በቤት ውስጥ ቱር ውድድር ዓለም ኢትዮጵያውያኑን አትሌቶች ይጠብቃል

ይህ ወቅት በአትሌቲክስ ፖርት የቤት ውስጥ ውድድሮች በስፋት የሚከናወንበት መሆኑ ይታወቃል። በየካቲት ወር አጋማሽ ላይ ስፖርቱን በሚመራው አካል የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና የሚካሄድ መሆኑን ተከትሎ በመላው ዓለም በሚገኙ በርካታ ከተሞች ውስጥ የቤት ውስጥ ቱር ውድድሮች ይከናወናሉ። በአውሮፓ፣ እስያ እና ሰሜን አሜሪካ አህጉራት በሚገኙ 20 ከተሞች ውስጥ ከ50 በላይ የሚሆኑ ውድድሮች የሚደረጉ ሲሆን፤ እነርሱም በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ፣ የብር፣ የነሃስ እንዲሁም ውድድር የሚል ደረጃ ተሰጥቷቸዋል።

የፈረንጆቹ አዲሱ ዓመት ከመግባቱ ከሁለት ቀናት በፊት የተጀመረው ይህ የቱር ውድድር የዓለም ቻምፒዮናው ከመካሄዱ 6 ቀናት በፊት የሚጠናቀቅ ሲሆን፤ በሜዳ ተግባራት እንዲሁም ከ60 ሜትር እስከ 5ሺ ሜትር ባሉት ርቀቶች አትሌቶችን ያፎካክራሉ። እያንዳንዱ የቱር ውድድር የገንዘብ ሽልማት ሲያስገኝ፤ አትሌቶች በሚኖራቸው ተሳትፎ የሚያስመዘግቡት ነጥብ ተደምሮ በዓለም አቀፉ ቻምፒዮና በቀጥታ ሃገራቸውን ወክለው የሚሳተፉበትን እድል ሊያስገኝላቸው ይችላል። ከዚህም ባለፈ ከፍተኛ ነጥብ የሚያገኙ አትሌቶች በመጨረሻው ውድድር 10ሺ የአሜሪካ ዶላር ጉርሻ በማግኘትም በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያው በሆነው ዓለም አቀፍ ቻምፒዮና የሚፎካከሩም ይሆናል። በእንግሊዟ ግላስኮ አዘጋጅነት የሚደረገው ይህ የቤት ውስጥ ቻምፒዮናም ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ ይደረጋል።

በዓለም አትሌቲክስ ደረጃ የተሰጣቸው የቱር ውድድሮች በተከታታይ እየተካሄዱ ሲሆን፤ ታዋቂ አትሌቶች በተለይ የሚካፈሉባቸው የወርቅ ደረጃ ያላቸው ውድድሮች ግን ከቀናት በኋላ ነው የሚጀምሩት። የእስያዋ ካዛኪስታን በዋና ከተማዋ አስታና የምታካሂደው ውድድር ቀዳሚው ሲሆን፤ በውድድሩ ዝናን ያተረፉ አትሌቶች መሳተፋቸውን አረጋግጠዋል። ነገር ግን ከእነዚህ መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያዊቷ የመካከለኛና ረጅም ርቀት አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ተሳትፎዋን እንደሰረዘች ታውቋል። የቤት ውስጥ ቻምፒዮናን ጨምሮ በኦሊምፒክ፣ በዓለም ቻምፒዮና፣ በዳይመንድ ሊግ እንዲሁም በሌሎች ውድድሮች ኢትዮጵያን ያስጠራችው የ5ሺ ሜትር ንግስቷ፤ የውድድር ዓመቱን በካዛኪስታን ትጀምራለች በሚል ቢጠበቅም ለቀናት ማራዘሟ ነው የተረጋገጠው። ነገር ግን በ1ሺ 500 ሜትር ርቀት እንደምትሳተፍ አስቀድማ ያሳወቀችው አትሌት ሂሩት መሸሻ እንዲሁም በ3ሺ ሜትር የሚሮጠው አትሌት አሊ አብዲልማና ሃሳባቸውን ሳይቀይሩ የሚሮጡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።

ጠንካራዋ አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ በበኩሏ የወርቅ ደረጃ ባለውና ቦስተን ላይ በሚካሄደው ኒው ባላንስ ግራንድ ፕሪክስ የተለመደ አስደማሚ ብቃቷን ለማሳየት ተዘጋጅታለች። ባለፈው የውድድር ዓመት አስደናቂ ጊዜ ያሳለፈችው አትሌቷ ከቡዳፔስቱ ስኬታማ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና መልስ በዳይመንድ ሊግ የ5ሺ ሜትር ክብረወሰን መስበሯ የሚታወስ ነው። በዚህም አትሌቷ የዓለም ምርጥ አትሌት እጩ መሆኗ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ጉዳፍ በቤት ውስጥ ውድድርም በ1ሺ500 ሜትር ስኬታማ ስትሆን፤ እአአ 2016 ፖርትላንድ ላይ ሃገሯን በመወከል የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤት ነበረች። ኢትዮጵያ ከዓለም አንደኛ ደረጃን ይዛ ባጠናቀቀችበትና ከሁለት ዓመት በፊት ቤልግሬድ ላይ በተደረገው ቻምፒዮና ደግሞ በዚሁ ርቀት የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቅ ችላለች። በመሆኑም አትሌቷ ካለችበት ወቅታዊ አቋም እና ካላት ልምድ አንጻር በቱር ውድድሩ ከፍተኛ ነጥብ በማስመዝገብ ለቻምፒዮናው ቀጥታ መሳተፍ የምትችልበትን እድል ታገኛለች የሚለው ግምት በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ አይሏል።

በሌላ በኩል በዚህ መድረክ እጅግ ተጠባቂና ውድድሩንም ከሚያደምቁ አትሌቶች መካከል አንዱ ኢትዮጵያዊው ለሜቻ ግርማ ነው። በዓለም ቻምፒዮና የሶስት ጊዜ እንዲሁም በኦሊምፒክ አንድ ጊዜ የብር ሜዳሊያ ያገኘው ወጣቱ አትሌት ኢትዮጵያን በ3ሺ ሜትር መሰናክል ካስጠሩ ጥቂት አትሌቶች መካከል አንዱ ነው። ቤልግሬድ ላይ በነበረው ቻምፒዮናም በተመሳሳይ የብር ሜዳሊያውን መውሰድ ችሎ ነበር። ይህ አትሌት ባለፈው ዓመት ሌቪን ላይ በተደረገው የቤት ውስጥ ቱር ውድድር ርቀቱን 7:23.81፣ ከቤት ውጪ ደግሞ 7:52.11 በሆነ ሰዓት በመሸፈን ሁለቱንም ክብረወሰኖች ከእጁ ማስገባቱም አይዘነጋም። ይህም ውድድሩን አጓጊ የሚያደርገው ሲሆን፤ ተፎካካሪዎቹን በአሳማኝ ብቃት በመርታት ግላስኮ ላይ ኢትዮጵያን የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ያደርጋታል የሚለውም ተጠባቂ ነው።

በዚህ ውድድር ከሚካፈሉና አሸናፊ ይሆናሉ በሚል ተስፋ ከተጣለባቸው አትሌቶች መካከል ኢትዮጵያዊቷ ወጣት አትሌት መዲና ኢሳ ትጠቀሳለች። የዓለም ከ20 ዓመት በታች የ5ሺ ሜትር ክብረወሰን ባለቤቷ ወደ አዋቂነት የሚያሸጋግራትን ብቃት እንደምታሳይም ተገምቷል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን  ጥር 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You