የፊታችን ቅዳሜ ጥምቀት ነው፡፡ በጃን ሜዳ ኢትዮጵያን እናያለን፡፡ እርግጥ ነው በዓሉ ሃይማኖታዊ ነው፡፡ በጃን ሜዳ የሚታየው ግን ሁለቱም ነው፡፡ ከትሪቡኑ ጊቢ የዲያቆናትና ካህናት ዝማሬዎችና ሌሎች ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ይከወናሉ፡፡
ጃን ሜዳ ከመግቢያ በሮች ጀምሮ ሙሉ ሜዳው ግን በባህላዊ ጨዋታዎች ይደምቃል፡፡ ወደ ጃን ሜዳ በሚወስዱ መንገዶችም እንደዚያው። እነዚህ ጨዋታዎች በመላው ሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የሚከወኑ ናቸው፡፡
አንዳንድ ፖለቲከኞቻችን የመከፋፈልና የመነጣጠል ሥራ ለመሥራት ከፋፋይ ንግግሮች ሲያደርጉ ስንሰማ ኖረናል፡፡ ከአንዲት ሀገር ውስጥ ‹‹ይሄ የአንተ አይደለም፤ ይሄ አይመለከትህም፤ ይሄን አታድርግ!›› ሲሉ ይታያል፡፡ ይባስ ብሎም አንዱ ብሄር በሌላው ላይ የጫነው ነው በማለት ጫኚና ተሸካሚ ያደርጉታል፡፡ የኢትዮጵያ መለያ ሆኖ የኖረ ምልክት ወይም ጌጥ ‹‹አይ! ይሄማ የእገሌ ብሄር ነው›› በማለት የዚያ ብሄር ተወላጅ ያልሆኑ እንዲጠሉት ይደረጋል፡፡ ለመሆኑ የኢትዮጵያ ባህል የማነው? የአንድ ብሄር ነው ከተባለ የየትኛው ብሄር ነው? የዚህ ብሄር መለያ የሆነው ከመቼ ጀምሮ ነው? ከዚያ በፊት የማን ነበር?
እነዚህን ጥያቄዎች ስንጠይቅ መልሱ አንድ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የሁሉም ብሄር ነበር፡፡ የሆነ ወቅት ላይ ኦሮሞ ውስጥ ይታይ የነበረው በሂደት አማራ ወይም ትግራይ ውስጥ ይገኛል፡፡ አማራ ወይም ትግራይ ውስጥ የነበረው ከሆነ ዘመን በኋላ ኦሮሞ ወይም ሶማሌ ውስጥ ይገኛል። በቀደመው ዘመን የነበሩ ወታደራዊ ዘመቻዎች ይህን ለማድረግ ያስገድዳሉ፡፡
ደራሲ በዕውቀቱ ሥዩም ከተናገረው አንድ ገጠመኝ ልነሳና ወደ ዋናው ትዝብት ልግባ፡፡ በዕውቀቱ ጎጃም ውስጥ ነው ተወልዶ ያደገው፡፡ ጎጃም አማራ ነው።
እናም እሱ ባደገበት አካባቢ እንዲህ ይባላል አለ፡፡ ‹‹በሆነ ነገር ሲደነግጡ ‹አቴቴዬን› ገፈፍከው!›› ይላሉ። አቴቴ ቃሉ ኦሮምኛ ነው፤ ባህሉም ኦሮሚያ ውስጥ የነበረ ነው፡፡ እነሆ የጎጃም እናቶች እየተጠቀሙበት ነው። የአጼዎቹ የፈረስ ስም ‹‹አባ›› የሚል ቅጽል አለው። አባ ማለት ኦሮምኛ ነው፤ በኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ የሚባል ነው፡፡ እነሆ የአጼ ቴዎድሮስ፣ የአጼ ምኒልክ፣ የአጼ ኃይለሥላሴ … የአጼዎች ሁሉ የፈረስ ስም መነሻው ‹‹አባ›› ነው፡፡ አባ ታጠቅ፣ አባ ዳኛው፣ አባ ጠቅል… እየተባሉ ይጠራሉ፡፡
