ያልተጠበቁ ውጤቶችን እያስመለከተ የሚገኘው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች የሚደረጉ ሲሆን፤ ለዋንጫ ተጠባቂ የሆኑ ቡድኖች የሚገናኙባቸው የዛሬዎቹ ጨዋታዎች እጅግ ተጠባቂዎቹ ናቸው:: ከከባድ ሚዛን ምድብ ከሚካተቱት ቡድኖች መካከል፤ በተለይ መልካም አጀማመር ያልነበራቸው የግብጽና የጋና እንዲሁም የኮትዲቯርና የናይጄሪያ ግጥሚያዎች የእግር ኳስ ቤተሰቡ በጉጉት የሚመለከታቸው ናቸው::
ፈርኦኖቹ ከጥቋቁሮቹ ከዋክብት የሚያደርጉት የምድብ ሁለት፣ ሁለተኛው ዙር ብቸኛ ጨዋታ ከ11ሺህ በላይ ተመልካች በሚይዘውና አቢጃን በሚገኘው ፌሊክስ ሆፕሆት ቦግኝ ስታዲየም ይከናወናል:: በአፍሪካ ዋንጫው ምናልባትም የስፖርቱ አፍቃሪያን ሊመለከቱ ከሚናፍቋቸው ጨዋታዎች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ቡድኖቹ ለመሸናነፍ የሚያደርጉት ፍልሚያም ተጠባቂ ነው:: የአፍሪካ ዋንጫን ለሰባት ጊዜ በማንሳት የበላይነቱን የወሰደችው ግብጽ ከሞዛምቢክ ጋር በነበራት የመጀመሪያው ጨዋታ ነጥብ ተጋርታ ከሽንፈት የዳነችው በተጨማሪ ሰዓት በተገኘ ቅጣት ምት መሆኑ የሚታወስ ነው:: ለአራት ጊዜ የውድድሩ ቻምፒዮን የሆነችው ጋናም በአፍሪካ ዋንጫው ተጠባቂ ትሁን እንጂ በኬፕ ቨርዴ ሽንፈትን በመከናነብ ነው የጀመረችው::
በመሆኑም ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ ሶስት ነጥብ ለማሳካት ተጠናክረው ወደ ሜዳ መግባት ይጠበቅባቸዋል:: በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተጫዋቾቻቸው በመልካም ጤንነት ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ በጉዳት ምክንያት ባለፈው ጨዋታ ያልተካተተው የዌስትሃም እና የጋና ቁልፍ ተጫዋች መሃመድ ኩዱስ በዛሬው ጨዋታ እንደሚሰለፍ ይጠበቃል:: በዚህ ውድድር ላይ ይደምቃሉ ተብለው ከተለዩ ተጫዋቾች መካከል ግብጻዊው የሊቨርፑል የፊት መስመር ተጫዋች መሀመድ ሳላህም ሀገሩ እንድታሸንፍ የሞት ሽረት ትግል ያደርጋል:: ለረጅም ጊዜ ሀገሩን በአፍሪካ ዋንጫ የወከለው ተጫዋቹ የዘንድሮው የመጨረሻው ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል::
በኳታሩ ዓለም ዋንጫ ላይ ሀገሩን በአሳዛኝ ሁኔታ ማሳለፍ ካለመቻሉ ባለፈ ከሁለት ዓመት በፊት በካሜሩን በተካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ፍጻሜ ጨዋታ ዋንጫውን ማሳካት አለመቻሉ ይታወሳል:: በመሆኑም በዚህ ውድድር ፈርኦኖቹ እንዲሁም የ31 ዓመቱ ሳላህ ለዋንጫና ኮኮብ ግብ አግቢነት ይጠበቃሉ:: በሌላ በኩል እአአ ከ2017 ወዲህ በተካሄዱት ሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች ባልተጠበቀ ሁኔታ በጊዜ ከውድድሩ ለመሰናበት የበቁት ጥቋቁሮቹ ከዋክብት ዋንጫውን ወደ ሀገራቸው በመውሰድ ደጋፊዎቻቸውን መካስ ይገባቸዋል:: ለዚህ ደግሞ እንግሊዛዊው የፕሪምየር ሊጉ አሰልጣኝ ክሪስ ሂውተን የቤት ሥራውን ተረክበዋል::
ሌላኛው የእለቱ ተጠባቂ ጨዋታ ደግሞ በአፍሪካ ዋንጫው አዘጋጅ ሀገር ኮትዲቯር እና ናይጄሪያ መካከል የሚደረገው ነው:: በመጀመሪያው ምድብ ከተደለደሉትና ጠንካራ የሚባሉት ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ የሚኖራቸው ጨዋታ በደረጃ ሰንጠረዡ የዝሆኖቹን የበላይነት የሚያረጋግጥ አሊያም የንስሮቹን እጣ ፋንታ አጣብቂኝ ውስጥ የሚከት ይሆናል:: ጊኒ ቢሳውን 2 ለምንም በሆነ ውጤት መርታት የቻሉት ዝሆኖቹ ዋንጫውን ሀገራቸው ላይ ለማስቀረት ፍላጎት ያላቸው እንደመሆኑ በደጋፊያቸው ፊት ቀላል ተጋጣሚ አይሆኑም::
ባለፈው ጨዋታ ከኢኳቶሪያል ጊኒ ጋር አንድ እኩል የተለያዩት ንስሮቹ የአፍሪካ ዋንጫውን ያነሳሉ በሚል ከሚጠበቁት ቡድኖች መካከል ይገኛሉ:: የአፍሪካ ዋንጫን ሶስት ጊዜ በማንሳት ከኮትዲቯር የተሻለች ትሁን እንጂ በካሜሮኑ የአፍሪካ ዋንጫ ግን ሩብ ፍጻሜውን መቀላቀል ተስኗት ነበር:: በመሆኑም የዛሬው ሶስት ነጥብ 16ቱን የመቀላቀል ተስፋቸውን የሚያለመልም ይሆናል:: በዚህ ውድድር ድንቅ ብቃታቸውን ያሳያሉ በሚል የሚጠበቀው ናይጀሪያዊው የናፖሊ አጥቂ ቪክተር ኦስሜን በዛሬው ጨዋታም ይጠበቃል:: የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋቾች ሽልማትን ያሸነፈው የ24 ዓመቱ ኦስሜን ሀገሩን ለዋንጫ ያበቃል የሚል ኃላፊነትም ተጥሎበታል::
በተያዘው መርሀ ግብር መሰረት የምድብ አንድ ሁለተኛው ጨዋታ በኢኳቶሪያል ጊኒ እና ጊኒ ቢሳው መካከል የሚደረግ ነው:: በመጀመሪያው ጨዋታ ባልተጠበቀ ሁኔታ ለናይጄሪያ ጠንካራ ተጋጣሚ በመሆን ነጥብ ተጋርታ የወጣችው ኢኳቶሪያል ጊኒ፤ በአዘጋጇ ኮትዲቯር ብልጫ የተወሰደባት ጊኒ ቢሳውን ለመርታት ወደ ሜዳ ይገባሉ:: ይሁንና ጊኒ ቢሳው ከምድቡ አልፎ 16ቱ ውስጥ ለመግባት የሚኖራትን እድል ሙሉ ለሙሉ ላለማጣት ወሳኝ በሆነው ጨዋታ ላይ ለተጋጣሚዋ ፈተና በመሆን ነጥብ ለማስመዝገብ ትጥራለች::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 9/2016