ቋንቋቸው ጉራማይሌ ነው። ባህላቸውም የትየለሌ፤ የአይን ውበት፣ የማንነት ድምቀት ናቸው። በኢትዮጵያዊነት ልክ የተሰፉ የኢትዮጵያዊነት ሸማ ናቸው። የኢትዮጵያን ቱባ የባህልና ጥበብ ውበት ፍለጋ ጓዙን ሸክፎ ለወጣ ደመ ነብሱ ወደዚያች እጹብ ምድር ይመራዋል። ወደ ማዕከላዊቷ ኢትዮጵያ፤ ወደ ዛላዎቹ ምድር ያመራ ሰው ልክ እን’ደኔ እንዲህ ማለቱ አይቀርም።
ባጥቢያ ውበት በኦጎቴ፤
አዴ ጉባ . . .
ሚሽላ ሚሽላ ቸለሎቴ፤
በሴራችሁ ይሁን ሞቴ፤
ኢዮሲማ ሀራባኒ በማለቴ።
ነቅታችኋል በነቀታ፤ በመንገሳ፤
ስነቃሉ ብዙ ቢሆን የቱን ላንሳ፤
ኢዮሲማ ሲሉ ሰማሁ ኦሮሪማ፤
ሚዮሲማ ኦሮሪማ ሀላባኒ ቃራሪማ።
ዛላ እኮ ነው በርበሬያቸው፤
ያ ለምለሙ ምድራቸው፤
ሀመልማሎው ምግባቸው፤
ጥም ቆራጭ ነው ፍቅራቸው።
ቋንቋውቸውም ጉራማይሌ፤
ጭፈራቸው ቸለሎቴ ፤
ቃላ ቢሆን ሪብሪቦቴ፤
ሀላቢዮ ሀላብ ጎቴ።
አዴ ጉባ አዴ ሲሉት፤
አዬ ወዬ ሲባዬነት፤
ጥበብ ናቸው በጥበባት፤
በሙሀባው ቅኔ ውበት።
በሀላባ ምድር፤ በሀላባውያኑ መንደር በባህልና ሥርዓት መኖር ምርጫ አይደለም። ፍቅርን ለብሶ በፍቅር ማጌጥ ባህል እንጂ ታይታ አይደለም። ከጥበብ ጋር ኖሮ ከጥበብ ጋር መሞት፤ ኪነ ጥበብን በየአይነቱ በየፈርጁ መስማትም ሆነ ማየት ከቶውን ብርቅ አይደለም። ስለ ኪነ ጥበብ ስላወቁና ስለተረዱ “ምን ልሥራ . . . እንዴት ልሥራ?” ብለው ሳይሆን የሚወዱትና የሚሳሱለት ያ ውብ ባህላቸው እራሱ ኪነ ጥበብ በመሆኑ ነው። ሀላባና ነዋሪዎቿን ብሎ የወጣ፤ እሩብ ጨረቃ መሳይ ዛላ በርበሬያቸውን ብቻም ሳይሆን ያልተሰሙና ያልታዩ የባህልና የኪነጥበብ ወንዞቻቸው በአራቱም አቅጣጫ ሲፈሱ ይመለከታል። የጥበብ ባለጸጋዎቹ ሀላባውያን የበርካታ ጥበባት ባለቤት ናቸው። እጅግ የሚያምሩ ፉከራና ሽለላዎች፣ የወንዶችና የሴቶች ሙዚቃዊ ጨዋታዎች፣ የስነ ግጥም ሀብቶቻቸው አጃኢብ የሚያስብሉ ናቸው።
ከጥንት እናትና አባቶቻቸው ቃላዊ በሆነ የቅብብሎሽ መንገድ የመጡ ስነቃላዊ የባህል ትውፊቶቻቸው ናቸው። ባህሎቻቸውን የሚገልጹት ኪናዊ ለዛን በተጎናጸፈ መልኩ በመሆኑ ባህላቸውን ከኪነጥበብ ለመለየት አይቻልም። የእምቅ ጥበባት ባለቤት ናቸው። ከእነዚህም ስነቃላዊ ግጥሞቻቸው አንደኛው ነው። አብዛኛዎቹ በሙዚቃዊ ቅላጼ የሚዜሙ ቢሆኑም አንዳንዶቹ ግን የዜማ ሥርዓትን አይከተሉም።
“ቃላ” በሀላባ ሴቶች ዘንድ ብቻ የሚዜም ባህላዊ የሴቶች ዘፈን ነው። አዘውትሮ ከመጫወት ይልቅ ቃላ የራሱ የሆነ ጊዜና ቦታ እንዲሁም ሥርዓት አለው። ጀግናን ይበልጥ ያጀግኑበታል። ስመጥሮቹን በስም እየጠሩ ያሞግሱበታል። በዋናነትም አንድ ነገር አለ፤ በማህበረሰቡ የሴራ ሥርዓት መሠረት በአዋቂነቱና በዳኝነት የአስተዳደር ችሎታው ተመርጦ የመጨረሻውን የስልጣን ደረጃ ለሚሰጠው የማህበረሰቡ አውራ ለሆነው “ኢማም” እንዲሁም የኢማሙን ዘርና ጎሳ ለማወደስ ይጠቀሙበታል።
ኮራኮሮሔ ኖጋይ
ሀላቢ ኦ . . . ሶጋሔ
….