ደራሲ በዕውቀቱ ሥዩም ከዓመታት በፊት በጻፈው ጽሑፍ፤ አንድ የብሄር አቀንቃኝ ፖለቲከኛ ከእንቁ መጽሔት ጋር ያደረገውን ቃለ መጠይቅ ይጠቅሳል። ፖለቲከኛው ‹‹የኢትዮጵያ ሀገራዊ ማንነት የምንለው የአማራ ባህላዊ ማንነት ነው›› ብሏል፡፡ በዕውቀቱ ደግሞ ታሪክን እየጠቀሰ የአንድ ብሄር ብቻ እንዳልሆነ ይሞግታል፡፡ ፖለቲከኞች ለራሳቸው ቁማር የአብሮነት ባህሉን እየጣሉ የሚነጣጥል ዘዴ ነው የሚፈልጉት፡፡ ኢትዮጵያውያን የውጭ ጠላትን ድል ያደረጉት በጋራ እንደሆነ የጠላት ሀገር ሰዎች ሳይቀር መስክረዋል፡፡ አጼ ዮሐንስ አራተኛ ኤርትራ ውስጥ የግብጽ ወራሪን ድል ሲያደርጉ ከግብጽ በኩል ሆኖ ይዋጋ የነበረው አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ዊልያም ዴይ አጼ ዮሐንስን ለማገዝ የኢትዮጵያ ብሄሮች ከጫፍ እስከ ጫፍ ይጠራሩ እንደነበር መስክሯል፡፡
በእንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ነው የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ወግ የተወራረሰው፡፡ ‹‹ከተለያዩ ማዕዘናት የመጡ እነዚህ ኢትዮጵያውን ከዘመቻው የሚያገኙት ድልን ብቻ አልነበረም፡፡ በዘመቻ ወቅት ባህል ይዋዋሳሉ፣ ቃላት ይወራረሳሉ፣ ስንቅ ያዋጣሉ፣ ልምድ ይለዋወጣሉ፡፡ በሂደት ተቃራኒ ከሚመስሉ ልማዶች የነጠረ ኢትዮጵያዊ ባህል እንደ አረቄ ይወጣል፡፡ ይህን በመዋጮ የተገኘ ባህል ‹የአማራ ባህል› ብሎ ማጥበብ የጸና ድጋፍ ያለው አይመስለኝም›› ይላል ጸሐፊው በዕውቀቱ ሥዩም፡፡ ከበዕውቀቱ ጽሑፍ አሁንም እንቀንጭብ፡፡
‹‹ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ስራ ሲሠራ አስቀድሞ የሚመጣው የቡና ሥነሥርዓታችን ነው፡፡ አንዲት ጠይም፣ ባለሹርባ ሴት፣ የሐበሻ ቀሚስ ለብሳ ቡና ስትቀዳ የሚያሳይ ምስል በየቦታው ማየት የተለመደ ነው፡፡ ይህ ምስል በሥነ ሥዕል ብቻ የተወሰነ አይደለም። ቢዮንሴ እና ጆን ኬሪ ሀገራችንን በጎበኙበት ሰዓት የቡና ሥነ ሥርዓት ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ይህ ማለት የውጭ እንግዳ የቡና ሥርዓታችንን እንደ ኢትዮጵያዊ መለዮ እንዲመዘግብልን ፈልገናል ማለት ነው።››
ይሄን የቡና ሥነ ሥርዓት ዘርዝረን እንየው። የእያንዳንዱ ብሄር መዋጮ አለበት፡፡ የልጅቷ ሹሩባ የሐማሴን ወይም የተምቤን ባህል ነው፡፡ የሐበሻ ቀሚሷን የሸመነው ሽሮ ሜዳ የሚሠራ የጋሞ ተወላጅ ነው፡፡ ጀበናውን የሠራው የጅማ ሙስሊም ነው፡፡ አቦል፣ ቶና እና በረካ የሚለው የአረብኛ ቃል ነው፡፡ ታዲያ ይሄንን ውህድ ባህል የአማራ ወይም የኦሮሞ ወይም የትግሬ ነው ማለት ፍትሐዊ ነው?
ባህል በጊዜ ብዛት ይለዋወጣል፡፡ የሰው ልጅ ከሥልጣኔ ጋር ራሱን ይለውጣል እንጂ ባለበት አይቆምም፡፡ በዚህም ልውውጥ አንድ አካባቢ የነበረው ወደ ሌላ አካባቢ ይሄዳል፡፡ በዘመን ቅደም ተከተል እንየው ከተባለም፤ ድሮ በባዶ እግሩ ይሄድ ነበርና አሁንም ይሂድ ማለት አይቻልም። ድሮ የወንዝ ውሃ አጎንብሶ ይጠጣ ነበርና አሁንም የወንዝ ወይም የኩሬ ውሃ ይጠጣ ማለት አይቻልም፡፡
ባህል ለምን ተወራረሰ ካልን፤ ድሮ የሰው ልጅ የኑሮ ሥርዓት ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ አስገዳጅ ነበር። እንደ ዛሬው ከቤቱ ቁጭ ብሎ በበይነ መረብ የፈለገውን ማዘዝ አይችልም፤ በቴሌቪዥን መስኮት የፈለገውን ማየት አይችልም፡፡ ያዘዘውን ነገር በቀላሉ ማስመጣት አይችልም። ያለው አማራጭ መሄድና መገበያየት ነበር። ጎንደር ላይ የሚመረት ነገር ወለጋ ውስጥ አይኖርም፤ የወለጋው ጎንደር ውስጥ አይኖርም፡፡ የጅግጅጋው ነዋሪ መቀሌ ድረስ ይሄዳል፤ የመቀሌው ሰው አሶሳ ወይም ጋምቤላ ይሄዳል። በእነዚህ ሁሉ መስተጋብሮች የባህልና የታሪክ ውርርስ ነበር። እንዲህ ነው ኢትዮጵያን የገነቧት።
ከላይ ለዘረዘርናቸው ነገሮች የሰሞኑ የጥምቀት በዓል ምስክራችን ነው፡፡ ጥምቀት የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች በዓል ነው፡፡ የበዓሉን ባህላዊ ይዘት ልብ በሉ! ለዚህ በዓል ብዙ ነገሮች ይገዛሉ፡፡ የበዓሉ ቀን ልብ ብላችሁ ከሆነ ጎዳናው ሁሉ በሻጮች የተጥለቀለቀ ነው፡፡ ያ ሻጭ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ላይሆን ይችላል። እሱማ ልብሱን ለባብሶ ታቦት ያጅባል። የእስልምና ወይም የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዩ ግን የሥራ ልብሱን ለብሶ ለእሱ የጦፈ ገበያ ነው፡፡ አንድ ባለ ሱቅ ሙስሊም የጥምቀት በዓል መምጣት ከኦርቶዶክሱ በላይ ያስቸኩለዋል፡፡ ኦርቶዶክሱ ‹‹ምን ልግዛ?›› እያለ ሲያስብ፤ ሙስሊሙ ምን ላስመጣ? እያለ ያስባል፡፡ ለጥምቀትና ለገና በዓል የሚገዛዙ ስጦታዎችን ያስመጣቸው የመርካቶ ሙስሊም ነጋዴ ነው። ከዚህም አለፍ ሲል፤ የራሱ የሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱ መለያ የሆነውን መስቀል የሚሠራው ሙስሊም የእጅ ጥበበኛ ነው፡፡
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ብሄራዊ ቴአትር በተዘጋጀ አንድ መድረክ ላይ የተናገረው ነገር ትዝ አለኝ፡፡ የብሄር ብሄረሰቦች የአጨፋፈር ባህል እንኳን አቅጣጫውን ተከትሎ ሙሉ ኢትዮጵያን የሚያሳይ ነው፡፡ ከሰሜን ኢትዮጵያ ሲጀምር የትግራይ አጨፋፈር ከአንገት በላይ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው፡፡ የአማራ አካባቢዎች በትክሻ እንቅስቃሴ የሚደረግ ነው፡፡ የኦሮምኛ የባህል አጨፋፈር በአንገትና በወገብ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ወደ ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ስንሄድ ደግሞ በዳሌና በእግር (ለምሳሌ ጉራጌ) የሚደረግ ነው፡፡ በአንድ መድረክ ላይ ሙሉ ኢትዮጵያን ያሳያል ማለት ነው፡፡
ስለዚህ ባህሎቻችን በስሪት የጋራ እንደ ሆኑ ሁሉ፣ በመንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብትም የሁላችንም ናቸው!!!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥር 8 ቀን 2016 ዓ.ም