በ1939 ዓ.ም በመስከረም አንድ የዓውዳ ዓመቱ ግርግር በደመቀበትና ልጃገረዶች አበባዮሽ (አበባ አየሽ ወይ?) በሚጨፍሩበት ዕለት እችን ምድር ተቀላቀለች። በተወለደችበት ቀን የሰማችው የልጃገረዶች ዜማ ይሁን የአጋጣሚ ነገር ከልጅነቷ አንስቶ ለሙዚቃ የተለየ ፍቅር ነበራት፡፡ የእሷን መወለድ ተከትሎ ከአዲስ አበባ ቀጨኔ መድኃኒያለም አካባቢ የፈለቁ አርቲስቶች ቁጥር በአንድ ከፍ ብሏል፡፡ የዚህ ምክንያቱም ከቤት አልፋ የመንደር፤ ከመንደር አልፋ የሀገር ድምቀት የሆነችው አርቲስት ሙናዬ መንበሩ የልደት ቀን መሆን ነው፡፡
ለዘመን መለወጫ አበባየሆሽን ከጓደኞቿ ጋር መጫወት የዓመት ከዓመት ልማዷ ነው፡፡ ከሰፈር ጓደኞቿ መሐል ማራኪ ድምፅ አላትና እሷ ዋና አውራጅ፤ ሌሎቹ ተቀባይ ሆነው ሰፈሩን በአበባየሆሽ ዜማ ያዳርሱታል። ይሄ የዓመት ልምዷ ታዲያ አንድ የበዓል እለት በሻህ ተክለማርያም ከሚባሉ የሀገር ፍቅር መሥራች ደጅ አደረሳት፡፡ የልጃገረዶቹ ወደ ጊቢው አገባብ የደንቡን ለማድረስ እንጂ የቤቱን ጌታ አውቀው አልነበረም፡፡ ሌሎች ልጃገረዶች እያጀቧት አበባየሆሽን በግሩም ድምፅ በምታዜመው ሙናዬ ድምፅ የተገረሙት የቤቱ አባወራ ታዳጊዋን ለማየት ከቤት ወደ ደጃፍ ብቅ አሉ፡፡ ያኔም በ12 ዓመቷ ታዳጊ ብቃት የተደነቁት በሻህ “ለምን ሀገር ፍቅር አትቀጠሪም?” አሉ፡፡ መልሷ አላውቀውም ቢሆንባቸው፤ ሀገር ፍቅርን የሚያሳያት ሰው ሊመድቡላት ተነጋግረው ተለያዩ፡፡
አበባየሆሽ ከሁነኛ ሰው ቤት ያደረሳት ሙናዬ በ12 ዓመቷ ሀገር ፍቅር ላወጣው ማስታወቂያ እንድትመዘገብ መንገድ ከፈተላት፡፡ ፈተናውን በአጥጋቢ ውጤት በማለፏ ትያትር ቤቱን በሁለ-ገብ ባለሙያነት ተቀላቀለች፡፡ ታዲያ ኋላ ላይ የትዳር አጋሯ የሆነው በቀለ ወልደፃዲቅ ቀድሟት የትያትር ቤቱ ሠራተኛ ነበርና ከፈታኞቿ መሐል ነበር፡፡ ታዳጊ እያለች የተቀላቀለችው ሙናዬ በሀገር ፍቅር ያልሆነችው የለም፤ ተወዛዋዥ፣ ድምፃዊ ደግሞም ሀገር ያደነቃት ተዋናይ ነበረች፡፡ ያም ቢሆን ብዙዎች እንዲያውቋትና ስሟን እንዲያነሱ ያስገደዳቸው የትወና አቅሟ ነው። በተለይ “የቀለጠው መንደር” የተሰኘው ትያትር ላይ የነበራት ትወና ታዳሚን በሙሉ የሚያስደምም ነበር፡፡
ትያትሩ ለአምስት ዓመታት በመድረክ ላይ በቆየበት ቀን ሳምንት በሳምንት ያለመታከት አዳዲስ ዲያሎጎችን መፍጠር መለያዋ ነበር፡፡ በተለይ እሷ ወክላት የምትሠራት ነገረኛ የሆነች ሴተኛ አዳሪን ገጸ-ባሕሪ ነበርና ከሳምንት ሳምንት የምታመጣቸው አዳዲስ ስድቦች ደሞ ባሁኑ ምን ብላ ትሳደብ ይሆን? በሚል በጉጉት ይጠበቅ ነበር፡፡ ሙናዬ ስትተውን ሁለመናዋ ይተውናል፤ የሷን ትወና የማይተባበር የአካል ክፍል የላትም፡፡ እጇን የምታንቀሳቅስበት መንገድ፤ ዓይኗ አብሮአት ሀሳቧን ሲደግፍ፤ ሰውነቷ ሲታዘዛት ለጉድ ነው፡፡