እያለች የዜማው መሪ የሆነችው ሴት ባማረ ቅላጼ ስታዜም፤ የቡድኑ አባላት ይህንኑ ግጥም በመድገም በእኩል ይሉታል። በሀላባ ማህበረሰብ ሁሉም የራሱ የሆነ ጥበባዊ የባህል ቅኝት አለው። ሴቶቹ በቃላ የሙዚቃ ስልት ጨዋታቸውን ሲያደሩ፤ ወንዶቹ ደግሞ በቸለሎቴና ሪብሪቦቴ ዜማዎቻቸው በህብራዊ ቃና የደስታን ማማ ይረግጡበታል። ታዳጊ ልጆችም ቢሆኑ ከጥበብ መንደር አይጎድሉም። ከዓመት ዓመት በልዩ ልዩ ጨዋታዎቻቸው ፍልቅልቅ ብለው ይኖራሉ፤ ከሁሉም ግን ወርሃ ጥር ወይንም በእነርሱ አጠራር የ“መንገሳ” ወር ከሁሉም ይለያል። ለእነዚህ ልጆችም ወሩ የተቀደሰና ዓመቱን ሙሉ በጉጉት የሚጠብቁት ነው። የራሳቸው የሆነ የዘመን አቆጣጠር ባለቤት የሆኑቱ፣ የሀላባውያኑ የዘመን መለወጫ
ወይንም “መንገሳ ሴራ” በዚሁ ወር ላይ ነው። የልጆቹን ልብ በጉጉት ቀጥ ማድረጉ ክብረ በዓልነቱ ብቻ ሳይሆን በዓሉን ተከትሎ ለልጆቹ የሚመጡ በርካታ ነገሮች በመኖራቸው ነው። የልጅነት ወግ ማዕረጋቸውን የሚያዩበት የተለየ ዓለማቸው ነው። የሚፈልጉት ሁሉ ይደረግላቸዋል። ልብስ ይገዛላቸዋል። በመንገሳ ያልተገረዙ ይገረዙበታል፤ የሚጠብቃቸውም ብዙ ነው። ተልከው ሲሮጡም ሆነ ከብቶቻቸውን ከሜዳ ግጦሹ ሲያሰማሩ ከእጃቸው ዋሽንት፤ ከአፋቸው ሙዚቃ አይጠፋም። በግልም ሆነ በጋራ “መንገሳ” የምትለዋን የባህል ዜማቸውን በናፍቆት ያዜማሉ።
የሀላባ ማህበረሰብ አልባሳቱ የባህሉ ጌጥ ናቸው። ውበቱን የሚያንጸባርቅበት በመሆኑ የተለየ ፍቅርና ክብር ለአልባሳቱ አለው። ሴቶቹ “ቆሜ” የተሰኘውን የባህል ልብሳቸውን ጨምሮ በልዩ ልዩ ዲዛይን በተሠሩ አልባሳቶቻቸው ማጌጥ የአንዳንድ ጊዜ ሳይሆን የሁሌም ልማዳቸው ነው። ወንዶቹም፤ መለያቸው በሆነው ባለ ቀለም ቆብና ባለ ዘርፉ ቁምጣ በሄዱበት ሁሉ መድመቂያቸው ነው። ሴቶች ሴትነታቸውን፤ ወጣቶች ወጣትነታቸው ለማሳየት ከአልባሳቱና ጌጣ ጌጡ በስተጀርባ ሁሌም ሙዚቃ ሁሌም ኪነ ጥበብ አለ።
ከአመጋገብ እስከ አጊያጌጥ፤ ከባህላዊው ሙዚቃና ጭፈራ እስከ ልዩ ልዩ ትውፊታዊ ክንዋኔዎቻቸው ድረስ ከሴራ ባህላቸው ጋር የተቆራኘ ነው። በሀላባውያኑ የሴራ ክብረ በዓል ዕለት ዘንካታው ሶታ ጎረምሳ፤ የባህል አልባሱን ለብሶ፤ ጸጉሩን ክምክም ተስተካክሎ፤ ውሀ አጣጪውን ፍለጋ ይወጣል። ዕለቱ የትጭጭትም ጭምር ነውና። ከዚያ ሁሉ ሕዝብ መሀል በውበት ዛላ ደርበብ ብላ ከባህል ቀሚሷ በአንገቷ ጌጡን በእግር አልቦ የእጅ አንባሩን አጥልቃ እኔም አላገባሁም ምልክት ጸጉሯን ጋሜ ተሠርታ ሽቅርቅር የምትለዋን የሀላቢቾን ኮረዳ በአይኑ እያማተረ ይፈልጋታል።
ሴራ እንደሆን ሀላባውያኑን ከልጅነት እስከ እውቀት እየመራ ሁሉን ማቃናቱ ልማዱ ነው። በሴራ ባህል መሠረተ በሰሞነ ሴራ ይገረዛል። በሴራ ተኮትኩቶ ያድጋል። በሴራ ዕለት ተጫጭቶ ደግሞም በሴራው ሥርዓት ከሴራው ክብረ በዓል አጥቢያ ያገባል። እንግዲህ በዓመቱ ሴራ ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ ይዞ ይመጣል። የአባቱ ልጅ ደግሞ ይቀጥላል። በሴራ መንገሳ መች ወጣቱ ብቻ ሆነና እናቶችም አሉ። ከላይ እስከ ታች በባህላዊ አልባሳቶቻቸው ውበትን ደፍተው ይወጣሉ። ለማግባታቸው ምልክት ከወገባቸው ላይ መቀነቱን ሸብ አድርገው ከበሮዎቻቸውን በመያዝ ሰብሰብ ብለው በያካና ቃላ የባህላዊ ሙዚቃዎቻቸው እየጨፈሩ ወደ አደባባይ ይወጣሉ።
ከልጅነት እስከ እውቀት ሴራ አለ። ከልጅነት እስከ እውቀት ኪነጥበብ አለ። ታዳጊዎች ወደ ወጣትነትና ከቤተሰቦቻቸው ሙሉ ኃላፊነትን ተቀብለው ለመሸከም ወደ ሚችሉበት የዕድሜ ክልል ሲሸጋገሩ የሚከወነው የ”ሁሉቃ” ሥርዓት ማሳያ ነው። ልጆች ገና ከህጻንነታቸው፤ በግርዛት ወቅት የሚጠቀሙት የዋሽንትን ድምጽ የሚሰጥ ሌማት፤ ወይንም ከቀርክሀ ዛፍ የሚሰራ “ኡሉሌ“ የሚሰኝ የሙዚቃ መሳሪያ ይይዛሉ። የሚዘጋጀውም በራሳቸው ነው። ካደጉ በኋላም እንደ ሙዚቃ መሳሪያ የሚያገለግለውንና የማህበረሰቡ መገለጫ የሆነውን ፊሽካ ይይዛሉ።
መነሻውን ኡሉሌ አድርጎ ዛሬም ድረስ የሀላባ የሙዚቃ መሳሪያ በመሆን ያገለግላል። የተለያዩ የባህል የኪነት ቡድኖች በተለያዩ ጊዜያት እስከ ጦር ግንባር ድረስ ሔደው ጀግናውን እያበረታቱና እያሞገሱ የሠራዊቱን ወኔ ቀስቅሰውበታል። በየሠርግና የደስታ ቦታዎች ሁሉ ከመጠቀምም ባሻገር በየዓመቱ የሴራን ክብረ በዓል ለማድመቅ ይጠቀሙበታል። ጭፈራ ባለበት ሁሉ ኡሉሌ አለ። ታዲያ ኡሉሌ ብቻውን አይደለም የላመውን የጎማ ከመነዳሪ ከእንስራ አፍ ላይ የተወጠረ፤ እንደ ከበሮ ያለው “ደንበሌሳ”ም አለ።
ድምጻዊ ኑረዲን ያሲን በሀላባ ማህበረሰብ እውቅ ድምጻዊ ነው። ከዚያም ባሻገር በማዕከላዊ ኢትዮጵያ የሀላባ ዞን የባህል አምባሰደርም ጭምር ነው። በሥራውም ነጠላ ዜማዎችንና “አባዲጋ” የተሰኘ አንድ አልበም እንዳለው አጫውቶኛል። ኪነጥበብና የሴራ ባህል ወዳጅነት የገዘፈ ነውና ይህን እያነሳ ስለ አንዳንድ ጉዳዮች እንዲነግረኝ በጠየቅኩት ጊዜ እንዲህ አለኝ፤ “ባህሉን ለማንጸባረቅ እንደ ኪነጥበብ ያለ የለም። በሀላባ ሴራ ውስጥ ከመነሻው ጀምሮ በኪነጥበብ የታጀበ ነው። በዚህ የሞቀው የሴራ በዓል ኪነጥበባዊ ክዋኔዎች ክብረ በዓሉን የደመቀ ለማድረግ ከመሀል የፈረስ ጉግስ ስለመኖሩም ላክልበት” አለ። ያክልበት፤ እሱስ ቢሆን መች ከኪናዊነት የራቀ ሆነና። ከእነዚህ የጉግስ ፈረሶች በስተጀርባ ሌላ ታሪክም ስለመኖሩ ኑረዲን አንስቶልናል።
