ማህበራዊ መስተጋብርም ይከወንበታል። በዓሉ በርካታ ሰዎች በሀገር ባህል ልብስ ደምቀው የሚታዩበትና የዕደ-ጥበብና ኪነ-ጥበብ ውጤቶች በስፋት የሚደመጡበት ነው።

ታዲያ ወይዛዝርቱ ለጥምቀት በዓል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተውበውና ደምቀው በዓሉን ለማክበር የመጀመሪያው እቅዳቸው ልባቸው የከጀለውን የባህል ቀሚስ መርጠው መዋብና መልበስ ነው። ለዚህም ነው ‹‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ››ተብሎ የተተረተው።

ጥምቀት ከሃይማኖታዊ እሴቱ በተጨማሪ ባህልና ወግን ማሳደጊያ፣ መተጫጫ፣ የሥነ-ልቦና ማደሻ፣ በመንፈስና በአካል ጎልቶ የመታያና የማንነት መገለጫ እንዲሁም ማህበራዊ መስተጋብር ጎልቶ የሚወጣበት ባህል ነው ያሉት በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የአዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ዳይሬክተር መስፍን ፈቃዴ (ዶ/ር) ናቸው።

ጥምቀት የተነፋፈቀ ዘመድ የሚገኛኝበት፣ ወጣቶች የትዳር አጋራቸውን የሚመርጡበት በዓል ነው። በዚህም ሰዎች በበዓሉ አዲስ ለብሰው፣ አጊጠውና በባህላቸው ደምቀው ሃይማኖታዊም ባህላዊም ሥነሥርዓቶችን የሚያከብሩበት መሆኑን ያስረዳሉ።

በጥምቀት በዓል አለባበሱ እንደየአካባቢው ይለያያል። የክትና የአዘቦት የአዘቦት አለባበስ አለ። ለበዓል የክት ይለበሳል። የቀደምት ኢትዮጵያዊያን ባህላዊ አልባሳት በአብዛኛው የሚዘጋጀው ከጥጥ ነው የሚሉት ዶክተር መስፍን፤ አዘገጃጀቱ ባህልንና እምነትን መሰረት ያደረገ ነው ይላሉ።

ቀሚስ፣ ኩታ፣ መቀነት፣ ጋቢ፣ ነጠላና ሌሎችም ከጥጥ የሚዘጋጁ ባሕላዊ አልባሳት የጥምቀት ዋነኛ ማጌጫ ናቸው። በበዓሉ ደምቀው የሚታዩ ልጃገረዶችም በርካታ ናቸው። በመሆኑም ባህሉንና ወጉን ጠብቆ ማቆየትና ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ተገቢ መሆኑን የመከሩት።

በአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከፍተኛ የቅርስ ጥናት ተመራማሪ የሆኑት መምህር መክብብ ገብረማርያም ደግሞ በበኩላቸው፤ ጥምቀት ሴቶች ጸጉራቸውን ሹሩባና ሌሎች ባህላዊ ቁንዳላዎችን ተቆንድለው ፣ እጅና እግሮቻቸውን በእንሶስላ አስጊጠው፤ አምባር፣ አልቦ፣ ድሪ፣ ጉትቻና በሌሎች ጌጣጌጦችን ተውበው የሚታዩበት የአደባባይ በዓል ነው ይላሉ።

ለጥምቀት በዓል ሕፃናት፣ ወጣቶችና አረጋውያን እንደ ዕድሜ ክልላቸው “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” የሚለውን ስነቃል መሰረት በማድረግ ዘንጠው ይወጣሉ። ጥምቀት የሃይማኖት፣ የማንነት፣ የባህልና የውበት መገለጫ በመሆኑ አለባበሱም ልክ እንደዚያው እነደየአካባቢው ይለያያል ሲሉ ያስረዳሉ።