ስለሙናዬ ምስክርነት የሚሰጡ አብረዋት የሠሩ የሙያ ባልደረቦቿ የተሰጣትን ገጸ-ባሕሪ በማዳበር (ኢምፕሮቫይዜሽን) ጎበዝ ናት ይላሉ። እሷ ስትተውን ሁለመናዋ አብሯት ይተውናል፡፡ አንገቷ የራሱ መልዕክት አለው፤ ሲያስፈልግ ዓይኗም ይታዘዛል፤ እጇም የግሏ ነው። እሷ ጋ ዝም ብሎ ቃለ ተውኔቱን ማነብነብ አይታሰብም። ታማ እሷን የሚተካ የለምና በደጋፊ ከአልጋ ወርዳ ወደ መድረክ ስትወጣ ከበሽታዋ ጋር ትለያያለች በማለት አብረዋት የሠሩና የቅርብ ቤተሰቦቿ ይመሰክሩላታል። በተደጋጋሚ እያመማት ሥራ ከሚቋረጥ ብላ ለሥራዋ በድጋፍ ትመጣለች፡፡ ከዛ ተደጋግፋ ወደ መድረክ ትሸኛለች፤ ከዛማ ምን ጥርጥር አለው፣ የድሮዋ ሙናዬን ትሆናለች፡፡ ታዳሚንም አብረዋት የሚተውኑትንም አስደምማ ከመድረክ ትወርዳለች፡፡
ሐምሌ 17 ቀን 1958 ዓ.ም ቀኑ አጀማመሩ ከወትሮው የተለየ አይመስልም፡፡ ሙናዬ ከወትሮ በተለየ ሙሉ ቀኗ በሥራ ፕሮግራም ተጣቧል፡፡ በጠዋት ለንጉሥ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መዝሙር የማቅረብና አበባ የመስጠት ፕሮግራም ሥላለ በማለዳው 12፡00 ሰዓት ሀገር ፍቅር ድረሱ ተብለዋል፡፡ ከሰዓት ደግሞ “ምቀኛው እድሌ” የተሰኘው እሷ በትወና የምትሳተፍበት ትያትር በትያትር ቤቱ ለተመልካች የሚቀርብበት ዕለት ነው፡፡ ዓመት ከቀናት የሆናት የመጀመሪያ ልጇ ቶንሲል አሟታል። ከቤት የወጣችው በጠዋት ቢሆንም የእናት አንጀት ነውና በሌሊት ተነስታ ልጇን አጥባና መግባ ነበር፡፡
የልጇ ሕመም ለክፉ ይሰጣል ብሎ የገመተ ባይኖርም፤ ሙናዬን የራሷ መታመምም ሆነ የልጇ መታመም ከሥራዋ ለማስቀረት በቂ አይደሉም፡፡ ከቤቷ ስትወጣ ሀገሩም፣ መንደሩም፣ ቤቷም ሠላም ነበር፡፡ ለነገሩ ለእሷ ሠላም ባይሆንም በሥራዋ ቀልድ አታቅም። እንደታሰበው ማልደው በመሥሪያ ቤታቸው ተሰባስበው ወደ ቤተመንግሥት አመሩ። የጠዋት ፕሮግራማቸው በሠላም ተጠናቀቀ፡፡ ከሰዓቱን ዘወትር መድረክ ሲኖራት እንደምታደርገው ቀድማ በትያትር ቤቱ ቅጥር ተገኝታለች፡፡ ከዚህ በኋላም ነገሮች በሠላም ቀጠሉ፤ እንደወትሮው እራሷን ለትወና አዘጋጀች። ታዳሚው ሠዓቱን አክብሮ የትያትር ቤቱን አዳራሽ ሞልቷል፡፡
ትያትሩ ተጀመረ፤ ሙናዬም የገጸ-ባሕሪ ልብሷን ቀይራ እሷ የምትተውንበት ትዕይንት ሲደርስ ለመግባት በንቃት ትጠብቃለች፡፡ በዚህ መሐል መልዕክት አድርስ ተብሎ ከተላከው የባለቤቷ ታናሽ ወንድም ጋር ተገናኘች። “እናቴነሽ ሞተች” አላት፤ እሷ ግን ጠዋት በሠላም ስማት የተለየቻት ልጅ የምትሞትበት ምክንያት አልታያትምና ልታምነው አልፈለገችም፡፡ ባልደረባዋን ጠርታ “ይሄን ልጅ አንድ በይልኝ” ስትል ወደ መድረክ አመራች፡፡ ባልደረቦቿ ለማጣራት ሞከሩ እውነትም መርዶው እውነት ነው። ትያትሩን ያለሷ መጨረስ የማይታሰብ ነው፡፡ ከመድረክ ስትመለስ በጓደኞቿ ለቅሶ የልጇን ሞት እውነትነት አረጋገጠች፡፡ አብዛኞቹ ትያትሩ ተቋርጦ እንድትሄድ ሀሳብ ቢያቀርቡም እሷ ግን አይሆንም አለች፡፡ “አቋርጬ ብሔድም ልጄ አትመለስም” ስለዚህ ተዋናዩንም ጥበብንም አክብሮ የተገኘውን ሕዝብ አክብራ ለመሥራት ወሰነች፡፡
ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ በትያትሩ ላይም ሙናዬ የምትወክላት ገጸ-ባሕሪ እናቷ ሞታ የምታለቅስበት ቦታ አለና ልጇን አስታውሳ አምርራ አለቀሰች፡፡ እሷን ብሎ፣ ጥበብን አክብሮ ትያትር ቤቱን የሞላውን ሕዝብ እንደፈለገ ከልጄ ሞት አይበልጥብኝም ብሎ ጥሎ የሚሄድ አንጀት አልታደለችም፡፡ እዛው አልቅሳ ወደ ትወናዋ ተመለሰች። ትያትሩ ሲጠናቀቅ ለታዳሚዎች የልጇን ሐዘን ተቋቁማ መሥራቷ ተገለጸ፡፡ ያከበረችው ሕዝብም ከመድረክ መልስ አጅቦ አልቅሶ ልጇን ቀበረ፡፡ ያኔ ታዲያ የሷ ሥራ ወዳድነት ሀገር ምድር ያስገረመ ነበርና ወሬው በወቅቱ የሀገር መሪ የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጋ ደረሰ፡፡ በሰሙት የተገረሙት ንጉሡም “ከኃዘኗ ስትጽናና፤ አምጡልኝ አሉ፡፡ እንደተባለውም ስትበረታ ንጉሡ ፊት ቀረበች፡፡ ንጉሡም የ“ምን ላርግልሽ? ጥያቄ አቀረቡ፡፡ እሷም “ደሞዜን ጨምሩልኝ በማለቷ ደሞዟ ከነበረበት 15 ብር ወደ 20 ብር ከፍ ተደረገላት፡፡
ታማ የተሰጣትን ግሉኮስ ነቅላ ወደ ሥራዋ መሄድ ለሷ አዲስ አይደለም፡፡ የታዘዘላትን መርፌ መወጋት ትታ ሥራ ላይ መገኘት ተደጋጋሚ ተግባሯ ነው፡፡ ታዳጊ የሀይስኩል ተማሪ ልጇ በግርግር በተተኮሰበት ጥይት ሞቶ ከባድ ኃዘን ውስጥ ብትሆንም፤ በሠልስቱ ሕዝቡን አክብራ አስቀድሞ የተዋወቀ ትያትር ላይ ተውናለች። በትወናው ዓለም የሙናዬ ልጇ ሞታ መድረክንና ታዳሚን አክብራ መተወን ሲነገር እዚህ ደርሷል። አዘጋጆች አሁን ድረስ በፕሮግራም የሚያረፍድ ተዋናይ ሲገጥማቸው “ሙናዬ የልጇን አስከሬን ቤት አስቀምጣ ትተውናለች። እናንተ እንዲህ በመድረክ ቀልዱ።” እንደሚባል ከሷ ዘመን በኋላ የመጡ ተዋንያን ያነሱታል፡፡ በርካታ ተዋንያን እንደሷ ለመሆን እየሞከሩ የእሷን ትወናዎች ለማምጣት መስታወት ፊት ቆመው ተለማምደዋል፡፡
ሙናዬ በሥራዋ ምክንያት ያልደረሰችበት የሀገራችን አካባቢ የለም፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሆላንድ፣ ካናዳ፣ ግብፅ፣ ታንዛኒያ፣ አልጄሪያ፣ ናይጄሪያ ተጉዛ ሥራዋን ካቀረበችባቸው በርካታ ሀገሮች መካከል ይገኙበታል፡፡ በተለይ የፈረንሳይ ጉዞዋ ለየት ያለ ታሪክ አለው፡፡ በወቅቱ ሙናዬ ነብሰጡር ነበረች፤ ይሄ ዜና አለቃዎቿ ጆሮ ይደርሳል፡፡ ያኔ አለቃዋ ቢሮአቸው ጠርተው “እርጉዝ ነሽ አሉ” ሲሉ፣ እሷ “ማ እኔ? ኧረ እርጉዝ አይደለሁም።” ብላ በመካዷ “ሄዳ ትመርመር ተባለ፡፡ የቢሮ መኪና ተዘጋጅቶና አብሯት የሚሄድ ሰው ተመድቦ ወደ ሕክምና ተቋም አመራች፡፡ ወቅቱ “ጉብልዬ” የተሰኘው ዘፈኗ የገነነበት ወቅት ነበርና ሲስተሯ ገና እንዳየቻት “ምነው ምን እንርዳሽ?” አለቻት፡፡ ያኔ የውጭ እድል ገጥሞኝ መሥራት እየቻልኩ “ነፍሰጡር ናት ብለው ሊያስቀሩኝ ነውና ምን ይሻላል ስትል ተነፈሰች፡፡ ሲስተሯም ከዶክተሩ ጋር ተነጋግረው “ነፍሰጡር አይደለችም የሚል ማስረጃ ተሰጣት፡፡
ማስረጃውን ያዩት አለቃዋም አይ የሰው ወሬ ብለው ተገርመው ወደ ፈረንሳይ እንድታቀና ተደረገ። ለፈረንሳይ ተዘጋጅታ የነፍሰጡርነት ልብሷን በሻንጣ ሸክፋ ተጓዘች። ፈረንሳይ ገብተው ማረፊያ ክፍል እንደተሰጣቸው ከአወቁ አላወቁብኝ ልብሶች ተላቃ የነፍሰጡር ዘና የሚያደርግ ልብሷን ለበሰች፡፡ ያኔ ያዩትን ያለመኑት አለቃዋ ምነው ሙናዬ ምነው እንደዚህ ጉድ ታደርጊኝ አለ፡፡ እሷ ማን ናትና አታርግዙ አትውለዱ የሚል ሕግ አለ አላወኩም ነበር ሆነ መልሷ፡፡ በይ አሁን ትያትር ነው የምትሠሪው እንደመጣሻት አርገሽ ሆድሽን አጥፊ ተባለች እሷም ወደ ኩርሲዋ ተመለሰች፡፡
ሙናዬ እንደሷ ሁለገብ ከነበረችው በላይነሽ አመዴ (ኩንስንስ) ጋር የነበራቸው ወዳጅነት የተለየ ነበር። ስለሷ ስታወራ “በላይዬ አመዴ፣ ልቅም እንደስንዴ፣ ይወድሻል ሆዴ።” ከምትላት በላይነሽ ጋር በክፉም ሆነ በደግ፤ እንዲሁም በሥራ የማይለያዩ ወዳጆች ነበሩ፡፡ እሷ ያኔ በሕይወት ሳለች ጊዜ የማይለውጣት ባልንጀራዬ ብቻ ሳትሆን እህቴ ናት ትላት ከነበረው ኩንስንስ ጋር በርካታ ሥራዎችን በጋራ ሠርተዋል፡፡ ተጫዋች ናት። እሷ ካለች ሳቅ መፍጠርን፣ ሰው ማዝናናትን ተክናበታለች። ለዛም ይመስላል የሚያኮርፍ ሰው አልወድም ትላለች። በአንድ ወቅት በሬዲዮ በእንግድነት በቀረበችበት ወቅት ከመጀመሪያ የትዳር አጋሯ ጋር የተለያዩት እራሱ በኩርፊያውና በቀናተኛነቱ መሆኑን ተናግራ ነበር። የምትፈልገው ሕይወት የሳቅና የፈገግታ መሆኑን ትናገራለች፡፡ በሕይወቴ የሚያኮርፍ ሰው አልወድም ትል ነበር፡፡
አሁን አርቲስቶች ብራንድ አምባሳደር ሆነው በሚሊዮኖች ለመከፈል ቢደርሱም እሷ ግን ከ44 ዓመት አገልግሎት በኋላ ደሞዟ 900 ብር ነበር፡፡ በመሐል ኑሮዋን ለማሸነፍና ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ካዛንችሽ መጠጥ ቤት ከፍታ ነበር፡፡ በቤቱ የሙዚቃ መሣሪያ ባይኖርም ባንኮኒውን እየመታች ትዘፍን ነበር። ገበያውም ደህና የነበረ ቢሆንም ከመሥሪያ ቤቷ ሁለት ሥራ መሥራት አይቻልም የሚል ደብዳቤ ሲደርሳት እርግፍ አርጋ ተወችው፡፡
