ለፈጣንና ተከታታይ እድገት – የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ

ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደጊዜ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ መድረክ ተሰሚነቷ እየጎለበተ መጥቷል። በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዲፕሎማሲው መስክ እያስመዘገበች ያለው ስኬት ብዙዎቹ አገራት በራቸውን ያለአንዳች ማቅማማት እንዲከፍቱላትም ምክንያት ሆኗል።

አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ትኩረት አድርጋ እየተንቀሳቀሰች ያለችው በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ላይ እንደሆነ ይታወቃል። ቀጥተኛ የውጭ ምንዛሬን በማምጣት እና ከዚህ ጎን ለጎን በአገር ውስጥ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶችንም በመደገፍ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው አይነተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ሲባል የራሱ መገለጫ እንዳለው በዘርፉ የተጻፉ መረጃዎች ያመለክታሉ። የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ሲባል የንግድ ልውውጥን በማሳደግ፣ ኢንቨስትመንቶችን በማስተዋወቅ፣ በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን የንግድ ስምምነቶች ላይ ትብብርን እና የመሳሰሉትን በማከናወን የአገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚደረግ አካሄድ ነው ሊባል ይችላል። የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ፣ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ብልጽግናን ለማጎልበት የሚያስችል ቀዳሚው ዲፕሎማሲ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአብዛኞቹ የዓለም አገራት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እየሆነ መጥቷል።

የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ዘርዘር ባለ መልኩ ሲታይ ደግሞ የመንግስትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያራምድ ማንኛውም ዲፕሎማሲያዊ ተግባር ተብሎ ሊገለጽ እንደሚችል በዘርፉ የሰፈረው ማረጃ ያመላክታል። አንድ የተወሰነ የውጭ ፖሊሲ ዓላማን ለማሳካት የኢኮኖሚ ሀብቶችን የሚጠቀም ዲፕሎማሲንም ሊያካትት እንደሚችል ያስረዳል። በሌላ በኩል ደግሞ በነጠላ ትርጉሙ ሲታይ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የኤክስፖርት ማስተዋወቅ እና የውስጥ ኢንቨስትመንት ሲሆን፣ ይህ አንዳንዴ የንግድ ዲፕሎማሲ ሊባል እንደሚችልም ይገለጻል።

በዘርፉ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ጠቀሜታው የንግድ እና የንግድ ኃይሉን በመጠቀም አገሮች እርስ በእርስ አዎንታዊ ግንኙነቶችን መፍጠር ማስቻሉ ነው። መተማመን እና መግባባት ላይ መድረስ፣ ለዕድገት እና ለልማት አዳዲስ ዕድሎችን መፍጠርም ሌላው ጠቀሜታው ነው። በመሰረቱ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ፖለቲካዊ ዓላማን ለማሳካት ኢኮኖሚያዊ መንገዶችን መጠቀም እንደማለት ነው።

የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ዓላማዎች ከሆኑት መካከል ዋናው ትኩረት ማስተዋወቅ፣ የውጭ ንግድን፣ ኢንቨስትመንቶችን፣ ቴክኖሎጂን እና ቱሪስቶችን መሳብ ነው። የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ከፖለቲካዊ፣ ህዝባዊ እና ሌሎች የዲፕሎማሲ ስራዎች ክፍሎች ጋር በቅርበት የሚገናኝም ነው።

ከኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዋነኛው አዕማድ መሆኑ ነው። በዚህም አገሪቱ የኢኮኖሚያዊ ጥቅሞቿን በዓለም አቀፍ ግንኙነት መድረክ ለማሳካት የምትችልባቸውን ልዩ ልዩ ተግባራት ስትከውን ቆይታለች። የውጭ መዋዕለ ነዋይ በሰፊው ለመሳብና ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት የማሳደግ የኢትዮጵያ ምርቶች ገበያ እንዲያገኙ ዋነኛ ግቧና መርህ አድርጋ ወደ ሥራ በመግባቷ ውጤት እያስመዘገበች መሆኑንም ያመለክታል።

እንደመረጃው ከሆነ፤ ይህን ለማሳካት ፖሊሲ ነድፎ ሳቢ እና አስቻይ ሁኔታዎችን የመፍጠር ሥራዎችም ተሰርተዋል። የግብር እፎይታ፣ ከቀረጥ ነፃ ፈቃድ እና ሌሎች መደላድሎችን የማዘጋጀት ጥረት ተደርጎ የውጭ ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲያለሙ ስራዎች በመሠራታቸው በርካታ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተዋል። ይህ ምቹ ሁኔታ በዲፕሎማሲ ጥረት ታግዞ መልካም ውጤት ተገኝቶበታል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በዲፕሎማሲው መስክ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እና የቀድሞ ዲፕሎማትና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር አምባሳደር ጥሩነህ ዜናን ባነጋገረበት ወቅት አምባሳደር ምስጋኑ እንዳሉት ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ለአገራችን ልማት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ በመሆኑ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራበት ይገኛል። በአሁኑ ወቅት የፖለቲካ ዲፕሎማሲው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲውን ማዕከል እንዲያደርግ በመሰራት ላይ እንደሆነም አስረድተዋል።