እንደሚታወቀው አርበኞቹ አባቶቻችን በጣሊያን ወረራ፤ እንዲሁም በተለያዩ ጦርነቶች ሲጠቀሙ የነበሩት ታንክ የጫነ ዘመናዊ ተሽከርካሪ ሳይሆን ኮርቻና ግላስ የተሸከሙ ፈረሶችን ነበር። የሀገርን ታላቅነት በሚያወሳው ሙዚቃ ግለት እሳት ፍም ለብሰው፤ በግጥምና ዜማዊ ፉከራና ሽለላ በያዙት ጎራዴና ጦር ከልባቸው ውስጥ እሳቱን ለኩሰው በፈረሶቻቸው ወደ ጠላት መንደር ይገሰግሳሉ። ደርሰውም በያዙት ጎራዴና ጦር ከልባቸው እሳቱን እየለኮሶ የጠላትን ዘመናዊ የጦር ታንክ አመድ ያደርጉታል። ለምስክርነትም ሁለት የጠላት ታንኮች ዛሬም ድረስ በሀላባ ምድር ይገኛሉ። ይህ የሆነው በሂሊኮፕተር አልነበረም፤ በፈረስ እንጂ።
ኪነጥበብ ከስሜት ጋር ሲዋሀድ ከሰማይ ላይ እንደ አሞራ የሚበረውን የጦር ሂሊኮፕተር ከምድር ፈረስ ላይ ተቀምጠን እኛም እንደ አባቶቻችን ወደ መሬት እንጥለዋለን። የፈረስ ጉግሱም ከጉግስነት በተጨማሪ ይህንን ያስታውሰናል። የሀላባ ባህልና ኪነጥበብ፤ ኪነጥበብና ሴራ ተጋምዷቸው እንዲሁ በዋዛ የሚፈታ አይደለም”። በሴራ ጥበባት በየአይነቱ በየፈርጁ ይዘንባሉ። ግጥም ‘ሴነፎ’ . . . የእናቶች ‘ቃላ’ . . . ወጣቶቹ በሽለላና ፉከራ “እሪ!” እያሉ ወኔን ከውስጣዊ ስሜት ጋር ይቀሰቅሱበታል። ሀላባውያን በሴራ ኪነጥበብ ሀገር፣ ቤተሰብና እራሳቸውን ከመጠበቅ/ማስጠበቅም ባለፈ ያስከብሩበታል።
ድምጻዊ ኑረዲን ካነሳቸው ሀሳቦች መሀል ድንገት አንዲት ጥያቄ ሽው አለችና እንዲያው ግን የሀላባ ማህበረሰብ ለ7 መቶ ዓመታት ያህል የሴራን ሥርዓቶች ሳይቆራረጥና ሳይሸራረፈ ከትውልድ ትውልድ ተሸጋግሮ እዚህ ሲደርስ የሴራ ሥርዓት ከኪነጥበብ ጋር አንገት ለአንገት የተቃቀፈ ስለመሆኑ ማህበረሰቡ ልብ ብሎ ተመልክቶት ይሆን? የምትለዋን ጥያቄ ጣል በማድረግ ምላሹን ጠበቅኩኝ። “ይሄ የገባን ጥቂቶች ነን። ማህበረሰቡ ግን ጥንቱን በሴራ ሥርዓት ኪነጥበብን ለይቶ እንደ ዛሬው ለማጣፈጫነት ሳይሆን እራሱን ኪነጥበብን እየፈጠረ ባህሉ አድርጎት ነበር።
በዚህ ምክንያትም ኪነጥበብ የማህበረሰቡ ባህል ማዳበሪያ ሳይሆን ባህሉ እራሱ ኪነጥበብ ነበር” የምትለዋን ምላሽ አስከተለ። ነገሩ እውነት ነው። ዛሬ ላይ የእውቀትን የዋንጫ ጽዋ በፊደል ስናነሳ ኪነጥበብን ከባህል ደም ስር ውስጥ ለይተን በማውጣት “ኪነጥበብ” የሚል የስም ቡልኮ ደርበንለት እንደ አዲስ ያገኘነው መሰለን እንጂ በጥንታዊያኑ የኛ አባቶች ዘንድ ስለዛሬው የኛ ኪናዊ ፍልስፍና ሳይጨነቁ ኪነጥበብ እራሱ እንደ ባህር አሳ ከባህሎቻቸው ተነጥሎ ለመኖር የማይችል ባህላቸው ነበር። ዛሬ ዛሬ ሳይንሳዊ እውቀታችን እየሰፋ ዘርፉን አንዘርፍፈን በየጎራው መለየታችን ድንቅ ቢሆንም፤ ነገር ግን ዘመኑ በጨመረ ቁጥር ከባህሎቻችን ራቅ እያለ ዛሬ ላይ ባይተዋርነት እየተሰማው ይሆን? የሚል ሌላ ጥያቄ ከአዕምሮዬ ቋት ሲወነጨፍ ተሰማኝ፤ ጥያቄው ግን ለድምጻዊው ሳይሆን ለራሴና ለውስጤ ብቻ ነበር።
በሴራ መንገሳው ዕለት ከህጻናት እስከ አዛውንቱ በቁሊቶ ከተማቸው አደባባይና ጎዳናዎች ላይ ፈሰው ከአልባሳትና ጌጦቻቸው ጋር ሲታዩ በንጉሥ ቤተ መንግሥት የተነሰነሱ አበባ መስለዋል። አይኔን አማትሬ ሁሉን ለመመልከት ብሞክር ያይን አዋጅ ሆነብኝ። ከአንደኛው አውራ ጎዳና ላይ በባህል ልብስ ያሸበረቁ በርከት ያሉ ወጣቶች ሰብሰብ ብለው በጭፈራ አቧራውን ያጨሱታል። ከሙዚቃው ስልት ጋር በቀኝ እግራቸው መሬቱን እየደቁ፤ ከበሮውን ይደልቁታል። ፊሽካውን ፒርር እያደረጉ ጭፈራውን ያደምቁታል። አለባበሳቸው አይንን፤ ዜማቸው ቀልብን ይስባል። ድንገት ከመሀል አንዱን ወጣት ጠርቼ ጥቂት አወራሁት።
ለግላጋው ወጣት ራህመቶ መሀምድ እንደሚባል ከነገረኝ በኋላ፤ “ይሔ ጭፈራ ምን ይባላል?” ስል ጠየቅኩት። “ጭፈራውማ ቸለሎቴ ነው፤ ቀጥሎም ያካ ይኖረናል” ቋንቋችሁ ጉራማይሌ ነው፤ ከብዙ ቋንቋዎች ጋር የሚመሳሰል ይመስላልና ይሔስ ነገር እንዴት ነው? “ቋንቋችንም ከበርካታ የሀገራችን ቋንቋዎች ጋር ዝምድና አለው፤ ከዚህም ከዚያም የተወራረሰና በቃላት የተጋመደ ነው። ሀላባ የብዙ ብሔሮች መኖሪያና ብዙዎች በህብረትና ፍቅር ያቆሟት ናት። የሀላባን ባህል መጠበቅ ኢትዮጵያን መጠበቅ ነው” አለኝ። በርግጥም ልክ ነበር።
ገና ያላወቅነው እንጂ አውቀን የጨረስነው ኢትዮጵያዊነት የለም። ገና ምኑንም ያላየነውና ያልሰማነው ኪናዊ የባህል ዳርቻ እንጂ “አይቼ፣ ሰምቼዋለሁ” ብለን በአራት ነጥብ የምንዘጋው የለም። ብንል እንኳን የኩሬ ታህል አትሆንም። ሀላባዎቹ በዪኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች ማህደር ውስጥ ለማስፈር በአሁኑ ሰዓት ላይ ታች እያሉለት ያለውን የሴራ መንገሳ ባህልን፤ እኔም ከባህሩ የኩሬ ያህሏን አየሁ እንጂ አይቼና አውቄ አልጨረስኩትም። የሀላባውያኑን ሴራ መንገሳ ከመሳሰሉት ውስጥ እንዲህ ያሉ ውብ የባህል እሴቶቻችን ይፈልቃሉ። እነርሱም እንደሚሉት ኪነጥበባችን ያለ ሴራ አይቆምም፤ ሴራችንም ያለ ኪነጥበብ አይኖርም።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ጥር 9/2016