የተሰጣትን ገጸ-ባሕሪ ጥንፍፍ አርጋ እስከጥግ ትተውናለች፤ ስለዚህም እንዲህ ብትጨምር ይሄን ብታስተካክል ይሉ አስተያየት አይሰማም፡፡ ሀገር ፍቅር እየሠራች የጡረታ መውጫ እድሜዋ ቢደርስም መሥሪያ ቤቷ “ስለምትፈለጊ ∙ ∙ ∙ በሚል የጡረታ እድሜዋ እንዲራዘም አድርጓል፡፡ ከሙናዬ በፊት የትዳር አጓሯ ለበርካታ ጊዜ ታሞ ነበር፡፡ እሱን ስታስታምም ስለሱ ስታስብ ያልተጠበቀችው እሷ ቀድማ አረፈች፡፡ የቅርቦቿ በሽታዋ የሦስት ቀን ብቻ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እሱም ቢሆን እየሳቀች፤ እየተጫወተች ነሐሴ 10 ቀን 1995 ዓ.ም ሳትታሰብ ይችን ምድር ተሰናበተች፡፡ ያኔ በ15 ብር ደሞዝ ሥራ የጀመረችው ሙናዬ ከ44 ዓመት አገልግሎት በኋላ ደሞዟ 900 ብር ደርሶ ነበር፡፡
በትወና ከተሳተፈችባቸው ከመቶ በላይ ሥራዎች መካከል “የቀለጠው መንደር”፣ “የጠለቀች ጀንበር”፣ “ታጋይ ሲፋለም”፣ “አንድ ቃል”፣ “የቆጡን አወርድ ብላ”፣ እና “የቬኑሱ ነጋዴ” ይገኙበታል፡፡ ሙናዬ ሁለት የሙዚቃ ካሴቶችን ያወጣች ሲሆን፣ “ጉብልዬ” እና “ትዝታዬ”ተወዳጅ ሥራዎቿ ናቸው፡፡ ልጇን አጥታ፣ ኃዘኑን ተቋቁሟ በሠራችበት የሀገር ፍቅር መድረክ ልጇን በክብር ድራበታለች፡፡ የሀገር ፍቅር ትያትር ቤት ለሙያዋ ለነበራት ክብርና ፍቅር መታሰቢያዋ ይሆን ዘንድ ሐውልቷን በጊቢው ውስጥ አቁሞላታል፡፡
ሰኔ 3 ቀን 2015 ዓ.ም ብዙ ነገር በሆነችበት የሀገር ፍቅር አዳራሽ “ዝክረ ሙናዬ መንበረ የተሰኘ የ20ኛ ዓመት የሙት ዓመት መታሰቢያ ተደርጎላታል። ዝግጅቱ “ኅብር ግኝት የኪነጥበብ ማኅበር በተሰኘ የባለሙያዎች ስብስብ የተዘጋጀ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ልጇን በጊዜ የተነጠቀችው ሙናዬ፤ ከሷ ውጪ አምስት ልጆች አፍርታ ነበር፡፡ ሆኖም አንድ ወንድ ልጇ ከሷ ቀድሞ ሲሞት፤ እሷ እያለች በሕይወት የነበረው ሌላ ወንድ ልጇም አሁን በሕይወት የለም፡፡ ሦስት ሴት ልጆቿ ሥሟን ለማስጠራት የአቅማቸውን እየሞከሩ ነው፡፡ በተለይ አርቲስት ሐረገወይን በቀለ በሷ ሙያ ከመማረኳም ባሻገር ዝክረ ሙናዬን ያዘጋጀው ኅብር ግኝት የኪነጥበብ ማኅበር አባል በመሆን የእናቷን ሥም ለማስታወስ ትጥራለች፡፡
ሙናዬ ከተለየችን ጊዜው 20 ዓመታትን ቢሻገርም፣ በቅርብ ጊዜ በተፈጠረው የቲክቶክ መንደርም የሷን ቀደምት ሥራዎች በርካቶች የሚቀባበሉት ተወዳጅ ተዋናይ ነበረች፡፡ “ሙናዬ መንበሩ የሚለው ሥም ሠው በተሠማራበት የሥራ መስክ በትጋት ካገለገለ ሥሙ ከመቃብር በላይ እንደሚሆን ማሳያ የሆነ ሥም ነው፡፡
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን እሁድ ጥር 5 ቀን 2016 ዓ.ም