በጥምቀት በዓል የሃይማኖት አባቶች እንደቤተክርስቲያን ደንብ፣ ምዕመናኑ ደግሞ በባህላዊ አልባሳት ደምቀው መታየቱ በዓለም መድረክም ልዩ ያደርገናል የሚሉት መምህር መክብብ፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት ነገስታት በዓመቱ ውስጥ የተሰሩትንና በቀጣይ የሚሰሩትን ሁነቶች በባህላዊ አልባሳት አጊጠው ለሕዝቡ በማስተዋወቅ ለልማት ስራዎች ተባባሪ እንዲሆኑ ይጠቀሙበት እንደነበር ታሪክ ምስክር መሆኑን ይናገራሉ።

የጥምቀት በዓል የሰዎች ውበት እንደጥቅምት አበባ የሚፈካበት፤ መጤ ባህሎች ለመከላከል፣ ባህላዊ ምግቦችን ለማዘጋጀት፣ ቀደምት የኪነጥበብ ውጤቶች ለማንጸባረቅ እና በኢትዮጵያ የሚሰሩ ባህላዊ አልባሳትን፣ ጌጣጌጦችንና ገበያ ለማሳደግ ምቹ አጋጣሚ መሆኑን ነው ያብራሩት።

በጥምቀት ወቅት በተለይ ከሚደምቁ ገበያዎች አንዱ የሽሮ ሜዳ የባህል አልባሳት ገበያ ነው። በገበያ ማዕከሉ ወይዛዝርትና ወጣት ሴቶች መተላለፊያ እስኪጠብ ድረስ ሞልተው ይገበያያሉ።

ለጥምቀት የተሰሩት አልባሳት አብዛኞቹ ቱባ ባህልን የጠበቁ የሀገር ቤት የጥበብ ስራዎች ናቸው። የራያ ቀሚስ ከመቀነት ጋር (ቦፌ)፣የጎንደር ጥበብ፣ የትግራይ ጥበብ (ጥልፍ)፣ የወሎ፣ የሸዋ፣የጉራጌና የበርካታ አካባቢዎችን ቱባ ባህል የያዙ አልባሳት ለገበያ ቀርበዋል። ከስምንት ሺ ብር እስከ ሁለት ሺህ ብር የሚጠራባቸው የሴቶች የባህል አልባሳት አሉ።

በገበያ ማዕከሉ ካገኘናቸው ሶስት ወጣቶች መካከል አንዷ ለመግዛት ያሰበችው አንድ የባህል ቀሚስ ነው። ቢሆንም ሁለቱንም ለመውሰድ ብታስብም ዋጋው እንደገመተችው አልሆነላትም፤ ብር አነሳት፤ ጓደኞቿ ‹‹ሁሉ አማረሽን ገበያ አታውጧት›› በማለት ከተሳሳቁ በኋላ ያላቸውን ብር አዋጥተው ያማራትን ቀሚስ ደስ ብሏት እንድትገዛ አድርገዋል።

በገበያ ማዕከሉ ውስጥ የባህል ልብስ ነጋዴ የሆኑት ወይዘሮ ሰናይት ፀጋዬ፤ ብዛት ያላቸው የባህል አልባሳት የሚሸጠው ለጥምቀት በዓል ነው ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

ደንበኞች ለጥምቀት በዓል የሚመርጡት አብዛኛው ጊዜ ቱባ ባህሉን የጠበቀ የጥበብ ሥራ እንደሆነም ያስረዳሉ፤ በብዛት ግን መራጮቹ ሴቶች ናቸው።

በዓላቶቻችን ለኢኮኖሚው የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ቀላል እንዳልሆነ መገንዘብ ይቻላል የሚሉት ነጋዴዋ፤ ድንቅ ባህሎቻችንን በተለይ የበዓል ወቅት አለባበሶች ባህላዊና ትውፊታዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ የሚቆዩበትን መንገድ እያጠናከሩ መሄድ ይገባል ሲሉ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።

ሄለን ወንድምነው እና ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You