እርሳቸው እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ሠላምና የሀገር ውስጥ ልማትን በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጓል። በዲፕሎማሲው ዘርፍ ዋነኛ የትኩረት ማጠንጠኛ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የኢኮኖሚው ዲፕሎማሲ አንዱ ነው። በመሆኑም በዚህ ዲፕሎማሲ መስክ አዳዲስ የሥራ ስምምነቶች ተደርገዋል።

የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ተጨማሪ የቴክኒክ እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማምጣት እንዳለበትም የሚናገሩት አምባሳደሩ፣ የሀገር ውስጥ የልማት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በውጭ ሀገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች እንዲታገዙ በማድረግ ልማትን ለማፋጠን ሰፊ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል። የገበያ ተደራሽነትንም ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ፣ ቱሪዝሙን በማስተዋወቅ፣ የውጭ ኢንቨስትመንት ከመሳብ አኳያ የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ፎረሞችን በማዘጋጀት እንዲሁም አዳዲስ የገበያ ትስስሮችን በመፍጠር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እየተሠራ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ከዚህም የተነሳ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ለኢትዮጵያ ልማት እና እድገት ድርሻው ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል።

የቀድሞ ዲፕሎማትና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር አምባሳደር ጥሩነህ ዜና በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ረገድ ውጤት አስመዝግባለች። በተለይም ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያደረገችበት ጊዜ ቢኖር ያለፈው ዓመት 2015 ዓ.ም ላይ ነው። ዓመቱ ኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት ያስመዘገበች ነው የመባሉ ዋንኛው ምስጢር የብሪታንያ፣ ራሽያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ ኮሪያን ያቀፈው የብሪክስ አባል አገር እንድትሆን መደረጉ ሲሆን፣ ይህም ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲን የሚያሳይ ነው።

እርሳቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆን መቻሏ በራሱ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። ብዙዎች ስለብሪክስ ብዙ ግንዛቤ ላይኖራቸው ይችላል። ነገር ግን ኢትዮጵያ የዚህ ቡድን አባል አገር መሆኗ አንዱ የተፈላጊነቷ ብቻ ሳይሆን የተጽዕኖ ፈጣሪነቷም ጭምር ማሳያም ነው። ይህ ውጤት እንዴት መምጣት እንደቻለ ለሚያውቅ አካል ግን ጉዳዩ ትልቅ ስኬት የተገኘበት ነው። መጤን ያለበትም ከዚህ አኳያ ነው።

አምባሳደር ጥሩነህ፣ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን፣ በኢኮኖሚያቸውም ከፍ ያሉ እና በፖለቲካው ዘርፍ የተሻሉ ናቸው የሚባሉ ከአፍሪካም ሆነ ከአህጉራችን ውጭ የሆኑ አገራት የብሪክስ አባል ለመሆን ጠይቀው እድሉን ማግኘት አልቻሉም። ኢትዮጵያ ከተመረጡ ጥቂት አገራት ውስጥ የምትገኝ ሲሆን፣ ይህ በብዙ ፈተና ውስጥ ሆና ያገኘችው ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።

የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ፣ የወጪ ንግዱን ለማሳለጥ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር የነፃ ንግድ ቀጣናዎች በመቀላቀል በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ሰፊ ሥራ መከናወኑን የሚናገሩት አምባሳደር ምስጋኑ፣ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው በተሠሩ ሥራዎች ኢትዮጵያ በአፍሪካ ምርጥ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ከሚባሉ ሀገራት ውስጥ ተካታለች ብለዋል። ኢትዮጵያ ከቀን ወደቀን ለምታመርተው ምርት የተለያየ የገበያ መዳረሻዎችን እያሰፋች ነው። በዚህ እንቅስቃሴዋም መልካም የሚባል ውጤት እያገኘች ነው።

ከአገራት ጋር ያለውን ትብብር የሚያጠናክሩ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች መከናወናቸውን የሚያስረዱት አምባሳደሩ፣ በተለይ ተቋርጠው የነበሩ ግንኙነቶችን እንደገና በማስቀጠል እገዳ የተጣለባቸውን የፋይናንስ ድጋፍና የሰብዓዊ ርዳታዎች መጀመራቸውን አመልክተዋል። በየአገራቱ የሚከፈቱ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች የአገር ውስጥ ልማትንም ለማፋጠን የሚያግዙ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው ብለዋል። የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲውን እንቅስቃሴ ለማስፋፋት ኢንቨስትመንት፣ የገበያ ዕድል፣ የቱሪዝም አቅምና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚገኙባቸው አካባቢዎችን ታሳቢ በማድረግ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

