በአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ

34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከተጀመረ ዛሬ አራተኛ ቀኑን አስቆጥሯል፡፡ ኮትዲቯር ለሁለተኛ ጊዜ እያስተናገደች ባለችው በዚህ ውድድር ላይ የመክፈቻው ጨዋታ ጊኒ ቢሳውን በማሸነፍ የጀመረች ሲሆን፤ በቀጣዩ ቀን ደግሞ የምድቡ ቡድን የሆኑት ናይጄሪያ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ በአቻ ተለያይተዋል፡፡ በሌላኛው ምድብ ግብጽና ሞዛምቢክም በተመሳሳይ አቻ ሲለያዩ ኬፕቨርዴ ጋናን 2 ለ1 በሆነ ጠባብ ልዩነት ያልተጠበቀ አሸናፊነትን ተቀዳጅታለች፡፡

ትናንት በተደረገው የምድብ ጨዋታም በምድብ ሶስት ሴኔጋል ከጋምቢያ እንዲሁም ካሜሮን ከጊኒ ተጋጥመዋል፡፡ አልጄሪያ እና አንጎላ ደግሞ በአራተኛው ምድብ ጨዋታቸውን ያከናወኑ ቡድኖች ናቸው፡፡ ዛሬ በዚሁ ምድብ አንድ ጨዋታ የሚከናወን ሲሆን፤ ከምድብ አምስት ደግሞ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡ በዚህም መሰረት የመጀመሪያው ጨዋታ በቡርኪና ፋሶ እና ሞሪታኒያ መካከል ስታዴ ዴ ላ ፔክስ በተባለውና 40ሺህ ታዳሚ በሚይዘው ስታዲየም ይካሄዳል፡፡

በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አራተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የቡርኪና ፋሶ ብሄራዊ ቡድን በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ካለፈው ጊዜ በተሻለ ብቃት የተመለሰ ይመስላል፡፡ በአውሮፓ ክለቦች የሚጫወቱ በርካታ ተጫዋቾች ያሉትና ሶስት ጊዜ ለፍጻሜ የደረሰው ይህ ቡድን ቀላል ግምት የማይሰጠው ሲሆን፤ ለዋንጫ መድረስ ባይችል እንኳን ለትልልቆቹ ቡድኖች ሳይቀር ፈታኝ ተፎካካሪ እንደሚሆን ይገመታል፡፡

የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ክለብ በሆነው ሉተን ታውን የሚጫወተው የቡርኪናፋሶው ኢሳ ካቦሬ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ሲሆን፤ በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ይደምቃሉ ተብለው ከተለዩ ተጫዋቾች መካከልም አንዱ ነው፡፡ የአስቶንቪላው በርትራንድ ትራዮሬ በክለቡ ተሰላፊነት የተቀዛቀዘ ቢሆንም ለሃገሩ ግን ከዚህ ቀደም ባስቆጠራቸው 17 ግቦች ላይ ከመጨመር ወደ ኋላ አይልም፡፡ ሞሪታኒያ በበኩሏ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ስኬቷ ይህ ለሶስተኛ ጊዜ ነው፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በተለያዩ ጊዜያት እርስ በእርስ ተገናኝተው አምስት ጊዜ በማሸነፍ ቡርኪና ፋሶ የበላይነቱን ትይዛለች፡፡ ይህም የጨዋታው የበላይነት የቡርኪና ፋሶ የመሆን እድሉ የሰፋ እንደሚሆን በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ የሚጠበቅ ነው፡፡

ቱኒዚያ ከናሚቢያ የሚያደርጉት ጨዋታ ደግሞ በአማዱ ጎን ኩሊባሊ ስታዲየም የሚከናወን ነው፡፡ 20 ሺህ ተመልካቾችን በሚይዘው በዚህ ስታዲየም በሚደረገው ጨዋታም የአሸናፊነት ቅድመ ግምቱ ወደ ሰሜን አፍሪካዊቷ ሃገር ያደላ ሆኗል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ለምትገኘው ናሚቢያ ይህ አራተኛ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎዋ የሆነው ናሚቢያ ከምድቧ የዘለለ ታሪክ የሌላት ሲሆን፤ ይህ ተሳትፎዋ ከ11 ዓመታት በኋላ የተገኘ ነው፡፡ “ተዋጊዎቹ″ የሚል ከባድ ቅጽል ስምን የተሸከመው ቡድኑ ባለፉት የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎዎቹ አንድም ግብ ከመረብ ባለማሳረፍም ይታወቃል፡፡

በአንጻሩ የካርቴጅ ንስሮቹ በመድረኩ በርካታ የተሳትፎ ታሪክ ያላቸውና እአአ በ2004 ውድድሩን በማዘጋጀት ዋንጫውን ማስቀረት ችለዋል፡ ፡ በካሜሮኑ የአፍሪካ ዋንጫም ጠንካራ የፍጻሜ ተፋላሚ ሆነው በመቅረብ አራተኛ ደረጃን ይዘው ነበር ያጠናቀቁት፡፡ በማጥቃት ላይ የተመሰረተ ኳስ የሚጫወተው የቱኒዚያ ብሄራዊ ቡድን በዛሬው ጨዋታም ናሚቢያን አሸንፎ የመጀመሪያውን ሶስት ነጥብ እንደሚያስመዘግብ ነው የሚገመተው፡፡

በጨዋታ መርሃ ግብሩ መሰረት በተመሳሳይ ስታዲየም የሚደረገው ቀጣዩ ጨዋታ ደግሞ የማሊና ደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች ነው፡፡ በካሜሮኑ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ያልተሳተፉት ባፋና ባፋናዎቹ ወደ ናፈቁት መድረክ የተመለሱ ሲሆን፤ ከሌላኛው የምድቡ ጠንካራ ቡድን ጋር ይፋለማሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካ በውድድሩ ጠንካራ ቡድን ካላቸው ሃገራት መካከል የምትመደብ እንደ መሆኗ ከምድቧ አልፋ 16ቱን የምትቀላቀል ትሆናለች በሚል ብትጠበቅም በአውሮፓ ክለቦች በሚጫወቱ ተጫዋቾች የተዋቀረው የማሊ ቡድን ግን በቀላሉ እጅ የሚሰጥ አይሆንም፡፡ አንድ ጊዜ ዋንጫውን ያነሱት ባፋና ባፋናዎች ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁበት ሌላኛው የስኬት ታሪካቸው ሲሆን፤ ያለፈው ተሳትፏቸው ግን የተጠናቀቀው በሩብ ፍጻሜ ነበር፡፡

በምድቧ የመጀመሪያ ጨዋታ ተሸንፋ የማታውቀው ማሊ በበኩሏ በረጅም ጊዜ የተሳትፎ ታሪኳ ዋንጫውን ባታነሳም “የተሻለ″ የሚባል ተሳትፎ አላት፡፡ እአአ በ2021ዱ የካሜሮን አፍሪካ ዋንጫ ግን ከ16ቱ ማለፍ በመቻሏ በጊዜ ነበር ከውድድሩ የተሰናበተችው፡፡ ይሁንና፣ በዛሬው ጨዋታ ላይ ነጥብ በማስመዝገብ ጠንካራ ቡድን መሆኗን ዳግም የምታስመሰክርበትን አጨዋወት ይዛ እንደምትታይ ይጠበቃል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ጥር 7/2016

Recommended For You