አምባሳደር ጥሩነህ እንደሚናገሩት፤ ባለፉት ሁለት ሶስት ዓመታት የደረሰብን ፈተና ግልጽ ነው። እንደዚያ አይነቱ ችግር በሚያጋጥም ወቅት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መፍትሔ መስጠት የሚችል ነው። ለአብነትም ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል አገር መሆኗ ሊያግዛት የሚችል ወዳጅ አገኘች ማለት ነው። ስለዚህ የሚያጋጥመን ተግዳሮት ካለ አብሮ የሚሆን አካል ከጎን መኖሩ ችግሩን አቅልሎ ለማየት ምቹ ከመሆኑም በላይ ለመጋፈጥ አቅም እንዲኖር የሚያደርግ ነው። ይህ ስብስብ በአሁኑ ጊዜ ባለው ሁኔታ የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ከ30 እስከ 40 በመቶ የያዘ ነው። ይህን ቡድን መቀላቀል መቻል ትልቅ እድል ነው።

አምባሳደር ጥሩነህ፣ እኛ ኢትዮጵያውያን በኢኮኖሚያችን በጣም ማደግ እንሻለን። ይህ ጊዜ በጣም በከፍተኛ ደረጃ እየተነሳሳን ያለንበት ወቅት ነው። ስለሆነም የብሪክስ አባል መሆናችን ኢኮኖሚያችንን ለማሳደግ ለምናደርገው ሩጫ የሚጠቅመን ይሆናል ያሉት አምባሳደር ጥሩነህ፣ ለዚህ ደግም የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል።

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ እንደ አገር ብሔራዊ ጥቅም ሊከበርባቸው የሚችሉ መድረኮችን በሙሉ በመከታተል ለጋራ ጥቅምና ዕድገት ይሰራል። ዲፕሎማሲ መነሻውም መድረሻውም የአገርን ሰላም፣ ልማትና ደኅንነት እንዲሁም ዕድገት ሊያረጋግጥ የሚችል መሆን አለበት። ኢትዮጵያ ወዳጅ ለመሆን ብቻ ወዳጅ የምትሆን አይደለም፤ ለአገር ሰላም እና ልማት ምን ይገኝበታል በሚል እሳቤ የሚደረግ ነው።

የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሲቀረፅም በእነዚህ መርሆዎች ላይ ያተኮረ ነው። ከአገሮች ጋር በከንቱ ውዳሴ የሚደረግ ግንኙነት የለም። ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ደኅንነት፣ ለአካባቢዋ፣ ከክፍለ አህጉሩም ሰላም አልፎ ለዓለም ሰላም የምትሰራበት ስለሆነ አሰላለፏ ከአይዲዮሎጂ ጋር ሳይሆን ከብሔራዊ ጥቅም ጋር ተያይዞ አንድ ቦታ የተቸከለ አይደለም። ስለዚህ ዛሬ ላይ ለልማታችን ተጨማሪ ፋይናንስ፣ የፖሊሲ ተመጋጋቢነት፣ አጋርነት እናገኛለን ብለን ነው በዋነኛነት በመሪ ደረጃ ተይዞ ብሪክስ እንድንቀላቀል የተደረገው ሲል መረጃው ያትታል።

በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ላይ የበለጠ ትኩረት የመስጠት አስፈላጊነት እውቅና አግኝቷል። ፖለቲካ ኢኮኖሚውን ሳይሆን፤ ኢኮኖሚው ፖለቲካን መምራት እንዳለበትም ይነገራል። የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የመንግስት እና የመንግስት ግንኙነቶችን ለማካሄድ ኢኮኖሚያዊ መሳሪያዎችን በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ ደህንነትን እና የሀገሪቱን ስትራቴጂካዊ ጥቅሞችን የማገልገል ጥበብ ሆኗል።

ይህ በመሆኑም ኢትዮጵያም ከዚህ የተለየ አካሔድ እንደሌላት ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር ምስጋኑ ተናግረዋል። የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ለኢትዮጵያ ልማት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ተደርጎ እየተሰራበት እንደሚገኝም አስረድተዋል። አሁን አሁን የፖለቲካ ዲፕሎማሲው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲውን ማዕከል እንዲያደርግ የግድ ስለሚል በዚሁ መሰረት እየተሰራ እንደሆነም አመልክተዋል።

ሌላው የቀድሞ ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፈጣን በሆነ መልኩ ማደግ ይጠበቅባታል። በአሁኑ ጊዜ በኢኮኖሚ እድገቱ ኢትዮጵያ እያንሰራራች እንደምትገኝም አመልክተው ለዚህ እድገት ደግሞ አገሪቱ የብሪክስ አባል መሆኗ ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ ለምታደርገው ሩጫ ጠቃሚ ነው ብለዋል።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ጥር 7/2016

Recommended For You